May 4, 2022
24 mins read

የኢዜማ መኢሶናዊ ጉዞ – በኡመር ሽፋው

የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ተብሎ ይጠራ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት በደርግ ወይም ወይም በወታደራዊው አገዛዝ ጊዜ ከመንግሥት ጋር ተለጥፎ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አባሎች ላይ ምን ዓይነት ግድያ፣ እሥራት፣ አፈናና ድብደባ እንዳስፈጸመ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ ባለፈው አራት ዓመት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ  (ኢዜማ) ከለየለት ዘረኛና ተረኛ የአብይ አህመድ መንግሥት ጋር ድንበር የለሽ ቅርርብ በማድረግ ከሞላ ጎደል መኢሶን የሄደበትን ጎዳና ለታክቲክም ይሁን ለስትራትጂ ተጉዞበታል ማለት ይቻላል። ዶ/ር መረራ ጉዲና የነበሩበትን መኢሶንን የጠቀስኩት ከኢዜማ ጋር ለንፅፅር ስለተመቸኝ እንጂ ከኢሕአፓ ጋር ለመወገን እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ።

የኢዜማ አመራሮች የአብይ መንግሥት ሕብረብሔራዊ ነው፣ ያሻግራናል፣ በአብይና በታከለ ኡማ ላይ እምነት አለን እያሉ ሲምሉና ሲገዘቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው አራት ዓመት ከሆነው ይልቅ ያልሆነውን የግፍ ዓይነት መቁጠር ሳይቀል የሚቀር አይመስለኝም። አማራው በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል-ግሙዝ ክልሎች በገፍ ታርዷል፣ በጅምላ ተቀብሯል። አሸባሪው ሕወሃት በከፈተው ጦርነትና መንግሥት በፈፀመው ሴራ በአማራና በአፋር ክልሎች ከተሞች ፈራርሰዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በበሽታና በረሃብ በማለቅ ላይ ይገኛሉ። የሁለቱ ክልልሎች መሠረተ ልማቶች እንዳሉ ወድመዋል። ታሪካዊ አብያተክርስቲያናትና መስጊዶች ተቃጥለዋል፣ ረክሰዋል፣ ቅርሶቻቸው ተዘርፈዋል። የሁለቱ ክልሎች ልማት ወደኋላ ሰላሳ ዓመት ሂዷል ቢባልም መልሶ ለመገንባት መቶ ዓመት ሊፈጅ ይችላል። ምን ያልደረሰ ስቆቃና ግፍ አለ? መንግሥት  በድል ተጠናቋል ያለው ውጊያ ዛሬም እንደቀጠለ ነው። ይህ ሁሉ የሆነው ኢዜማ ዝንቡ እሽ እንዳይባልበት በሚፈልገው በአብይ አህመድ ዘመነ መንግሥት ነው።

ይህ ሁሉ ሲሆን ኢዜማ አልፎ አልፎ ብቅ እያለ መግለጫ በማውጣት ሕዝቡን ለማስተኛት ከመሞከርና  ከብአዴን የበለጠ የኦሮሙማ አገልጋይ መሆኑን ለማሳየት ከመፎካከር በስተቀር የአብይ አህመድ መንግሥትን የተሳሳተ አቅጣጫ ለማረም አንድም መሬት ላይ የወረደ ሥራ ሲሠራ አልታየም። እንዳውም የይስሙላውን ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ነበር ለማሰኘትና የአብይ አህመድን ገጽ ለመገንባት በምርጫው ቢሳተፍም ጥረት ያደረገው ግን  ለራሱ ወንበር ለማሸነፍ ሳይሆን ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማሸነፍ ዕድል ለመንፈግ እንደነበረ በተደጋጋሚ ክስ ይቀርብበታል። ከዚህም ተጠቃሚው የአብይ አህመድ ብልጽግና ፓርቲ ስለነበር ዋለ ለተባለው ውለታ ለሊቀመንበሩ የትምህርት ሚንስትርነት ማዕረግ ተችሮታል። ሌሎችም የኢዜማ አመራሮች በተዋረድ ሥልጣን አግኝተውም ሊሆን ይችላል።

