ከምርጫው መቃረብ ጋ ተያይዞ ጎልተው መሰማት ያለባቸው አንዳንድ ሃሳቦች – መሰረት ተስፉ

መንግስት በማንኛውም ጊዜ በአጠቃላይና በምርጫ ጊዜ ደግሞ በተለይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበር ተፈጥሯዊ ግዴታው መሆኑ ይታወቃል። እነዚህ መብቶች መንግሥት ሲፈልግ የሚቸራቸው ሳይፈልግ ደግሞ የሚነሳቸው፤ ሲችል በግልፅ፤ ካልተመቸው በስውር፤ ወይም ደግሞ ፍትሃዊነት የጎደለው “ህጋዊ” መንገድን በመከተል የሚሸራርፋቸው እንዳልሆኑ በግልፅ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የሁሉም ዜጎች የመምረጥ፣ የመመረጥ፣ የመሰብሰብና ተቃውሞን በሰላማዊ መንገድ የመግለፅ፣ በህግ እኩል የመታየትና እኩል ጥበቃ የማግኘት፣ በጡንቻ ሳይሆን በህግ የመዳኘት፣ በማንነታቸው የመከበር፣ በህይወት የመኖር፣ የመንቀሳቀስ፣ በነፃ የመደራጀትና የመሳሰሉትን መብቶች ማክበር ብቻ ሳይሆን ሌሎች እንዲያከብሯቸውም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል። ከነዚህ መብቶች ውስጥ ላሁኑ ከምርጫ ጋ በተያያዘ አንገብጋቢ ናቸው በምላቸው በተወሰኑት ብቻ ትኩረት ላደርግ እሻለሁ።

የመጀመሪያው የመምረጥ መብት ሲሆን ይህ መብት በሕገ-መንግሥቱ ለእያንዳንዱ ዜጋ የተረጋገጠ ብቻ ሳይሆን፤ ዋነኛ ሥልጣኑም፣ ኃይሉም ነው። የመመረጥ መብትም እንዲሁ። እነዚህ መብቶች ፍትሃዊ በሆነ የህግ አግባብ ካልሆነ በቀር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊከበሩ የሚገባቸው የግልም፣ የቡድንም መብቶች ናቸው። የመምረጥና የመመረጥ መብቶች ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ  መከበር ያለባቸው ለተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ዜጎች  የፈለጓቸውን ተወካዮች ያለምንም ተፀእኖ መርጠው በእነሱ እየተመሩ የተረጋጋ ህይወት ይመራሉ ተብሎ ስለሚታመን ነው።

በእኔ እይታ መንግስት ምርጫውን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የግድ የውጭ ልምድ ለመቅሰም መዳከር ያለበት አይመስለኝም። የ1997 ዓመተ ምህረቱን የምርጫ አፈፃፀም ሂደት ቢከተል ተዓማኒ የሆነ ምርጫ ማካሄድ ይችላል ባይ ነኝ። እንደሚታወቀው በ1997ቱ የምርጫ ሂደት ወቅት የምርጫ ስነ ምግባር መመሪያ (Code of Conduct) ተዘጋጅቶ ያለብዙ የመንግስት ካድሬዎች ጣልቃ ገብነት ምርጫው ተከናውኖ ነበር። እውነት ለመናገር በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ወጤቱ እስኪገለፅ ድረስ ኢህአዴግ ስልጡንነቱን ያሳየበትና ዴሞክራሲውን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ተግባራትን የፈፀመበት ሂደት ነበር ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም።

ይሁን እንጅ ይህ ስልጡንነትና ዴሞክራሲያዊነት ሩቅ አልተጓዘም። የምርጫውን ውጤት መነሻ በማድረግ ሁሉም ነገር ወደነበረበት ብልሹ አሰራር እንዲመለስ ተደረገ። ይህ እንዲሆን ደግሞ አሁን ያሉትን ጨምሮ ብዙ የኢህአዴግ አመራሮችና አባላት አሉታዊ ሚና እንደነበራቸው የሚያጠራጥር አልነበረም። እነዚህ አመራሮችና አባላት በወቅቱ ያዩት ሥልጣን ለመልቀቅ የመጨረሻው ጫፍ ላይ መድረሳቸውን እንጅ የህዝቡ መብት መከበሩን አልነበረም። ከዚህ በመነሳት የመረጡት መንገድ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ሰፍኖ አገሪቱ በፅኑ መሰረት ላይ እንድትገነባና እንድትጓዝ ሳይሆን፤ እንደለመዱት ማንኛውንም አይነት መንገድ ተጠቅመው ገደብ የሌለው ሥልጣን ላይ ተጣብቆ መቆየትን ነበር። ይህ ከምርጫ ጋ ተያይዞ የተፈጠረው ምስቅልቅል ከሌሎች ችግሮች ጋር ተደማምሮ በተለያዩ ጊዚያትና ቦታዎች ለሀገር ሰላም፣ እድገት ብሎም ዴሞክራሲያዊ አንድነት ከፍተኛ አደጋና ቀውስ ደቅኖ የነበረ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም።

