የኣገራችን የፍትህ ስርዓት አየተሻሻለ ይመጣል የሚለው ተስፋ የተጫረው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አንደሆነ ብዙዎች ኣንደሚስማሙበት ኣምናለሁ። አርግጥ ነው፣ የኣገራችን የመብት ጥሰቶች ማደግና የህግ ስርዓቱንም የስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያ ሆኖ በቆየበት ስርዓት ውስጥ ለኖረች ሃገር የነበረውን ስርዓትን ለማሻሻል የሚጠይቀው ጥረት ቀላል ኣንደማይሆን ለመረዳት ኣያዳግትም። ተስፋ የሚሰጡ ርምጃዎች ከጊዜ ወደጊዜ አየታዩ ነው በሚል ህዝቡ በተስፋ አየጠበቀ ቆይቷል። ለውጡ ጊዜ የሚወስድ ሂደት መሆኑ ቢታመንም፣ ለፍትህ መከበር የሚጣሉ መሰረቶችና የሚወሰዱ የማሻሻያ ርምጃዎች የሚያመጡትን ውጤት ህዝቡ በታላቅ ንቃት ኣንደሚከታተል ማወቅ ይገባል።
የፍትህ ስርዓትን ለማሻሻል መጀመሪያ የህግ መኖር መሰረታዊ ነው። የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ህገመንግስት የተቀረጸው በ1923 ዓመተ ምህረት ኣንደነበረ ጽሁፎች ያስረዳሉ። ይህ ህገመንግስት ኣንደገና በ1948 ዓመተ ምህረት ተሻሽሏል። ኣገራችን ኢትዮጵያ በህገመንግስት መተዳደር ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የህግ ስርዓት ኣፈጻጸም ለመመልከት ዕድል ያገኘንና ያነበብን ሰዎች ሁሉ አንደምንረዳው የህግ የበላይነት በተሻለ ሁኔታ የታየው በንጉሱ በኣጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አንደነበር ግልጽ ነው። ይህ ሲባል ስርዓቱ ጉድለት የሌለበት ነበር ለማለት ኣይደለም። ግን ጉድለቶቹ ቀጥለው ከመጡት መንግስታት ኣንጻር ሲታይ የህግ ስርዓቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው ብል የተሳሳትኩ ኣይመስለኝም።
የኣንድ የህግ ስርዓት ሶስት ኣምዶች ህግ ኣውጪው፣ ህግ ተርጓሚና ህግ ኣስፈጻሚው መሆናቸውን ኣንረዳለን። ሁሉም የሚያገለግሉት የሁሉም የበላይ የሆነውን ህግን ነው። የመጀመሪያው ህገመንግስት ከንጉሱ ስርዓት መውጣቱና በጊዜ ሂደት አንዲሻሻል መደረጉ በወቅቱ ለህግ የተሰጠውን ክብርና ትኩረት ያሳያል። ፍርድ ቤቶችና ፖሊሶች ምን ያህል በትክክል ይሰሩ ነበር ለሚለው ጠለቅ ያለ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ ህግ ተላላፊዎች ግን የሚቀጡት በፍርድ ቤት ውሳኔ አንደነበር መመስከር ይቻላል። ለዚህም ማስረጃ የሚሆኑ መረጃዎችን በቀላሉ በወቅቱ ይወጣ ከነበርው `ፖሊስና ርምጃው` ከተሰኘው ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ የወጡ በርካታ የውንጀልና ፍርድ ጉዳዮችን ኣንብቦ ለመረዳት ይቻላል። ሙስናን ጨምሮ በወቅቱ በውስጥ ሊኖር የሚችለውን ኣድሏዊ ኣሰራር ለኣጥኚዎች ልተወውና በኣጠቃላይ ሲታይ ህግን የጣሱ ወንጀለኞ ፍርድ ቤት ቀርበው ከተከራከሩ በኋላ ፍርዳቸውን ያገኙ ነበር፣ በመጨረሻም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በፖሊስ ኣስፈጻሚነት ፍርዳቸውን ይቀበሉ ነበር፣ ብሎ መመስከር የሚቻል ይመስለኛል።
የ1948ቱ ማሻሻያ የሚከተሉትን የያዘ ነበር።
- ኣንቀጽ 37። ማንም ሰው በሕግ እኩል ሆኖ ይጠበቃል።
- አንቀጽ 38። በብሔራዊ (ሲቪል) መብቶች በመጠቀም ረገድ፡ በኢትዮጵያውያኖች (የኢትዮጵያ ተገዦች) መካከል ምንም ልዩነት አይኑር።
- አንቀጽ 39። የኢትዮጵያ ተወላጅነትንና የኢትዮጵያ ዜግነትን ለማግኘትና ለማጣት የሚያስችሉ ኹኔታዎችን ሕጉ ይቀምራል (ይወስናል)።
