የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሕመም እና መድኃኒቱ (በፍቃዱ ኃይሉ)

የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት የተመሠረተው ብዙ ብሔረሰቦችን በአንድ ግዛተ ዐፄ ውስጥ አቅፎ ነው። ብዙ አገረ መንግሥታት ከተመሠረቱ በኋላ ተከትሎ የሚመጣው የብሔር ግንባታ ከዚህ ብዝኃነት አንፃር የአንዱ ቡድን ቋንቋ እና ባሕል በሌሎቹ ላይ የመጫን እና የመጨፍለቅ ስጋት ፈጥሮ ነበር። የዚህ ስጋት የወለደው የብሔረሰቦች ጥያቄ በመባል የሚታወቀውን ንቅናቄ ፈጥሯል። የብሔረሰቦች ንቅናቄ ደግሞ የብሔር ፌዴራሊዝሙን ወልዷል።
የብሔር ፌዴራሊዝሙ የቀደሙ ብሔር ነክ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቢፈጠርም፣ ራሱ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን ፈጥሯል። የብሔር ፌዴራሊዝሙ የፈጠራቸው ክልላዊ መንግሥታት የየራሳቸው ራስ ገዝ አስተዳደርና ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤት እና ፖሊስ፣ ሕገ መንግሥት እና ሰንደቅ ዓላማዎች አፍርተዋል። እነዚህ ሁሉ ተቋማዊ ለውጦች ከተደረጉም በኋላ የብሔር ጥያቄዎች ዛሬም ጮክ ብለው ይሰማሉ። የማያባሩ ብሔር ተኮር ግጭቶችና ነውጦችም ከዚያና ከዚህ እየተሰሙ ነው። ሌሎችም ኅዳጣን ቡድኖች አቤቱታ አልቀነሰም። የመሐል አገር ለዳር ዳር አገር መገፋፋትም እንዲሁ ቀጥሏል። በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ አገር ያላት ኅልውና አደጋ አፋፍ ላይ ቆሟል። ለዚህ እና ለሌሎቹም ችግሮች የብሔር ፌዴራሊዝሙ ከትችት ያረፈበት ጊዜ የለም። ነገር ግን በእርግጥ ፌዴራሊዝሙ ጉድለቶቹ ምንድን ናቸው? ይታረሙ ይሆን? እንዴት? የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ በርካታ የጥናት ሰነዶችን ቃኝቻለሁ።
በዚሁ መሠረት ስድስት የፌዴራሊዝሙን እንከኖች እና የእርምት እርምጃ ጥቆማዎችን አቀርባለሁ።
1) የመንደር ግጭቶችን ክልላዊ ማድረግ
በኢትዮጵያ በግጦሽ መሬት እና በመጠጥ ውሃ ሽሚያ የሚቆሰቆሱ የጎሳ ግጭቶች ለረዥም ዓመታት ነበሩ። ፌዴራሊዝም እንዲህ ያሉ ግጭቶችን እዚያው በመንደር ውስጥ በመቆጣጠር እንዳይስፋፉ ያስችላል ተብሎ ይታመናል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ከተመሠረተ በኋላ የጎሳ ግጭቶች እያደጉ ብቻ ሳይሆን የመንደር ወይም የጎሳ ግጭቶችን ክልላዊ ገጽታ እና ስፋት እያላበሷቸው እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። እንደምሳሌ በ2009/2010 ተከስቶ የነበረው የቦረና ኦሮሞ እና የገሬ ሶማሌ ግጭቶችን መውሰድ ይቻላል። ግጭቶቹ ነባር ቢሆኑም አሁን ግን በሁለቱ ክልሎች (ኦሮሚያና ሶማሊ) ሚሊሻዎች ተሳትፎ፣ እንዲሁም የክልሎቹ ባለሥልጣናት የቃላት እሰጣገባ ተባብሶ ጦሱ ከግጭቱ አካባቢ 500 ኪሎሜትር ያህል ርቀት ጅግጅጋ እና አወዳይ ድረስ ዘልቆ ለንፁሃን ኦሮሞዎች እና ሶማሊዎች ሞት እና መፈናቀል ተርፏል።
2) የበላይነት ሽሚያ
የኢትዮጵያ ክልሎች አግድም መበላለጥ ከፍተኛ የሆነ የድርድር አቅም ልዩነት በመፍጠሩ በተለይ በሕዝብ ብዛት ግዙፎቹ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ለበላይነት የሚፎካከሩበት ፌዴሬሽን ሆኗል። ይህም ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ኅዳጣን ማኅበረሰቦች ይልቁንም ከመሐል አገር የበለጠ ወደ ዳር የሚገፋ ጉዳይ ሆኗል። እንደምሳሌ ሐረሪ ክልል በስፋት 858 እጥፍ፣ በሕዝብ ብዛት ከ142 እጥፍ በላይ በሚበልጣት ኦሮሚያ ተከብባለች። እነዚህ ሁለት ክልሎች በፍፁም ተቀራራቢ አቅም ፌዴራል ጉዳዮች ላይ የመወሰን ዕድል የላቸውም። በዚህ ረገድ የፌዴራል ስርዓቱ ብሔሮችን አጠናከረ ቢባልም፣ መልሶ ያዳከማቸውና ወደዳር የገፋቸው ቡድኖች በርክተዋል።
