አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ፈተናዎችን አልፋለች። አሁን ያለችበት ፈተና ግን እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው። በፊቷ የተደቀኑ በርካታ አደጋዎች በቶሎ እንዲቀረፉ ካልተሰራ ምን አልባትም በቅርብ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ላትኖርም ትችላለች።
ከአራት አመታት በፊት መደመር በሚል ፣ ለውጥ የተባለው በመጣ ጊዜ፣ ከምድር ጫፍ እስከ ምድር ጫፍ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ተስፋ ሰንቀው ነበር። የኢትዮጵያ ትንሳኤ እየመጣ ነው በሚል የደስታ ድባብ ሰፍኖ ነበር። ሆኖም ግን በአራት አመት ውስጥ መደመርን ሳይሆን መፈናቀልን፣ ጄኖሳይዶችን፣ ጭፍጨፋዎችንና የሚሊዮኖች መቀነስን ነው ያየነው። ሰላምን ሳይሆን ደም መፋሰስንና ጦርነትን፣ ብልጽግናን ሳይሆን ድህነትና ረሃብን ነው ያየነው።
አገራችን አሁን ባለችበት ቀውስ ውስጥ መግባቷ አንዱ ምክንያት የሕወሃትና የኦነግ አሽባሪ ቡድኖች ተግባራት መሆናቸው የሚካድ አይደለም። ነገር ግን ሕዝብን ከነዚህ አሽባሪዎች ሆነ ከሌሎች አገራዊ አደጋዎች የመጠበቅ ሃላፊነት ያለበት የብልጽግና መንግስትን እንደ መንግስት መስራት ያለበት መስራት ባለመቻሉ፣ ከኦነግና ከሕወሃት ባልተናነሰ ተጠያቂ ነው።
በቅርቡ ሕወሃትና ኦነግ በአገራችን ክፍል በከፈቱት ጦርነት ብዙ ጥፋት አይተናል። በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት ፣ ፈጽመዋል። ዜጎችን በጅምላ ጨፍጭፈዋል። እናቶቻችንና እህቶቻችን የጾታ ጥቃቶች ደርሶባቸዋል። የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ሕልፈት ምክንያት ሆነዋል።
መንግስት ሃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉም፣ “ከአቅሜ በላይ ነው። በመደበኛ የወታደራዊ አደረጃጃት የኦነግና የሕወሃት ጥቃት መመከት አይቻልም” በሚል፣ ለሕዝብ ባደረገው ጥሪ መሰረት፣ ሕዝብ፣ የአማራና የአፋር ልዩ ኃይሎችና ሚሊሺያዎች፣ የአፋር አርብቶ አደሮች፣ የራሳ ገበሬዎች፣ ፋኖዎች ከመከላከያ ጋር በመሆን፣ ሕወሃትን በበርካታ የአማራና የአፋር ክልል ወረዳዎች ነጻ ማውጣት ችለዋል። በዚህ ሂደት ቀላል የማይባሉ ወገኖች ውድ ሕይወታቸውን ገበረዋል።
ሆኖም መጀመሪያዉኑ አገር እዚህ ደረጃ እንዳትደርስ ስራዉን መስራት ያልቻለው፣ በዶር አብይ አህመድ የሚመራው፣ የብልጽግና መንግስት፣ በሕዝብ የተገኘን ድል መልሶ በመቀልበስ፣ ሕወሃቶች ትግራይን ብቻ ሳይሆን ራያንና ጠለምትን እንደያዙ እንዲቀጥሉ፣ መከላከያ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲቆም ወስኗል። ያ ብቻ አይደለም፣ በጦርነቱ የታሰሩ፣ አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ሌሎች የሕወሃት የጦር እስረኞች ለቀዋል።
የብልጽግና መንግስት ወደዚህ ውሳኔ እንዴት ሊመጣ እንደቻለ በዝርዝር የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ ህወሃቶች አሁንም በአማራና በአፋር ክልል ውጊያዎች እያደረጉ ባለበት ሁኔታ ፣ ጦርነቱ ገና ሳያልቅ፣ ህዝቡን አሁን አደጋ ላይ እያለ፣ የሕወሃት ሰዎችን መልቀቅ ተገቢ ነው የሚል እምነት የለንም። በተለይም በአፋርና በአማራ ክልል የተከፈለውን መስዋትነት ያረከሰ፣ በአማራና በአፋር ክልል ላይ የተፈጸመ ትልቅ ክህደት ነው እንላለን።
ይህ ክህደት በቀላሉ መወሰደ አለበት ብለን አናምን። የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የአማራና የአፋር ክልል መጠየቅ አለበት፣ ዝም ማለት የለበትም ብለን እናምናለን። የዶር አብይ አህመድ መንግስት በዚህ መልኩ፣ ለሕዝብ ንቀት በማሳየት፣ በተናጥል፣ የሕዝብ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ እንዲወስን ሊፈቀድለት አይገባም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ይሄን ውሳኔ የወሰኑ የብልጽግና አመራሮች በአስቸኳት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መልቀቅ አለባቸው እንላለን ። ህዝብን ፣ ፓርላማውን፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፣ ባለድርሻ አካላትን ሳይመክሩበት፣ አምባገነናዊ በሆነ ሁኔታ አሸባሪ የህወሃት መሪዎች እንዲለቀቁ በማድረግ አገርን የበለጠ አደጋ ውስጥ የከተቱ መሪዎች እንዲቀጥሉ መፍቀድ ማለት የአገርን ውድመት እንዲቀጥል መፍቀድ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ስልጣናቸውን ማስረከብ አለባቸው !!