” ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ ። ” ይላሉ አበው ። ጥፋትን አውቆ ወዶ ና ፈቅዶ ወደ ጥፋት የገባ ወይም የዘንዶ ጉድጎድን በእጄ ካለካው ብሎ በአጉል ድፍረት ፤” ተው ዘንዶ አለ … ” ብትለው ” አልሰማህም ! ምን አገባህ !? ” በማለት እጁን የሰደደ አለአመዛዛኝ ሰውን ፤ታዝበህ ፣ በሐዘኔታ ከንፈርህን ከመምጠጥ በሥተቀር ከቶም እጁን ከማጣት ልታድነው አትችልም ። የዚህ እውነት ማጠናከሪያ አንድ ተረት ልጨምርለህ ። እንሆ !
” የፍርደ ገምድል አገር ። ”
“ አንድ ሰው ከእጅ ወደአፍ ኑሮ በመጥላቱ ፣ ‘ ተው አንድ ቀን አብርን ያልፍልናል ፡፡ አገርህን ለቀህ የትም አትሄድ ፡፡ የዛሬን ሳይሆን የነገ ልጆችህን ተስፋ ና እድል ተመልከት ፡፡ ’ እያለ ፣ ጎረቤት ና ዘመድ አዝማድ ቢለምነው እምቢ ብሎ ፣በወሬ በሰማው ፣ ሀብት ወደተፍረፈረበት አገር አቅጣጫ ፤ ቅልና ጨርቁን ጥሎ ፣ ሚስቱን ና ልጆቹን አንጠልጥሎ ፣ ጉዞ ጀመረ ። ቀን እና ሌት ተጉዞም ወደ ሁለት አገር መግቢያ ድንበር ላይ ደረሰ ፡፡ መንገዱ መስቀለኛ ነበር ፡፡ ያ የሰማው የተሻላ ፣ የጥጋብ አገር የቱ እንደሆነ ለማወቅ በየአገሩ ድንበር ላይ ያሉትን ሰዎች ጠየቀ ።
በቀኝ አቅጣጫ ፍትህ ፣ ርዕት እና የሰው እኩልነት ያለበት ፣ ደኞች ያለአድሎ ለሁሉም ትክክለኛ ፍትህ የሚሰጡበት ። ሁሉም በችሎታው ሰርቶ የመኖር መብቱ የተረጋገጠበት ፣ የተሻለ ኑሮ ለመኖርም እጅግ ልፋት የሚጠይቅ አገር ሲሆን ፤ በስተግራው አቅጣጫ ያለ አገር ግን ፤ በፍርደ ገምድልነት የታወቁ ዳኞች የበዙበት ፡፡ ህግና ሥርዓት የማይከበርበት ፡፡ የምን ግዴ መንግስት ያለበት ፡፡ ምግብ ና መጠጥ የተትረፈረፈበት ፡፡ ዜጋው ማጭበርበርን ስራዬ አድርጎ በሌላ ሰው ድካም እንዳሻው እንዲሆን ህጋዊ ከለላና እውቅና የተሰጠበት አገር ነበር ። ይህንን እውነት ስደተኛው ተረዳ ፡፡ እናም ” ከርሃብ ጥጋብ ይሻላል ፡፡ ህግ ከሚከበርበት ና ችጋር ከሞላበት አገር ይልቅ ፤ ያለህግ በመኖር ሰማይን በእርግጫ መምታት ያስደስታል ፡፡ ” በማለትም ፣ የጥጋብ እና የፍርደ ገምድል አገርን መረጠ ፡፡
ምንግዴ ፣ጥጋባኛ ና ፍርደ ገምድልነት በሞላበት አገርም ፣እንዳሻው እየበላና እና እየጠጣ ( ሰማይን እየረገጠ፣ዓለም በጎኔ አለፈች እያለ ) ሀብት አፍርቶ ፣ ተጨማሪ ሁለት ልጆች ወልዶ በደስታና በተድላ እየኖረ ሳለ ፣ ከአጠገቡ ጎጆ ቀልሶ የሚኖር የአገሬው ተወላጅ ፤ ልጅ ሥለሌለው ቀናበትና ” ሚሥትህን ሥጠኝ ።” ብሎ ጠየቀው ፡፡ ይኽ ጥያቄ ላገሬው እንግዳ እና ያልተገባ አልነበረም ፡፡ ሆኖም ይኽንን ጥያቄ ለማስተናገድ ፍቃደኛ ሳይሆን ቀረና ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡
ከሳሹም ፣ “ ይኼ ጎረቤቴ ብዙ ልጆች አሉት ። እኔ ግን የለኝም ። እናም ሚስቱን ሰጥቶኝ ለእኔ ልጅ ትውልድልኝ ዘንድ ብጠይቀው እንቢ አለኝ ። ክቡር ዳኛ ያለልጅ መቅረት የለብኝምና ወላድ ሚስቱን ይሰጠኝ ዘንድ ለክቡር ፍርድ ቤቱ አመለክታለሁ ። “ በማለት ክቡር ፍርድ ቤቱን ጠየቀ ፡፡
ዳኛውም ” ሥማ ተከሳሽ ፣ ሚስቴን አልሰጥም ስትል ፣ አንተ በለ ብዙ ልጅ ሆነህ ፣ እርሱ ልጅ ሳይኖረው ይቅር ማለት ነው ? ሚስቴን አልሰጥም ብሎ ነገር በዘህ አገር ህግ የሚስቀጣ ነው … ይሁን እንጂ እስራቱን ትቼልህ ፣ ከዚህ ደቂቃ ጀምሮ ምሽትህ የእርሱ ሆና እንድትወልድለት ወስኛለሁ ። …” በማለት ፣ የተከሳሹን መከላከየ ቃል እንኳን ሳያጠይቁ ፣ በሀገሬው ህግ መሰረት ስደተኛውን አሥደንጋጭ ፍርድ ሰጡ ። ሚስቱንም ተነጠቀ ፡፡ በዚህ ፍርደ ገምድል በሆነ ፍርድ ሚስቱን የተነጠቀው ያልፍልኛል ብሎ ከአገሩ የተሰደደው ሰውም ፣ በእዛኑ ዕለት ክፉኛ ታመመ ።
የአገሬው ሰዎችም ( ጎረቤቶቹ ) ተሰብስበው ሲያዩት ሲያቃሥት እና አይኑንን ሲያሥለመልም አዩና “ይኽ ሰው ነገ ከሞተ ሥራ ያሥፈታናል ፡፡ ዛሬውኑ ከእነ ህይወቱ እንቅበረው ። ” አሉ ። ልጆቹም ” እንዴት ሳይሞት አባታችን ከእነ ህይወቱ ይቀበራል ? ” በማለት ተቃወሙ ። ይህም ጭቅጭቅ ተባብሶ አካባቢውን በማወኩ በፖሊሥ ተይዘው ሁለቱም ወገኖች የአገሬው ዳኛ ፊት ቀረቡ ።
“ የጠባችው መንስኤ ምንድነው ? “ ሲል ጠየቀ ዳኛው ።
“ የታማሚው ልጆችም አባታችን ታሞ እቤት ተኝቷል ። እነዚህ ጎረቤቶቻችን ነገ ሥራ ሥላለብን አባታችሁ ከሞተ ሥራ ያሥፈታናልና ዛሬውኑ እሥከነ ነፍሱ እንቅበረው ። “ ነው ፤ የሚሉት በማለት ለዳኛው አሥረዱ ። ዳኛውም ” ነገ ሞቶ ሥራ ከሚያሥፈታችሁ ዛሬውኑ ወሥዳችሁ ቅበሩት ። “ በማለት በተለመደው ፍርደ ገምድልነት ትዕዛዝ ሰጠ ። በፖሊሶች ትዕዛዝ አሥፈፃሚነትም “ ኧረ አልሞትኩም ። በህይወት እያለሁ እንዴት ትቀብሩኛላችሁ ? ! እባካችሁ ማሩኝ ። አትቅበሩኝ ። ነገም ላልሞት እኮ እችላሉ ፡፡ እመኑኝ ነገ አልሞትም ። ኡ !ኡ ! …” እያለ ልጆቹ በፖሊስ የፊጥኝ ተይዘው አይናቸው እያየ እሥከነ ህይወቱ አባታቸውን አፍር ና ዲንጋይ ጫኑበት ፡፡
እንደዚህ ተረት አይነት እውነት በገሃዱ ዓለም ቢሰራ ና ብዙሃኑ በዜና ቢሰማ እንኳ ፣ እውነት አይመሥለውም ። ይሁን እንጂ በፍርደ ገምድልነት ያለጥፋታቸው ብዙ ሰዎች በዓለም ላይ ታስረዋል ፡፡ የሰው ይቅርና የዶሮ ነፍስ ያላጠፉ ንጹሐን ሰዎች በሐሰት ውንጀላና ፣ በቀጣፊ ምስክሮች እገዛ ተገድለዋል ፡፡ ግፍ የተፈፀመባቸውን ሰዎች በእውነቱ አንድ ሁለት ብሎ መቁጠር ያዳግታል ፡፡ ይኽንን ፍርደ ገምድልነት የዛሬው የዓለም አንዳንድ መንግስታትም ቀጥለውበታል ፡፡