3) ባለቤት እና ባዳ
የፌዴራሉ መንግሥት ሕገ መንግሥት ዜጎቹን የሚረዳቸው የብሔር ብሔረሰቦች ስብስብ አድርጎ ነው። የክልሎቹ ሕገ መንግሥቶችም ከዚሁ በተቀዳ በሚመስል አስተሳሰብ ለክልሎች የብሔር ባለቤትነት ዕድል ሰጥተዋል። ለምሳሌ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሕገ መንግሥት “የክልሉ ባለቤቶች” በሚለው አንቀጽ 2 ውስጥ አምስት ብሔረሰቦችን ብቻ ይዘረዝራል። ካልተዘረዘሩት ውስጥ የክልሉ ነዋሪ የሆኑትን አማራ እና ኦሮሞን ብንወስድ ሁለተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ እናገኛቸዋለን። ሆኖም በፌዴራሊዝሙ አወቃቀር ፍልስፍና ምክንያት እንደ ባዳ ይቆጠራሉ። ከዚህ በፊት እንደተስተዋለው፣ ብዙዎቹ ብሔር ተኮር ግጭቶች የሚከሰቱት በባለቤት (ነባር) እና ባዳ (መጤ) አስተሳሰቦች ነው። የክልሉ “ባለቤቶች፣ ባዳዎቹን” ማስወጣት ይፈልጋሉ። ይህ ዓይነቱ ግንኙነት በሌሎች ሰብኣዊ መብቶችን የሚያከብሩ አንቀፆች ይካካሳል የሚል ክርክር ቢነሳም መጀመሪያውኑ ክፍተት መተው በምንም መልኩ ከተጠያቂነት አያድንም።
4) ከብዝኃነት ተቃርኖ
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም በአንድ ቦታ የሰፈሩ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በብሔረሰብ ዞን ወይም በልዩ ወረዳ ያስተናግዳል። ሆኖም ቅይጥ ብሔረሰቦች በሚኖሩባቸው ቦታዎች ግን ይህ ነው የሚባል የብዝኃነት ማስተናገጃ ዘዴ የለውም። ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑት ሐረሪ ክልል እና ድሬዳዋ ናቸው። ሁለቱም ክልሎች በውስጠ ፓርቲ ሥምምነት – በሐረሪ ‘ሃምሳ-ሃምሳ’ በሚሉት ሐረሪዎች እና ኦሮሞዎች፣ በድሬዳዋ ደግሞ ‘አርባ-አርባ-ሃያ’ በሚሉት ኦሮሞዎች፣ ሶማሊዎች እና ሌሎች በኮታ ተከፋፍለው እንዲያስተዳደሩት ተወስኗል። ሆኖም፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስርዓት ይህ ሥምምነት ፋይዳ የለውም። የወደፊቱ ዘመን ከተሜነት የሚስፋፋበት ከመሆኑ አንፃር ደግሞ ቅይጥ ማኅበረሰቦች ውስጥ የአካታችነት ዘዴ የሌለው ስርዓት አዋጭም፣ ዘላቂም አይደለም።
5) አስተዳደራዊ ተግዳሮት
የመሠረተ ልማት ዕድገቱ ዝቅተኛ በሆነበት ሁኔታ እና ዋና ከተሞች የአገልግሎት እና የኢኮኖሚ ዕድሎች ማዕከል በሆኑበት ሁኔታ በስፋት ትልልቅ የሆኑ ክልሎች መኖራቸው የሕዝቡን የአስተዳደራዊ ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እና መሬት የረገጠ ችግሮቹን መፍታት የማይችል ነው። በተጨማሪም የፌዴራሊዝሙ መዋቅር ብሔርን ብቻ ብቸኛ የማንነት መለያ አድርጎ በመሠመሩ በኢኮኖሚ መደብ፣ በፆታ፣ በእምነት፣ ወዘተ ያሉ ልዩነቶችን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ሆኖ ሌሎች አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን መመለስ ተስኖታል።
6) ብሔርተኝነትነትን ተቋማዊ ማድረግ
ከፌዴራል ስርዓቱ ፈታኝ ገጽታዎች አንፃር የግለሰቦችን የለት’ተዕለት ሕይወት በብሔርተኝነት እንዲቃኝ ተፅዕኖ ማድረጉ ሌላው የፌዴራል ስርዓቱ እንከን ነው። በአሁኑ ወቅት ከንግድ እስከ መዝናኛ ድረስ ብሔርተኝነት ያልተጫነው ነገር የለም። ዓለምን ያስተሳስራል የሚባለው እግር ኳስ ሳይቀር በኢትዮጵያ የብሔርተኝነት ሰለባ ሆኖ ፕሪሚየር ሊግ የተቋረጠበት ዓመት ነበር። ባንኮች ከደንበኞቻቸው እስከ ሠራተኞቻቸው ድረስ ብሔርን መሠረት ያደረገ አገልግሎት መስጠታቸው የተለመደ ነው። ማኅበረሰብ የሚቀርፁ ሚዲያዎች ሳይቀሩ በብሔርተኝነት ተወስደዋል። ይህ ሃብት እና ሥልጣን በብሔር የሚገኝበት ስርዓት በመዘርጋቱ ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው።
ምን ይበጃል?
