ሰባዊነትንና ኢትዮጵያዊነትን እናንፀባርቅ – አልማዝ አሰፋ

አልማዝ አሰፋ
Imzzasefa5@gmail.com

እንኳን ሰው ከሰው  እግር ከእግር  ይጋጫል ይባላል:: የሰው ልጅ የግል ማንነቱን የሚያስመሰክረው ያለውጭ ተፅኖ በራሱ ሃሳብ መመራቱ ነው:: በራስ ሃሳብ መመራት ማለት የራስን አመለካከት በሌላው ላይ መጫን  ወይም በጉልበት ሌላውን እኔ የምልህን ተቀበል ወይም በውሸትና በማታለል  ሌላውን ወደ ራስ አመለካከት ማምጣት  ሳይሆን እውነትና ሃቅን የተሞረከዘ ከራስ አልፎ ሌሎችን የሰው ልጆች  የሚጠቅም  ሃሳብ  ማቅረብ  ነው:: በአጠቃላይ ሰባዊነት የተሞላው አመለካከት ማፍለቅም ነው:: በዚህ የሃሳብ ወይም የአመለካከት አቀራረብ ላይ በሰው ልጆች መሃል ልዩነቶች ይፈጠራሉ:: እነዚህ ልዩነቶች የሂደት እንጂ የመጨረሻ ግብ ሊሆኑ አይገባም:: የሃሳብ  ግጭቶችና  ፍጭቶች  የጋራ ጥቅም ላይ  እንዴት እንደርሳለን ለሚለው ጥያቄ የምንሄድባቸው የተለያዩ መንገዶች እንጂ ፍፃሜዎች መሆን አይችሉም:: ግን በአገራችንም ሆነ በውጭ ያለው ትውልደ ኢትዮጵያ ሕዝብ የሃሳብ ልዩነቶችን አውቆ ወይም ባለማወቅ እንደ ግብ ቆጥሮ የእኔን ሃሳብ ወይም አመለካከት ያልተቀበለ ጠላቴ በማለት በሃሳብ ጎዳና ላይ እየተጠላለፈ በመውደቅ: የሚኖርበትንና የሚያስብለትን (በእርግጥ ከአሰበ) ህብረተሰብ: ሰባዊነት: አንድነትና ፍቅር  ያስተሳስረው  ሰላም የሰፈነበት የጋርዮሽ ኑሮ ፍፃሜጋ ሊያደርሰው አልቻለም::

ይህ ሾኬ መመታታት በኢትዮጵያውያኖች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደቅርስ እየተወራረሰ ይታያል::ይህንን መጠላለፍ የኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲከኞች ባህል አድርገውታል:: ይህንን የአስተሳሰብና የአመለካከት ጉድለት ተላላፊ በሽታ እያንዳንዳችን መዋጋትና ማጥፋት ይጠበቅብናል:: ልማትም ጥፋትም: ህብረትም  ልዩነትም: ፍቅርም  ጥላቻም: ሰላምም እረብሻም: መተቃቀፍም መገፋፋትም: መሰጣጣትም መነፋፈግም: አንድነትም መነጣጠልም: የእያንዳንዳችን ምርጫና ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም እያንዳንዳችን የሕብረተሰቡ አባል ስለሆንን ድምራችን ሕብረተሰብን ይፈጥራል:: የእያንዳንዳችን አስተሳሰብና አመለካከት ድምር የህብረተሰቡ ሂሊና ይሆናል:: የተጣመመና ጥፋት አዘል ሃሳብና አመለካከት ከእያንዳንዳችን ከመነጨ የህብረተሰቡ እጠቃላይ ሂሊና ህብረተሰቡን (እያንዳንዳችንን አጠቃሎ) ይጎዳል::

አንድ እንደፈለግነው ብንመነዝረው: ብንተነትነው: ሊቃዊ አመለካከት ብንሰጠው: ብንበርዘው ብንከልሰው የማይለወጥና የማይሸረሸር የሰው ልጆች የማይክዱት ሃቅ: ሰው ከሰው ተለይቶ መኖር አለመቻሉን ነው:: በፈለግነው መንገድ  እንደራጅ: ጠንቀኛውን የአንድነት ጠላት የሆነውን ጎሰኝነትን አካቶ አንዱ ጎሳ እንኳን ከሌሎች ጎሳዎች ተጎራብቶና ተዛምዶ ለትውልዳት የቆየው ይቅርና እራሱን በባህር የተከበበ ደሴት አድርጎ የተቀመጠም በዛሬ የዓለም አሰላለፍ ብቻውን መኖር አይችልም:: አንድ አገር ከሌሎች አገሮች ጋር የዲፕሎማሲ: የንግድ: የትምህርት: የመከላከያ: የእርዳታ ግኑኝነት በማድረግ የአስተዳደር ስርዓት: እውቀትና: ጥበብ እየተለዋወጡና እየተካፈሉ አገሮቻቸውን በማሳደግ ሕዝቦቻቸው ሰላም የሰፈነበትንና በልማት የበለፀገበትን ኑሮ በመኖር ፍቅርን: አንድነትን: መተባበርንና መተሳሰብን ለቀጣዩ ትውልድ ያወርሳሉ:: ይህ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍልና አባል በቅንነት ሰባዊነትን ከምንም በላይ ዋጋ በሰጡበት አገሮች የሚታይና የሚካሄድ ነው:: ችግር አይታይባቸውም ካልን ከእውነት መራቅ ይሆናል:: ግን ችግራቸውን: ጥላቻን ቅድምያ በመስጠት: የእግዚአብሔር ፍጡርን  ከተወለደበት ቦታ በማፈናቀልና ነፍስ በማጥፋት ሳይሆን በውይይት ገበታ ተቀምጠው በመፍታት ነው:: የትምህርት ዋና አላማም ለሰው ልጅ እውቀትን ማቅሰም  ነው:: ተምሬእለሁ እውቀት ቀስሜአለሁ ያለ የሰው ልጅ  እውቀትን ለሰባዊነት መጠቀም ትቶ ለጥፋት ካዋለ ትምህርቱ ርግማን ሆኖበታል ማለት ነው::

ኢትዮጵያውያኖች ውይይትን እንዴት እናያለን?  የችግርና የድህነት ታሪካችንን ስንመለከት በእርግጥ ውይይት ምን ማለት እንደሆነ የገባን አይመስልም:: ውይይት የሃሳብ ልዩነቶች ማቀራረቢያና ማጣጣሚያ ሂደት ነው:: በውይይት ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በመነጋገርና በመደማመጥ የሃሳብ ልዩነቶች ተወግደው ወደ ስምምነት መድረስ የስልጣኔ ምልክት ነው:: ወደ ውይይት ስንገባ: ውይይት የክርክር ወይም የስፓርት ውድድር ስላልሆነ: የማሸነፍና የመሸነፍ አቋም ለማጠናከር ሳይሆን አንዱ ሌላውን በመረዳት እርስ በርስ ተግባብቶ  ሁለቱን ወገኖችን የሚረዳና የሚጠቅም የጋራ ስምምነትና ውሳኔ ላይ ለመድርስ ነው:: እንዲህ ዓይነት የቀና ውይይት ባህል በኢትዮጵያውያኖች መሃል አይታይም:: ይህንን ስል የቀና ውይይት ባህል ፍፁም የለም ማለት ሳይሆን ዕድገቱ በእንጭጭ ደረጃ ላይ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል:: ለማንኛውም ውይይት ከመቅረባችን በፊት በግል ማሰብ ያለብን ምን ጥቅም እኔ አገኛለሁ ወይም የእኔ ወገን ያገኛል ሳይሆን ሁለቱም ወገኖች ከስምምነቱ እንዴት ይጠቀማሉ ነው:: የአገራችንን የሕዝብ አሰላለፍ ስናይ በሰባዊነት ተመርተን ማህበረሰባችን  የሰዎች ጥርቅም ነው ከማለት ይልቅ: ያለው አንድ የሰው ዘር መሆኑን ሳንገነዘብ:  በጎሳ ተከታትፈን ትልቁን የሰው ልጅ ጎሳ የእኛ ከማለት ትንሿ ሰው ሰራሹ ቁራጭ ጎሳነት ላይ በማተኮር ባህላችን የሆነውን ድህነት ልንላቀቀው አልቻልንም:: ድህነታችን የምግብ ዕጦት: የጤንነት ጉድለት: የልማት ወደ ሗላ  ቀርነት ብቻ ሳይሆን:በታላቅ ደረጃ የሚጎዳን የአስተሳሰብ  ድህነት በዕውቀት የላቁ ብለን በምናስባቸው ሰዎቻችን ላይ ጥቢጥቢ መጫወቱ ነው:: ይህንን የሃሳብ ድህነትና የአመለካከት  መንሻፈፍ እንዴት እንወጣዋለን? ለኢትዮጵያውያኖች ትምህርት ካመጣልን ጥቅም ጉዳቱ ይበልጣል:: ያልተማረው  ፈርሃ እግዚአብሔር  ያለው  የኢትዮጵያ ሕዝብ: ጎሳ:  ሃይማኖት ሳያይና ሳይል በአጠቃላይ ሰባዊነትን ታላቅ ክብር ሰጥቶ የሰው