ግጥም እንደመግቢያ
አባይ ነህ አብ’ይ አጉራሽ
አባይ !አባይ !አባይ ! አባይ
“አባ’ይ !” የኛ ቀለብ የሀገርህ ሲሳይ
የኢትዮጵያውያን ብርሃን የማትጠልቅ ፀሐይ።
አባይ ፣ “የአገር አባት “ ማደሪያ አጥተህ
ለዘመናት ግንድ ይዞ ዙዋሪ ነበርህ…
ይኸው፣ ዛሬ ልብ ገዝተን ልጆችህ
ቤንሻጉል ላይ ማረፊያ ፣ ቤት ሰራንልህ።
አባይ !አባይ ! አባይ !…
አባይ ነህ ፣አጉራሽ “አባ’ይ!”
የፈጣሪ ሥጦታ ፣ የሀገርህ ሲሳይ
ታቃለህ እውነቱን ፣ትላንት በተለያየ ሴራ
እኛው ለእኛው ፣እንዳንረዳዳ በዝቶብን ደንቃራ።
በነገድ ተከፋፍለን ፣ሠንጋደል ለይተን ጎራ
ቆዳችንን በማዋደድ፣ግብዝ ሆነን ሥናቅራራ።
ሰው መሆናችንን ረሥተን ፣በቋንቋ ሥንጠራራ
ህብረት ፣ አንድነት ና ፍቅር አጥተን ፣ ተጠምደን፣በጥላቻ ፉከራ።
ሆነህ ነበር እኮ ! አባይ “ የሀገር አባት “ የበረሃ ሲሳይ።
ዛሬ ግን ሆንክልን አባይ የኢትይጵያ “ አባ ‘ይ “
በቢሻጉል ከትመህ ብርሃን ሆንክልን ፣ የኛው ሲሳይ።
አባይ አባይ፣አባይ
የሀገሬ ሲሳይ።
አባይ ፣አባ’ይ ነህ፣ለእኛ ከቶም “ ናይል “ አይደለህም
እሥከ ኢትዮጵያ ጠረፍ “አባይ” እንጂ ሌላ ሥም የለህም።
ናይል ለሚሉህ ለጋሥ ነህ እንጂ ፣ ንፉግ አይደለህም
ይህንን ያላወቁ ፣ለጋሥነትክን የካዱ ፣ልጆችህን ባይወዱንም።
ባጎረስካቸው ሊነክሱህ ለጥፋት ሁልጊዜ ቢያደቡም
ዛሬም እንደትላንቱ የኢትዮጵያን እድገት ባይወዱም።
አባይ ! አባይ ! አባይ !…
ሆነሃል ዛሬ የሀገሬ ሲሳይ።
አባይ ! አባይ ! አባይ !
ሆነሃል ዛሬ፣ የኢትዮጵያውያን ሲሳይ።
አባይ ! አባይ ! አባይ !
“አብ’ይ” ነህ ፣የኛው ፣ አጉራሽ ሲሳይ
የኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ።
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
2013 ዓ/ም
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሚናገሩት ሥህተት መሆኑንን የሚያውቁት ከተናገሩ በኋላ እንኳን ያለመሆኑ ለአሜሪካ ዜጎች ሐፍረትን ያላብሳል። እንዲህ አይነት የወረደ ፣ዩሉንታ እና ፈረሃ እግዛብሔር የሌለው፣ፕሬዝዳንት አሜሪካ በታሪኳ አላጋጠማትም።እኚህ የአሜሪካ ፕረዚዳንት በጣም አሥገራሚ፣አሳዛኝና አሥቂኝ መሪ መሆናቸውን ደጋግመው ያሳዩን ናቸው። ትላንት ለኮቪድ በረኪናን እና የመሳሰሉት አጠቃላይ ጀርሟችን ከዕቃዎች እና ከቁሳቁሶች ላይ ለማሥወገድ የሚያገለግሉትን “በደም ሥራችሁ ውሰዱ።” በማለት ከመናገራቸውም በላይ የወባ መድሃኒት የሆነውን ክሎሮኪውን ” የኮቪድ 19 መድሃኒት ነው።” እሱን የወሰደ ይፈወሳል።” በማለት በአደባባይ መናገራቸውን እናሥታውሳለን።ይህም ብቻ አይደለም የሲኤን ኤን ጋዜጠኛዋን ከአንድ ፕሬዝዳንት በማይጠበቅ የንቀት ንግግር ሲያበሻቅጡ ተሥተውለዋል።