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን እንከኖች መዘርዘር ብቻ ሳይሆን መፍትሔዎቹን መጠቆምም እንዲሁ ፈታኝ የቤት ሥራ ነው። ይሁንና ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ስንመለከት ችግሮቹ ተደራራቢ እንደመሆናቸው ተደራራቢ መፍትሔዎችንም ይፈልጋሉ። የሚከተሉት ሰባት የመፍትሔ ሐሳቦች በተናጠል ወይም በጋራ ቢወሰዱ ይበጃሉ የምላቸውጥቆማዎች ናቸው።
1ኛ. ቋንቋን ከብሔርተኝነት መነጠል።
ቋንቋ መግባቢያ እንደመሆኑ መጠን በተናጋሪ መጠን ከአንድ በላይ የፌዴራል እና የክልሎች የሥራ ቋንቋዎች እንዲኖሩ መሥራት።
2ኛ. ክልሎችን ከብሔርተኝነት መነጠል።
ክልሎች የራሳቸው የሥራ ቋንቋ ቢኖራቸውም የአንድ ብሔር ተወላጆች ንብረት ብቻ ሳይሆኑ የነዋሪዎቻቸው በሙሉ ዕኩል መኖሪያ እና መሥሪያ መሆናቸውን የሚያበረታታ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ መዋቅር መዘርጋት።
3ኛ. ክልሎችን በንዑስ አስተዳደራዊ ክፍሎች መከፋፈል።
ሰፋፊ ክልሎችን በቋንቋ አንድነት ከሚመሠረቱ የብሔረሰብ ዞኖች ጋር የሚመሳሰል ነገር ግን በብሔራዊ ዳራ ሳይሆን በጋራ ነዋሪነት ላይ ብቻ የሚመሠረት ራስ ገዝ ንዑስ አስተዳደሮችን በመፍጠር ያልተማከለ አስተዳደርን ማስፋፋት።
4ኛ. የመንግሥት ስርዓቱን መቀየር።
መሪዎች በፓርቲ ተወካዮች የሚመረጡበትን ነባሩን ፓርላመንታዊ ስርዓት፣ በቀጥታ በዜጎች እና ነዋሪዎች በሚመረጡበት ፕሬዚደንታዊ ስርዓት በመተካት የፌዴራሉን እና የክልሎቹን መንግሥታት ፕሬዚደንቶች እንዲሁም የከተሞችን ከንቲባዎች በቀጥታ እንዲመረጡ በማድረግ ዕጩዎች ከአንድ በላይ የብሔረሰብ አባላትን የሚጠቅም ዕቅድ ይዘው በማግባባት እንዲመረጡ ማድረግ።
5ኛ. የምርጫ ስርዓቱን መቀየር።
ነባሩን ብዙ ድምፅ ያገኘ ድሉን ጠቅልሎ የሚወስድበትን እና የመራጮች ድምፅ የሚያባክነውን የምርጫ ስርዓት፣ በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓት በመተካት ኅዳጣን ቁጥር ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚወከሉበትን መንገድ ማመቻቸት።
6ኛ. ፌዴራሉን መልሶ ማዋቀር።
ትልልቆቹን ክልሎች ለሁለት ወይም ለሦስት በመከፋፈል እና ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ ትንንሾቹን ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር በመቀላቀል አግድም ተመጣጣኝ የሚሆኑበትን ስርዓተ ፌዴራል መዘርጋት።
7ኛ. ኅዳጣን የማኅበረሰብ ክፍሎች የወል የድርድር አቅማቸውን የሚያሳድጉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ዘውግ-ዘለል የኅብረት መድረክ ማቋቋም።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ለምንገኝበት እጅግ መሪርና አስከፊ እውነታ ተገቢውን ትኩረት እየሰጠን ካልተራመድን ...

