”የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” (ዘ-ጌርሣም)

ለዚህች አንስተኛ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተናገሩት ዕብሪት የተሞላበት አነጋገርና ጠብ አጫሪነት ነው።እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ተቆርቋሪ ዜጋ ከብስጭት በዘለለ የሚከፈል መስዋዕትነት እንኳን ቢኖር ከወገኖቸ ጎን ለመቆም እርግጠኛ በመሆንም ነው።

ዓለማችን በየዘመኑ በርካታ ጨካኝና ዕብሪተኛ መሪዎችን አስተናግዳለች።የራሳቸውን ጥቅም ለማጎልበትና የበላይነት ለማንገስ ሌሎችን በግፍ ወረዋል፣ብሔራዊ ሀብታቸውን ዘርፈዋል፤በቀጥታ መውረርና ማጥፋት ያልቻሉትን ለሌሎች የጦር መሣሪያ፣የገንዘብና የስለላ ድጋፍ እያደረጉ አስወርረዋል፤ከወረራ በዘለለም ማንነታቸውን በማጥፋትና ሀገራትን በመበተን፣ አብረው የኖሩ ህዝቦችን በማዋጋት በጠላትነት እንዲኖሩ አድርገዋል።ለሴራዎቻቸው ያልተንበረከኩ የህዝብ መሪዎችንም ገለዋል አስገድለዋል።የሀገራትን ሉዓላዊነት አፈራርሰው የጋራ ዕሴቶቻቸውን አጥፍተዋል።

ታሪክ ራሷን ትደግማለች እንደሚባለው  በታላላቆቹ የዓለም ጦርነቶችና በዘመነ ቅኝ ግዛት ወቅት የፈፀሙት ግፍ ሳይበቃቸው ይኽውና በሃያኛው ክፍለ ዘመንም ሊደግሙት ይዳዳቸዋል።

በነሱ አስተሳሰብ:-

 • ለማደግ የነሱን ፈቃድ መጠየቅ
 • ለመምረጥና መመረጥ የነሱን መስፈርት ማሟላት
 • እራስን ለመከላከል የንሱን ይሁንታ ማግኘት
 • ለመማርና ለመመራመር የነሱን ችሮታ መለመን
 • ጤናን ለመጠበቅ የነሱን ብቻ መድኃኒት መግዛት
 • የሰላም ድርድር ለማድረግ እነሱን ማስፈቀድ
 • ከጎረቤት አገራት ጋር ጤናማ ግንኙነት ለማድረግ እነሱን ማስፈቀድ ወዘተ

ሉዓላዊነቷን በልጆቿ መስዋዕትነት ጠብቃ የኖረችው ሀገራችን በማንም አይዞሽ ባይነትና ችሮታ አለመሆኑን ታሪክ ምስክር ነው፤እነሱም ያውቁታል።የተሰነዘሩባትን የጥቃት ጦርነቶች ለመመከት ልጆቿን እየገበረች ከዚህ ደርሳለች።ዛሬ ደግሞ ጊዜው ሌላ ነው፤የምርምር፣የውድድርና ራስን የመቻል ዘመን ነው፤የቅኝ ግዛት ዘመን አክትሟል፤ሉዓልዊነት ማለት ደግሞ ነፃ የሆነ በሔራዊ ክብርና ህልውና ነው።ማንም አገር የሌላውን አገር መብትና ክብር እስካልተጋፋ ድረስ ተፈጥሮ ባደለችው ብሄራዊ ሀብቱ መበልፀግ ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው ። አርሶ ለማምረትም ሆነ ኢንዱስትሪ ከፍቶ ምርትን ለማሳደግ፣ውሃ ለመገደብና ልዩ ልዩ መርሐ ግብራትን ማዘመን ተፍጥሮአዊና ሕጋዊ መብት ነው።ከጎረቤት ሀገሮች  ጋር ተስማምቶና ተጋግዞ ለመኖርም ሆነ በጋራ ለመበልፀግ የሚመለከታቸው ሀገሮች ፍላጎትና ስምምነት እንጅ ጉዳዩ የማይመለከተው የሦስተኛ አካል አይደለም።እኔ በምሰጣቸሁ የመኖር አቅጫ ነው የምትኖሩት ማለት ደግም ከመብት ገፈፋነት አልፎ ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሰት ነው።ዓለም አቀፍ ሕግጋት እስካልተጣሱ ድረስ ማንም ሀገር ለሚያደርገው ሰላማዊና ልማታዊ እንቅስቃሴ የኃያላን ሀገራትን ፈቃድና ይሁንታ መጠየቅ ፍትሐዊ አይደለም ፤እነሱ ማነንም ፈቃድ አይጠይቁምና።ነፃ ሀገር የሚባለው በቆዳ ስፋትና ጥበት ሳይሆን እኩል የሚያደርጋቸው የእያንዳንዱ ሉዓላዊነትና በሕግ ፊት የሚሰጣቸ የእኩልነት መብት ነው።ከሁሉም በላይ እኔ የለለሁበትና ያልፈቀድኩት የሚለው የበላይነትና ዕብሪት የተሞላበት አካሄድ ርቀት ካለማስኬዱም በላይ በሕግም ያስጠይቃል።