ምንም እንኳን ኢዜማ ሕብረብሄራዊና የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ነኝ ቢልም ባለፉት አራት ዓመታት ከፈጸማቸውና በቅርቡ ከወጡ መረጃዎች አንፃር ስንገመግመው ፓርቲው ከዜግነት ፖለቲካ ጋር የሚጋጩና ለሃገር ህልውና አስጊ የሆኑ አቋሞችን የሚያራምድ ሆኖ እናገኘዋለን። በቅርቡ የዲሲ ግብረሃይል አባሎች በኢትዮ360 ወጥተው እንዳፈረጡት አንዳንድ የኢዜማ አመራሮች ግንቦት-7  ውስጥ በነበሩ ጊዜ የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ሁለት ቋንቋ የግድ መቻል አለባቸው የሚል መመሪያ በተግባር ላይ በማዋላቸው በተለይ አማራው ከአመራር ሆን ተብሎ እንዲገለል እንደተደረገ ጠቁመዋል። ይህ አማራ አግላይ ባህል ኢዜማ ከተፈጠረ በኋላ ወደአማራ ጠልነት ለማዘንበሉ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ የኢዜማ አመራሮች አማራ የሆኑትንም ጨምሮ በሃገሪቱ ውስጥ የአማራን ዘር የማጥፋት ወንጀል እየተፈፀመ ነው ብለው አያምኑም። ከመሃላቸው የሚያምኑም ካሉ ድምፃቸውን ማሰማታቸውን በበኩሌ አላውቅም። በሌሎች ክልሎች የሚኖረውን አማራም “ፀጉረ ልውጥ”ና “መጤ” ብለው ከመጥራታቸውም በላይ እራሳቸውን በማንነታቸው ከሚያጠቋቸው አሸባሪዎች ለመከላከል የሚያስችላቸው የነፍስ ወክፍ መሣሪያ መታጠቅ የለባቸውም የሚል አቋም ሲያስተጋቡ ተሰምተዋል። እነሽመልስ አብዲሳ የዚህ ዓይነት ድጋፍ የልብልብ እንዲሰማቸው ስላደረጋቸው የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ያለውን አማራ እያደኑ ትጥቁን ስላስፈቱት የኦነግ ሸኔን አማራን የማረድ ተግባር አቅልለውለታል። ይህ ወንጀል እነሽመልስ አብዲሳን ብቻ ሳይሆን ኢዜማንም በተዘዋዋሪ መንገድ ያስጥይቃል ባይ ነኝ። ኢዜማ በፋኖ ላይ ያለው አቋም ከአብይ አህመድ አቋም እንደማይለይ በቀላሉ መገመት የሚቻል ይመስለኛል።

ኢዜማ ብዙ የሚጠየቅባቸው ጉዳዮች አሉ። የኢዜማ አገር ቤትና ዲያስፖራ ያለውን የተቃዋሚውን ጎራ በመከፋፈል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ስለሆነም የአብይ አህመድ መንግሥት ዕድሜ እንዲራዘም፣ የተቃዋሚ ጎራ እንዲዳከም፣ የወገናችን ስቆቃ ተባብሶ እንዲቀጥል አድርጓል። በተለይ በስሜን አሜሪካ በግንባር ቀደም የወገኑ ድምፅ የነበረውንና ለወያኔ ውድቀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገውን የዲሲ ግብርሃልን ለሁለት እንዲከፈል አድርጓል። ስለሆነም ኢዜማን የሚከተለው ወገን እንደኢዜማ አማራ የዘር ፍጅት አልተፈጸመበትም ወይም የዘር ፍጅት ጉዳይ ከሃገር ጉዳይ አይበልጥም፣ የሕሊና እስረኞች ጉዳይ አጀንዳችን አይደለም የሚል አቋም ይዞ ጭልጥ ብሎ የአብይ ካምፕ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ይህ ስም የለለው ፍንካች ስብስብ በውስጡ የታወቁ የኦነግ ደጋፊዎችን በአዲስ ፍቅር ያቀፈ ሲሆን፣ የ#NoMore Movementን ከማሳለጡም በላይ ዛሬ አሜሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚሰጠውን ማንኛውንም ዓይነት ትእዛዝ መሬት ላይ በማውረድ ይገኛል። ለዚህም አገልግሎታቸው አንዳንዶቹ አዲስ አበባ ላይ ቤትና መሬት እንደተሰጣቸውና የኢንቬስትመንትም ዕድል እንደተመቻቸላቸው ይነገራል። በተጨማሪ ኢዜማ ከዲሲ ግብርሃል ሌላ ዲያስፖራ የሚገኙትን የተለያዩ የምሁር ሥብስቦች በመከፋፈልና ወደአብይ ካምፕ በማስገባት የተጫወተው ሚና ቀላል አይደለም። የአብንንም ከፍተኛ አመራር ወደጠ/ሚንስትሩ እንዲጠጋ ያደረገው ኢዜማ እንደሆነ አሻራውን መደበቅ የሚችል አይመስለኝም።

