የተከበሩ የሚለው ስም በትክክልም ይገባቸዋል ብዬ ከማስባቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን ጸሐፊዎች መካከል እጅግ የተመረጠ ቋንቋ የሚጠቀሙ፣ የአባቶቻችን ዘመን ለዛና ትሕትና በብእራቸው ውስጥ የሚነበብና ምነው ጠፉብን? ብዬ ስጨነቅ የነበረ ሰው ናቸው — አቶ ባይሳ ዋቅ ወያ። የጽሑፋቸው ይዘት ብቻ ሳይሆን አጻጻፋቸው ራሱ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ሆኖ ነው የማገኘው።
ዋቅ ወያ የሚለው የኦሮምኛ ስም እግዚአብሔር ይሻላል ማለት ነው። በእውነት ከሰው ሕግ የእግዚአብሔር ሕግ ይሻላል። ደሃን የማይበድል፣ የማያገዳድል ሕግ ለሀገራችን ትውልዱ ማርቀቅና ማጽደቅ ይችል ዘንድ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን።
ትልቅ ርእስ ነው ያነሱት። ሕገ መንግሥት። ሰዉ ይረባረብበታል ብዬ ጠብቄ ነበር። ከጉዳዩ ክብደት አኳያ ብዙዎች ጠለቅ ብለው አስበው መልስ ሊሰጡበት እየተዘጋጁ ሊሆን ይችላል። እስከዚያው እኔ ትንሽ ልበልበት። ሕገ መንግስቱን።
ሀገራችንን እያጠፋ ስላለ ሰነድ ነውና ያነሱት በዚህ የመከራ ሰዓት የልብ እንጂ የማስመሰል ውይይት እንደማያስፈልግ በማመን በዚሁ መንፈስ ነው የምጽፈው። ዛሬ በመተከል ሰው ተገድሎ እንዲበላ ያደረገው ሕገ መንግሥቱ ነው። ተጠቂ ራሱን የሚከላከልበትን የፖለቲካ መብት በመንፈግ። አዎ ሕገ መንግሥቱ ነው፣ ከሰው ክፋትና ስግብግብነት ጋር ተደምሮ። ሰው አስፈጻሚ ያልሆነበት ሕገ መንግሥት ደግሞ በሰማይ ብቻ ነው ያለው። ስለዚህ “የአፈጻጸም ችግር ነው ያለበት” የሚለው የዋህነት እኔን አያሳምነኝም። ይህ ዘር ተኮር በደል የሕገ መንግሥቱ ጉድለቱ ሳይሆን ስኬቱ ነው። ይህንን ለማድረግ ሆን ተብሎ የተቀመረ ነበርና። የግሌ አስተያየት ነው። የምጽፈውም አቶ ባይሳ ዋቅወያ ባነሱት ጽሑፍ ላይ መልስ ወይም አስተያየት ለመስጠት ሳይሆን በግሌ ሕገ መንግሥት ስለሚባለው ሰነድ ያለኝን ስሜት በዚህ መልካም አጋጣሚ ለመግለጽ ነው። ለእሳቸው ጽሑፍ ባለሙያዎች አስተያየትና መልስ ይስጡበት። ጽሑፋቸው በሀገር ተቆርቋሪነት የተወጠነ እና ግሩም ሆኖ የተደራጀ ጽሑፍ ነውና ዝንባሌውና የሕግ እውቀቱ ያላችሁ ብትረባረቡበት መልካም ነው።
የሕግ እውቀት የለኝም። በዲግሪ፣ በዲፕሎማ ወይም በሥራ ልምድ የሚገለጽ። ለሕግም አክብሮት እንዲኖረን ሆነን አላደግንም። አውቶቢስ፣ ታክሲና ሀገርን በኩራት ሲሰባብሩና ሲያነኮታኩቱ በነበሩ ታላላቆች ጥላ ሥር፣ ሕዝቡንም በትእቢት እንደፈለገ ሲያነኩተው በነበረ መንግሥት ሥር ያደገው የኛ ትውልድ ለሕግ የተለየ አክብሮት የለውም። ሰው ጥሮ ግሮ ያገኘውን ባንድ ቀን ተወርሶ አይተናል። መወረሱ ሳያንሰው ወንጀለኛ ተብሎ ታስሮ፣ ተገድሎም አይተናል። በሕግና በመንግሥት። እስካሁን ባየነው ምድራዊ ሕግ ምክንያት ለሕግ ያደረብን ዋናው ስሜት ጥላቻና ፍራቻ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ተሰደንም ጥቁር ሕዝብ የሰው ግማሽ ሆኖ እንደ ውሻ በየመንገዱ ዳር ከመገደል የፖሊስ ቸርነት እንጂ ሕግ የማይከልለው መሆኑን ያየን፣ ይሄ ሕግ የሚባለው በጥልቅ ሳይገባን የምንኖር ትውልድ ነን። ነገር ግን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሀገራችንን ለመበተን የአካባቢ ነጻ አውጪ ነኝ ብለው የተነሱ ሰዎች ወረቀት ላይ የቸከቸኩትን ነገር እናሻሸለው ወይስ ሙሉ ለሙሉ ቀይረን ባዲስ ችክችክ እንተዳደር የሚለው ክርክር ከንቱ ጉንጭ አልፋ ውዝግብ ይመስለኛል።