ድህረ 1997 ምርጫ ተፈጥሮ የነበረው አደጋና ቀውስ አሁን ከሚካሄድው ምርጫ ጋርም ተያይዞ እንዳይፈጠር በተለይ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ከኢህአዴግ ስኬትና ውድቀት ልምድ በመቅሰም የምርጫ ሂደቱን ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በማድረግ ውጤቱንም በፀጋ ለመቀበል ዝግጁነቱን በአፍ ሳይሆን በተግባር ሊያፈጋግጥ ይገባል።

እንዳለመታደል ሆኖ ግን ከወዲሁ የምንሰማቸው እሮሮዎችና አቤቱታዎች በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እውነት ምርጫውን መሸከም ትችላለች ወይ የሚል ጥያቄ ለማንሳት የሚያስገድዱ ናቸው። በተለይ ሰሞኑን በሚኖሩበት ከተማ ውስጥ የኢዜማ የምርጫ አስተባባሪ ነበሩ የተባሉ ዜጋ በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውና ኢዜማም በግለሰቡ ላይ የተፈፀመው ግድያ ፖለቲካዊ ነው ማለቱ፤ እንዲሁም ኦፌኮንና ኦነግን የመሳሰሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮቻቸውና አባላቶቻቸው ህግዊ ባልሆነ መንገድ እየታሰሩና እየተዋከቡ ነው ማለታቸው በቀላሉ የሚታዩ ጉድዮች አይደሉም። ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመንቀሳቀስ የሚገኙ አብንንና የመሳሰሉ ፓርቲዎችንም ቢሆን ጦርነትን መርጠው መሳሪያ ካነሱ አደረጃጀቶች ጋር አመሳስሎ እንደጠላት መቁጠር ነገ ከነገ ወዲያ በሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳና ውድድር ላይ ሊደቅነው የሚችልን አደጋ ለመገመት አይከብድም። ስለዚህ ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግስት በዚህ ረገድ ያሉባቸውን ችግሮች ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ ፈትሸው አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ያን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ግን በኢህአዴግ ግዜ ከነበረው ምስቅልቅል የተሻለ ውጤት መጠበቅ የዋህነት ብቻ ነው የሚሆነው፡። ይህ የተሳሳተ መንገድ ደግሞ ሌላ የትርምስ አዙሪት ውስጥ የሚያስገባ መሆኑ አይቀርም።

ከምርጫ ጋ ተያይዞ ትኩረት የሚያሻው ሌላው መብት ሃሳብን ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ መግልፅ ነው። ይህ መብት ሚዲያ መጠቅምንና በየሚዲያው ላይ የሚደረጉ ገለፃዎችን እንዲሁም ማብራሪያዎችንም ይጨምራል። ይህን በተመለከተ መንግስት ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪዎችም ፍትሃዊ የሆነ ጊዜ ተመድቦላቸው አላማቸውንና ፕሮግራማቸውን ለመራጩ ህዝብ እንዲያስተዋውቁ ግልፅና ተጠያቂነት የተሞላበት አሰራር ሊዘረጋ ይገባል።

ሃሳብን በነፃነት መግለፅ የሚቻለው በሚዲያ ላይ ብቻ ሳይሆን አዳራሽ ውስጥም ሆነ ውጭ በሚደረጉ ስብሰባዎችና ውይይቶች፣ ሰላማዊ ሰልፎችና የመሳሰሉ መድረኮች ጭምር ነው። እነዚህ መድረኮች የሃገሪቱን ህጎች የተከተሉና ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ ምንም አይነት ክልከላ ሊደረግባቸው አይገባም። እንዲያውም ከመከልከል ይልቅ መፍቀድ ለመንግስት ለራሱ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም በአንድ በኩል መንግስት ከዜጎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ሰምቶ ጊዜ ሳያባክን የመፍታት እድል ያገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ ብሶቱን በአደባባይ በመግለፁ ምክንያት የሚሰማው እርካታ ስለሚኖር ለአመፅ የሚያነሳሳው የታፈነ ጩኽት እንዲሟሽሽ ያደርጋል።

