ግድፈቶችን በውስጣዊ ሥርዓት በማረምና አንድነታችንን በመጠበቅ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ኢዜማዊ ማህትማችንን ማሳረፋችንን እንቀጥላልን!

/

ሀገራችን ኢትዮጵያ እጅግ በተወሳሰቡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች፡፡ እኛም ዘመኑን የሚዋጅ፣ ወቅቱን ያገናዘበ፣ የሀገርን እና የህዝብን ጥቅም ያስቀደመ ሥራ መስራት ከምንጊዜውም በላይ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን እናምናለን፤ ፓርቲያችን ሀገራችን በምትፈልገው የኃላፊነት ልክ ዝግጁ እና ብቁ ሆኖ መገኘቱን በየጊዜው እየገመገምን መልካሙን እያጠናከርን ጉድለቶችን እየሞላን መጓዝን አጽንዖት ሰጥተን የምንተገብረው ጉዳይ መሆኑንም እንረዳለን።

የኢዜማ አባላት እና ደጋፊዎች እንደሚተጉትና እንደልፋታቸው፤ የሀገሪቱን ፖለቲካ በቅጡ የሚረዳ፣ ጠንካራ መዋቅራዊ ቁመና ያለው፣ አባላት እና አመራሩ ለስርዓት እና ድርጅቱ ላወጣቸው መርሆች ተገዢ የሆኑለት ድርጅት መሆኑን በየጊዜው መከታተል እና ጉድለቶች ሲኖሩ ማረም ድርጅታዊ ባህሉ እንዲሆን የሚተጋ አመራር ያለው ፓርቲ ነው፡፡ በአባላት፣ ደጋፊዎች እና በህዝባቸን የተጣለብንን ኃላፊነት ፓርቲያችንን የበለጠ ጠንካራ ቁመናና አፈጻጸም ያለው በማድረግ ልንወጣ ይገባናል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) ብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ጭምር ሲደረጉ የነበሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ምልልሶችን ጥር 25 ቀን፣ 2014 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ በሰፊው ተመልክቶ ተወያይቷል፡፡

የብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፣በሀገር ደረጃ አንድ ፓርቲ መልካም የሆነ ስርዓትን በማስፈን ሂደት ውስጥ በጎ ተፅዕኖ የሚኖረው በውስጥ አሰራሩ የፓርቲን ዲሲፕሊን የተለማመዱና ለፓርቲው ደንብ የሚገዙ አመራሮችን ያቀፈ ፓርቲ ሲሆን ነው ብሎ ያምናል፡፡ ወደተሻለ ነገ ለመድረስ ዛሬ ላይ የሚፈጠሩ ግድፈቶችን ማረምና ጉብጠቶችን ማቃናት እንደዚሁም ጥፋቶችን ማስተካከል እጅጉን አስፈላጊ እንደሆነ መግባባት ላይ በመድረስ የኢዜማ ከፍተኛ አመራሮች የፓርቲውን በርካታ የመወያያ መድረኮችና ስርዓታዊ አካሄዶች ተራምደው በማኅበራዊ ሚዲያ ተገቢ ያልሆኑ የሃሳብ ልውውጦችን ማድረጋቸው ስህተት እና የዲሲፕሊን ግድፈት መሆኑን በሙሉ ድምፅ ተስማምቷል፡፡ በመሆኑም ለፓርቲው የህገ-ደንብ ትርጉምና ዲስፕሊን ኮሚቴ የሚቀርበውን ሰነድ ለማጠናቀር አጣሪ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን ተፈፀሙ የተባሉ የስነ-ስርዓአት ግድፈቶችን አጠናቅሮ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሪፖርት እንዲያደርግ ወስኗል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በቂሊንጦ ግንቦት 7 ነው ተብሎ የታሰረው ወጣት 10 ጥፍሮቹን ነቅለው ብልቱ ላይ የላስቲክ ውሃ አንጠልጥለው እንዳሰቃዩት ተጋለጠ

ከምርጫ ወረዳዎች እስከ ማዕከል ባለው የኢዜማ አደረጃጀት የተዋቀሩ የህገ-ደንብ ትርጉምና ዲስፕሊን ኮሚቴዎች የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና የዲስፕሊን መመሪያዎችን በማያከብሩ አመራርና አባላት ላይ ጥብቅ ክትትል እያደረጉ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ውሳኔ ተላለፏል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢዜማ ሥም በተከፈቱና የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት እንዲሁም ሌሎች መምሪያዎች የማያስተዳድሯቸው ኢዜማን የማይመጥኑ፣ ለፀብና አምባጓሮ መጠንሰሻ የሆኑ የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገፆችን ከሚያስተዳድሯቸው አባላት ጋር በመነጋገር በፍጥነት የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ እያሳወቅን ለዚህም ስራ የትስስር ገፆችን የሚያስተዳድሩ አካላት ለሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ትብብር እንዲያደርጉ እናሳስባለን፡፡

ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በከፍተኛ ሁኔታ የምንደግፈውና የምንታገልለት ወደፊትም ሰፋፊ መድረኮችን በማዘጋጀት የምናዳብረው ቢሆንም ባልተገራ፣ ስነ-ምግባር በሌለውና የፓርቲውን አሰራር ባልጠበቀ መንገድ የሚደረግ የትኛውም አይነት ምልልስ ኢዜማን ለማጠንከር ዘለግ ሲልም የኢትዮጵያችንን ችግሮች ለመፍታት የሚጨምረው ቅንጣት ታህል አስተዋጽዖ ካለመኖሩም በላይ አብሮና ተከባብሮ የመስራት ባህላችንን በመሸርሸር፣ጉዟችንን ረጅም፣ውስብስብ እና አድካሚ ያደርግብናል፡፡

ዛሬም ኢዜማ የትኞቹንም አይነት ልዩነቶች በዲሞክራሲያዊ የውይይት ስርዓት እየፈታ እንደ አለት እየጠነከረ ለአባላትና ደጋፊዎቹ ኩራት ለሀገራችን ኢትዮጵያም ተስፋ እንደሆነ በፅናት ይቀጥላል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ)

ብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ጥር 26 ቀን፣2014 ዓ.ም

አዲሰ አበባ

1 Comment

  1. መከረኛው የአገሬህ ዝብ በሥልጣነ መንበር ላይ ለዘመናት በተፈራረቁና አሁንም በዚያው እጅግ አስከፊ በሆነ ምህዋር ላይ መሽከራቸውን በቀጠሉ ሸፍጠኛ፣ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖች እና ግብረ በላዎቻቸው ምክንያት በድንቁርና፣ በፍፁም የድህነት አኗኗር (መኖር ከተባለ) ፣በበሽታ ፣ በአስከፊ ፖለቲካ ወለድ አረመኔያዊ ግድያና በቁም ሰቆቃ (በቁም ሞት) ፣ ወዘተ አዙሪት ውስጥ እንዲቀጥል የመደረጉን ግዙፍና መሪር እውነት ለማስተባበል መሞከር የለየለት የፖለቲካ አስተሳሰብ ስንኩልነት እና የሞራል ውድቀት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
    በመጀመሪያ ስለ “የተፎካካሪ ፓርቲ” ተብየው ኢዜማ ስንነጋገር የምንነጋገረው በውስጡ ካሉ አመራር እና አባላት ብሎም ደጋፊዎች ለይተን ወይም ነጥለን አይደለም። የየትኛውንም የፖለቲካ ወይም ሌላ አይነት ቡድን (ድርጅት) ጥንካሬ ወይም ደካማነት በአመራር ላይ ከተሰየሙ ግለሰቦች ፣ አባላት እና ደጋፊዎች ነጥሎ ማየት ከቶ አይቻልም። አንዳንድ ግለሰቦችን በስም እየጠቀስን ወይም በደምሳሳው እገሌ ቅን አሳቢ፧ እገሌ ነገር አዋቂ፣ እገሌ ዲስኩር አዋቂ፣ እገሌ የተማረ ፣ እገሌ ዶ/ር ወይም ፕሮፌሰር ፣ እገሌ የህዝብ ተቆርቋሪ፣ እገሌ ግብረገባዊ፣ እገሌ ግሩም ተንታኝ፣ እገሌ ሰላምና ፍቅር ሰባኪ፣ እገሌ ብልፅግና ናፋቂ፣ ወዘተ ከማለት እና ለሌሎችን ደግሞ ተቃራኒ የሆነ የባህሪ ስያሜ በመስጠት የሚደረግ የድርጅት እይታ በእራሱ ወይ የለየለት ድንቁርና ወይንም የአድርባይነት ደዌ ነው። የትኛውም ሥርዓት ወይም ድርጅት የግለሰቦች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን እና የግለሰቦች በጎ ወይም አፍራሽ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ የእይታችን ትኩረት መሆን ያለበት ግን ድርጅቱ ወይም ሥርዓቱ እንደ ድርጅት ወይም እንደ ሥርዓት ምን አደረገና ምን እያደረገ ነው? በሚል ፈታኝ ጥያቄ ላይ እንጅ ይህ ወይም ያ ግለሰብ እና እነዚህ ወይም እነዚያ ግለሰቦች በሚል እጅግ ቁንፅልና አሳሳች እይታ ላይ መሆን የለበትም። ለዚህ ነው በኢዜማ ውስጥ እኮ ጥቂት እውነተኛለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉና የሚሠሩ ግለሰቦች አሉና … የሚለው ማስተዛዘኛ አይነት አመለካከት ጨርሶ ወንዝ የማያሻግረው።
