የአማሮች ሰቆቃ፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን የማጥፋቱ የተቀናጀ ሴራ ዋጋ ያስከፍላል!

በየነ ከበደ

የካቲት 12፣ 1929 ዓም ፋሺስቶች በአዲስ አበባ ላይ መዓት አወረዱ። የሰው ጭንቅላት ተቀላ፣ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፣ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ተፈጁ፣ የጥቁር አንበሳ አባላት እየተለቀሙ ተረሸኑ፣ በመንገድ ላይ የሚሄድ ኢትዮጵያዊ በፋስ ተቀጠቀጠ። ይህ አንድ ትውልድን ያጠፋው እጅግ መሪር ጥቃት ደርግ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ በታላቅ ሃዘን ይታሰብ ነበር። በየዓመቱ የካቲት 12 ኢትዮጵያውያን እኮታቸው ላይ ጥቁር ጨርቅ ለጥፈው፣ ወታደሮች ክንዳቸው ላይ ጥቁር ጨርቅ አስረው ባንዲራ ዝቅ ብሎ እለቲቱን በታላቅ ሃዘን ይዘክሯታል። በዚህን ቀን ጣልያኖች ወደ ውጭ መውጣት ይፈሩ ነበር።

ኢጣልያ አዲስ አበባ ላይ ዘር መርጣ አልፈጀችም። ዛሬ በኦሮምያ፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ምድር የሚኖረው አማራ እየተመረጠ ነው የሚገደለው« የዘር ፍጅቱ ኢጣልያ አድርጋው ከነበረው ጭፍጨፋ በአይነቱም በብዛቱም የተለየ ለመናገር እንኳን ዘግናኝ የሆነ ድርጊት ነው። በሰላሳ ዓመቱ የዘር ጥቃት አማሮች ከገደል ላይ እየተወረወሩ ለአውሬ ተሰጡ፣ እርጉዞች በገጀራ ተሰነጠቁ፣ ልጃገረዶች ወላጆቻቸው ፊት ሚስቶች ባሎቻቸው እያዩ ተደፈሩ፣ አባት ልጆቹ አያዩት አንገቱ በሜጫ ተቀንጥሶ ተጣለ፤ አማሮች ቤታቸው ውስጥ እንድተኙ በእሳት ጋዩ፣ የአማራ ሴቶች እንዳይወልዱ ተመከኑ፣ የአማራ መሬት ዘር እንዳያፈራ መድሃኒት ተርከፈከፈበት፣ በርካታ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያናት በእሳት ነደዱ። ህወሃት ተወገደ ቢባልም ጥቃቱ እጅግ በርትቶና ይበልጥ ተባብሶ አርሲ፣ ባሌ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ ቡራዩ፣ ቤንሻንጉል፣ ጉራፈርዳ፣ ወዘተ፣ አማሮች ለመናገር ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ የዘር ጥቃት ተደረገባቸው፣ ታላላቅ ንብረቶች ወደሙ፣ ቤት ንብረት ተቃጠለ፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን አመድ ሆነች።

ዛሬ በሃገሪቱ ላይ ምንም ችግር እንደሌለ የምዕራብ አገሮቹ ባህልና ድሎት ይዘፈንለታል። በአማራው ላይ ምንም ሰቆቃ እንዳልተፈጸመ ስብሰባው ይደራል። ቤንዚን ተርከፍክፎ የደሃ ቤት እየተቃጠለ አንዳች እንደሌለ ለውጭ ሃገር መሪዎች አቀባበል፣ ሽኝት ይደረጋል። ድርጅቶች እየተቃጠሉ – ምንም እንደለሌ – መዝናኛ ጣብያዎች ዝነኞችን እየጠሩ ቃለ ምልልስ ያደርጋሉ። የደሃው ገበሬ አማራው ልጆች ታግተው – ምንም እንደሌለ – ባለሥልጣናት ሃውልት ይመርቃሉ። ሃገሪቱ በደም ጎርፍ ተጥለቅልቃ – ምንም እንደሌለ – ባለገንዘቦች አሸሸ ገዳሜውን ያቀልጡታል። ፖለቲከኞች ፍትህ በሌለበት ስለ ምርጫ ኮሮጆው አደላደል ይወራሉ። በጣም የሚገርመው አማራው በዘሩ እንዲገደል ቤተ ክርስትያን እንድትቃጠል ሃሳብ የነደፉት ግፈኞች የአየር ሠዓት ተሰጥቷቸው ሲዋሹ ያለፈውን ቶሎ የረሳው (short memory) ወገኔም ቀልቡን ጥሎ ያዳምጣቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ይቺ ሌላ ያቺ ሌላ” አሉ አሉ አለቃ ገ/ሃና - አምባቸው ዓለሙ (ከወልዲያ)