ሰላማዊ ሰልፍን በተመለከተም ቢሆን ሰሞኑን እያየናቸው ያሉ ክስተቶች ምቾት አይሰጡም። ምክንያቱም በአንድ በኩል ገዥውን ፓርቲ የሚደግፉ ናቸው የሚባሉ ሰልፎች ያለምንም ተፀዕኖ እንዲያውም በመንግስት ተቋማት አጋፋሪናትና ቡራኬ ሰጭነት ሲካሄዱ እየተመለከትን ነው። በሌላ በኩል ግን የተፎካካሪ ፓርቲዎች የመሰብሰብ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ የመስጠትና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ጥያቄዎች በሰበብ አስባቡ እየታፈኑ እንደሆነ የሚያሳዩ ቅሬታውች ጎልተው እየተሰሙ ነው። ይህ አካሄድ ከወዲሁ ታርሞ ሁሉንም እኩል ወደሚያስተናግድ አሰራር መግባት ይኖርበታል። መንግስት ሰላማዊ ሰልፎችና መሰል መድረኮች ላይ ክልከላ ጥየ የስልጣን ዘመኔን አራዝማለሁ የሚል ቅዠት ውስጥ ከገባ ግን የታፈነ ነገር ሁሉ መተንፈሻ ካጣ ግድቡንና አጥሩን ጥሶ ሊወጣ እንደሚችል መገንዘብ ይኖርበታል። በዚህ መንገድ የገነፈለ ህዝብ ደግሞ የትኛውንም አይነት የፀጥታ ሃይል በመጠቀም እንኳ ልመልስህ ቢሉት የሚመች እንዳልሆነ የህወሃት መራሹን ዘመን ዘወር ብሎ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው።

ሶስተኛውና ከፍተኛ ትኩረት የሚሻው ከምርጫ ጋ የተያያዘ መብት ደግሞ ፍትህ ነው። ፍትህ ማለት በሰዎች አያያዝ ላይ መኖር የሚገባው ሚዛናዊነት ማለት ነው። ፍትህ ካለ መቻቻል፣ መከባበር፣ መተማመን፣ እድገት፣ ብልፅግና አንድነት ያብባሉ። ፍትህ ከሌለ ግን መጠራጠር፣ ጥላቻ፣ ቂም፣ በቀል፣ ድህነት፣ ርሃብና ልሽቀት መስፈኑ አይቀርም። ስለዚህ ፍትህ የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከዚህ በመነሳትም ነው ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት ብቻ ሳይሆን ፍትህን ማዘግየት ጭምር ፍትህን እንደመንፈግ የሚቆጠረው።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ የሆኑ አወንታዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል። በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆናቸውንና እኩል የህግ ጥበቃ የሚደረግላቸው መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት። ዜጎች ህግን ተላልፈው የሚገኙ ከሆነ ደግሞ ሊጠየቁ የሚገባቸው እንደየጥፋታቸው እንጅ ለገዥው ፓርቲ ወይም ለመንግስት ወይም ደግሞ “ለባለስልጣን” እንዳላቸው እርቀትና ቀረቤታ መሆን የለበትም።

መርሁ ይህ ቢሆንም በተግባር ግን እየቀረቡ ያሉ ቅሬታዎች እየጨመሩ ነው። ከሚነሱ ቅሬታዎች ውስጥ ፍርድ ቤት ከእስር እንዲፈቱ የወሰነላቸውን ዜጎች የአስፈፃሚው አካል “ጡንቻውን” ተጠቅሞ እዛው እስር ቤት አግቶ ያቆያቸዋል የሚለው አንዱ ነው። በዚህ ረገድ የአቶ ልደቱ ጉዳይ ጎልቶ ይነሳ እንደነበር አስታውሳለሁ። ኦነግም እንዲሁ አመራሮቼ ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ቢወስንም በአስፈፃሚው አካል እምቢተኝነት እስካሁን በእስር ላይ ናቸው እያለ በተደጋጋሚ ቅሬታውን እያቀረበ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከነጃዋር የህክምና ጉዳይ ጋ በተያያዘም የፍርድ ቤት ውሳኔዎች እየተከበሩ አይደለም በሚል በተደጋጋሚ እየቀረቡ ያሉ ቅሬታዎች ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳሉ። ምናልባትም እየቀረቡ ያሉት ቅሬታዎች እንደሚባለው እውነት ከሆኑ መንግስት ከህግ በላይ እየሆነ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም። ከህግ በላይ የሆነ መንግስት ደግሞ ምርጫ አደረገም አላደረገም ያው እንደ ኢህአዴግ፤ ካልሆነም በባሰ ሁኔታ አምባገነን መሆኑ አይቀርም። እንደ ኢህአዴግ አምባገነን መሆን ደግሞ እንደ ኢህአዴግ መክሰምንም እንደሚያስከትል ማስታወስ ጠቃሚ ይሆናል።

እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ከህዝቧ ጋ ለዘለአለም ትኑር!

መሰረት ተስፉ ([email protected])

 

 

2 Comments

  1. አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 13 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ “የፈንቅል ሊቀመንበር የነበረው መ/ር የማነ ንጉሴ በትሕነግ/በህወሀት ታጣቂዎች መገደሉ ተነገረ::”

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.