የትኛውም የብአዴን አመራር ከሥልጣን ሊነሳ የሚችለው አንድም የመንግሥትን አካሄድ ሲቃወም፣ አንድም የሕዝብን በደል ተጋርቶ ሲያልጎመጉም የተገኘ ቀን ነው፡፡ አለቀ፡፡
በተረፈ ለሥርዓቱ ታማኝ መሆኑን እስካረጋገጠና የሕዝብን ጉዳይ ‹‹ምን አገባኝ›› በሚል ስሜት ማለፍ እስከቻለ ድረስ በስነ ምግባር ጉድለትም ሆነ በኪራይ ሰብሳቢነት ጎዳና ውስጥ ተዘፍቆ ቢገኝ የሚያባርረው ቀርቶ የሚገመግመው አይኖርም፡፡ እንደውም የተሻለ ሥልጣን ሊሰጠው ይችላል፡፡
ከዚህ አንጻር ከዓመታት በፊት አቶ ዘርዓይ አሰገዶምን እና አባይ ወልዱን ተጋፍጠው የህውሓት ውድቀት ላይ ጉልህ ሚና የተጫወቱት አቶ ገዱና አቶ ንጉሡ ጥላሁን ዛሬ ከሥልጣን የተገፉት በሆነ መድረክ ላይ የሕዝብን ሕመም የሚጋራ ንግግር አድርገው ካልሆነ በቀር ‹‹የአማራን ሕዝብ ባግባቡ እያገለገላችሁ አይደለም›› ተብለው አይመስለኝም፡፡
ያመኑበትን እውነታ ያለምንም ማቅማማት በመናገር እና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል የሚታወቁት አቶ ጸጋ አራጌና አቶ ዮሐንስም ተመሳሳይ እጣ ያጋጠማቸው ‹‹ለዙፋኔ እስከታመኑ ድረስ ቢሞስኑ ምን አገባችሁ›› ተብለው ካልሆነ በቀር በሥልጣናቸው ሲባልጉ ተገኝተው አይመስለኝም፡፡
ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን… በብልሹ ሥርዓት ውስጥ የሹመት እድገት የሚያገኙ አመራሮች መባረር ቀርቶ መታሰር የሚገባቸው ሲሆኑ የሚባረሩት ደግሞ የተሻሉት መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ዮሐንስ ቧያለውን፣ አቶ ጸጋ አራጌን እና አቶ ንጉሡን ከሥልጣናቸው ያነሳው አካል በቅርቡ ደግሞ ጠባቂዎቻቸውን ማንሳቱን እየሰማን ነው፡፡
ከሕዝብ የሚነጥል ጥፋት ቢያገኝባቸው ኖሮ ዶክመንታሪ ሠርቶ ከማሰራጨት ወደኋላ የማይለው መንግሥት የፈጸሙት ጥፋት ከሕዝብ የሚቀላቅል መስሎ ስለታየው ከወንበርም አልፎ ወደ መቃብር ሊያወርዳቸው ድምጹን አጥፍቶ እየተሳበ ነው፡፡
ሆኖም ግን የማካቬሌ አስተምህሮ ‹‹ከሕዝብ ጉያ ሳታወጣ- ተቀናቃኝህን አትቅጣ›› የሚል ምክር የሚሰጥ በመሆኑ… ይሄን ተልዕኮ የወሰዱ ተላላኪዎችም እኒህ አመራሮች ከመንግሥት ጥርስ ውስጥ ባስገባቸው ጥፋት ፈንታ በሥልጣን ዘመናቸው የፈጸሙትንና በሕዝብ የሚታወቀውን ስህተት መንቀስ ጀምረዋል፡፡
እኔ ግን እልኻለሁ…
እንዲህ ያለው መንቻካ ክስ በትናንት ጥፋት ተጸጽተው ወደ ትክክለኛ ጎዳና ለመግባት የሚያስቡ ባለሥልጣናትን የሚያከስም መሆኑን አውቀህ እኒህን አመራሮች ከሥልጣናቸው ባለፈ ጠባቂዎቻቸውን እስከማንሳት ያደረሰውን ምክንያት ወይም ጥፋት እስክታውቅ ድረስ ጠባቂያቸው ሁን፡፡