ምዕራብ ጎጃም የተጠለሉ ተፈናቃዮች አቤቱታ

ከኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በነበሩና አሁንም በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ከአለፈው ዓመት ጀምሮ እየተፈናቀሉ ወደ አማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም የደረሱ ተፈናቃዮች አስፈላጊው እርዳታ አልተደረገልንም፣ መንግስት በዘላቂነትም ሊያቋቁመን አልቻለም ሲሉ ያሳስባሉ።

መንግስት በበኩሉ ከሚመጣው ተፈናቃይ ቁጥር አንፃርና ካለው የእርዳታ እህል እጥረት አኳያ ችግሮች መኖራቸውን አምኗል፡፡ ተፈናቃዮቹ በነበሩባቸው አካባቢዎች ሀብት አፍርተው ልጅ ወልደውና ለቁምነገር ባደረሱበት አካባቢ በማንነታቸው ብቻ እየተሳደዱ እንደሆነ ነው ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት፡፡ በተለይ ከወለጋ እንደተፈናቀሉ የሚናገሩ አንድ ተፈናቃይ በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው ኦነግ ሸኔ በተባለ ታጣቂ ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን አስረድተዋል፡፡
ምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከደረሱ በኋላም ምንም እርዳታ ባለማግኘታቸው ሲፈናቀሉ ይዘው የመጡትን አብቃቅተው እየኖሩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
“የምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ምላሽ ሊሰጠን ባለመቻሉ በ200ሺዎች የምንቆጠር ተፈናቃዮች ለክልሉ መንግስት ለማሳወቅ ወደ ባሕር ዳር በእግር እየተጓዝን ነው” ሲል ሌላው ተፈናቃይ አመልክቷል፡፡
ቀደም ሲል አቤቱታቸውን ለማሰማት ከምዕራብ ጎጅም ተነስተው ባህር ዳር ከተማ ከደረሱት መካከል አንድ ተፈናቃይ የሚላክልን የስንዴ ቀለብ ባግባቡ እየደረሰ አይደለም ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ መንግስት ዘላቂ መፍትሔ ይፈልግልን፣ ትኩረት ተነፍገናል ነው የሚሉት፡፡

amhara ተፈናቃዮች በባህር ዳር

የምዕራብ ጎጃም ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተዋቸው ዓለማየሁ በዞኑ ከ290 ሺህ በላይ ነባርና ሌሎች በርካታ አዳዲስ ተፈናቃዮች መኖራቸውን አመልክተው፣ መንግስት ቀደም ሲል ከፈቀደው አቅርቦት መካከል አሁን የተፈቀደው 70 ከመቶ ብቻ መሆኑና የተፈናቃይ ቁጥር መጨመሩ ለችግሩ መባባስ ዋና ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን በበኩላቸው ከ250ሺህ በላይ ተፈናቃይ በዞኑ እንደሚኖር አስታውሰው፣ እርዳታ ባልተቆራረጠ ሁኔታ እንዲደርስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ያለው የተፈናቃይ ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ አሁን ከአንድ ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ መድረሱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ልደት አበበ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዕዉነት እና ለነፃነት የምንኖረዉ መቸ ይሆን ? -

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share