ከሁሉም በላይ ግን ኢዜማ የቀድሞው ግንቦት 7 ንብረት የሆነውን የኢሳትን ሚድያ የአብይ አህመድ ልሳን በማድረግ ወገናችንን በጣም ጎድቶታል። ይህም ሁኔታ የዛሬ ሦስት ዓመት ኢሳትን እንደዲሲ ግብረሃይል ለሁለት እንዲከፈል አብቅቶታል። የአብይ አህመድ አገልጋይ ላለመሆን የመረጡት ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ተንታኞች ግን ኢትዮ360ን አቋቁመው የተገፋው ወገናቸው ድምፅ ሲሆኑ ቀሪው ኢሳት ግን አስነዋሪ ፀረሕዝብ ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ከOromo Broadcasting Network (OBN)፣ ከኢቲቪ፣ ከዋልታና ፋና ቢበልጡ እንጂ አይተናነሱም። እንዳውም OBN ከኢሳት የለዘበ ነው የሚሉም አሉ። “የአሜባ ባህሪ ያለው” ኢሳት እንደገና በቅርቡ ለሁለት ሲከፈል አይተናል። ሁለቱም አዲሶቹ ፍንካቾች አንዱ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሌላው ተደላድሎ አዲስ አበባ ከመቀመጣቸውና የትኛቸው የአብይ አህመድን አገር የማጥፋት አጀንዳ በበለጠ እንደሚያራግብ ለማሳየት ከመፎካከራቸው በስትቀር የይዘት ለውጥ ፈጽሞ አይታይባቸውውም። ሌሎችም የመገናኛ ብዙሃን የኢሳትን ፈለግ ተከትልው የአብይ አህመድን አጀንዳ መዳረሻቸው እንዳደረጉ ልብ ይሏል።

ባለፉት አራት ዓመታት ኢዜማ ከአብይ አህመድ በላይ አብይ አህመድ የሆነባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም። የሃገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ሁሉን አካታች ጊዜያዊ መንግሥት ይቋቋም የሚል ሃሳብ ሲቀርብ ቀድመው የሚቃወሙት የኢዜማ አመራሮች ነበሩ። የአብይ አህመድ የይስሙላ ምርጫ ከመደረጉ በፊት ብሔራዊ ውይይት ይደረግ ሲባል ከብልጽግና ፓርቲ ቀድመው በመቃብራችን ላይ የሚሉት እነሱ ነበሩ። ብሔራዊ ውይይት ይደረግ ሲባል ከነታየ ደንዳአ ቀድመው ጊዜ ወርቅ ነው፣ በውይይት ልናባክነው አይገባም የሚሉት እነሱ ነበሩ።  ዛሬ ላይ ግን፣ አብይ አህመድንና ኦሮሙማን በሥልጣን ኮርቻ ላይ በደንብ ካፈናጠጡና ካደላደሉ በኋላ፣ አዋጅ የወጣለት የብሔራዊ ምክክር ለችግራችን ሁሉ መፍትሄ ያስገኛል እያሉ አቀንቅነው ሳይጨርሱ፣ በድንገት የብልጽግና ፓርቲ ሕብረብሔራዊ አይደለም። ዘር ተኮር መሆኑ አሁን ገና ተገለጸልን የሚል መግለጫ አወጡ። ከዚህ የበለጠ በወገን ላይ ማላገጥ፣ መሳለቅና ማሾፍ ከየት ይመጣል?! ይህንን የኢዜማ የአዞ እንባና ድንገቴ መወራጨት መጠርጠር ከተገቢም በላይ ተገቢ ነው።

“ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ከውጭ ታስድራለች” እንዲሉ በማንነቱ ጧትና ማታ በሚታረደውና በሚፈናቀለው ወገናችን ላይ መቀለዳቸው በቀላሉ የሚቆም አይደለም። ምክንያቱም ጥገኝነታቸው  ሥልጣን ከስሜን ወደደቡብ መሸጋገር አለበት በሚል ፀረ አማራ የሃሰት ትርክትና ተረኝነትን የሚያበረታታ እሳቤ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው። በአጭሩ ባለፉት ምዕተዓመታት የሰሜኑ ክፍል ሃገሪቱን ገዝቷታል፣ ዛሬ የደቡቡ ተራ ነው የሚል ነው። ይህ አመለካከት ከኦነጋውያን አመለካከት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሄድና የእነአብይ አህመድን ተረኝነት አምኖ የተቀበለ ለመሆኑ የሚያከራክር አይደልም። ስለሆነም ኢዜማ በዚህ መንገድ ከኦሮሙማ ጋር አንሶላ እየተጋፈፈ ለዜግነት ፖለቲካ የቆምኩ ነኝ፣ የፍትህና የእኩልነት ዋርካ ነኝ የሚለው ፈጽሞ ውሃ አይቋጥርም።

በኖቨምበር 2016 በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ይመራ የነበረው አርበኖች ግንቦት 7፣ በሌንጮ ለታ ይመራ ከነበረው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር (ODF)፣ በዶ/ር ኮንቴ ሙሣ ይመራ ከነበረው የአፋር ሕዝቦች ፓርቲና በአቶ በቀለ ዋዩ ይመራ ከነበረው የሲዳማ ሕዝቦች ዲሞክራቲክ ግንባር ጋር በመሆን “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ” ወይም “ጥምረት” ተብሎ የተጠራውን የጋራ ግንባር አቋቋሙ። “ጥምረቱ” ሁለት ሰብሳቢዎች ነበሩት። አንደኛው አቶ ሌንጮ ለታ ሲሆኑ የጥምረቱ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ነበሩ። “ጥምረቱ” ሲመሠረት  በተለይም የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባርን (ኦዲግ) ለማስደሰት ሲባልና ሌሎችም ተልካሻ ምክንያቶች በመደርደር የአማራን ብሔር የሚወክል ድርጅት እንዳይካተትበት ተደረገ። ቢሆንም “ጥምረቱ” ለሕዝብ ይፋ በሆነበት መድረክ ላይ አማራን በመወከል “በታዛቢነት” አንድ ግለሰብ እንዲገኝ ዕድል ተችሮት ነበር። ይህንን ያመጣሁት ኢዜማ ፀረ አማራ ትርክቱን ከየት እንዳመጣውና በግንቦት-7 በኩል የኦሮሙማ አገልጋይነቱ መቼ እንደተጀመረ ለማሳየት ነው።

የኤፕሪል 2018ቱን ለውጥ ለመውለድ ሃገራችን በምጥ ላይ እንዳለች የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር ጓዙን ጠቅልሎ በድንገት አገር ቤት እንደገባ ይታወሳል። በዚያን ጊዜ “ጥምረቱ” ሙሉ በሙሉ የከሰመ መስሎን ነበር። ኦዲግንም ከሃዲ በማለት የጠራነው ጥቂቶች አልነበርንም። ለውጡን ተከትሎ አርበኞች ግንቦት-7  አገርቤት ከገባ በኋላ መሪው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደዋሺንግተን ዲሲ ተመልሶ ነበር። እንደተለመደው አዳራሽ ሙሉ ሕዝብ ተቀብሎት እንደነበር አስታውሳለሁ። የተለያዩ ጥያቄዎች ከታዳሚው ቀርቦለትም አስተናግዷል። አንድ የጋምቤላ ተወላጅ የሆነ ወገናችን በወቅቱ ያቀረበውን ጥያቄ ፈጽሞ አልረሳውም። ጥያቄው በአጭሩ ኦዲግ (ODF) ቀደምብሎ አገር ቤት በመግባት ነገሮች የሚያስተማምኑ መሆናቸውን ካረጋገጠላችሁ በኋላ አርበኞች ግንቦት-7 አዲስ አበባ የገባችሁ ይመስላል የሚል ነበር። ዶ/ር ብርሃኑ ጥያቄውን በፈገግታና በተድበሰበሰ መልክ ቢያልፈውም ዛሬ ኢዜማ ለአብይ አህመድ ያለውን ቅርበትና አገልጋይነት ስናይ የጠያቂው ጥርጣሬ ልክ እንደነበር መረዳት ይቻላል። ስለሆነም በተወሰነ ደረጃ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ” ወይም “ጥምረት” ለየት ባለ መልክ ዛሬም አለ፣ ሕያው ነው ቢባል ስህተት አይመስለኝም። ስለዚህ በተለይም ግንቦት 7 ውስጥ የነበሩት የኢዜማ አመራር አባላት ከጊዜ ወደጊዜ የሚያሳዩት አማራ አግላይ አቋም ሊደንቀንና ሊያስደነግጠን አይገባም።

