ሁለት የቅርብ ጓደኛሞች በየጊዜው እየተገናኙ ቀልድና ቁምነገር ያወጋሉ።ምስጢርም ሆነ ተንኮል በመካከላቸው አይስተዋልም።ቅርበታቸው ከጓደኝነት አልፎ በሌሎች ዕይታ ወንድማማች አስመስሏቸዋል፤ብዙ ጊዜ አብረው ሲወጡ ሲገቡ ይታያሉ።
ከዕለታት አንድ ቀን አንደኛው ህልም ያይና በከፍተኛ ደስታ ተውጦ ለጓደኛው ለመንገር ይጣደፋል።ስልክ ሲደውል መልስ በማጣቱ ቤቱ ድረስ ይሄዳል፤በአጋጣሜ ቤትም አልነበረም፤ ወደ ሥራ ቦታው ቢሄድ አሁንም የለም።ተመልሶ ወደ ቤቱ ሲሄድ መንገድ ላይ ይገናኛሉ፤በጣም እንደፈለገውም ይነግረዋል።ተፈላጊው ጓድኛም ባልተለመደ መልኩ ፈገግታና ደስታ በፈላጊው ጓደኛው ላይ ያነባል።ምን የተለየ ደስታ አገኘህ ? ፊትህና ፈገግታህ ያሳብቃል ሲለው እኔን ብቻ ሳይሆን አንተንም የሚያስደስት በመሆኑ ሳንቀመጥ መንገድ ላይ አልነግርህም ይለዋል። ወሬውን ለመስማት በመቋመጥ ታክሲ እንያዝና ተሎ እንሂድ በማለት ታክሲ ይዘው ወደ ወሬው ባለቤት ቤት ሄዱ።እንደደረሱም ወሬውን ለመስማት የቸኮለው ጓደኛ ፈጥኖ ሶፋው ላይ ፊጢጥ በማለት በል ሆድ ቁርጠት አታስይዘኝ ንገረኝ ይላል።የወሬው ባለቤትም በደስታ ፈንድቆና ተኩራርቶ እንዲህ በማለት ይጀምራል፤ችግርን ተመልሳ እኔን እንዳታይ አድርጌ አሰናበትኳት፤ከአሁን በኋላ እንኳንስ እኔን አንተን ዘወር ብላ አታይህም ሲለው እንዴትና ምን ማለትህ ነው ? ብሄራዊ ሎተሪ ደረሰህ እንዴ ! በማለት ሲጠይቀው ሎተሪ ምን ቁም ነገር አለውና ከዚያ የበለጠ ነገር ላገኝ ስለሆነ እንኳን አንተንም ደስ ያለህ ሲለው በደስታ ስሜት ዘና ብሎ በል አታቋምጠኝ ንገረኝ ሲለው በቅድሚያ ወገብክን ወደ ሶፋው ደልደል አርገህ በማስደገፍ ተቀመጥ ፤ተዝናና ማለቴ ነው ይልና ወሬውን እንዲህ ሲል ይጀምራል።
ዛሬ እንዴት ያለ ደስ የሚል ህልም አየሁ መሰለህ፤በህይወቴ እንደ ዛሬ ደስ ብሎኝ ተኝቸ ያደርኩበትና ስነቃም የተደሰትኩበት ቀን የለም ይላል
እንዴት ደስ ይላል፤እስኪ ንገረኝ እባክህ ልሰማው ቸኮልኩ ሲለው
መንገድ ላይ ያልነገርኩህ እኮ ሁልጌዜም የኔ ደስታ ያንተም መሆኑን ስለማውቅ በደስታ ብዛት ስትጮህ ስዎች እንዳይሰሙና ለምቀኛ እንዳንመቻች በማሰብ ነው፤ህልም ስትፈታም ጎበዝ መሆንህን ስለማውቅ ለአንተ ብቻ ነው የምነግር ብየ ወሰንኩ
ጥሩ ነው ያረከው፤ለህልም አፍታቱማ አምጡ ድገሙ ቢባል የሚስተካከለኝ እንደሌለ እኔም አውቃለሁ፤በል አሁን እኔንም አታስጎምዠኝ ንገረኝ አለው
እንዲህ ነበር ያየሁት በማለት ጀመረ፤ሽህ ሰው ከፊቴ ሽህ ሰው ከኋላየ እኔ በተ ሽለመች በቅሎ ለይ ተቀምጨ ታጅቤ ስሄድ አየሁ ሲል
ስዓሊ ለን ቀድስት ! አቤት! አቤት! እንዴት በገሃድ አሳየህ ! ሽህ ሰው ከፊት ሽህ ሰው ከኋላየ ያልከው አልቃሹና አስለቃሹ ህዝብ ነው።አንተ ከበቅሎ ላይ የተቀመጥከውም አስከሬንህ ታጅቦ ሲሄድ ነው ሲለው
ከበቅሎዋ ላይ ወረዱ እኮ!
እኽ ! እሱማ ግብዓተ መሬት ስትገባ ነዋ!
እንግዲያውስ ምንም ህልም አላየሁም ሲል
ምንም በል ምን በቅርቡ የሆነ ነገር ታያለህ ፤ልታመልጥ አትችልም ሲለው
እንግዲያውስ ከዛሬ ጀምሮ ሳልተኛ ቁጭ እያልኩ አድራለሁ በማለት ወጋቸውን ቋጩት