በዛሬው ዓለም ያሉ አንዳንድ መንግስታት በተለይም አሜሪካና በአውሮፓ ያሉ ጥቂት መንግስታት ፣ ከጥቅም አንፃር ሁሉን ነገር መዝነው ፣ ነገ እናገኛለን የሚሉት ሀብት ከሰው ህይወት በልጦባቸው ፣ በፍርደ ገምድልነት ከቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮቻቸው ጋር በመወገን ምንም የማያውቀውን የአፍሪካ ህዝብ እያስጨረሱት ነው ፡፡ ( ትላንት 800 ሺ ሩዋንዳውያን ያለቁት ፣ ለነማን ጥቅም እንደነበር የዛሬዋን ሩዋንዳ ፈትሽ ፡፡ )
በአፍሪካ ውስጥ ሰዎች በውሸት ትርክት ሰው መሆናቸውን ዘንግተው ፣ ራሳቸውን ቋንቋ ና ኃይማኖት በማድረግ ፣ ይኽ ነው የሚባል ፣ ለመጠፋፋት የሚያበቃ ቂምና ቁርሾ ሳይኖራቸው ፣ እንዲገዳደሉ ፣ ማነው አስቀድሞ ህሊና ቢሱን እያጠመደ መልምሎ በየአፍሪካ አገሩ የሚያሰማረው ? ለመሆኑ በአፍሪካ ውስጥ ፣ ሰው ፣ ሰው መሆኑን ክዶ ፣ በዘር ና በቋንቋ እንዲቧደን ማነው እያደረገ ያለው ? ሰው ፣ ሰው ጠል ሆኖ ፣ በቋንቋና በኃይማኖት የሚቧደንባት አህጉር አፍሪካ አይደለችም እንዴ ? ፡፡ ( በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ፣ በመንግስት ደረጃ የሚራገበው ዘረኝነት ፣ ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠላ ነው ፡፡ )
እርግጥ ፣ ይህንን ፀረ ሰው ሆኖ ፤ ፀረ ሰው ቡድንን በቅኝ ግዛት ዘመን የፈጠረው የአውሮፓው ቱጃር እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል ፡፡ ዛሬም ደካማ ና አእምሮ የጎደላቸውን ዜጎች እየመለመለ ፣ በየደሃ አገሩ ለጥፋት አሰማሪው ፣ ይህው አልጠግብ ባዩ ፣ አውሮፓዊ በዝባዥ ቡድን ነው ፡፡ ዘመናዊ ትጥቅ እያቀረበ ፣ ከዳቦ ችግር ጀምሮ በአያሌ የድህነት ችግር የተከበበውን እርስ በእርሱ እንዲጠፋፋ ና ያለቸው የደሃ ንብረቱ እንዲወድም ፣ ዋናውን የጥፋት መንገድ የሚያመቻምቸውም ፣ ይኸው ሥልጡን ነኝ ባዩ ፣በጣት የሚቆጠረው ፣ ግፈኛና ጨካኝ አውሮፓዊ የናጠጠ ቱጀር ነው ፡፡ ይኽ ቱጃር የተር መሳሪያ ፋብሪካ ያለው ነው ፡፡ የመድሃኒት ፋብሪካ ያለው ነው ፡፡ የቴክኖሎጂ ማምረቻ ፋብሪካ ያለው ነው ፡፡ እጅግ ዘመናዊ ሆስፒታሎች ና ከፍተኛ ገንዘብ ተከፋይ ሳይንቲስቶች ያለው ነው ፡፡ እንኳን ምድርን ሰማዩን ተቆጣጣሪ ነው ፡፡ የሣተላይት መገናኛ ብዙሃን አውታሮች በሙሉ የእሱ ናቸው ፡፡ ፌስ ቡክ ፣ ቲዊተር ፣ ዩቲዩብ ወዘተ ፡፡ የእርሱ ናቸው ፡፡ ..እናም በአፍሪካዊው ምንዱባን እልቂት ፣ ውድመት ና ጥፋት ቢደሰት ምን ያስገርማል ?
ነገ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ለግሌ እና ለጥቅም ተጋሪዎቼ እንዲሁም አጋሬ ሆነው ብዝበዛውን ላመቻቹልኝ በሙሉ ፣ ያልደከመበትን እና የማይገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ፣ በመንግስቴ በኩል ማድረግ እችላለሁ ፡፡ ” እያለ በህቡና በግልፅ ሲንቀሳቀስስ ማን አቆመው ? በስውርና በግልጽ ፣ በተለያዩ ሰብዓዊ ድርጅቶች ፣ ሚዛናዊነት በጎደለው ፐሮፖጋንዳ እየታገዘ ፣ ” ለእኔ ብዝበዛ እንቅፋት የሆነ አገር ፣ እንደ ሱማሊያ ፤ የመን ፤ ሊብያ ና ሶርያ ይሆናል !! ” ብሎ በግልፅና በስውር በማስፈራራት ፤ ይኽንን እኩይ ውጥኑን ለማሳካት ፣ ያለ እንቅልፍ ሲጥርስ ማን ተው ፣ እረፍ ፣ ደሃን ባትፈራ እንኳን ፈጣሪውን ፍራ ፡፡ ብሎ ገፀሰው ?
ይኸው ዛሬ ኃይ ባይ አጥቶ ፣ በፍርደ ገምድልነቱ በየደሃ አገሩ የሚያቧችረው ፣ የአውሮፓን እና የአሜሪካንን መንግስት ሥልጣን የተቆጣጠረው ፣ ይኸው ፣ በጣት የሚቆጠረው የዓለም አንድ ርሰንቱ ቱጃር ኃይል አይደለም እንዴ ? ለዚህ ገንዘብ አምላኩ ለሆነ ኃይል ሰው እረሱ የሚሸጥ ሸቀጥ ነው ፡፡ ፍርደ ገምድሎች እንዲበረከቱ በመላ አፍሪካ ዶላሩን የሚረጨውም ሰው ልጅ ሸቀጥ እንደሆነ በማመን ፣ ሁለንተናውን በገንዘብ እገዛለሁ ብሎ ስለሚያምን ነው ፡፡
የሆነ ይሁንና ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ፤ እውን ድህነት በተሰራፋበት አገር ፣ ሥርዓተ አልበኝነትን ፣ ልቅ በሆነ በዘር ፖለቲካ ማስወገድ ይቻላል ብለን እናምናለን እንዴ ? የዛሬ አንአዳንድ የመንጋ ና የነጻ አውጪ ነን ባዮች ፍርዶችስ ፣ እጅግ አብራርቼ ከተረትኩት ተረት የባሱ እንደሆኑ መገንዘብ የመንግስትን ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር አያስገድደንም ወይ !? እስቴ በሞቅታ ሳይሆን በስክነት ፣ ሰርተው ለመኖር ለሚተጉ ዜጎች በማሰብ ትክክለኛውን መንገድ እንምረጥ እና አገራችንን ከጥፋት እናድናት ፡፡