    የምናወራው ስለ ግለሰቦች ቅን ወይም የተወላገደ ባህሪና አካሄድ ሳይሆን ግለሰቦቹ እንደ ቡድን ወይም እንደ ሥርዓት አባልነታቸው አነሳሱና አካሄዱ ከራሱ አልፎ የህዝብን የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ሥርዓት ፍለጋ ተጋድሎ የሚያጨናግፍ (የሚያመክን) አስተሳሰብና ቁመና የተጠናወተውን ቡድናቸውን ወይም ፓርቲያቸውን በወቅቱና በአግባቡ ለማስተካከል ምን ያህል ጥረዋል? አሁንስ ምን እያደረጉ ነው? ከሚል መሠረታዊ ጥያቄ አንፃር ባለመሆኑ ከክስተቶች የትኩሳት መጠን ጋር ከፍና ዝቅ ከሚል እጅግ አስቀያሜ የፖለቲካ አዙሪት ለመውጣት ከቶ አልተቻለንም።
    በሌላ አገላለፅ የትክክለኛና እውነተኛ የፓርቲ ፖለቲካ (genuine and appropriate party politics) ለውጥ ሃዲዱን በመሳት ለእራሳቸው “ብልፅግና” የሚል እጅግ አሳሳች (highly deceptive) ስያሜ በመስጠት የቤተ መንግሥት ፖለቲካውን በተረኝነት ከተቆጣጠሩት ሸፍጠኛ ፣ሴረኛ፣ ፈሪ ጨካኝ የኢህአዴግ አንጃ (faction) ቡድኖች ጋር ያልተቀደሰ (unholy) ጋብቻ በመፈፀም እነ አብይን (“የለውጥ ሃዋርያትን”) መቶ በመቶ (ከራሱና ከእራሱ ፓርቲ ተብየ) በላይ እንደሚያምናቸው መሪ ተብየው ያለምንም ሃፍረት (እንዲያውም በኩራት ) የነገረንን ኢዜማ ከላይ በተገለፀው አጭር የፖለቲካ ድርሰት ለመሸፋፈን መሞከር ከስህተት ያለመማር እጅግ አስቀያሜ የፖለቲካ አስተሳሰብ ደዌ ነው። መሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግዙፍና መሪር ሃቅ ጋር እንኳን ለማጣጣም ለማስመሰለም ፈፅሞ አይቻልም።
    የግንቦት ሰባት መሪዎች በመሆን ቅጥፈት በተሞላበት (እጅግ አሳሳች) ዲስኩር በየአደባባዩና በየአዳራሹ ሲያስጨበጭቡን ቆይተው ሥርዓት ባልተለወጠበት ወይም እንዲለወጥ የሚያስችል የፖለቲካ ሃይል በሌለበት የኢህዴግ አንጃ “የለውጥ ሃይል” ተለጣፊዎች በመሆን የመከረኛውን ህዝብ የመከራና የውርደት እድሜ እንዲራዘም ማድረጋቸውን ለመረዳት ቅንና ሚዛኑዊ ህሊና ብቻ በቂ ነው። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቸግር በቅን ልቦና እና በጠንካራ ድርጅታዊ ይዘትና ቁመና የመታገል እንጅ መሪ እና ሊቀ መንበር የሚል የአደረጃት እርከን (ዝባ ዝንኬ) መፍጠር ያለመቻል ጉዳይ ይመስል “ኢዜማችን ልዩ ነው” ሲሉን ህሊናቸውን ጨርሶ አይጎረብጣቸውም።
    ከላይ የሚያስነብቡንን የፖለቲካ ድርሰታቸውን ዘመኑን የዋጀ፣ ወቅቱን ያገናዘበ፣ የአገርንና የህዝብን ጥቅም ያስቀደመ ፣ ወዘተ በሚል ቅድመ ሃሳብ (መንደርደሪያ) ለማንቆለጳጰስ ሲሞክሩ ይሉኝታ የሚባል የህሊና ዳኝነት ጨርሶ የላቸውም።