የግፍ ጽዋው ሞልቶ ተርፎ ፈሶ እያለ – የየሜድያው የልማትና እድገት ዜና ሽፋን፣ ሠበር ዜናውና ከበሮ ድለቃው የአማራውን ዋይታና ሰቆቃ – የቤተ ክርስትያንን ቃጠሎና ምዝበራ መደበቅያ – የዘር ፍጅቱ እቅድ ማስቀጠያ – መርሃ ግብር ነው። አማራው ይህ ሁሉ መዓት እየወረደበት፣ ጥቅመኖች አቅጣጫ ማስቀየርያ አጀንዳ ቢያቀርቡም ውሎ አድሮ ዋጋ ያከፍላሉ። አማራው አጠገቡ ባለው ወልዶ ከተዋለደው ጎረቤቱና ነዋሪው አይደለም ጥቃት የተሠነዘረበት። ይልቁንም ቀድሞ የሚደርስለት፣ ደሙን የሚጠርግለት፣ አንጀቱ ላይ የተሰነቀረውን ቀስት የሚነቅልለት፣ ቆፍሮ የሚቀብረው ጎኑ ያለው ደጉ ወገኑ ነው። ይህ የዘር ፍጅት ዝርፊያን ለመፈጸም በገሃድ በተደራጁና ከእነርሱ ጋር ውልና ስምምነት ባደረጉት ክፉዎች ረቂቅ ስልት የሚከናወን ነው። ይህን ረቂቅ ስልት – በልጦ በተገኘ ረቂቀ ስልት – መዋጋትና ማክሸፍ የሚገባው ግዙፍ መሳርያ የታጠቀው መከላከያና የሃገሪቱ የደህንንነት መስሪያ ቤት ነበር። መንግሥት ይህን ማድረግ ለምን እንደተሳነው ወይንም እንዳልፈለገ ማወቅ አልተቻለም።

ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ሃገር ባቀናች፣ ጽህፈት ባስተማረች፣ ከባዕድ አምልኮ ፈልቅቃ እውነተኛውን የእየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በሰበከች፣ ደንብና ሥርዓትን ባነጠፈች፣ በወራሪ ጠላቶች ላይ ተነሱ ባለች፣ የኅልውና ምልክቷን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ዓላማዋን ከፍ ባደረገች – ይህ ሁሉ በደል ይገባት ነበርታታሪው አማራ – ሃገር በጠበቀ፣ እርሻን ባስተማረ፣ ባህልና ወጉን ባካፈለ፣ አብሮ በበላ – የዘር ጥቃት ነው ምላሹ?

ፈሪሃ እግዚአብሄር ያደረበት ሁሉ ማቅ ለብሶ መቀመጥ አለብት። ደም እንደ ጎርፍ እየፈሰሰ፣ አማሮች ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎ እዱር እዋሻ እያደሩ፣ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በህይወትና ሞት መካከል ሲሰቃዩ አይተን እንዳላየን፣ ምንም እንደሌለ ተደላድለን ብንበላ ብንጠጣስ አንጀት ጠብ ይላልሃገር እያነባች ጎጆ ብንቀልስ አያኮራ፣ ብንቀማጠል አያምር፣ በውጭው ዓለም ደልቶን ምግብ፣ መኪና፣ ልብስ ብናማርጥ ከንቱነት እንጂ ውዳሴ አይሆን። ለነፍስ ነው ለሥጋ ይህ ሁሉ መራወጥ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትግል… ሽንፈት፤ …ድል፤ ሽንፈት…(ከተመስገን ደሳለኝ)