ይህንን የምልበት ምክንያት የምንወዛገብበት ጉዳይ አንድ ሕንጻ ቢሆን ኖሮ፤ አፍርሰን እንስራው ወይስ እናድሰው? የተወሰነ ግድግዳ እንተው? መሠረቱን ሳንነካ በላዩ እንገንባ? እንጨት፣ ሸከላና ድንጋዮቹን እንጠምቀምባቸው? ምንትስ እያልን ጠቃሚ ውይይት ልናደርግ እንችል ነበር ይሆናል። ይሄ ወረቀት ላይ የተቸከቸከ የቃላት ጋጋታ ግን ሰላም ከነሳን ዘንድ ሌላ አዲስ የቃላት ጋጋታ በሚያስማማን መልኩ ቸክችከን መጠቀም እንጂ በድንጋይና በእንጨት በብረት የተሠራ አለት ላይ የተቀረጸ ነገር ይመስል እናድሰው እንከልሰው እያሉ አጉል ጊዜ ማጥፋት ፋይዳው አይታየኝም። ማንንም የማይወክሉ ጉልበተኞች ተሰብስበው፤ ለአፍሪካ መልካም የማያስቡ ጌቶቻቸው የሰጧቸውን ከፋፋይ አፓርታይዳዊ ሕግ ተብዬ ሞነጫጭረው ስለጫኑብን ስንወዛገብ የምንኖርበት ምንም ምክንያት የለም።
እውነት ይሄ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያን ያውቃታል? ብዬ ራሴን ጠይቄአለሁ። እኔ ለምሳሌ ሕገ መንግሥቱ አያውቀኝም። በነጠላ ማንነቴ አያውቀኝም፣ በውሕድ ማንነቴ አያውቀኝም፣ በዜግነትም አያውቀኝም። በመተከል ከሦስት ነገዶች እወለዳለሁ፤ የክልሉ ሕገመንግሥት አንዳቸውንም አያውቃቸውም። “መኖር ይፈቀድለታል” የሚል ይጠቅሳሉ። “እስከተፈቀደለት ድረስ ማኗኗር ይፈቀድለታል” ቢሉት አይሻልም? እናም በጠመንጃ ስለጸና ነው እንጂ እኔም ካልተገደድኩ ሕገ መንግሥቱን አላውቀውም። አላከብረውም። ዛሬ በትግራይ ሰርጥና ጉድጓድ ውስጥ የተቀበረው ድርጅትና የሱ መንትያ ኦነግ ጸረ አፍሪካ የሆነ ቅራቅምቦ ሕግ ብለው በዋናው መርዝ ዙሪያ ሌላ ደማቅ ድሪቶና ትርኪ ምርኪ ጨማምረው ስለቸከቸኩ ከነርሱ ጋይ እዚያው ደደቢት ወርዶ ይቃጠል እንጂ በምን እዳችን የነርሱን ፈንጂ ይዘን እንኖራለን?
እነሱ በሀገር ጥላቻ፣ የግል ሥልጣን ለማመቻቸትና ባእዳን ጌቶቻቸውን ለማስደሰት የቃላት ኮተት ሰብስበው ሕግ ብለው ማስጠረዝ ከቻሉ እኛም ካልጠፋ ወረቀትና ቃላት የራሳችንን ሀገራችን፣ ትውልዳችን እና ዘመኑን የሚዋጅ፣ ለሁላችንም ሰላም የሚበጅ አዲስ የቃላት ጋጋታ በአዲስ ወረቀት ላይ መጻፍ ይሳነናል? ከተለያየ ቦታ ከስታሊንም ከተባበሩት መንግሥታትም ከሌላም ኮረጁት እንበል፣ በቃ እኛን አላማከሩንም፣ አላሳተፉንም፤ አጨፋጨፈን እንጂ አልጠቀመንም። ለእነሱም አልጠቀማቸውም። በመጡበት ሰርጥና ዋሻ መልሶ ወተፋቸው እንጂ። እንዲጠቅም ሳይሆን ሀገር እንዲበድል ነው ጌቶቻቸው ድሮውንም ሰነዱን ያስደረቷቸው። ስለዚህ አዲስ ነገር መፍጠር ቢያቅተን እንኳን ለኩረጃ ለኩረጃ በሰላም የሚኖር ሀገር እንምረጥና የነሱን ሕግ ገልብጠን በሰላም እንኑር። ለምንድነው የፈረሱ ሀገራትን ሕግ መኮረጅ ያስፈለገው፤ ሲጀመርስ?