- አንቀጽ 40። የሕዝቡን መልካም ጠባይ ወይም ፀጥታን ወይም በፖለቲካ ረገድ የሚያውክ ካልሆነ በቀር፡ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት የሚኖሩ ሰዎች በሕግ መሠረት የሃይማኖታቸውን ሥርዓት አክብረው በነፃ ከመፈጸም አይከለከሉም።
- አንቀጽ 41። በመላው የንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ውስጥ በሕግ መሠረት የንግግርና የጋዜጣ ነፃነት የተፈቀደ ነው።
- አንቀጽ 43። ማንኛውም ሰው ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት ውስጥ ሕይወቱን ነፃነቱን ወይም ንብረቱን ያለ ሕግ አያጣም።
- አንቀጽ 45። የኢትዮጵያ ዜጎች በሕጉ ተዘርዝሮ በሚወስነው መሠረት የጦር መሣሪያ ሳይዙ ሰላማዊ ስብሰባ ለማድረግ መብት አላቸው።
- አንቀጽ 46። በሕግ ካልተከላከለ በቀር በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ውስጥ ከሥፍራ ወደ ሥፍራ የመዛወርና መኖሪያ ሥፍራን የመለወጥ ነፃነት ለንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዜጎች ሁሉ ተረጋግጧል።
- አንቀጽ 47። ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በሕግ መሠረት ማናቸውም ዓይነት ሥራ እየሠራ ለመኖር፤ ማናቸውም የሥራ ማኅበር ለማቋቋምና በማናቸውም ማኅበር አባል ለመሆን መብት አለው።
- አንቀጽ 49። ማንኛውም የኢትዮጵያ ተገዥ ከንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውጭ ለመሳደድ (ሌቅቆ እንዲወጣ) ሊገደድ አይችልም።
ከንጉሱ ዘመን በኋላ በመጡት መንግስታት ጊዜ ሁሉ ከላይ ከተጠቐሱት ኣብዛኞቹ ህገመንግስታዊ መብቶች በአጅጉ ሲጣሱ ኖረዋል። በንጉሱ ዘመን በኣንቀጽ 40 ላይ የተመለከተው የሃይማኖት ውይም የዕምነት ነጻነት ተከብሮ ኖሯል፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት ኣደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው የተዘገበም ሆነ የተጻፈ ነገር ኣላየሁም። ማስረጃ ካለ አታረማሉሁ። በተመሳሳይ በኣንቅጽ 46 የተጠቀሰው በኣገሪቱ ውስጥ ከስፍራ ወደ ስፍራ ተዘዋውሮ የመኖር መብት ተጠብቆ ኖሯል ብዬ ኣምናለሁ። አነዚህ መብቶች ኣሁንም ባለው ህገመንግስት ወስጥ የተካተቱ ሲሆን ከመቼውም በበለጠ ባለፊት ሶስት ኣስርት ኣመታት በስፋት ሲጣሱ የሚታዩ የህግ ድንጋጌ ጥሰቶች ሆነው ቀጥለዋል።
የህግ የበላይነት የሚለው ሃረግ ኣሁን ኣሁን ፖለቲካዊ (politicise) አየተደረገ የመጣ ስለሆነ ደረጃውን ያጣ ይመስለኛል። ስለዚህ ቢያንስ ህግ ከሁሉ በላይ መሆኑን የሚገልጽ ሌላ ሃረግ ቢፈለግለት የተሻለ ነው። ከዚያ ወዲህ በታዩ መንግስታት በመጀመሪያ የተጣሰው ዋና ነገር የህግ የበላይነት መሆኑ በተጨባች ተረጋግጧል፣ አየተረጋገጠም ነው። ለናሙና ያህል፣ ደርግ 60 ታላላቅ የሃገሪቷን ኦውቅ ማሁራንና መሪዎች ከህግ ስነስርዓት ውጪ በሆነ መንገድ ገደሏል፣ በተመሳሳይ በዚሁ በደርግ ኣገዝዝ ዘመን በኣስር ሺህዎች የሚገመቱ ወጣቶች በቀይ ሽብር ያለ ህግ ስነ ስርዓት ተገደለዋል፣ በርካቶች ያለፍላጎታቸው በሰፈራ ክኖሩበት ቀዬ አንዲጋዙና በሌላ ክፍለ ሃገር ኣንዲሰፍሩ ተደረጓል። ይህ ሁሉ በፖለቲካ ውሳኔና ያለ ህግ ኣግባባ የተፈጸመ ነበር ብዬ ኣምናለሁ።
