ነገሩ ግራ ገብቶኝ እኔን ነው? ብዬ ኼድኩ። “አዎ አንተን ነው።” አለ መንገዱን ተሻግሮ ወዳለ ወጣት ማእከል እያመለከተና እምባ እየተናነቀው “በወለጋ ከመታረድ ተርፈው የመጡ ንፁሐን አማራዎች ናቸው። ይኸው መኮሮኒ ላቀብላቸው ብዬ ብመጣ ተከለከልኩ። ሰው በገዛ ሀገሩ ከመታረድ አምልጦ ሲመጣ እንኳን በረሀብ እንዲሞት ይፈረድበታል?” በእልህ እየነገረኝ ነበር። “መኪናውን አዙረውና እንሞክር” አልኩ።
መኪናውን በማዞር ላይ ሳለ አንዲት የግቢው አስተባባሪ ናት የተባለች እህት መጥታ “እኛም ጨነቀንኮ በቃ ያሉኝን ይበሉኝ ሰው በረሐብ ሲሞት አላይም የያዝከውን አስገባና አብስለው ይብሉ” አለች። ፖሊስ አልታዘዝኩም ቢልም ሴትየዋ ፈቅዳልናለች ብለን ሩዝና መኮረኒውን (25/25ኪሎ) አውርደን ወደበሩ ተጠጋን ከውስጥ ንፁሐኑ ቆዝመዋል። እናቶች በረሀብ ይቁለጨለጫሉ፤ህፃናት (የታዘሉትን ጨምሮ)ይላቀሳሉ። መጠጋት አቃተኝ ወጣቶች መጥተው ተቀብለውን ገቡ። ሰውየው መውረጃዬ ደርሶ እስኪያወርደኝ እያለቀሰ ነበር።
እነዚሁ ንፁሐን ከሰአት በኋላ ከማእከሉ ውጡ ተብለው ጃንሜዳ አስፋልት ላይ ተበተኑ። ወጣት ማእከሉ ውስጥ ለጥቂት ቀናት የቆዩትም ወረዳው ላይ ባለ ሰብዐዊነት በሚሰማው አንድ አመራር እንደሆነና ይኸው ሰው “በበላይ አካል” በአስቸኳይ አስወጣ የሚል ማስፈራሪያ እንደደረሰበት እያለቀሰ ለተፈናቃዮቹ መጥቶ እንደነገራቸው ሰምቻለሁ።
ጃንሜዳ መውደቃቸውን ጥቂት ሚዲያዎችና የባልደራስ አመራሮች መናገራቸውን ተከትሎ ዛሬ ደግሞ “አዲስ አበባን አታቆሽሹ” ተብለው ወደ ደብረብርሀን መሸኘታቸውን ሰማን። ሰው በገዛ ሀገሩ ለምን ከሞት ተረፍክ ተብሎ መሳደድ አለበት? ይህ ተግባርስ ለምን ከሞት ተረፋችሁ ማለት አይደለም? አንገት ደፍተን ሁሉን እስከተቀበልን ድረስ ግፈኞች አይረኩም። አንዳንዴ እምቢታም ጥሩ ነው።
ተዋርደን አንቀርም!!