ልጅነትን ችቦ እያበራ  ለዘመናት አንድ ኢትዮጵያን ጠብቆ እስከ ዛሬ  አቆይቷል:: ታዲያ ምን ይደረግ! ተምሯል: ዲግሪ ይዟል:ተመራምሯል: አውቋል: ማመዛዘን ይችላል የተባለው ክፍል  ጦርነትን ማስወገድ: ድህነትን መዋጋት: እርሃብን ማጥፋት: በሽታን መከላከል: ማህይምነትን ማባረር  ትቶ: ለእነዚህ ለማህበረሰብ ዕድገትና የወደፊት እርምጃ  እንቅፋት ለሆኑት  በሽታዎች መስፋፋትና ለሕዝባችን ዕልቂት ምክንያት እየሆነ ይገኛል:: እኔ: የእኔ: የእኔ ወገን: የእኔ ጎሳ: የሚለው ግላዊነት: ወገናዊነትና ጎሰኛነት ኢትዮጵያውያን ምሁራንን የተማሩ ደንቆሮዎች ከማድረጉ በላይ ዛሬ አገሪቱ ላለችበት ጠንቅ ተጠያቂ  ያደርጋቸዋል:: ይህንን ስል ሁሉንም የአገራችንን ምሁራን ባንድ ላይ ለመደቆስ አይደለም:: የብዙሃኑ የኢትዮጵያ ምሁራን ትኩረት: ሳይደመጥ ሳይሰማ እንደሌለ ድምፁን አጥፍቶ መኖርን የመረጠ ነው:: ራሱን ችግር ውስጥ መክተት አይፈልግም:: እራሱን ገለልተኛ በማድረግ ከደሙ ንፁህ ለመሆን እጁን በመታጠብ ያስመሰከረ ድምፀ አልባ የሆነ የማህበረሰቡ ክፍል ነው:: ለሰባዊነት: ለሰው ልጅ ደህንነትና አንድነት  ድምፁን ቢያሰማ ደስ ያሰኛል:: ግን የሰው ልጆች በሰላም: በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩትን ባልሆነ በሆነው ከሚያጋጭና  ከሚያጋድል  ድርጊት ላይ ከመሰማራት ድምፀ አልባነቱ ይመረጣል:: የአንድ  ኢትዮጵያዊ  ጉዳት የሁሉም ኢትዮጵያውያኖች  ጉዳት መሆኑን የማይረዳ  የዚያች ደሃ አገር ተወላጅ: ሰባዊነቱ ሳያቀው ምን ያህል  ከውስጡ እንደተሟጠጠ እራሱን መመርመር  ይገባዋል:: የአማራ: የትግሬ: የኦሮሞ: የሃዲያ: የወላይታ: የሲዳማ: የጉጂ: የሱማሊ: የጋምቤላ: ወዘተ ተወላጅ ጉዳትና መፈናቀል የማንኛውም  ኢትዮጵያውያዊ ጉዳትና ጭንቀት እንደሆነ ሁላችንም መገንዘብ አለብን:: ምክንያቱም አንዱ የኢትዮጵያ ክፍል እየተጎዳና እየተሰቃየ ሌላው ሰላማዊ ኑሮ ይኖራል ማለት ዘበት ነው:: የጎረቤት ቤት እየተቃጠለ ሌላው ወፍራም  እንቅልፍ ይተኛል ብትሉኝ ስለሞተ ሰው ታወሩኛላችሁ እላላሁ እንጂ በሕይወት ስላለ ሰው ሊሆን አይችልም:: የአማራ ክልል ኢትዮጵያዊ እየተበጠበጠ: የአፋር ክልል ኢትዮጵያዊ እየታመሰ : የኦሮሞ ክልል ኢትዮጵያዊ እያለቀሰ: የትግራይ ክልል ኢትዮጵያዊ ልጁን ትክክለኛ ላልሆነ ጦርነት እየገበረ : የሱማሌ ክልል ኢትዮጵያዊ እየተገረፈ: የደቡብ ክልል ኢትዮጵያዊ እየተፈናቀለ: የጋምቤላ ክልል ኢትዮጵያዊ መሬቱን እየተቀማ ሌላው ፀጥታና ሰላም ይጎናፀፋል ማለት እውነትን አለመረዳት ነው:: ለምን አይሆንም ለሚል ሞኝ ሰው ማስታወስ የምወደው የአገርንና  የበረትን ተመሳሳይነት ነው:: አንድ በረት ውስጥ አንድ በጥባጭና ነገረኛ ከብት ካለ በረቱ ሲበጠበጥ ያድራል:: የበረቱ ሰላምና ፀጥታ የሚመለሰው ያ በጥባጭና ረባሽ ጥጋበኛ ወይፈን ከበረቱ ሲወገድ ወይም አንድ ትግስቱ ያለቀበት ሰላም ፈላጊ የበረቱ ነዋሪ ትልቅ በሬ  ያንን ነገረኛ ወይፈን ሲወጋው ወይም በአገራችን ውስጥ ለሰላሳ አመት በካድሬ የሚመራው የፖለቲካ ሂደት አኳያ አገርን የሚበጠብጡት ከርሳምና ራስወደድ የሆኑትን