ከደርግ በኋላ የመጣው መንግስት ገና ጫካ ሳለ የጻፈውን ማኒፌስቶና ያቀደውን የብሄረተኝነት ትልም ህጋዊ ለማድረግ በራሱና በመሰሎቹ ኣማካኝነት ህገመንግስት ኣወጣ። ዋና ዋናዎቹ ዓላማዎቹን ቦታ ካስያዘ በኋላ የተቀረውን ዓለም በሚመራበት የነጻነትና የዲሞክራሲ ጽንሰሃሳብ ላይ የተመሰረቱ ህግጋትን ኣካቶ ኣጸደቀ። ሆኖም የኋላ ኋላ ህግን ማስከበርና የዜጎችን መብት ማስጠበቅ ዓላማውን ለማሳካት ኣንደማይረዳው ሲገነዘብ፣ ህግን በፈለገው መንገድ ደጋግሞ በመከለስ ለኣገዛዙ ኣመቻቸ፣ ፍርድ ቤቶቹንና የፖሊሱን ሃይል በራሱ ኣባላትና ታማኞቹ በማስያዝ ተቆጣጠረ።
ይህ ኣገዛዝ ከፍተኛ የህግ ጥሰትን የጀመረው ከተማ በገባ ማግስት በሌብነት ስም ግለሰቦችን በየመንገዱ ህዝብ መሃል በመረሸን ነበር። የኤርትራን መገንጠል ተቃውመው በሰላም በተሰለፉ ተማሪዎች ላይ ያለህግ ስነስርዓት የጅምላ ግድያ ተካሄደ። በዘር ማጥፋት ስራ ያለህግ ስነስርዓት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብዙዎች ህይወታቸውን ኣጥተዋል። ከዚያም በመቀጠል ባለፉ ሶስት ኣስርት ኣመታት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ግን በሚሊዮኖች የሚገመቱ ሰዎች ተገድለዋል፣ ኣካላቸው ጉድሏል፣ በዓለም የተከለከለ የማሰቃየት ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል፣ የንብረትና የገንዘብ ዘረፋም በሰፊው አንደተካሄደ የኣደባባይ ሚስጥር ሆኗል። በመሆኑም፣ በርካታ የህግ ጥሰቶች ተካሂደዋል።
ህግ የበላይነት ተረጋገጠ ማለት ሁሉም ሰው ከህግ በታች ሆነ ማለት ነው። ሁሉም ሰው ከህግ በታች ሆነ ማለት ደግሞ በህግ መጣስ የተሰማሩ ሁሉ በህግ ይቀጣሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሁለት ጥቅም ኣለው። ኣንደኛ ፍትህ ለተጎዱ ወገኖች ያስገኛል። ሁለተኛ ደግሞ የመብትና የህግ ጥሰትንና የወንጀል ስራን ይከላከላል።
እሁን በያዝነው ዘመንም የመብት ጥሰቶች ቀጥለዋል። ስለመብት ጥሰት ስናወራ፣ ግለሰቦችና ቡድኖች በህዝብ ላይ የሚያካሂዱት የመብት ጥሰት ሲሆን፣ መንግስትም ደግሞ በሁለት መንገድ፣ ኣንዱ በቀጥታ የሚካሄድ የመብት ጥሰት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመብት ጥሰት ለደረሰባቸው ዜጎች ተገቢውን ፍትህ ኣንዲያገኙ ባለማድረግ መንግስት የህዝብን መብት ይጥሳል። በምሳሌነት በቅርቡ በሻሸመኔና በሌሎች የኣገራችን ከተሞች በተፈጸመው የአረጠሩ ሰዎች ጉዳይ አየተቅዛቀዘ መሄዱ ለዚህ የቅርብ ጊዜ ማስረጃ ነው። ይህን የቅርብ ጊዜ ግርጊት በመሆኑ ተጠቀሱ ኣንጂ፣ ወደኋላ መለስ ብለን ብንመረምር በርካታ ወንጀሎችና ግድያዎች `አየተጣራን ነው` በሚል ምክንያት በርካታዎቹ ወደ ህግ ሳይደርሱ ቀርተዋል መይም የፍትህ ሂደታቸው ሳይጠናቀቅ ተደናቅፏል።
በመሆኑም፣ ብዙ ፍትህ ያላገኙ ወገኖች አንዳሉ ሆኖ በጅምር የቀሩ የፍትህ ሂደቶችን በማጠናቀቅና ለወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት በማሰጠት መንግስትና የፍትህ ኣካላት ሁሉ ለህግ የበላይነት ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል። ህዝቡና ለሰው ልጅ የቆሙ ድርጅቶች ሁሉ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ዝርዝር በመያዝ ክትትል የሚያደርጉበትን ስርዓት ማበጀት ይገባል።
ኣስተማማኝ ፍትህ በሌለበት ዴሞክራሲን ማስፈን ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ኣይቻልም!
የዘገየ ፍትህ ከተነፈገ ፍትህ ይቆጠራል።
አግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ያድን!
ገብረ ኣማኑአል