ነዋሪነታቸው በጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ የሆኑና ባልና ሚስት የነበሩት አቶ ደሴ ጌታቸውና ወይዘሮ ገነት አለብኝ የሦስት ልጆች ወላጆች ናቸው። የእንስሳትም የሰውም ህይወት ሳይመርጥ ባገኘው ቦታ በጦር መሳሪያ እየጨፈጨፈ ያለው አሸባሪው ህወሓት ለእነ አቶ ደሴና ባለቤታቸውም አልራራም፤ መንገድ ላይ በጥይት ደብድቦ ገድሏቸዋል።
ሟች አቶ ደሴ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ገነት የሁለት አመት ልጃቸውን ይዘው መንገድ ላይ በነበሩበት አጋጣሚ ነው ከአሸባሪው ታጣቂዎች ጋር የተገናኙት። አረመኔዎቹ የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ህጻኑ ፊት እናቱንና አባቱን በጥይት ደብድበው ልጁን በወላጆቹ ሬሳ መሀል ጥለው ሄደዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች የሟች ቤተሰቦች ቤት ድረስ በመሄድ ምን እነደተፈጠረ ለመረዳት ጥረት አድርጓል።
ከታጣቂዎቹ ግፍ በህይወት የተረፈውን ህጻን ከሁለቱ ሟቾች ሬሳ መሀል በደም ተለውሶ እንዳገኙት የሟች እናት ወይዘሮ አባይ አንዳርጌ ተናግረዋል፡፡
የሁለት ዓመቱ ህጻን አማን ደሴ እናቱን እነ አባቱን በታጣቂዎቹ ስለመነጠቁ ያወቀ አይመስልም፤ አሁንም ድረስ ናናዬ እያለ እናቱን እየጠበቀ በር በሩን እየተመለከተ እነደሆነ አያቱ ነግረውናል፤ እኛም ያንኑ ተመልክተን አረጋግጠናል።
በግቢው ያለው ለቅሶ የወላጆቹ ሞት መሆኑን ያልተረዳው ህጻን በየመሀሉ ደግሞ በኮልታፋው አንደበቱ “እናናዬን ድው አደረጋት” እያለ የተመለከተውንና ውስጡ የቀረውን የታጣቂዎች ግፍ ይናገራል።
በአዲሱ ገረመው (ነፋስ መውጫ)
(ኢ ፕ ድ)