ጎሰኝነትንና ፅንፈኝነትን የሚያራምዱትን በውስጥ ወይም በውጭ ያሉትን ፀረ ኢትዮጵያውያንንና ፀረ አንድነት የሆኑትን የሰው አውሬዎችን ወግተንና ረግጠን ስናጠፋቸው ብቻ ነው:: የሰው ልጅ ማስተዋልና  ቻይነት አለው:: አንዱ ሌላውን በመጉዳት የሚያገኘው ጥቅም ዘለቄታ የለውም:: ተጎጂዉም ትእግስቱ መጠን የለሽ ስላልሆነ ትእግስቱ ሊያልቅበት ይችላል:: ያኔ የሚመጣው ግጭት ለማንኛቸውም አይበጅም:: በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የጠባብ ጎሰኝነት እንካ ሰላምታ ጠቅላላ አገሪቱን ጥፋት ውስጥ እየከተታት ይታያል:: በዚህ በጎሰኝነትና በፅንፈኝነት ቁምጥና አእምሮአቸው የተሰናከለባቸውን ግለሰቦችና በሕዝብ ደም የሚነግዱትን የግል ጥቅም ላይ ያተኮሩትን የፖለቲካ ዝሙቶችን ማስወገድ ተገቢ ነው:: የኦሮሞን : የአማራን : የትግራይን : የወላይታን : የሲዳማን : የጉራጌን : የሱማሌን : የአፋርን : የጉሙዝን : የጋምቤላን ወይም የማንኛውንም : ጠባብ ጎሰኝነትና : ፅንፈኝነትን ከኢትዮጵያ አስተዳደር ማላቀቅ የዶ/ር አቢይ አህመድ አስተዳደር ሥራ መሆን ተገቢ ነው:: በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ችግሩ ሰላም ማጣቱና ድህነቱ ነው:: ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለው ሕዝብ በእራብና በበሽታ እየተሰቃየ ይገኛል:: ኢትዮጵያ ያዘለችው: ምሳ ከበላ ለእራት እርግጠኛ ያልሆነ ሕዝብን ነው:: ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት አጥታ: ለም መሬት ሳይኖራት ቀርቶ ሳይሆን: ተምረው ይመሯታል  ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ምሁራን ሕዝብን አንድ አድርገው ልማት ላይ ከመስራት ይልቅ በጎሳና በሃይማኖት እየከፋፈሉ ሕዝብን ማጋጨት ቅድመ ስራቸው ስላአደረጉ ነው:: እነዚህ የበረት በጥባጭ ወይፈኖች የሆኑ ምሁራን በየጎሳው ውስጥ ተሰቅስቀው የረብሻ ጥሩንባቸውን እየነፉ በማያምኑበት ጉዳይ : እውነት የተናገሩ ለመምሰል የመብት ጥያቄን እንደ ዳዊት እየደገሙ ሕዝብን  እየደለሉ በሕዝብ መሃል ያለውን ሰላምና አንድነት እያናጉ ይገኛሉ:: ይህንን ስልም ማስረገጥ የምፈልገው አብዛኛው የኢትዮጵያ ምሁራን ከዚህ የተንኮል ሴራ ድርጊት ነፃ ነው:: ጥሩና ሰባዊነት የተሞላቸው ወገናዊና ጎሰኝነት ያልመረዛቸው ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊ ምሁራኖች አሉን:: ግን መድረኩን የተቆጣጠሩት ጎሰኛና ወገናዊ መርዝ የሚረጩ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው:: እነዚህ መርዘኞች የያዙት ድምፅ ማጉለያ በጣም ትልቅ ነው:: ኢትዮጵያውያኖች አብሮ መኖር: ሰላም: አንድነት: ህብረት: አብሮ መስራት: አብሮ ማደግ  ያስፈልጋቸዋል የሚለው ክፍል በጥባጮች የያዙትን ፀረ-ሰላም: ፀረ-እንድነት: ፀረ-ሕብረት: ፀረ-ጋርዮሽ ማራመጂያ የድምፅ ማጉሊያ መንጠቅ: ንቃተ ህሊና  ያለው የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ:: አንዳንድ ጠባብ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ተሳታፊዎች  ከባህር ማዶ ኑሮአቸውን መስርተው  የጥላቻና የጠብ እሳት በሐገሪቱ ላይ እየጫሩ ሲመቻቸው ውስጥ ገብተው : ከፋ ሲልባቸው ሮጠው  ከባህር ማዶ የምቾት ኑሮአቸውን በመኖር የግል ጥቅማቸውን ሲያራምዱ ይታያሉ:: ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ የሃይማኖት

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፈረስ ተቀይሯል!! ጋላቢው ማን ይሆን? - ጌድዮን በቀለ

መሪዎችና አስተማሪዎችም በሕዝብ አንድነትና ህብረት ላይ የሚፈፅሙት ደባና በደል ሊጠቀስ ይገባል::  በእስልምና ዕምነት ያሉትን ችግሮች ለመገምገም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ስላልሆንኩና ዕውቀቱ ስለሌለኝ ከመናገር እቆጠባለሁ:: የእስልምናና የክርስትና ሃይማኖቶች አንድ የጋራ መተሳሰሪያ ነገር አላቸው የምለው ሁለቱም በአንድ አምላክ ማመናቸው ነው:: ለአማኞች ሁሉ ያለው አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው:: ይህ አምላክ ግድያና ፍጅትን የማይቀበል ነው:: የሁለቱም ሃይማኖቶች  ግድያንና እግዚአብሔር በፈጠረው የሰው ልጅ ላይ ፍጅትን ማራመድ ኢሃይማኖታዊ መሆኑን ያስተምራሉ ብዬ እተማመንባቸዋለሁ::  ያውቁታልም:: ሆኖም  ችግሩ ከግድያና ከፍጅት ለመቆጠብ አለመቻል ነው:: ይህ የግል አመለካከቴ ነው:: ወደ እራሴ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ስመጣ: መፅሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንና የኛ ድርጊት ኩታ አይገጥሙም:: የትምህርቱን ፅንሰ ሃሳብ ተረድተን ተግባር ላይ ማዋል አልቻልንም:: እኛ ተማሪዎቹ ብቻ ሳንሆን የሃይማኖት አስተማሪዎቹም እውነትንና ሃቅን ምስክራቸው ለማድረግ ባለመቻላቸው  የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን እያቀጨጯት ይገኛሉ:: ይህን ችግር በአሜሪካ  ውስጥ በግልፅ ይታያል::  ያሉት ምእመናን በአንድ ቤተክርስትያን ውስጥ ተሰባስበው በአንድነት አምላካቸውን እንዳያመሰግኑ በአልሆነው በሆነው ሃይማኖታዊ ያልሆነ ችግር እየፈጠሩ ሕዝብን በማከፋፈል የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ወደ ውድቀት የሚመሩ የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች እንደ አሸን ከየስርቻው እየፈሉ ይገኛሉ::  እንደ ፖለቲከኞቹ የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎችም ለግላቸው እንደሚመቻቸው ያንን የዋህ ምእመናን እንደቅርጫ ስጋ እየተከፋፈሉት ይገኛሉ:: ለግል ጥቅማቸው ሲሉ አኩርፈው ጥለው ያመጣቸውን ቤተክርስትያን አዘግተው የግል ንብረት የሚያደርጉትን ሌላ ቤተክርስትያን ለመክፈት ሃይማኖታዊ አነጋገርን አስታከው ጉድ ሽር