ሕግ ወይም ሕገመንግሥት ሳይመጣ መተከል ላይ በሰላም የኖረ ሕዝብ ሕግ ሲመጣ እየተራረደና እየተበላላ እንደአውሬ የሚሳደድ ከሆነ ሕግና ሕገ መንግሥት ምን ያደርግለታል? ሕግና ሕገመንግሥት ያስፈልገዋል ከተባለ፣ በሰላም የሚያኖረውን አዲስ ሕግ አርቅቆ ማጽደቅ እንጂ ይሻሻል ምንትሴ እያሉ ለካድሬ ካልሆነ ለተራው ዜጋ ምንም ያልፈየደ የእልቂትና የመበታተን ሰነድ ላይ ጊዜ ማጥፋት ምንም አይጠቅምም።
ሕገ መንግሥቱን የጻፉት ለዚያች ለአንድ የመገንጠል አጀንዳ ማሳለጫ እንዲሆን ነበር። ለምን ይዋሻል? ታድያ ደራሲዎቹ ‘ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ’ በነበሩበት ጊዜ እንኳን የፈለጉትን ነገር አግኝተው ሊጠቀሙበት አልቻሉም። ትርፉ ሰላሣ አመት በስጋትና በቁስለት መኖር ብቻ ነው የሆነው። ዓላማውም ይኸው ነበር፣ ነውም። በኢትዮጵያ ውስጥ የምንኖር አፍሪካውያን በማሕበራዊ ስጋት ውስጥ ሆነን ለዘላቂ ሰላም፣ ለዘላቂ እድገት፣ ለዘላቂ ብልጽግና ማሰብና መሥራት የማንችልበት የተሸበረ ሥነ ልቡና ውስጥ ተዘፍቀን በድህነት እንድንዳክር።
ከመቶ በላይ በጎች ያሏቸው አንድ የዋሕ ቤተሰብ አንድ ቀን ጠዋት አንዱ በግ ሞቶ ያገኙታል። ሲደርሱ ገና ነፍሱ አልወጣችም ነበር፣ መሬት ላይ ወድቆ ፈርገጥ ፈርገጥ ሲል ቢላዋ አምጥተው ያርዱት እና ይበሉት አይበሉት እንደሆነ እና ከበሉት ደግሞ በምን መልኩ እንደሚበሉት ሲሟገቱ ይውላሉ። የሙግቱ ምክንያት ደግሞ፣ በጉ እባብ ይንደፈው፣ አውሬ ወይም መኪና ይግጨው፣ በሽታ ይኑረው፣ ወይስ ምን ሌላ ምክንያት ለሞት ጣእር እንዳበቃው ባላማወቃቸው ነበር። ብንቀቅለው እኮ በሽታ ከነበረበት በሽታውን እሳቱ ያጠፋዋል ይባባላሉ። መርዝ ከሆነ ግን ይባስ የሞቀ መርዝ ከመሆን በስተቀር በመቀቀል ላይጠፋ ይችላል። ደግሞ ይላሉ። ዘልዝለን አድርቀን ቋንጣውን መብላቱ ይሻል ይሆን? እየተባባሉ የጎረቤት ሽማግሌዎችንም እስከማማከር ደረሱ። ታድያ ምነው ካላጣችሁት ከመቶ ምናምን በግ ሌላውን አንዱን በግ አርዳችሁ ብትበሉ? ይህንን ወደዚያ ቅበሩት ብለው መከሯቸው ይባላል። እርግጥ የሚበላ ጠፍቶ ያላቸው ያ አንድ ሟች በግ ብቻ ቢሆን ኖሮ ውዝግባቸው ትርጉም ይሰጥ ነበር። ካልጠፋ በግ፣ እኛም ካልጠፉ ቃላት ምነው ተመርዞም ይሁን ልክፍት ይዞት ሲንፈራገጥ በነበረው ሟች እጣ ፈንታ ላይ ንትርክ መያዝ አለብን?
በመጨረሻም ይህ ሕገመንግሥት በጀም አልበጀ በራሱ አናቅጽ ጉድለት የመንግሥት እድሜ እንዲያልፍበት አድርጓል። አሁን ራሱም ካድሬዎች ለሥልጣን ማራዘሚያ እንዲሆናቸው የጎለቱት አጎበር ነው። የነሱን በሕገ መንግሥቱ አናቅጽ የሞተ ሥልጣን በሐሰት ድሪቶ ነፍስ ከዘሩበት በኋላ ያ ነፍስ የሌለው አጎበር ደግሞ የእነሱን ሥልጣን ነፍስ እንዲዘራበት ያደረጉት ከቁማርም ከፍ ባለ የአስማት ሥራ ነው (ትርጉም ጂኒ ብለው 5 ቁጥር ሲተረጎም ስንት ቁጥር ይሆናል? ዓይነት ሿሿ በመሥራት)። ሁሉም ሞተው (የሥልጣን ዘመንም ሕግም) አሁን አፈ ሙዝ ብቻ ነው ዳኛው። ሌላው ማጭበርበር ነው። ነጭ ነጯን ስንነጋገር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆን በ”ሕግ” እና በ”ሕገ መንግሥት” ይገደደላል እንጂ ያለ “ሕግ” በሰላም መኖር ያውቅበታል። ያውቅበት ነበር ማለት ይሻል ይሆን?