    ሁለቱ የኢህአዴግ አንጃዎች (ህወሃት እና ብልፅግና ተብየው) በሥልጣን የበላይነት ሽኩቻ ምክንያት በፈጠሩት ውዥንብርና ጦርነት በመከረኛው ህዝብ ላይ ታይቶ የማይታወቅ ሰቆቃና እልቂት ሲደርስበት እንኳንስ በድርጊት ትርጉም ባለው የቃል ወይም የወረቀት ላይ መግለጫ የመሞገትና የማውገዝ ወኔው ሳይኖራቸው አሁን ደግሞ እንዲህ ዓይነት ድርሰታቸውን ከምር እንወስድላቸው ዘንድ ጫጭረው (ፅፈው) ሲለጥፉልን እናንተ እነማን ናችሁ? በሎ መጠየቅ ተገቢ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
    በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን እነዚህ የኢዜማ መሪዎች የአስከፊ ተለጣፊነት (አሽከርነት) ልክፍተኞች ከሆኑት እና የአማራን ማህበረሰብ በተለይ እና የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ ከመከራና ከውርደት ሥርዓት እንዳይላቀቅ ካደረጉት ብአዴናዊያን ፣ እና እጅግ አሳፋሪ በሆነ አኳኋን ፖለቲካን እስከ ሚኒስተርነትና የተከበሩ የፓርላማ አባልነት ለሚደርስ የጥቅም ወይም የፍርፋሪ ማስገኛ ወይም መልቀሚያ ካደረጉት አብን ተብየዎች በምን ትለያላችሁ? ተብለው ቢጠየቁ ከዚያው ከለመደማቸው የቅጥፈት ዲስኩር የተሻለ መልስ አይኖራቸውም።
    “በሁለንተናው የተሟላለት ድርጅት መሪዎች ስለሆን ዲሲፕሊን በሚጥሱት ላይ ተገቢውን እርምትና ሌላም እርምጃ እንውስዳለን” ሲሉን ስለ የትኛው እውነተኛና ገንቢ ዲሲፕሊናችሁ ነው የምታወሩት? ግዙፍና መሪር መስወእትነት በተከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጅማሮ ላይ የበረዶ ውሃ ቸልሶ ከሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ተረኛ የኢህአዴግ አንጃ (ብልፅግና ተብየ) ጋር በፖለቲካ አመንዝራነት ከመተሻሸት የከፋ (የባሰ) የበጎ ዲሲፕሊን ፣ ራእይ፣ መርህ፣ ዓላማና ግብ ዝቅጠት (ውድቀት) አለ እንዴ? ብለን በግልፅና በቀጥታ መጠየቅ የግድ ነው።
    አዎ! ከእንዲህ አይነት እጅግ ወራዳና አዋራጅ የፖለቲካ አስተሳሰብና የሞራል ድህነት በአሸናፊነት መውጣት ካለብን እስከዚህ ድረስ ነው መነጋገር ያለብን። ኢዜማ ተብየውን በእጅ መንሻነት (በሥጦታ መልክ) አስረክበው የሚኒስትርነት ሹመት ሲቸራቸው ህሊናቸውን ሳይጠይቁና አይናቸውን ሳያሹ በመቀበል የሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ተረኛ ኢህአዴጋያን/ብልፅግናዊያን ፖሊሲና ፕሮግራም አስፈፃሚ በሆኑ ኢዜማዊያን የፖለቲካ ጨዋታ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ትሆናለች ብሎ መጠበቅ ወይም የለየለት ድንቁርና ወይም የምን አገባኝነት ደዌ ወይንም የአስከፊ አድርባይነት (ልክክስክስነት) ልክፍት ነው ።
    በእንዲህ አይነት እጅግ ግልፅና ግልፅ የወረደና አዋራጅ የአሽከርነት (የተለጣፊነት) ፖለቲካ አረንቋ (disgraceful political quagmire) ውስጥ ተዘፍቆ “ልዩነቶችን በዴሞክራሲያዊ ወይይት እየፈታን እና እንደ አለት እየጠነከርን እንቀጥላለን” የሚለውን የወረቀት ላይ ድርሰት በመሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር እንኳን ማጣጣም ማመሳሰልም ጨርሶ አይቻልምና የሚሻለው ሃቁን ተጋፍጦ እራስን ከተዘፈቁበት ክፉ አዙሪት ለማውጣት እጥፍ ድርብ ጥረት ማድረግ ነው!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share