የሚሉ በአሜሪካ ከተማዎች በዝተዋል:: ታላላቅ የሃይማኖት መሪዎችም እንደ ግጭት ጫሪ ፖለቲከኞች ወገናዊና ቡድናዊ እየሆኑ ይቅርታን ሳይሆን ቁጭትን: ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን: አንድነትን ሳይሆን መከፋፈልን: አብሮ ማምለክን ሳይሆን ተለያይቶ መፀለይን: መመራረቅን ሳይሆን መረጋገምን በሰፊው እያናፈሱ ይታያሉ:: በሃይማኖት ረገድ የሃይማኖት አባቶች በተለይ ጳጳሳት የሁሉም አባቶች: ቻይዎች: ትእግስት የተጎናፀፉ: እስታራቂዎችና የፍቅር ችቦዎች ይመስሉኝ ነበር:: የወደዱትን ጥሩና የተቀደሰ: የተቀየሙትን እርኩሶች በማለት የስድብ አለንጋ ያለ አግባብ የሚሰነዝሩ አይመስሉኝም ነበር:: በሃይማኖት አኳያ ባለኝ ማህይምነት ሰለሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች የነበረኝ አመለካከት ቢሰደቡም ቢዋረዱም ይቅር ለእግዚአብሔር በማለት ትህትና:  ትእግስትና ማሳለፍን ያስተምራሉ የሚል ግምት ነበረኝ:: በስሜትነት ተመርተው የጠሉትን በየሄዱበት ቤተክርስትያን ሰበካ ላይ ስም እየጠቀሱ የእርግማኔ ውርጅብኝ ያወርዳሉ የሚል አስተሳሰብ አልነበረኝም:: እረጋ ብለው በጥሞና እኛ አማኞች ኃጢአተኞች መሆናችንን ተረድተው በተሰጣቸው  የሃይማኖት አባትነት ስለ ፍቅር: ስለ አንድነት: ስለ ሰባዊነት ያስተምራሉ ተብለው የሚጠበቁ ጳጳሳትና ካህናት በሚያሳዩት ባህሪ ምእመናኑን ተስፋ እያስቆረጡና እያሳዘኑ ይገኛሉ:: አዎን ከምእመናኑም ማህል ይህን ሃይማኖታዊ ክስረት አውቀውም ሆነ ሳያውቁ እንዲራመድ የሚያደርጉ አሉ:: ከእነዚህም ምእመናን በጣት የሚቆጠሩ ሆነ ብለው በሃይማኖት አስታከው የመከፋፈልን ፖለቲካ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ያካሂዳሉ:: ታቦትን ሳይሆን ለሰው የሚሰግዱም አልጠፉም:: ኧረ ጉድ ነው የደረስንበት የጨለማ ዘመን! ቤተክርስትያንን ለሰው ብሎ ጥሎ መሄድ! ሃይማኖት ለፖለቲካ ዓላማ ሲያገለግል! በዚህ አጋጣሚ በሃይማኖታቸው ፀንተው: እውነትንና ሃቅን የሕይወታቸው ምሰሶ አድርገው በመቆም: የንዋይ ፍቅር ሳይኖራቸው በነፃና ለመሳፈሪያ በማይበቃ ክፍያ ቤተርክስቲያናቸውንና ምእመናታቸውን በማገልገል ወንጌሉን የሚያስተምሩ ቅን ካህናት በየቦታው ይገኛሉ:: በወጣትነት ዘመኔ ሲኖዶስ ሁለት ቦታ ይከፈላል ተብሎ ቢነገረኝ ተናጋሪውን ምን ሰይጣን ወረረህ እለው ነበር:: የሃይማኖት መሪዎቻችንና አስተማሪዎቻችን የግል ጥቅም አሳዳጂዎች ይሆናሉ ብዬ አልገምትም ነበር:: ኢትዮጵያዊነት እንደዚህ የጎሳ ቅርጫ ትሆናለች ብዬ አስቢያትም አላውቅም:: እግዚኦ ማረን ክርስቶስ! ብለን ማለፍ ብቻ ነው::

ተጨማሪ ያንብቡ:  በድር ድርጅታችን ወደ የት እያመራ ነው? (ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን)