ዶናልድ ትራምፕ የራሳቸው የውስጥም ሆነ የውጭ ችግሮች እንዳሉባቸው የአደባባይ ምስጢር መሆኑ እይታወቀ ይህን ውጥረት ለማርገብ እየሄዱበት ያለው መንገድ የሚያዋጣቸው አይሆንም።

ከብዙዎቹ የዶናድ ትራምፕ ችግሮች ውስጥ ጎልተው የሚታዩት:-

በሀገር ወስጥ ፖለቲካ

 • ኮሮና ቫይርስ (Covid-19) በሕዝባቸው ላይ ያደረሰው ጥፋትና እየደረሰባቸው ያለውን የአያያዝ ጉድለት ወቀሳን መቋቋም አለመቻል
 • ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ በሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳ ከተፎካካሪያቸው ጋር ራሳቸውን ሲያውዳድሩ የመሸነፍና የመረበሽ ስሜት ስለሚታይባቸው
 • ከምርጫው ጋር በተያያዘ የሚወረወሩባቸውን ክሶችና የስም ማጠርሸት መቋቋም ስለተሳናቸው ወዘተ

በውጭ ፖለቲካ

 • ከብዙ ሀገራት ጋር ያጋጠሟቸው አለመግባባትና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሰረዝ
 • በንግዱ ዓለም ከጠንካራዎቹ የንግድ አጋሮቻቸው ጋር መጣላታቸውና ግንኙነቶችን ማቋረጣቸው
 • ለዓለም ጤና ድርጅት አሜሪካ ትሰጥ የነበረውን ዕርዳታ ማቋረጣቸው
 • በአንዳንድ ሀገራት ላይ ያለአግባብ የሚሰነዝሩት ዘለፋና መሠረት የሌለው ትችት
 • ለእርሳቸው ተንበርካኪ ላልሆኑ አገሮች አሜሪካ ትሰጥ የነበረውን ዕርዳታ ማቋረጣቸው

ይህ በእንዲህ እያለ ኢትዮጵያ ራሷን ችላ እየገነባች ያለውን የህዳሴ ግድብ ግብፅና ሱዳን በጦርነት እንዲያወድሙት ቅስቀሳ ሲያደርጉና ሲያበረታቱ ይደመጣሉ።ለመሆኑ ግብፅና ሱዳንስ ለራሳቸው የሚጠቅማቸውንና የሚጎዳቸውን የማይረዱ ይመስላቸው ይሆን ? ይህን ዓይነት ቅስቀሳ ሲያደርጉስ እነዚህ የተጠቀሱ ሀገራት እንደ ሉዓላዊ ሀገራት የሚኖሩ አልመሰላቸው ይሆን ? ይልቅስ ሌላ ከሳቸውና ከታላቋ አሜሪካ የሚጠበቀውን የኃያል ሀገር ስምና ክብር ማስጠበቁ አይሻልም ነበር ? የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” የሚባለው እኮ ይህን ዓይነቱን ነው።

ጌታ ሆይ !!!

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ አንተ ዘርግታለችና እባክህ ጠብቅልን ????

 

1 Comment

 1. እኔ የሚገርመኝ እብድ ተናገረ ተብሎ መናደድ አያስፈልግም እማዝነው ለተከበረው የአሜሪካን ህዝብ ነው በእንደዚህ ያለ ወደል እብድ መመራታቸው

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.