2 Comments

  1. ፀረ ኢትዮጵያው ወያኔ ክልሎችን ሲፈጥር በተግባርም ባይሆኑ በፅንሰ ሀሳብ ሉዐላዊ ሀገሮች አድርጎ ነው:: ከእነዚህም ትግራይን በሀገርነት ገንጥሎ እንዳይሄድ ትግራይ እራሷን መመገብ ስለማትችል ለዘረፋ እንዲመቸው ኢትዮጵያ ላይ እንደ አሜባ ተጣብቆ 27 አመታት ቆይቷል::
    የዶክተር ዐቢይ ፈተና ክልሎችን እሱና በተለይም የአማራ ክልል ባለስልጣናት እዚህ ላይ አቶ ሙስጠፌንም እጨምራለሁ የሚያዩት የአስተዳደራዊ ወሰኖች አድርገው ነው::

    ኦሮሚያ እንደ አካባቢ ክፍለ ሀገር የአስተዳደር ወሰን ብቻ ሆኖ ቢታይ ተግባራዊ ለማድረግ አደጋ የለውም:: ኦሮሚያ የምትባል ክፍለ ሀገር የሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት የጋራ ስፍራ እስከሆነች ድረስ ችግሩ ሆኖም የኦሮሞ ልሂቃን ተብዬዎች ልክ እንደ ልዑላዊ ሀገር የሚታገሉ ከሆነ የእነሱም እድል ከህውሀት የተለየ አይሆንም:: ህውሀት እንኳ የትግራይን ህዝብ ጨምድዶ ይዞ በ3 ሳምንታት ተንኮታኮተ:: የኦሮሚያን ካርታ የሚመለከት የኦሮሚያ ሉዐላዊ ሀገርን አይመኝም:: ከኢትዮጵያዊነት ጋር የሚጋጭ ሁሉ መጥፊያው እሩቅ አይደለም::
    በእኔ ግምት የህገመንግስቱ ችግር ትናንሽ ሉዐላዊ ሀገሮችን የሚፈጥር ፅንሰ ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያውያንን ያገለለ ነው:: ዶክተር ዐቢይ ከሚያስበው የአስተዳደር ወሰን ጋር ህገመንግስቱ ይጋጫል:: ኢትዮጵያውያንም ተቀምጠን ትችት ከማብዛት ሁላችንም ብንረዳው ጥቅሙ ለሀገራችን ነው:: የፖለቲካ ደላላዎች የዐቢይን ቆፍጣና ኢትዮጵያዊነትን ጥላሸት ሲቀቡ ማየት ያሳዝናል:: ፅንፈኛ ኦሮሞዎች ዐቢይን እንዴት እንደሚጠሉት ማን በነገራቸው:: ወያኔ ቀብሮት የጠፋው የጥላቻ ሰንድ ሰንኮፉ አልተነቀለም:: የእኔ ምኞት ከተሜዎች ኢዜማን ቢመርጡ ሌላው አካባቢ ብልፅግናን ይመርጣል::ከሁለቱ የተጣመረ ኢትዮጵያዊ ጠረን ያለው መንግስት ይፈጠራል: ብዬ አስባለሁ::

  2. ጥሩ ነው፤ ግን እስካሁን ያልተባለ አንድም አዲስ ነገር የለውም፤፤ እንዲያውም መሰረታዊውን ነገር በዝምታ አለፍከው፤፤ ይህን ሁሉ ለማስፈጸም ህገ መንግስቱ ካልተቀየረ እንዴት ይሆናል? ይቀየር ከተባለ ደግሞ መቼ እና እንዴት የሚሉት መመለስ አለባቸው፤፤ ምንም አላልክም፤፤ መቼም አቢይ ህገ መንግስቱን በጉልበት ይቀይረው አትልም ብዬ ነው፤፤ ቢልም እንደማይችል ለአንተ የሚጠፋህ አይመስለኝም፤፤
    በአጠቃላይ ብዙ ሰዎች ትጽፋላችሁ፤ ነገር ግን ጽሁፎቻችሁ የቃላት አስካክ እና ቅላጼ እንጂ የይዘት ልዩነት የላችውም፤፤ እና አሁን አሁን መፍትሄ እየተባሉ የሚጻፉት “Rhetoric” እየሆኑ መጡ፤፤ ለዚህ ችግር የተለየ መፍትሄ እንዲህ በአጭር ጊዜ አይመጣም፤፤ ከመጣም በሂደት፤ ለዛውም [ከተመረጠ] በዶ/ር አቢይ መሪነት ብልጽግና ፓርቲ በዉስጠ ጥንካሬ ከቀጠለ ነው፤፤ ፈጣሪ ይርዳን!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share