ስለዚህ  ይህንን በኢትዮጵያ  ላይ የሚያንዣብበውን የችግር ደመና ማስወገድ የሚቻለው እያንዳንዳችን ሰባዊነትን ተገንዝበን ሌላ ሰው ላይ የሚደርስው ጥቃት የእኔም ጥቃት ነው ብለን ስንረዳ ይሆናል:: ሌላው አሳሳቢና ጥልቅ ግንዛቤ ማድረግ ያለብን ነጥብ  በዳዴ ላይ ያለው የመልካም መንግስት አስተዳደር  ለውጥ እንዳይቀለበስ መጠንቀቅ ነው:: ሕይወት ማንም የፈለገውን ሁሉ አትሰጥም: አታሟላም:: እኛ ሚዛናዊ ከሆንን ሕይወት የምታቀርብልን ሚዛናዊ ነው:: ፍፁምነት በሰው ልጅ የሚታይ ባህርይ ስላልሆነ ከማንም ሰው ሆነ ከመንግስትም  መጠበቅ አይገባንም:: መንግስት የሕዝብ ከሆነ ሕዝብ መንግስት ላይ ችግር እንዳይደርስ ግዴታውን አውቆ ከመንግስት ጎን መቆም አስፈላጊ ነው::

ሃያ ስምንት ዓመታት ኢሰብዓዊነት የተሞላበትን የበሰበሰ ስርዓት በሶስት አመት ተኩል ቀልብሶ ማስተካከል ቀላል አይሆንም:: በወሬ ቀላል ነው:: በተግባር ቀላል አይደለም::  መረሳት የሌለበት ዛሬ ያለው አብላጩ የኢትዮጵያ ሕዝብ እድሜው ከ50 ዓመት በታች ነው:: ይህ አብላጩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደገው ጠባብ ጎሰኝነት እንደ ሃይማኖት ትምህርት እየተሰበከው ነው:: ይህንን አንድነት አጥፊ ዘረኝነት ወይም ጎሰኝነት ለማስወገድ የሁላችንንም ጥረት ይጠይቃል:: አንድነት ኃይል መሆኑን ማስተማር በዲያስፓራ ተበታትኖ የሚኖረው የኢትዮጵያ ተወላጅ ግዴታ ነበር:: ሃያ ስምንት ዓመታት ሙሉ በክልል ደረጃ  የተቀበረውን የጎሰኝነት መርዛም ቦንብ : የተለያየ ተጣራሪ የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚያንፀባርቁባት ኢትዮጵያ በሶስት አመታት ተኩል ጥፋቶችን ፈንቅላ ለማጥፋት ትቅርና አንድ ቋንቋ የሚናገርና አንድ ዓላማ የሚያራምድ አገርም የሚችል አይመስለኝም:: ስለዚህ መንግስት ያለሕዝብ ድጋፍ ወደ ፊት መራመድ አይችልም:: ምክንያቱም መንግስት የሕዝብ ተወካይና ጉዳይ አስፈፃሚ መሆኑን እናስተውል:: ለጥሩ መንግስታዊ አስተዳደር ሕዝብ የተቻለውን እርዳታ ማድረግ ይገባዋል:: ለማመስገንና ለማውገዝ መቸኮል የለብንም:: ይህንንም በአለፉት ሶስት አመታት ተኩል ዶ/ር አቢይንና ከጎናቸው የቆሙትን ባለስልጥናት የለውጥ ሐዋርያቶችን እያልን ስናቆላምጣቸው ስንቀድሳቸው ሃውልት ለማቆም ስንሯሯጥላቸው ነበር:: በሶስት አመት ተኩል እንዳልነበሩና እንዳልሰሩ እያረግናቸው ስንረግማቸው:ችግራችን ከራሳችን አመለካከትና ችኩልነት እንጂ ከእነሱ ሊሆን አይገባም:: በአጭር ጊዜ ወርቅ እናነጥፍላችሗለን ብለው የገቡልን ቃል ኪዳን የለም:: የተናገሩት የተጀመረው የለውጥ ሂደት በጣም ከባድና እንቅፋት የበዛበት መንገድ: የለውጡ ተራራ የረጠበ ቀይ መረሬ ጭቃ ስለሆነ ሲወጣ እያንሸራተተ አዳልጦ እንደሚጥል ነው::  ይህንን አስችጋሪ ተራራ ለመውጣት ሾኬ መመታት ሳይሆን ተያይዘንና ተደጋግፈን በአንድነት መጏዝ ያስፈልገናል:: በተለይ በዲያስፖራ የሚነቃነቁ አክትቪስቶች ለውጡን ማገዝ ካልቻሉ እንቅፋት አይሁኑ:: ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም:: የተጀመረው ለውጥ ጊዜ ይፈልጋል:: ሕዝብም ቅድመ አያቶቹም ሆኑ የበፊቱ ትውልዶች በደማቸውና በአጥንታቸው እንደ አንድ አገር ያስጠበቋትንና ሕዝብ አብሮ መኖርን እንዳስተማሩ መማር ይጠበቅበታል:: አንዱ ጎሳ ሌላውን ጎሳ አልበደለም:: በጥቂት ጥቅማቸውን ብቻ በሚያስጠብቁ ስግብግብ በሆኑ ስልጣንን የግል ሀብታ ማካበሪያ ባደረጉት ከሁሉም ጎሳዎች ተውጣጥተው ኢትዮጵያ ዛሬ ላለችበት ችግር ተጠያቂ በሚሆኑት ግለሰቦች  ሁሉም ጎሳዎች ተበድለዋል:: የአማራ ደሃ ሕዝብ የትግራይን ደሃ ሕዝብ : የትግራይ ደሃ ሕዝብ የኦሮሞን ደሃ ሕዝብ : የኦሮሞ ደሃ ሕዝብ የሶማሌን ደሃ ሕዝብ: ወዘተ አልበደለም:: ጠቅላላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፋፍለህ ግዛ መንግስታዊ አስተዳደር በእኩል ደረጃ ተብድሏል: ተጎድቷል: እየተጎዳም ነው:: ይህንን እውነት መክዳት አይቻልም:: ጣታችንን ከመቆሰራችን በፊት ነገሮችን አውጥተን አውርደን በማሰላሰል እራሳችንን መገምገም ተገቢ ነው:: ዛሬ ስለሕዝብ ጭፍጨፋና እልቂት እያጋነንን ብናወራ : የትኛው ሕዝብ ወይም የትኛው አገር ሕዝብ ተብለን ብንጠየቅ : አገር ከሌለ መልሳችን ስለጎሳ ወይም ብሔር ይሆናል ማለት ነው:: የአገር ልዑላዊነት በአስጊ ደረጃ ላይ እያለ ስለጎሳ ተበዳይነትና ስለመንግስት ውጤታማ አለመሆን ማውራት የነገሮችን ቅድመ ተከተል የማይውቅ ወይም የጁንታው ድብቅ አጋዢና ደጋፊ እንዲሁም የውጭ ጠላቶች ቅጥር ነው:: አገር ከጎሳ በላይ ናት:: ስለጎሳ መብት ከማውራት በፊት ለዘመናት  ከትውልድ ወደ ትውልድ በርሃብ የሚሰቃየውን ሕዝብ መመገብ ተገቢ ነው::  በዲያስፖራና  በአገር ውስጥ በተደላደለ ኑሮ እየኖሩ በርሃብ የሚሰቃየውን ሕዝብ ለችግር ማጋለጥ ኢሰባዊነት ነው::  እንዲያውም የሕዝብ መሰረታዊ ፍላጎት እስቲሳካ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሕግ እያስከበረ ልማትና እድገት ላይ የሚሰራና የሚያሰራ የቻይና አይነት መንግስት ነው:: መብት እያለ የሌላውን መብት ማክበር የማይችሉና ግዴታቸውን  የማይረዱ ፖለቲከኞች በበዙበት አገር ስለመብት ማውራት እንቆቅልሽ ነው:: ይህ የመብት ጥያቄ የከርሳም ፖለቲከኞች እንጅ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ አይደለም:: የሰፊ ሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ ሰላምና ርሃብን ማሸነፍ ነው:: ለዲሞክራሲ ሕዝባችን ገና ነው:: በቅድሚያ ሰላምና ምግብ ያግኝ:: ሕዝብ መንግስትን: መንግስት ሕዝብን መጥለፍ : በሾኬ መምታት ለቆምንለት የእድገትና የአገርን ልዑላዊነት የማስጠበቅን ዓላማ አያሳካልንም:: ሰከን ብለን ሰባዊነትንና ኢትዮጵዊነትን እናንፀባርቅ:: ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ያሽንፋሉ!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹የኦሮሙማን ጠቅላይ ጦር ሠፈር አውድም!!! የሜ/ጀኔራሎቹ የደም መሬት! Bombard the Orommuma Headquarter!››

1 Comment

  1. አልሚ ተናገሩኝ ብለሽ መጻፍ አለማቆምሽ ድንቅ ነው። መጻፍ ጥሩ ነው እዚህኛው ላይ ቢናገሩሽም እንዳላነበብሽ ተቆጥሮ እለፊው ጊዜ የማይሽረው የለም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share