በኢዜማ አመራር ውስጥ ከሰማያዊ ፓርቲ እንደነየሺዋስ አሰፋ እና ሌሎችም እንዲሁም ከአሁን በፊት ለከፈለው መስዋዕትነት ሕዝብ የሚያከብረው አንዱዓለም አራጌ ስላሉበት ፓርቲው ብዙ መልካም ሥራ ለወገኑ ይሠራል፣ የሃገሪቱን ሕገመንግሥታዊ ችግር በመቅረፍ በኩል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር። አመራሮቹ ግን ተረኛው የአብይ አህመድ መንግሥት ተመችቷቸው በሰመመን ላይ ቢሆኑም በባነኑ ቁጥር ግን መግለጫ ማውጣት አልነፈጉንም። በድርጅት ደረጃ ኢዜማዎች ያላቸው አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ በግለሰብ ደረጃ አገር ስትፈርስ ለምን ዝም ትላላችሁ ተብለው ሲጠየቁ አይናቸውን በጨው አጥበውና ህሊናቸውን ደፍጥጠው የፓርቲያችን የአሠራር ደንብ አሥሮ ይዞን ነው ሲሉ ይሰማሉ።

ኢዜማ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር እንዳይቀረፍ የማይቧጥጠው ዳገት የለም። ደጋፊዎቹን አሰማርቶ እንደHR6600ና S3199 የመሳሰሉትን የሕግ ረቂቆች በአጭር ለማስቀረት እየኳተነ ይገኛል። ምክንያቱም ረቂቆቹ በአሜሪካ ኮንግረስ ፀድቀው ሕግ ሆነው ቢወጡ ከአብይ አህመድ መንግሥት ጋር ባላቸው ድንበር የለሽ ቅርበት የተነሳ የኢዜማ አመራሮች ከተጠያቂነት እንደማያምልጡ ግልጽ የሆነላቸው ይመስለኛል። የሚገርመው ከኢዜማ አመራሮች ውስጥ ከፊሎቹ በወያኔ ጊዜ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዝሬ እንዳይኖራት፣ የተለያዩ ማእቀቦች እንዲጣሉባት፣ ለአባይ ግድብ ብድር እንዳይገኝና ገንዘብ እንዳይሰበሰብ ማህበረሰቡን ይቀሰቅሱና ይመሩ የነበሩ መሆናቸው ነው። በወያኔ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ አገር ለቆ የወጣ ይመስል፣ ከወያኔ በበለጠ የሃገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ የጣለ ተረኛና ዘረኛ መንግሥት ላይ ተስፋ ጥለው ዛሬ ማእቀብ ሕዝቡን ይጎደዋል ይሉናል። የሆነው ሆኖ የኢዜማ አመራሮች አገሪቱን ወደሲኦል ይዞ ከሚጓዘው የኦሮሙማ መንግሥት ጋር በመተባበራቸው በታሪክና በተተኪው ትውልድ ተወቃሽ እንደሚሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ከዚህ ባለፈ ፍትሃዊ እንሁን ከተባለ ጊዜ ፈቅዶ ሌሎቹ ለፍርድ የሚቀርቡ ከሆነ እነሱም ባደረሱት የጥፋት መጠን ለመቀጣት በፍርድ ተጠያቂ የማይሆኑበት ምክንያት አይታየኝም።

በኡመር ሽፋው (May 5, 2022)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop