ከመከራ ካለመማር የባሰ ምን አይነት ክፉ አባዜ ይኖራል? – ጠገናው ጎሹ

September 13, 2020
ጠገናው ጎሹ

የሰው ልጅ በማህበራዊና ፖለቲካዊ እንስሳነቱ እስከቀጠለ ድረስ አብሮ በሚዘልቅ ጥልቅ ብሂላቸው

(አባባላቸው) የሚታወቁት ቀደምት ወላጆቻችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ጥፋት ወይም ስህተት ውስጥ የሚያገኙትን ግለሰብ ወይም ማህበረሰብ ከፈታኙ የገሃዱ ዓለም ያካበቱትን ተሞክሮ ዋቢ አድርገው ገንቢ ምክራቸውን ከለገሱ በኋላ ከስህተት አለመማር የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት ሲያስገነዝቡ “ምከረው ፣ምከረው፣ ምከረው ፤ እምቢ ካለ ግን መከራው ይምከረው” ነበር የሚሉት።

እርግጥ ነው ይህ አባባል አሁንም በዚህ በእኛው ዘመን ይባላል ወይም ይነገራል ። ከንግግር ማድመቂያነት አልፎና ወደ መሬት ወርዶ ህይወት ለመዝራት አለመቻሉ ላይ ነው ፈተናውና ውድቀቱ ። አዎ! በሸፍጥና በሴራ የተካኑ እና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸው በንፁሃን ደም በተነከረ ገዥ ቡድኖች መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እውን ሆኖ የመከራና የውርደት ዑደተ ህይወት ፍፃሜ ያገኛል ብለን ያመንንና ተደማሪዎቻቸው (ተለጣፊዎቻቸው) የሆን እለት ነበር ስለመከራ እየጮህን የመከራ ዘመን አራዛሚዎች መሆናችን ግልፅ የሆነው ። አዎ! እንዲህ አይነቱ የወራዳነት (የልክስክስነት) የፖለቲካ ሰብእና መዳረሻው ጥርሱን ነቅሎ ከአደገበት የህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ሥርዓት ሸፍጥንና ሴራን ከግል የሥልጣን ሱሰኛነት ጋር አጣምሮ በተካነ ጠቅላይ ሚኒስትር መሪ ተዋናይነት በሚቀመር ርካሽ የፖለቲካ ቀመር አማካኝነት ይካሄዳል በሚባለው ምርጫ ተብየ የሚዘጋጁ ጥቂት የፓርላማ ወንበሮችን ተረክቦ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የባለገውን ኢህአዴግ ብልፅግና በሚል የተጀመረውን የፖለቲካ ጨዋታ ወደ ላቀ ርካሽ የፖለቲካ ተውኔትነት ይሸጋገር ዘንድ በአጃቢነት ማገልገል ነው። እውነትን የመጋፈጥና መልሰንና መላልሰን ከምንወድቅበት አዙሪት ሰብሮ የመውጣቱ ወኔ ስለሚከዳን የምንመርጠው እውነቱን መካድ (denialof the reailty) እየሆነብን ተቸግረን ነው እንጅ የማያወላዳው መሪሩ እውነት ይኸው ነው።

ብዙውን ጊዜ የማንወደውን ሃሳብ የሚሰነዝሩ ወገኖችን ምክንያታዊ በሆነ ሃሳብ መሞገት ሲያቅጠን ወይም ሳንፈልግ ስንቀር በደምሳሳው ውሸታሞች ፣ ደንቁሮዎች፣ ጨለምተኞች፣ ምቀኞች ፣ቅናተኞች ፣ ጭፍን ጥላቻ አራማጀች ፣ የምፅዓት ቀን ናፋቂዎች፣ ወዘተ ማለቱ ነው የሚቀናን ። ይህን አስተያየቴንም ከዚህ ደምሳሳ አስተሳሰብ አንፃር ለማየት የሚፈልጉ አፍቃሪ “የለውጥ ሃይል” ወገኖች ቁጥራቸው ቀላል እንደማይሆን እገነዘባለሁ ።ይህ አይነት ደምሳሳ አስተሳሰብ በእውን የሚጠቅም ቢሆን ኖሮ እንኳን የእኔ የተራ ኢትዮጵያዊው አስተያየት ተመሳሳይ አስተያየት ሊኖራቸው የሚችሉ ሊቀ ሊቃውንት አስተያየትም ፉርሽ ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር ። በመሬት ላይ ያለው ወይም የእያንዳንዱ ዜጋ የእለት ተእለት ህይወት የሚናገረው መሪር እውነታ ግን ፈፅሞ ይህን አይደለም ። ታዲያ ከረጅም ጊዜና እጅግ አስከፊ ከሆነ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ከምር በመማር እና በከፍተኛ ዋጋ የተገኘውን መልካም የለውጥ እድል (አጋጣሚ) ከሸፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ/ብልፅግና ፖለቲከኞች በመከላከል ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን መሆን ፀንቶ ከመሥራት ይልቅ ለዘመናት ከመጡበት አዙሪት ተመልሶ ከመዘፈቅ የከፋው የፖለቲካና የሞራል ውድቀት የትኛው ነው?

እንዲህ አይነቱን እጅግ አስከፊ አስተሳሰብና አካሄድ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት ከተከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ አንፃር በጥሞና ተገንዝቦ በስሜታዊነት የፖለቲካ ትኩሳት ናላው የዞረውን ትውልድ ከምር የመከረ ወይም ትክክለኛ አቅጣጫንና አመራርን ለማሳየት የደፈረ ሽማግሌም ሆነ ምሁር በሚፈለገው መጠንና ብቃት ለማግኘት አለመቻል የማያስጨንቀን ከሆነ ስለ ምን አይነት ዴሞክራሲ ነው የዲስኩርና የትንታነኔ ድሪቶ የምንደርተው? የቀደምት ወላጆቻችንን የአንድን ጉዳይ አነሳስ፣ አካሄድና ሊያስከትል የሚችለውን በጎ ወይም ክፉ ውጤት በቅጡ አጢኖ የመመካከር ፣የመምከርና የሚበጀውን የጋራ መፍትሄ የመፍጠር መልካም ባህል ካለንበት ዘመን ጋር አዘምነን ሥራ ላይ ከማዋል ይልቅ ይባስ ብለን ወደ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ መጫወቻ ካርድነት ለውጠን የምናነበንበው ንድፈ ሃሳብና የምንደርተው የትንታኔ ድሪቶ ምን ፋይዳ ሊፈይድ ይችላል? የሞቱትን የደም እንባ እየተራጨን አፈር በማልበስ ወደ የቤታችን ስንመለስ ሸፍጠኛና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) ላዘጋጁልን ርካሽ የፖለቲካ አጀንዳ ሰለባዎች እየሆን እና ሰማዕታትን እንዳልነበሩ እየረሳን የመቀጠላችን መሪር እውነት የሚነግረን በቁም የሞትን መሆናችን ካልሆነ ሌላ ምን አይነት ብሥራት ሊሆን ይችላል? ይህን እጅግ አስቀያሚ ወድቀታችንን ለማወቅ የተለየ መረጃ ወይም ማስረጃ ፍለጋ ሳያስፈልገን ለዘመናት የመጣንበትንና አሁንም የምንገኝበትን መሪር እውነት ነፃነትንና ፍትህን በሚሻ የአርበኝነት ህሊና ማስተዋል ብቻ በቂ ነው።

በእንዲህ አይነት እጅግ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ግን ቅን አሳቢዎች ብቻ ሳይሆኑ ቅን የተግባር ወገኖች ጨርሶ የሉም ፤ ከውድቀታቸው መማር የሚችሉም የሉም (አይኖሩም) ማለት አይደለም። የጋሞ ወላጆችና የእድሜ ባለፀጋዎች (ሽማግሌዎች) መልካም አርአያነት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። አሁን ከምንገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ አንፃር ከመከራ ተምሮ ቢያንስ ተጨማሪ መከራ እንዳይመጣ ለመከላከል መቻል በእጅጉ የሚያበረታታ ነውና።

እስክንድር ነጋንና የትግል አጋሮቹን ጨምሮ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ከምር ያሳስበናል በሚል መስዋእትነት የከፈሉ ፣ እየከፈሉ ያሉ እና ለመክፈልም ዝግጁ የሆኑ የእናት ኢትዮጵያ ልጆች አርያነትም አልገፈፍ ብሎ በእጅጉ እያስቸገረን ባለው የመከራና የውርደት ደመና ውስጥ አንፀባራቂና ተስፋ ሰጭ መሆኑን ሳይጠቅሱ ማለፍ ትክክል አይሆንም።

የውድቀታችን መጠንና ጥልቀት አስከፊ ካደረጉብንና እያደረጉብን ካሉት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ከቁጥራችን አንፃር በጣት የሚቆጠሩ የብርቱ መንፈስ ፣ የፅዕኑ መርህና ዓላማ ባለቤት የሆኑ ወገኖችን እጅግ ግልብ በሆነውና በተንሸዋረረው አስተሳሰባችን ማንኳሰሱ ሳያንሰን የርካሽ ፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ በሆነው የፍትህ ሥርዓት ተብየ ሥር በውሸት ክስና ሥልጠና በተሰጠው ምሥክር ተብየ ህጋዊና ሰብአዊ መብታቸው በጭቃ ላይ ሲጎተት እየታዘብን “እድሜ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለአስተዳደሩ በጥልቅ ተሃድሶ የታደሰው የፍትህ ሥርዓት ፍሬ እያፈራ ነው” በሚል የዋሁን ህዝብ የማሳሳታችን አስከፊ ባህሪ ነው።

የጥቂቶቹ ቅን ሃሳብና ተግባር ግራ በተጋባው ወይም ምን ቸገረኝ በሚለው ወይም የጎሳ/የመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ልክፍተኛ በሆነው ወይም በአድርባይነት ደዌ በተለከፈው ወገን ተፅዕኖ ሥር በወደቀበት መሪር እውነት ውስጥ ከገሃዱ ዓለም ባገኘነው ተሞክሮ መክረንና ተመካክረን የጋራ መፍትሄ በመፍጠር ረገድ እንደ ወላጆቻችንና ቅድመ ወላጆቻችን ነን ማለት እራስን ከማታለል አያልፍም ።

ይህ ባይሆንማ ኖሮ እንደ ወላጅ ወልደን ያሳደግናቸው ልጆቻችን ፣ እንደ ጎረቤት ልጆች ከልጀቻችን ጋር አብረው ያደጉ ልጆች እና በአጠቃላይ የጋራ እጣ ፈንታው በአንድ አገር ልጅነት የተቆራኘው ታዳጊ ትውልድ የገንዛ ንፁህ ወገኑን ልክ በሌው ጭካኔ ገድሎ በአስከሬን ሲጫወት “እኔን ወይም እኛን አይወክልም” ከሚል የለየለት የሞራልና የመንፈስ ዝቅጠት ውስጥ እራሳችንን ባላገኘነው ነበር።

ይህ ባይሆንማ ኖሮ “ግድብ ወይም መንገድ ወይም የመናፈሻ ፓርክ ወይም ሌላ ፕሮጀክት ከተሠራ ልጄ ወይም ባለቤቴ ወይም የቤተ ዘመድ አባል ወይም ሌላ ንፁህ ዜጋ የቁም ስቃይና የጭካኔ ግድያ ሰለባ እንኳን ሆነ “ የሚል ወላጅ ወይም ዘመድ ወይም ባለ መልካም ህሊና ወገን የሚኖር ይመስል ፕሮጀክት በግፍ የተጨፈጨፉ ንፁሃን ወገኖችን የማስረሳት ርካሽ ፖለቲካ ፍጆታ ሲውል ባላየንና ባልሰማን ነበር።

አዎ! ይህ ባይሆንማ ኖሮ በህይወት የመኖር እና በነፃነት የመፍጠርና የመሥራት እድሉ ቢሰጣቸው ኖሮ ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖች እንደ መንግሥትነታቸው ሃላፊነት እዚህና እዚያ ከጀመሩት ወይም ከሚያካሂዱት እና የርካሽ ፖለቲካ ፍጆታ ካደረጉት ፕሮጀክት በላይ መጥቀው በመሄድ አገራቸውን አገረ ገነት ለማድረግ የሚችሉ አያሌ ንፁህና አርበኛ ወገኖችን ከማጣት መሪር ውድቀት ተምረን የመከራውና የውርደት ሥርዓት ይወገድና የሚበጀን ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ በአብሮነት ቆመን መታገል በቻልን ነበር።

በእጅጉ ህሊናን የሚያቆስለው ደግሞ በደም እንባ እየተራጨን አፈር አልብሰን በተመለስን ቁጥር አፈር ያለበስነው በእነዚያ ንፁሃንና ገና ሠርተው ባልደከሙ ወገኖቻችን አእምሮና ህሊና ውስጥ የነበረውንና በቀላሉ የማይተካውን እራሱን እውነትን እና እምቅ እውቀትና ክህሎትን መሆኑ ከምር ተሰምቶን ለውጤታማ ትግል አለማምረራችን ነው። እናም አሁንም በማያቋርጥ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ሥርዓት ሥር ሌላ አያሌ ዓመታትን ከማስቆጠር በጊዜ ስህተትን አርሞ ወደ ትክክለኛው አስተሳሰብ ፣ መስመርና ተግባር መሰባሰቡ የግድ ነው ። በእውን የነፃነትና የፍትህ ሥርዓትን የምንናፍቅ ከሆነ ።

ይህ ግን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን የህወሃት /ኢህአዴግ ሥርዓት ኦሮሙማን (ኦሮማይዜሽንን) ግባቸው ባደረጉ ሰነፍ ግን አደገኛ ፖለቲከኞች ተረኝነት በሚያስቀጥል የሸፍጥ/ የሴራ ተሃድሶ ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም። ይህ ይሆናል በሚል ቅዠት ውስጥ ወርቃማ ጊዜን እና የሰውና የማቴሪያል ሃብትን ማባከን ከዘመናት ብቻ ሳይሆን አሁንም በከፋ አኳኋን እየቀጠለ ካለው መከራና ውርደት ያለመማር አስከፊ ውድቀት ነው። ከዚህ የባሰ ከሰብአዊ ፍጡርነት በታች የሚያውል አስከፊ የአስተሳሰብና የሞራል ድህነትም የለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሕግ አምላክ! የኢትዮጵያን ታሪክ የቆነፀላችሁበት እና ያደበዘዛቹበት አቀራረብ ይስተካከል።የመንግስት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ድረ-ገፅን ይመለከታል።

ግፈኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ፣ ክፉ ውጤት የሚያስትለውን አስተሳሰብ እያወቁ ወይም የአስተሳሰቡ ድጋፍ ሰጭ እየሆኑ ፣ ለግፍ እቅድና አፈፃፀም ሴራ እውቅና እየሰጡ፣ እራሳቸውም እየገደሉና እያጋደሉ እና ከዚህ ሁሉ በከፋ ደግሞ እንደ ስፖርት ትርኢት ቆመው እየተመለከቱ ይህ “የእኔን ወይም የእኛን የተቀደሰ ምንነትና ማንነት አይወክልም ወይም አይመለከትም ” ሲሉን ቢያንስ የህሊና መንገጫገጭ ጨርሶ አይሰማቸውም። እኛም “ማነው ይህን ትውልድ በሥርዓተ ትምህርት ሳይቀር አዘጋጅቶ ሰብአዊ ፍጡርነቱን እስከሚስት ድረስ የሀሰት/የፈጠራ ፣ የጥላቻ ፣የጭካኔና የመጠፋፋት መርዝ እያጋተ ያሳደገውና መሣሪያ እያደረገው ያለው ?” ብለን ለመሞገት ወኔው ከድቶን ግዙፍና መሪር ዋጋ የተከፈለበትን መልካም የለውጥ እድል ህወሃት አልባ የሆነውንና ነገር ግን ከህወሃት በከፋ ሁኔታ በተረኝነት የቀጠለውን ሥርዓተ ኢህአዴግ/ብልፅግና ለሚዘውሩት ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች አስረክበን በዚያው ባለማመዱን የመከራና የውርደት አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀናል። እናም ከዚህ የከፋ ለዘመናት ከሰሙትና ካዩት ብቻ ሳይሆን ከእለት ተእለት ህይወት ጋር ከኖሩበት መከራና ውርደት ተሞክሮ ካለመማር የከፋ ልክፍት ጨርሶ የለም።

እጅግ አብዛኛወቹ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች ተብየዎችም የሩብ ምዕተ ዓመቱን የመከራና የሰቆቃ ህገ መንግሥት ፣ ሥርዓትና መዋቅር በተረኝነት በማስቀጠል የዋሁን ህዝብ የድንቁርና እና የሁለንተናዊ ጉስቁልና አዙሪት ወስጥ መልሰው እየዘፈቁት ያሉትን ሸፍጠኛና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያንን/ብልፅግናዊያንን በግልፅና በቀጥታ ከመሞገት ወይም ከመታገል ይልቅ “አገር እንዳይፈርስ” የሚል እጅግ ወራዳ (ልክስክስ) የሆነ የፖለቲካ ሰብእናቸውን በገፀ በረከትነት በማቅረብ በቤተ መንግሥት ተረኛ ገዥዎች ጫማ ሥር እጥፍና ዘርጋ ማለቱን ተያይዘውታል ። የህሊና ቢስነታቸውና መከረኛውን ህዝብ የመናቃቸው ጥግ ደግሞ ይህንኑ የተዋርዶ አዋራጅነት የፖለቲካ ማንነታቸውን ይነግሩን ዘንድ ባዘጋጁልን መድረክ ላይ ታዳሚዎች እንድንሆን “የማክበር ጥሪያችን ይድረሳችሁ” ሲሉን ነው ።

ለዋቢነት ስም ጠቅሸ ባላልፍ ደስ ባለኝ ነበር ። ነገር ግን የምጠቅሰው በአገር ላይ እየተቆመረ ስላለው የፖለቲካ ቁማር እና የቁማሩ አድማቂዎች ወይም ከቁማሩ አተርፍ ባይ የፖለቲካ ደርጅት መሪዎች አስተሳሰብንና ባህሪን እንጅ የግል ማንነታቸውንና የሙያ ክህሎታቸውን ባለመሆኑ መጥቀስ ትክክል ነው የሚል እምነት ስላለኝ እጠቅሰዋለሁ ።

በወቅቱ እኔንና መሰሎቸን ጨምሮ አያሌ ቁጥር ካላቸው ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ ወገኖች ከልብ የሆነ ድጋፍና አድናቆት ተችሮት የነበረው የቀድሞው አርበኞች ግንቦት 7 ሊቀ መንበር እና የአሁኑ የሸፍጠኛና ሴረኛ ኦህዴድግ/ብልፅግናዊያን ዋነኛ የተውኔት አጃቢና አድማቂ የሆነው የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከሰሞኑ ወደ ምድረ አሜሪካ ብቅ ብሎ ያሰማን “የለውጥ ሃዋርያቱ የፖለቲካ የልብ ትርታ እና የእኔና የመሰሎቼ የፖለቲካ የልብ ትርታ ልዩነቱ የስምና ሁለት አካል መሆኑ እንጅ ጨርሶ ልዩነት የለውም ። እንዲያውም የሃዋርያቱ የፖለቲካ የልብ ትርታ ከቆመ እንደ ድርጅት የእኛ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ የአገር የልብ ትርታ ይቆምና ህልውና ያከትማል” የሚል አይነት በእጅጉ የዘቀጠና “የቁርጣችሁን እወቁ” አይነት መልእክት ነው ያስተላለፈልን። ፕሮፌሰር ብርሃኑ መከላከያው ፣ፍትህ ሥርዓቱ ፣የፀጥታና ፖሊስ ሃይሉ ፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የመሳሰሉ ተቋማት “በጣም የጎላ የማሻሻያ ሥራ ተሠርቶባቸዋል” የሚል ትረካ የሚነግረን በሌላ ፕላኔት ላይ ወይም በምእናባችን ውስጥ ስለምትገኝ ኢትዮጵያ ነው ወይስ ከመቶ ሚሊዮን የሚበልጠው ህዝቧ በጥቂት የጎሳ/የመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ክፉ ደዌ በተለከፉ ገዥ ቡኖችና ግብረ በላዎቻቸው ሸፍጥና ሴራ ሁለንተናዊ የመከራ የውርደት ቀንበር ተሸክሞ እንዲቀጥል ስለተደረገባት ኢትዮጵያ ? ምነው ይህን ያህል እንኳን ፊደል የቆጠረው ለመቁጠር እድል ያላገኘው አብዛኛው የአገሬ ህዝብ ሊታዘበን እስከሚችል ድረስ ወደታች ወረድን ?

በወታደራዊ አገዛዝ ዘመን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች በክረምት የእረፍት ወቅት ለመሠረተ ትምህርት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መዝመት ነበረባቸውና እኔም ወደ አንዱ የአገሬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ዘምቼ ነበር ። ወቅቱ ደርግ ተቀናቃኞችን በማያዳግም ጨካኝ በትር መትቶ ሥልጣኑን ያደላደለበት ስለነበር የኢሠፓ ካድሬዎች (‘ጓዶች’) መሠረተ ትምህርትን ለማጠናከር በሚል ወደ ገበሬው እየዘለቁ ከጥሬ ገንዘብ ጀምሮ በአይነት እስከሚገኝ ጥቅማጥቅምን የሚሻሙበት ነበር። በአንድ እለተ ሰንበት ገበሬውን በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ በሚገኝ ሜዳ ላይ ሰብስበው ከገበሬ ማህበራት አገልግሎት ጋር በተያያዘ እርስ በእርስ የሚጣረስ ዲስኩርና ማብራሪያ ሲሰጡ ነገሩን ከልምድ አሳምረው የሚያውቁና የቁጭት ስሜት ያደረባቸው አንድ አዛውንት እጃቸውን አውጥተው ሲፈቀድላቸው ምርር ብለው “ተስማምታችሁ ብትበሉን ምን አለበት!” ያሉት አእምሮዬ ውስጥ አልጠፋም። አሁንም ኢህአዴጎች/ብልፅግናዎችና ተደማሪዎች መንግሥት እና ተፎካካሪዎች ነን እያሉ ይህን መከረኛ ህዝብ ግራ ከሚያጋቡትና በእጅጉ ከሚያሰለቹት ተስማምተው ሊገዙት እንደሆነ ቁርጡን ቢነግሩት ምን አለበት ?

ልብ ለማለት የሚያስችል የቅንነት ፣ ለእራስ የመታመን ፣በእራስ የመተማመን እና አገርን የማፍቀሩ አርበኝነት ስሜት ከውስጤ አልወጣም ፤ ሊወጣም አይችልም የሚል የአገሬ ሰው ይህን የእራሳችንን መሪር ሃቅ ለመቀበል የሚቸገር አይመስለኝም ። ችግሩ አብዛኞቻችን የእራሳችንን ልክ የሌለው ከመከራ ያለመማር መሪር እውነት አምኖ በመቀበል ተገቢውን እርምት የማድረጉ ፈተና ስለሚያስፈራን ቀላሉ መሹለኪያ እውነቱን መካድ (denial of the reaity) ከመሆኑ ላይ ነው።

ተማርኩ እና እየተማርኩ ነው የሚለው የህብረተሰብ ክፍል የዚህ አስቀያሚ የፖለቲካ ባህሪ ሰለባ ሲሆን ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አስከፊ ያደርገዋል። ከሚታየውና ከሚጨበጠው ብቻ ሳይሆን በውስጡ እየኖረበት ካለው የመከራና የውርደት መሪር እውነታ በመማር ውጤታማ ድርሻውን ለመወጣት የተሳነው ምሁር ወይም የተማርኩ ነኝ የሚል የህብረተሰብ ክፍል ከሚያነበው የንድፈ ሃሳብ መጽሀፍና ከሚደርተው የትንታኔ ድሪቶ ምን ሊማርና ሊያስተምር እንደሚችል ለመረዳት ያስቸግራል። ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር የማሰቢያና የማገናዘቢያ ጊዜና ትእግሥት ሳይኖረው ወይም ከርሱ (የሥጋ ስስቱ) አሸንፎት መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረው ሃይል ወይም ቡድን ጋር የሚገለባበጥ ወይም በተቀዋሚ (ተፎካካሪ) ፖለቲከኝነት ስም በቤተ መንግሥት ባለሟልነት (ተለጣፊነት) እጥፍና ዘርጋ የሚል ምሁር ወይም የተማርኩ ነኝ የሚል የህብረተሰብ ክፍል እንኳን ከመከራ ሊማር መከራ ያለም አይመስለውም።

ከጨዋው (ፊደል የመቁጠር እድል ካላገኘው) አብዛኛው የአገሬ ሰው ጀምሮ በዓለማዊው ወይም በመንፈሳዊው ወይም በሁለቱም የትምህርት ችሎታና ክህሎት ሊቀ ሊቃውንት ነኝ እስከሚለው የአገሬ ሰው ድረስ እኩያን ፖለቲከኞች ምስቅልቅሉን ያወጡትንና እያወጡትን ያሉትን ይህን ትውልድ እንደ ቀደምት ወላጀቻችንና አያቶቻችን ያጠፋውን ወቅሶ ፣የተበደለውን አስክሶ እና እየደጋገሙ የስህተትና የጥፋት አዙሪት ውስጥ መገኘት ከደመ ነፍስ እንስሳነት ተሽሎ አለመገኘት መሆኑን በግልፅ ነግሮና ተነጋግሮ ለአገር የሚበጅ ድርሻን ከመወጣት ይልቅ የአዙሪቱ ሰለባ ሆኖ ከመገኘት የባሰ ከመከራ ያለመማር ክፉ ልክፍት የለም።

ምንም እንኳ በተፈጥሮ ከተሰጣቸው ምንነትና ችሎታ አልፈው የመገኘታቸው አቅምና እርቀት ወደ የሰው ልጅ ልዩ ስጦታና ችሎታ ሊያሸጋግራቸው ባይችልም አንዳንድ ደመ ነፍስ እንስሳት ከሚያዩት ድርጊትና የምልክት ቋንቋ አስደናቂ ትምህርት ይቀስማሉ ። “ይህን ማድረግ ጥሩ ነው፤ ያኛውን ማድረግ ግን ይጎዳል” ተብለው የሰለጠኑበትን ወይም የተማሩትን ይከተላሉ።

እኛ ግን ለዘመናት ተዘፍቀን ከዘለቅንበትና አሁንም ቅርፅና ስያሜ እየቀየረ ከቀጠለው የእኩያን ገዥ ቡድኖች የመከራና የውርደት ሥርዓት ተምረን የሚበጀንን ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን ለማድረግ ባለመቻላችን ነገረ ሥራችን ሁሉ ባዶ ጩኸትና እግዚኦታ ሆኗል። ታዲያ ይህ አይነት ልክ የሌለው ውድቀት ከደመ ነፍስ እንስሳት ተለይተን ከረቂቅ አእምሮና ብቁ አካል ጋር በፈጣሪ አምሳል የተፈጠርን ማህበራዊ እንስሶች ነን ለማለት እንዴት ያስችለናል? ለዘመናት ተዘፍቀን ከኖርንበት መከራና ውርደት ተምረን የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴግ/ብልፅግና ከሥሩ ነቅለን መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችለንን ወርቃማ እድል (አጋጣሚ) ለሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች አሳልፈን ከመስጠትና ተመልሰን አስከፊው አዙሪት ውስጥ እራችንን ከማግኘት የባሰ ምን አይነት ከመከራ ያለመማር ልክፍት ይገኛል?

የዋሁ የአገሬ ህዝብ እንኳን ለእራሱ ለተቸገረ የባእድ አገር ሰው መትረፍ የምትችል ምድር (አገር) ዜጋ ሆኖ ሳለ በየዘመኑ መንበረ ሥልጣኑን በሚቆጣጠሩ እኩያን የገዥ ቡድኖች ምክንያት መሠረታዊ ፍላጎቱን (ምግብ፣ አልባሳትና መጠለያ) ሳይቀር ማሸነፍ ተስኖት ለዘመናት እየተመፀወተ መኖሩ ሳያንሰው (መኖር ከተባለ) “የመከራ ቀንበር የተሸከምኩበት ትክሻዬ ዛለ ወይም ቆሰለ” ብሎ ጩኸት ባሰማ ቁጥር ከቁም ስቃይ እስከ ህይወተ ህልፈት በሚደርስ ፖለቲካ ወለድ ቅጣት ሲቀጣ ከማየት የባሰ ምን አይነት አስተማሪ መከራና ሰቆቃ ይኖራል? ከዚህ ተምሮ የበኩልን በጎ ድርሻ ለመወጣት ካለመቻል ወይም ካለመፈለግ የከፋ ምን አይነት የሞራልና የፖለቲካ ኮስማናነትና ውድቀትስ ይኖራል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከፖለቲካ ነፃ የሆነ አንድም ሰው የለም ፣ በሀገር ጉዳይ ገለልተኛ መሆን አይቻልም!

በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የተከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን እውን የማድረግ ተጋድሎ ለሸፍጠኛና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን ፖለቲከኞች አሳልፈን ሰጥተን ከመጣንበት አስከፊ አዙሪት መውጣት አለመቻል ብቻ ሳይሆን ይበልጥ በባሰ አዙሪት ውስጥ እራሳችንን እንድናገኝ ካደረጉን አይነተኛ ምክንያቶች አንዱ ይኸው ከእራሳችን መከራና ውርደት ከምር ለመማር ያለመቻላችን ወይም ያለመፈላጋችን ክፉ አባዜ ነው።

በተሰጠው የኦሮሙማን (0romization) ፕሮጀክት በአዲስ አበባ የማስፈፀም ተልእኮው ስኬታማነት የሚኒስትርነት ሹመትን ተጎናፅፎ የተሸኘውን ታከለ ኡማን አዳነች አቤቤ ተክተዋለች ። በአዲስ ዓመት ዋዜማ ስም ይኸውና እየተተወነ ያለው ይቅርታን ለርካሽ ፖለቲካ ፍጆታ የማዋል ተውኔት በአዲስ አበባ መከረኛ ህዝብ ላይ ይተወን ዘንድ የተሰጣትን ተልእኮ ከመቅፅበት ጀምረዋለች ወይም አስጀምረዋለች ። ለዚህ ተልእኮዋም በየ መሥራያ ቤቱ እየተገለባበጠች ያገኘችው ልምድ በመኖሩና ጥርሷን ነቅላ ያደገችበት እኩይ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ከረጢት በመሆኑ አትቸገርም። እናም በእውን ሥራ ላይ ለሚያውለው እጅግ አስፈላጊና ውድ በሆነው የይቅርታ እሴት እየተሳለቀችና መከረኛውን ህዝብ እያደነዘዘቸ የታከለን ፕሮጀክት እንደገና በማጥናት ወይም በመከለስ እና መከረኛውን ህዝብ በሚያደነዝዝ ሥልት (አኳኋን) ፕሮጀክቱን ማስቀጠሏ አይቀሬ ነው። ከዘመናት የመከራ ሥርዓት ተምሮ “በመከራየና በውርደቴ መነገዱና መሳለቁ በቃ!“ የሚል የነፃነት ፣ የፍትህና የእኩልነት አርበኛ እስከ አልተገኘ ድረስ የኦሮሙማ ፖለቲከኞችን ቀጣይ የመከራና የውርደት ዘመን መቀበል የግድ ይሆናል ።

በሚያሳዝን መልኩ በእድሜም ሆነ በምሁረነት ተሞክሮ አንጋፋ ናቸው የምንላቸው ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መሰል ፖለቲከኞችና ካድሬዎች ሸፍጠኛና ስሜት ኮርኳሪ ዲስኩራቸው ገና ከአንደበታቸው ከመውጣቱ “የዘመናችን ሙሴዎች” በሚል በስሜታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ናላው የዞረውን ወጣት ትውልድ ማሳሳታቸው ያስከተለው ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ዘግናኝ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ትምህርት አልሆናቸው ብሎ ዛሬም የታከለ ኡማ በአዳነች አቤቤ መተካትን ከማሞካሸት አልፎ አዳነች አቤቤ ለምትደሰኩረው መከረኛውን ህዝብ የማደንዘዝ ሸፍጠኛ ዲስኩር ምርቃኑን ሲያዥጎደጉዱ መታዘብ በእውነት ምነው ምን ነካን ? ያሰኛል ። እያልኩ ያለሁት አያበረታቱና አይመረቁ አይደለም። እንዴት የሩቁ ቢቀር ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ዲስኩር ወይም ስብከት ገና በአየር ላይ እንደዋለ “የኢትዮጵያ ገድለ ትንሳኤ ከላይ በተላኩ የለውጥ ሃዋርያት ተፈፀመ ” በሚል ከመከራው ብዛትና አስከፊነት የተነሳ የሚሰማው በጎ ቃል ሁሉ እውነት እየመሰለው ያለምንም ሂሳዊ አቀራረብና ጥያቄ አሜን ብሎ የሚቀበለውን ህዝብ ጮቤ በማስረገጣችን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከተፈፀመው አሰቃቂ ፖለቲካ ወለደ ወንጀል ተምረን ቢያንስ በቂ የግንዛቤ ጊዜ እንዴት አይኖረንም ? ነው እያልኩ ያለሁት ። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሸፍጥ አቀነባባሪነት ታከለ ኡማን ወደ አዲስ አበባ አምጥቶ የሚጠበቅበትን የቤት ሥራ እንዲያከናውን ከተደረገ በኋላ የህዝብንና የታዛቢን ግፊት መቋቋም ሲያስቸግር በሚኒስተርነት ሹመት ዘወር አድርጎ ከተመሳሳይ የተበከለ የፖለቲካ ውሃ ምንጭ ( ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በእኩይ አስተሳሰብና ተግባር ከበሰበሰና ከከረፋ ሥርዓት) የተቀዳችውንና በችሎታም ሆነ በሃላፊነት ሥነ ምግባር ከታከለ ጨርሶ የማትሻል ካድሬን መተካት እንዴት አይነት ተአምራዊ የፖለቲካና የፍትህ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ለማሳመን ይቅርና ለማስመሰለም ብዙ አያስኬድም።

በነገራችን ላይ መበስበሱና መከርፋቱ በዋናነት የሚመነጨው ከሥርዓቱ እንጅ ከታከለ ኡማ ወይም ከአዳነች አቤቤ ወይም ከሌላ የኢህአዴግ/ብልፅግና ግለሰብ ካድሬ እኮ አይደለም ። ለዚህም ነው እኮ ግለሰብ ካድሬዎችን ከሥርዓቱ እየነጠሉ ወይ መመረቅ ወይም መራገም የምንፈልገውን ሥርዓተ ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ የምናደርገውን ትግል ወይም ጥረት በእጅጉ አስቸጋሪ ያደረገብን። አዎ!

ለዚህም እኮ ነው አገርን የሚታደግ ሌላ ሰው ወይም ድርጅት ለማፍራትና ለማጎልበት አቅቶን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ነፍስ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ነፍሶች ከተሸከመች አገር ህልውና ጋር እያቆራኘን ዛሬ ወይም ነገ አለቀልን እያልን እግዚኦ የምንለው።

እነዚህ ምሁራን ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ሌላ ባለሥልጣን ወይም ካድሬ በግል የዋለላቸው (የዋለባቸው ማለት ይሻላል) ውለታ ካለ ይህንኑ ግልፅ አድርገው የምሥጋና እና የምርቃት ድርሰታቸውን ማስደመጥ ወይም ማስነበብ መብታቸው ነው ። የመከራና የውርደት ሥርዓትን በለየለት ሸፍጠኛ ተሃድሶ ስም እንዲቀጥል በማድረግ የህዝብን የመከራና የወርደት ዘመን እያራዘሙበት ያሉትን ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን ማሞካሸትና መመረቅ ግን ከእውነተኛው የምሁርነት ትርጉምና እሴት ጋር ጨርሶ ዝምድና የለውም። ከእውነተኛው የመማር እሴት ጋር ዝምድና የሌለው ተማርኩ ባይነት ደግሞ ከህዝብ የመከራ ህይወት ተምሮ የህዝብን መከራና ሰቆቃ የመታደግ አቅም ጨርሶ የለውም።

አዎ! ሲሆን የቀደምት ወገኖቹን ሰፊና ጥልቅ ምክር ከምር በመውሰድ ፣ ካልሆነ ደግሞ ከራሱ እጅግ መሪር ተሞክሮ በመማር የመከራና የውርደት ቀንበር አሸክመው ዘመናትን ያስቆጠሩትንና እና አሁንም የበላይ ጠርናፊያቸውን ቀይረው እና ያንኑ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ወይም በአያሌ ንፁሃን ዜጎች ደም የተጨማለቀ ፖለቲካዊ ማንነታቸውን ብልፅግና በሚል የሸፍጥ ካባ ጀቡነው (አልብሰው) የሚሳለቁበትን ፖለቲከኞች በቃችሁ ለማለት ወኔው የጎደለው ምሁርና ፖለቲከኛ ስለ ህዝብ መከራና ውርደት የሚደርተው የትንታኔ ድሪቶ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም ።

ከዚህ በተቃራኒው የእውነተኛ አርበኝነት ስሜት ባለቤት የመሆን ብቻ ሳይሆን በተግባር ውሏቸውም ያስመሰከሩ ፣ በማስመስከር ላይ የሚገኙና ወደ ፊትም በዚሁ አርበኝነታቸው ፀንተው ሊቆሙ የሚችሉ የአገሬ ልጆች (ሰዎች) መኖራቸው እርግጥ ነው። በእጅጉም ያበረታታል !

ለዋቢነት እስክንድር ነጋንና የትግል ባልደረቦችን ፣ ደጋፊዎቹንና በአጠቃላይ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አገር ምሥረታ የሚያሳስባቸውን የአገሬ ሰዎች መጥቀሱ ተገቢ ነው።እስክንደር ነጋን ከጋዜጠኝነት ሙያው ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በፅዕናት በቆመለት ፣ መስዋእትነት በከፈለለትና አሁንም ፀንቶ በቀጠለበት ድንቅ የፖለቲካ ሰብእናውና ሥራው እንጅ በግል አላውቀውም ።እስክንድር እንደማነኛውም ሲሰራ ሊሳሳት እንደሚችል ሰብአዊ ፍጡር ሲሰራ አይሳሳትም ብሎ የሚከራከር ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

ነገር ግን የሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ገዥ ቡድኖች አቃቤ ህግ ተብየ በእስክንድርና የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ባልደረቦቹ ላይ ክስ የመሠረተባቸውን በእጅጉ አሳፋሪ ጉዳዮች (ጭብጦች) ለሚያነብ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው ከሥስት አሥርተ ዓመታት በኋላም እጅግ አስከፊ በሆነ አዙሪት ተመልሰን መዘፈቃችን ለመረዳት ብዙ ማሰብ ጨርሶ አያስፈልገውም ። የፍትህ ሥርዓትን ያህል እጅግ ቁልፍና ክቡር የመንግሥት አካል (branch of governmet) በዚህ ደረጃ ለማራከስ ህሊናቸውን ያልኮሰኮሳቸው ገዥ ቡድኖች “ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እያሸጋገርናችሁ ነው” በሚል ከሰብአዊ ፍጡር በታች አድርገው ሲገምቱን “ቀይ መስመሩን አልፋችሁ በንፁሃን ዜጎች ላይ ታይቶ የማይታወቅ የመከራና የሰቆቃ ዶፍ ስታወርዱ ታግሰናል፤ አሁን ግን በቃችሁ” ብለን ለመቆጣት አልቻልንም ወይም አልፈለግንም። እንደ አሜባ ተራብቶ አገሩን ያጣበበው ተፎካካሪ ተብየ ፖለቲከኛም ይደረጋል በሚባለው ምርጫ አንድ ብርቱ ተፎካካሪ ተዳከመልኝ በሚል ደስ የሚሰኝ እንጅ የንፁሃን የፖለቲካና የሰብአዊ መብት መደፍጠጥ የሚገደው አይደለም። በተለይም የኦሮሞን ማህበረሰብ ያስቆጣልናል በሚል እጅግ የወረዱና እንኳን እስክንድር ማነኛውም ስለ አገሩ መሠረታዊ የፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብር እውቀት ያለው ዜጋ ሊጠቀምባቸው የማይችሉ ቃላት ወይም አገላለፆች የሚያሳዩት አገራችን ጨርሶ ሃላፊነት በማይሰማቸው የገዥ ቡድኖች እጅ እንደሆነችና ይህም በወቅቱ ካልተገታ ከዚህ ወደ ባሰ አዘቅት ይዘውን እንደሚወርዱ ነው።

እነርሱ (ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች) ምንም ይበሉ ምን፦

እስክንድር ነጋ በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ የግፍና የመከራ አገዛዝ ሥር ከቤቱ ይልቅ የግፍ ማስፈፀሚና መፈፀሚያ የሆኑ እስር ቤቶች መኖሪያው እስኪመስሉ ድረስ መሪር መስዋእትነት የከፈለ እንቁ የእናት ኢትዮጵያ ልጅ ነው!

አዎ! እስክንድር ግፈኛና ጨካኝ የገዥ ቡድኖች በእርሱ ላይ የሚፈፅሙት ግፍና ሰቆቃ አልበቃቸው ብሎ ውድ ባለቤቱንም የአካልና የሥነ ልቦና ማሰቃያ እስር ቤቶቻቸው ሰለባ በማድረግ ወደ ዚች ዓለም በፍፁም ተስፋ የመጣውን ውድ ልጇንም (ልጃቸውንም) የሰቆቃና የመከራ እስር ቤት ልጅ ሲያደርጉበት ነፃነትና ፍትህ የሌለባት አገር ለልጄም ሆነ ለሌሎች ሚሊዮኖች ህፃናት በፍፁም ማውረስ አይገባም በሚል ወደር የሌለው ዋጋ የከፈለና እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ እውን እስከሚሆኑ ጨርሶ እረፍት የለኝም (የለንም) ለሚል ትውልድ አንፀባራቂ አርያነት ያለው የውድ እናት አገር ልጅ ነው!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮ ቴሌኮም ለውጪ ሀገር ድርጅት ይሸጥ ወይስ አይሸጥ ? (መላኩ ከአትላንታ)

አዎ! እስክንድር ነጋ የዋሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ልክ የሌለው የመከራና የውርደት ቀንበር አሸክመውት የኖሩትንና ዛሬም ህወሃትን ከሥልጣን ማእከሉ አስወግደው በተረኝነት ሸፍጥኛ ሴረኛ ፖለቲካ ጨዋታቸው የቀጠሉትንና ሁለት አመት ሙሉ ለማየትም ሆነ ለመስማት በሚዘገንን አኳኋን ንፁሃን ሲገደሉ፣ የቁም ሰቆቃ ሲፈፀምባቸው ፣ ጎጇቸው (መጠለያቸው) ፈራርሶና ተቃጥሎ ለመከራ ሲዳረጉ፣ ደም ተፍተው ያገኙት ንብረታቸው በደቂቃዎች ውስጥ እንዳልነበር ሲሆን ፣ወዘተ “በለውጥ ወቅት የሚያጋጥም ግጭት ነው” በሚል የተሳለቁትንና የሚሳለቁትን ደናቁርት ነገር ግን አደገኛ ፖለቲከኞችን (ገዥ ቡድኖች) አጥብቆ የሚፀየፍ የእናት ዓለም ኢትዮጵያ አርበኛ ነው!

አዎ! እስክንድር መከረኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በቃኝ ብሎ የተነሳበት እና ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ የፖለቲካ ወለድ ወንጀል ማስፈፀሚያ የሆነውን ህገ መንግሥት ጨምሮ ዋና ዋና መንግሥታዊ አወቃቀሩና ሰንሠለቶቹ ጨርሶ ባልተነኩበት በኢህአዴግ (በብልፅግና) የበላይ መሪነት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን አይሆንምና የሽግግር ሄደቱ በአገራዊ መግባባት ላይና በባለድርሻ አካላት ያልተገደበ ተሳትፎ ይካሄድ ዘንድ ሰላማዊ ትግሉ መቀጠል አለበት በሚል ከመንቀሳቀስ ውጭ ሌላ ዓላማና ፍላጎት የሌለው መልካም የእምዬ ኢትዮጵያ ዜጋ ነው!

አዎ! እስክንድር ባለጌና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች በጭፍን የጎሳ ማንነት ፖለቲካ ትኩሳት ናላውን ያዞሩትን ወጣት ብቻ ሳይሆን የሚያዙትን ፖሊስም ከቢሮው ጀምሮ ለስብሰባ ቀጥሮ በያዘበት ሆቴል ሁሉ እየላኩ በገንዛ አገሩ መላወሻ ሲያሳጡት አብረውት ያሉ ውጣቶች በስሜታዊነት ስህተት ውስጥ እንዳይገቡ ያለመታከት የሚያሳስብ ድንቅ የእማማ ኢትዮጵያ ልጅ ነው!

አዎ! እስክንድር በመከራ ውስጥ አልፎ ከመከራ የተማረና የመከራና የውርደት ፖለቲካ ታሪክ ምእራፍ ይዘጋ ዘንድ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን እውን ማድረግ የግድ ነው የሚል ፅዕኑ እምነት ያለውና ለዚሁ የተቀደሰ ዓላማም ተደጋጋሚ መስዋእትነት የከፈለና አሁንም በመክፈል ላይ የሚገኝ ብርቱ የእናት ኢትዮጵያ ልጅ ነው!

አዎ! እስክንድር በጎሳ/በመንደር/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ስሌት በተለከፉ ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች በገንዛ አገራችው ቤታቸውና ኑሯቸው ፈርሶ እንደ አልባሌ ነገር ወደ ጎዳና የተገፉ አያሌ ንፁሃን ዜጎች የሰቆቃና የድረሱልን ጩኸት በሚያሰሙበት ቦታ ሁሉ ከባልደረቦቹ ጋር ፈጥኖ በመገኘት ቢያንስ ሰቆቃቸው የሚጋራና ለህዝብም የሚያሳውቅ የትልቅ ሰብእና እና ሞራል ባለቤት የሆነ የውድ እናት ኢትዮጵያ ልጅ ነው!

አዎ! እስክንድር እነ ጀዋር መሃመድ አደገኛ የሆነ የጎሰኝነት ፖለቲካ ትኩሳት ሰለባ ያደረጉትና እራሱን በቄሮነት ስም የሚጠራው እና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በመንግሥት ተብየው አካላት በመታገዝ በገንዛ ወገኑ ላይ በዚህ ዘመንና በኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ለማየት ለማሰብም የሚጨንቅ ግፍ የፈፀመውንና ወደ ፊትም ሊፈፅም የሚችለውን ቡድን በአሸባሪነት ፈርጆ አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል የሚለው ትክክለኛ አቋሙ ምቾት አልሰጣቸው ያሉ ተረኛ ባለ ሥልጣናት (ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ) እና ካድሬዎቻቸው አጋጣሚ ጠብቀው የሰብዊ መብት መደፍጠጫ እስር ቤታቸው ሰለባ ያደረጉት ንፁህ የእናት ኢትዮጵያ ልጅ ነው ! የያኔዋ አቃቤ ህግ ተብየና የአሁኗ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አውቃም ሆነ አምልጧት “ባልደራስ እያለ እራሱን የሚጠራውና ቄሮ የሚሳደበው” ስትል በአደባባይ የነገረችን በእነ እስክንድር ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ አጋጣሚ ይፈለግ እንደ ነበረ ነው።

እነ እስክንድርን በመሰሉ የሞራልና የፖለቲካ ልዕልና መርህ ላይ ፀንተው በቆሙና በሚቆሙ የአገሬ ልጆች አስተባባሪነት ነው የአገሬ ህዝብ ለዘመናት የመከራና የውርደት ቀንበር አሸክመው ለመግዛት ሲሉ በፈፀሙት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል እጃቸው በንፁሃን ደም እንደተጨማለቀ አሁንም ለውጥ አመጣን በሚል የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታ በመጫወት ላይ ከሚገኙ ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን ነፃ ለመውጣት እና የነፃነትና የፍትህ ሥርዓትን እውን ማድረግ የሚችለው። እንዲህ አይነት የአገሬ ሰዎች (ልጆች) ናቸው ደጋግመን አይወድቁ ውድቀት ከወደቅንበትና እየወደቅን ካለንበት እጅግ አሳፋሪ የሞራልና የፖለቲካ እኛነታችን መሪር እውነት ትምህርት በመውሰድ እንደ ግለሰብ ዜጋና እንደ አንድ አገር ህዝብተከብረን ፣ተከባብረንና በልፅገን የምንኖርበትን ሥርዓተ ፖለቲካ እውን ለማድረግ የሚያስችሉን ።

አቤ ጉበኛ ከዛሬ 46 ዓመት በፊት ለህትመት ያበቀውን አልወለድም ለመፃፍ ያነሳሳውን ምክንያት በገለፀበት መግቢያ ላይ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እስከሚቻለው ድረስ የበጎ ነገር ተቃራኒ ከሆኑ ነገሮች እራሱን እያራቀ በጎ ወደ ሆኑት ማለትም እውነት፣ ፍትህ ፣ ቅንነትና ሃይማኖታዊ እምነት ለማምራት የሚጣጣር ህዝብ መሆኑን ይገልፅና ከዚህ በተቃራኒ የገጠመውን ፈታኝ ሁኔታ ይህ ቅንና መከረኛ ህዝብ ለዚህ በጎ ዝንባሌው የተከፈለው ዋጋ ህሊና በሌላቸው ዝቅተኛና ከፍተኛ ሹማምንት ተረግጦ መገዛትና እረኛ እንደሌለው በግ በደመ ነፍስ በሚንቀሳቀሱ ነጣቂ ተኩላዎች መበላት ነበር ። የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ቅን ጎዳና ለመመራት በተዘጋጀበት ጊዜ ቅን ዓላማውን ጠማማ ለሆነው የግል ፍላጎታቸው ለመሰዋት የተዘጋጁ አራዊት ተለቀቁበት።

ተዘረፈ

ተዘርፎም ተገረፈ።

ራሱ ተበደለ

ራሱ ተገደለ ሲል ህሊናን ወጥሮ በሚይዝ አገላለፅ ይገልፀዋል ።

ደራሲው ይህን መሪር እውነት በቅን ህሊናው ቃኝቶ ፣ በአስተዋይ አእምሮው አበጥሮ እና በሰላ ብእሩ ከትቦ ለንባብ ያበቃው ከዛሬ 46 ዓመታት በፊት (1966 ዓም) ማለትም በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ መሆኑን ልብ እንበል ። በሌላው በኩል ደግሞ ለሩብ ምእተ ዓመት የመጣንበትን በጎሳ/ በዘውግ ደምና አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ላይ ተመሥርቶ በመከረኛው ህዝብ ላይ የመከራ ዶፍ ሲያወርድ የኖረው ሥርዓት ውላጆችና ደቀ መዛሙርት ህወሃትን ተክተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስከተሉትንና እያስከተሉት ያሉትን ለመግለፅ የሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ቀውስ በስሜት ከመጋለብ ወጥተን ልብ እንበለው። ከ46 ዓመታትና በተለይም ከሦስት ዓሥርተ ዓመታት በኋላ የት ነን? ምን ሆንን? ብለን እራሳችንን ከምር እንጠይቀው። አዎ! ከመከራ ሥርዓት ወጥተን በነፃነት፣በፍትህ ፣በእኩልነት፣ በአብሮነትና በጋራ ብልፅግና ለመኖር ወደ እሚያስችለን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስተባብረውና መርተው ሊያሸጋግሩን የሚችሉ ስንት

የነፃነት አርበኞችን ለሸፍጠኛና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች ሰለባነት አሳልፈን ሰጠን? አሁንስ ምን እየሆንን ነው? ብለን የየእራሳችን ህሊና በጥያቄ እናስጨንቀው። መፍትሄ ሊወልድ በሚችል አኳኋን ካልተጨነቅንና በእውን ካልተቆጣን ለዘመናት ከተዘዘቅንበት የመከራና የውርደት አዙሪት ፈፅሞ መውጣት አይቻለንም።

ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ግመሉ ወደ ፊት ይገሰግሳል፥ ውሻውም ይጮሃል (the camel marches while the dog keeps barking)” በሚል ነበር ታግሎና አታግሎ እርሱ ይመራው ከነበረው በጎሳ/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ላይ የተመሠረተ የመከራና የውርደት ሥርዓት ነፃ የሚያወጣው መሪ (ሃይል) ለማውጣትና ለማጎልበት ባልተሳካለት መከረኛ ህዝብ ላይ ይሳለቅ የነበረው ። የዚያው ሥርዓት ውላጅ የሆነው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትርስ ተፎካካሪዎቼ ናችሁ” በሚል የሚሳለቅባቸውን ፖለቲከኞች ከምር ልብ ለሚል እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው አስቀያሚው የፖለቲካ ታሪክ እራሱን እየደገመ መሆኑን ለመገንዘብ ይሳነው ይሆን?

መከረኛው የአገሬ ህዝብ አለመታደል ወይም እርግማን ወይም የሃጢአት ሥርየት ሆኖበት ሳይሆን የጎሳ/የቋንቋ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴ ገዥ ቡድኖች ሥርዓትን አስወግዶ የነፃነት፣የፍትህና የጋራ ብልፅግና ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ሃይል (አካል) ለመፍጠር ባለመቻሉ ምክንያት ህወሃት መራሹ ግመል ወደ እርሱ የተጠጋውን ሁሉ እያግበሰበሰ እና መቃወም ብቻ ሳይሆን አብሬ አልግበሰብስም የሚለውን ደግሞ እየረጋገጠ ወይም እየጨፈለቀ ለሩብ ምዕተ ዓመት ዘልቋል ።

ዛሬም የትየለሌ መስዋእትነት የጠየቀውን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጥያቄ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ህወሃት/ኢህአዴግ በኦዴፓ/ብልፅግና ተክተው “ጥያቄው ተመልሷልና እየመጣችሁ ተደመሩ (ተጨመሩ)” በሚሉን እጅግ ፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ምክንያት ከመከራና ከውርደት አዙሪት መውጣት አልተቻለንም።

እኛም ለዘመናት ከዘለቀው የእራሳችን የመከራና የውርደት ህይወት ከምር ተምረን እየተመለስን ከምንዘፈቅበት አውደ ፖለቲካ ከመውጣት ይልቅ በሸፍጥና በሴራ መንበረ ሥልጣን ላይ የወጣው ፖለቲከኛ ሁሉ ለግልቡ ስሜታችን የሚመች ዲስኩር ሲደሰኩርልን “የዘማናችን ሙሴ” እያልን እና ከመጋረጃው ወይም ከአደባባይ በስተጀርባ የሚዶልተውና የሚያስዶልተው ክፉ ተግባራዊ እርምጃ ክፉኛ ሲያመን ደግሞ እያማረርንና እየተማፀን ቀጥለናል።

ከዚህ ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች እንድንለማመደው ካደረጉንና ከሰብአዊ ፍጡር በታች ከሚያውል እጅግ አስከፊ አዙሪት ለመውጣት በሚያስችል አኳኋን የየእራሳችንን ህሊና በጥሞና እና በአርበኝነት ስሜት መርምረን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ለመኖር እንደምንችል ያለኝን ተስፋ እየገለፅኩ አበቃሁ !

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share