ዛሬስ ምነው በዛ
እንጀራ፤ ዳቦ ድስቴ ጠነዛ
ልጆቼም ገልቱ ሆኑ ተረገሙ
ልሳን ድምጼንም አይሰሙ
ተጠላልተው፤ተገፋፍተው፤ ተናንቀው___እየተማሙ
በግብር በሃሳብ ገለሙ።
ገና ከማህጸን ሲወጡ ባርኬ
ቀለም ልቀሙ ብዬ አስኩዋላ ልኬ
ይገባቸው እንደሁ ጠልቆ
ያረቅቃቸው እንደሁ አምጥቆ
ያኖራቸው እንደሁ አስታርቆ
ከረሃብ፣ ከመከራ፣ ከድንቁርና፣ከእርዛት፣ ከስደት አላቆ፤
ግና!
ማን በረዘብኝ ቀለሙን
የጥበብ፣ የማስተዋል ጅረቱን
የሚያሳየውን ገላልጦ
ከጠዋት ጠሃይ ቱግታ አብልጦ፤
የአንድነት የፍቅር ብርታቱን
የታሪክ የባሀል ጥልቀቱን
የሃሳብ የምናብ ምጥቀቱን
የመኖርና ሰው የመሆን ር_ቀቱን።
ዋ!
ከንቱዎቼ ቀልባቸው ሆኖ ሆ! ና ዋ! ላይ
ሌላ ሆሄያትን የማይለይ የማያይ
የለቀሙት ተአስኩዋላው ተመላልስው
ገረጣ፣ ከሰረና መከነ እውቀታቸው
ሆነ ከንቱ አልባሌ
ለእኩይ ምግባር ገባ ሎሌ
እያወጀ እኔ ለእኔ
እያሰኘ
“አትቅረበኝ” ራቅ ከጎኔ፤
ተፈርጆ አጥርን ሰራ
ባጀ ተባ፣
ለጦርነት ለአተካራ
ዋ!
ባይገባው ነው በአንክሮ
ከጥንት አንስቶ ከድሮ
ቀለምን ሲያውቁ መርምሮ
ህይወት ሲገፉ ተባብሮ
ነው መድህኒቱ ለህይወት
ነግ ተነግ ወድያ ከርሞን ለማየት።
በላቸው ገላሁን
ሚያዝያ ፰ ፳፻፲፬ ዓ. ም.
U.S.A