ይህ የተለመደ ብልግናቸው ሥለመሆኑ ትሪቮር ኖህ የተባለው የሀገራቸው ቀልደኛ ፣እያዋዛ በቀልድ መልክ በመደረክ የሳቸውን ድምፅ እያሥመሠለ ነግሮናል። “ሴት በማቋሸሽ ረገድ ሰውየው ለሚሥታቸውም እንደማይመለሱም በእርሱ ቀልድ መሣይ ቁም ነገር መገንዘብ ይቻላል።” ትሪቮር ኖህ ቀልድም ተነሥቼ የአሜሪካ ዜጎች ፣በኦባማ ምትክ እንዲህ አይነቱን ማስተዋል የጎደለውን ፣ ሰውዬ ፕሬዝዳንታቸው እንዲሆን መፍቀዳቸው አሥገርሞኛል።
ሰውየው ፣በአሜሪካን ዜጎች ማሾፋቸው ና በተከበረው ሚዲያቸው ላይ መቀለዳቸው ፣እንዲሁም አጉራዘለል መሆናቸው ዓለምን እያሥገረመ ለአራት ዓመት መዝለቁ በራሱ ለአሜሪካን ዴሞክራሲ ና ወግ አጥባቂነት እንደተአምር የሚቆጠር ነው።ያ የዓለም አሥተማሪ የሆነ “ የመንግሥት ጥራታቸው “ እንዲህ ተበሻቅጦ በቆሻሻ ሲለወሥ የአሜሪካ የምክር ቤት ዓባላት እንደዋዛ ማየታቸው በራሱ እጅግ ያሥገርማል።በሥመ ጥሮቹ በእነ ጆርጅ ዋሽንግተን፣በነ አብርሃም ሊንኮን፣ በነ ቶማሥ ጀፈርሰን ፣ በነ ኦባማ …ወንበር ላይ ተቀምጦ፣ ከተናገረ በኋላ እንኳን ሥህተቱን አምኖ ይቅርታ የማይጠይቅ ፣ይልቁንም የተናገርኩት ዝባዝንኬ ሁላ እውነት ነው የሚል ከጥበብ የራቀ መሪ ፣ በራሱ አሜሪካኖችን ያሚያሳፍር መሆን ነበረበት።
የሰውየውን አሳፋሪነት የበለጠ ያጎለው ደግሞ በእኛ በኢትዮጵያውያን የኃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ግብፆች ጥቃት እንዲሠነዝሩ ምክር መለገሱ ነው።የአንድ ልዕለ ኃያል አገር መሪ በአንዲት ሉአላዊ አገር ላይ ” ውሃ ቀጠነ በሚል ሰበብ ” ጥቃት እንዲሠነዘር መምከር በራሱ ዶናልድ ትራፕን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን ብቃት እንደሌለው የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ “ሂትለራዊ አስተሳሰብ እንዳለው የሚያሰብቅም ነው።ሂትለራዊ አስተሳሰብን ደግሞ የተባበረው የአሜሪካ መንግሥት ዜጋ ሁሉ የሚጠየፈው ነውና ሰውየው ፣የኢትዮጵያውያኑን እራት እና መብራት ” እንዲወድም መፈለጋቸውን አጥብቆ እንደሚቃወምና በዘፈቀደ ንግግራቸውም ያወግዛቸዋል ብዬም አስባለሁ።
የአሜሪካ ዜጎች በሰውየው ንግግር በማፈር የሚሰጡትን ምላሽ ሳይረፍድ የምንሰማው ነው።በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይ ግን በዓይናችን ብሌን እንደመጡብን በጥሞና እንነግራቸዋለን ።
” የአባይ ህዳሴ ግድብ ለእኛ የዓይን ብሌን ነው።ግድቡ በደማችን እና በአጥንታችን የተገነባ ነውና ይህ ግድብ አንድ ነገር ቢሆን የግብፅ ህዝብም እንደማይኖር ይወቁት። እኛ ኤሌትሪክ አመጭተን ብርሃን እና ኃይል እናግኝ እንጂ ውሃውን ገድበን ለመሥኖ እናውል አላልንም። “
