መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ከኢሳት የተለዩ ጋዜጠኞች ከሚዲያ ተቋሙ ጋር የተለዩበትን ምክንያት ለህዝብ ይፋ ባደረጉበት ወቅት በተደጋጋሚ የፓርቲያችንን ሥም በሐሰት በመወንጀል ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሥም ከሚድያ ባለቤትነት እንዲሁም ለኢሳት የተሰበሰበ ገንዘብን ከመውሰድ ጋር ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡
ፓርቲያችን በጋዜጠኞቹ የቀረበበትን ሥም ማጥፋት ፈፅሞ አይቀበልም፡፡ ኢዜማ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የሚድያ ተቋምን በባለቤትነት ከያዘ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትልቅ እንቅፋት እንደሚፈጥር የሚያምን ሲሆን ይህ በአገራችን ህግም በግልፅ የተከለከለ ነው። ስለሆነም ኢዜማ በእንዲህ ያለ ድርጊት ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም በጥብቅ ይታገላል፡፡
ለኢሳት የተሰበሰበ ገንዘብ ለፓርቲያችን ኢዜማ ተላልፏል የተባለውም የፈጠራ ክስ ነው። ገንዘቡ በማን አካውንት እንዳለ የቦርድ አባላቱ እና አሁን በኢሳት ውስጥ ያሉትም ሆነ ተለየን የሚሉት ጋዜጠኞች በሚገባ የሚያውቁት ሃቅ ነው።
እንዲህ አይነት አሉባልታዎች የፖለቲካ ባህል እየሆኑ የመጡበትን ሁኔታ የምንገነዘብ ቢሆንም የሙያ ስነ-ምግባር አላቸው ብለን ከምናምናቸው እና ሰፊ ልምድ ካካበቱ ጋዜጠኞች ያልጠበቅነው በመሆኑ ሀፍረት እንደተሰማን ለመግለፅ እንወዳለን።
በመጨረሻም ኢዜማን በግልፅ በከሰሳችሁበት የሚድያ ባለቤትነት ጉዳይ፣ እንዲሁም ለኢሳት ተሰብስቦ ለፓርቲያችን ተላልፏል ስላላችሁት ገንዘብ ያላችሁን ማስረጃ ለህዝብ በግልፅ እንድታቀርቡ፣ ያለዚያ እውነቱን እያወቃችሁ የዋሻችሁት ህዝብ ፊት ፓርቲያችንን በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቁ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
ኢዜማ በጠንካራ የድርጅት ባህል እና ሀላፊነት በሚሰማው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
መጋቢት 18 ቀን 2014 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