እባካችሁ ወደ ልቦናችን እንመለስ፣ መዓቱ ይወገድ ዘንድ መለኮታዊ ፍትህ እስኪወርድ እንጸልይ፣ በመከራ ላሉት እንድረስላቸው። መዝናናቱም፣ ቃለ መጠይቁም፣ ምርቃቱም፣ ጉብኝቱም – ነገ ሃገር ስትረጋጋ ይደርሳል። እግዚአብሄር ዝም ስንል አይወድም። ደም እንደጎርፍ የፈሰሰባት ሃገር በአንበጣ ወረርሽን እየተጠቃች ነው፤ አቤቱ እግዚአብሄር ማረን፣ ከመዓቱ ሠውረን አድነን እንበል። የአማሮች ሰቆቃና ዋይታ፣ የክርስቶስ ሰውነት የሆነችው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን የቃጠሎዋ የጭስቱደመና እላይ እግዚአብሄር ዘንድ ደርሰዋል። እግዚአብሄር በራሱ ጊዜ ፍርዱን ይሰጣል።

ብዙዎች አላስተዋሉም እንጂ በደም በጠለሸ ሥልጣን ንዋይ ቢከምሩ – ደመንዋዩ ወደ እቶን እሳቱ ንዳድ ወደ ገሃነም መዳረሻ እንጂ ፀጋ አይሆንም። በአማራው ላይ የሚደርሰው ገደብ የለሽ የዘር ፍጅትና ሰቆቃ – ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያንን የማጥፋቱ የተቀናጀ ሴራ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል። ወገኖቼ – እንጸልይ፣ ለተጎዱት ያለንን እናካፍላቸው፣ እንጩህላቸው።

1 Comment

  1. “ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ሃገር ባቀናች፣ ጽህፈት ባስተማረች፣ ከባዕድ አምልኮ ፈልቅቃ እውነተኛውን የእየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በሰበከች፣ ደንብና ሥርዓትን ባነጠፈች፣ በወራሪ ጠላቶች ላይ ተነሱ ባለች፣ የኅልውና ምልክቷን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ዓላማዋን ከፍ ባደረገች – ይህ ሁሉ በደል ይገባት ነበር? ታታሪው አማራ – ሃገር በጠበቀ፣ እርሻን ባስተማረ፣ ባህልና ወጉን ባካፈለ፣ አብሮ በበላ – የዘር ጥቃት ነው ምላሹ?”

    ልክ ነህ፡፡ በፍጹም! አማራም ኦርቶዶክስም፤ ማንም አይገባውም፡፡ ግን ምክንያቶችህ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አለው ብለህ አታስብ፡፡ አማራ ሌላውን የኢትዮጵያ ህዘብ እንደጠቀመ ብቻ እንጂ አማራ ከሌላው ምንም ያልተጠቀመ አስመስልከው፡፡ በቅርቡ የታዘብኩትን ልንገርህ፤ በአሁኑ ወቅት አርሲ ውስጥ ያለ የቤተክርስቲያን ቁጥር ከጎንደር ይበልጣል፡፡ ሊገርምህ ይችላል፡፡ ግን ነው፡፡ ጠይቅ፤ አጣራ፡፡ በኦርቶዶክስነት ቢሆን እኮ ትግራይም 98% ኦርቶዶክስ ስለሆነ ከአማራ መዎገን ነበረበት፡፡ ግን አይደለም፡፡
    እቴጌ ጣይቱ ናችው አሉ “እኛ ጎንደሬዋች ባንመጣ ሸዋዎች ምን ትበሉ ነበር” ብለው ጠየቁ (ሞያ የላችሁም ማለታቸው ነው፡)
    ሽዋዎችም ታዲአ የዋዛ አልነበሩምና “ንግስት ሆይ፤ እርስዎም ቀርተውብን ምግቡም በቀረብን” አሉ ይባላል፡፡
    እየተስተዋለ ቢሆን ለማለት ነው፡፡ በምንም ግፊት አተያያችን ከሰውነት ደረጃ አይውረድ፡፡ አንዴ ወደ ቡደን (በዘርም ይሁን በሃይማኖት) መውረድ ከጀመርክ ቁልቁለቱ ማቆሚያ የለውም፡፡ አብንም “አይጥ ወልዳ፤ ወልዳ፤ ጂራቷ ላይ ስትድርስ ሲጢጥ አለች” እንዲሉ በዚህ አስቸጋሪ ሰአት የተቃውሞ ሰልፍ ጠራ፡፡ለ”ፌዴራሊስት ኃይሎች” ትልቅ ድል ነው፡፡ በጣም በጉጉት የሚጠብቁትን ነው ያገኙት፡፡ “እንኳን ደስ አላችሁ” እንኳ ቢቀር ስልታችውን ያልማድነቅ ይከብዳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share