ምንም እውቀት ሳይኖራቸው ልክ ሙሉ ወንዙ እንደተገደበ በድፍረት ማውራታቸው ግን ያሳዝናል። በበኩሌ እማዝነው ለታላቋ አሜሪካ ነው።ሰውየው እያወቁ አላዋቂ በመምሠል ሥለ አባይ ግድብ ኤሌትሪካ ማመጫነት እያወቁ ፣የአባይ ውሃን ወደ ግብፅ ና ሱዳን እንዳይፈሥ የተገደበ ግድብ አሥመሥለው ፣በማውራት ፣በሂትለራዊ ፕሮፖጋንዳ፣የኤሌትሪክ ማመንጫ ግድባችን ፣ እንዲጋይ ሃሳብ ማቅረባቸው በበኩሌ ደደብነታቸውን ሳይሆን መሠሪነታቸውን የሚያሳብቅ ነው።
ትራፕ በብዙዎች ደደብ ተብለዋል።ደደብነት ግን የሰው ልጅ ፀጋ ሥለሆነ እኔ ትራፕን ደደብ አልላቸውም። “ትራምፕ በድንቁርና ማጥ ውሥጥ እሥከነአፍንጫቸው የተነከሩ ለአሜሪካ ዜጎች የማይመጥኑ መሪ ናቸው እንጃ!” እላለሁ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሆይ ፣ ከመሠሪነት እና ከድንቁርና ወጥተው በጠራ ህሊና የአፍሪካን ህዝቦች መመልከት አሥካልቻሉ ድረሥ የመላ አፍሪካ አሜሪካንን ድምፅ ፣በምርጫ ወቅት እንደማያገኙ ይወቁት።
ወደ ርእሴ ልመለሥና፣ የገነባነው የኃይል ማመንጫ ግድብ ለግብፅም ሆነ ለሱዳን እጅግ ጠቃሚ እና የውሃ ብክነትን የሚቆጥብላቸው እንጂ ውሃን የሚያሥቀርባቸው እንዳይደለም እወቅ።የአባይ የህዳሴ ግድብ ተርባይኖችን አንቀሳቅሶ ወደ ሱዳን እና ግብፅ የማፈሥ ውሃ ነው።በሠላም ያለማቋረጥ ለሚፈሥ ውሃ የአባይ ልጆች ደም እንዲፋሰሱ፣” ቢላዋ ማቀበልም” በእውነቱ ” የናዚነት ” ሥም የሚያሰጣቸው ነው። ።ለግብፆች የአባይ ግድብን አጋዩት ብሎ መምከርም ” እብደት” ነው።
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ በትሪሊዮን ዶላር የሚቀሳቀሱ “ድንበር ዘለል ” ከበርቴዎች እብዶች ናቸው።ትርፍን ከሰው ሞት ይፈልጋሉና።ትርፍን ከአፍሪካ ሰቆቃና ከህዝቦቿ ድህነት እና ድንቁርና ይሻሉና!!ትርፍን ከእርሥ በእርሥ ጦርነት እና ከሀገር መከፋፈልና ዘጠኝ መሆን እንደሚያገኙ ያውቃሉና!!ትላንት ያደረጉትን ዛሬም በእጅ አዙር የሚያደርጉትን ማሥተዋል ያላቸው የዓለም መሪዎች ይገነዘባሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕም ሀፍረተ ቢስ በመሆን በደም እና በአጥንታችን የተገነባው የአባይ የህዳሴ ግድብ ግብፆች እንዲያጋዩት መምከራቸው ፣የሞት ነጋዴ እና በአፍሪካውያን እልቂት አትራፊ መሆናቸውን የሚመሠክር ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም።እሳቸው “ሀፍረተ ቢስ “ በሆነ ንግግር ሊያሥፈራሩን ቢቃጡም እኛም በእጃችን በሶ እንዳልጨበጥን የግብፅ መንግሥት ሥለሚያውቅ ፣በእሳት ለመጫወት ይቃጣል ብለን አናሥብም።ከቃጣም” እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው ።” እንደሚባለው ተረት የግብፅ ፍፃሜ ይሆናል።