ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል – ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

መቅድም

መሪነት ከተጠሪነትም በላይ ፊታውራሪነት ነው፡፡ በቁሙ ሲወሰድ ደግሞ በምድር እግዜርነትን ያክላል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ አገር በመሪዎቿ በኩል ትወከላለች፣ ትታፈራለች፣ ትከበራለችም፡፡

እንደሀበሻ የኑሮ ልማድ ከሆነ ብዙኃኑ ህዝብ በጨዋነትና በታማኝነት የሚያገለግሉትን ሀቀኛና ትጉሃን መሪዎች ያለመደናገር ነው የሚያዳምጠውና አርኣያነታቸውን የሚከተለው፡፡ መልካም እረኝነታቸውን ከተቀበለም ያለጥበቃ ይተዉኛል ወይም ለጠላት አሳልፈው ይሰጡኛል ብሎ ከቶውንም ስለማይጠራጠር አንዳች ስጋት አይሰማውም፡፡

የተለያዩ ማሕበረ-ሰቦችን ከማቀራረብ ይልቅ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መከለልና በብሔራዊ ማንነታቸው መደልደል በሚቀናው ሕገ-መንግሥታችን መሰረት በሀገራችን የተፈጠሩት ክልሎች ብዛት ሲዳማን ጨምሮ እነሆ አስር ደርሷል፡፡ ኦሮምያም በትልቁ የተከለለ አንደኛው የኢትዮጵያ አንኳር ክፍለ-ግዛት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ኦሮሞ ግን ከራሱ ከክልሉ በላይ ብዙ የገዘፈ፣ ኩሩና ገናና ህዝብ ነው፡፡

ዳሩ የቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛት ብቻውን ለአንድ አካባቢ ምን ያተርፍለታል?

ከዚያ ይልቅ በዚህ ወሳኝ የፈተና ወቅት የክልሉ ሰፊ ህዝብ የሚፈልገው ብልህ፣ ሚዛናዊ፣ አርቆ አስተዋይ፣ ምራቃቸውን የዋጡና በአቋማቸው የመጽናት አቅምና ልምድ ያላቸውን መሪዎች ነው፡፡

በመሰረቱ ድርብ ሥልጣን ለድርብ ኀላፊነት ያሳጭ እንደሆነ ነው እንጂ የልዩ እውቀት ማረጋገጫ ማህተም ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም ተጨማሪ ሥልጣን ተጨማሪ ግዴታን ነው የሚያስከትለው፡፡

አገር ከመምራት በፊት ራስን መግዛትና አንደበትን መግራት ያስፈልጋል፡፡ እውነቱ ይኸው ሆኖ ሳለ በዶ/ር አቢይ አህመድ አማማጪነት ተንጠላጥለው ወደመንበረ-ሥልጣን የመወጣጣት እድል ያጋጠማቸው የወቅቱ የኦሮምያ ክልል መሪ ከሀጫሉ ሁንዴሳ ድንገተኛ ህልፈተ -ህይወት በኋላ ያን ሰሞን ኦሮሞ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦ.ብ.ን) ዘንድ ቀርበው ነበር፡፡ ከተጠቀሰው ጣቢያ ጋር ያካሄዱት ቃለ-ምልልስ አድማጭ-ተመልካቾቻቸውን ግራና ቀኝ እያወናጨፈ ሲያነታርክ ሰንብቷል፡፡

ይኸው ያነሰ ይመስል ታዲያ ከስምንት ወራት በፊት በህቡእ አድርገዉታል ተብሎ እንደዘመኑ አደገኛ ቫይረስ በመሰራጨት ላይ ያለና በድምጽ የተቀረጸ ሌላ የቆየ ንግግራቸው ድንገት አደባባይ ላይ ውሎ ብዙዎቻችንን አስደንግጦናል፡፡

ፕሬዚደንቱ ጥቂት ጋሻጃግሬዎቻቸውን በዝግ አዳራሽ ሰብስበው በአፋን ኦሮሞ ያደረጉት ይህ ንግግር ወደአማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ እንደተከታተልነው ከሆነ ፍጹም አናዳጅና ለአንድም ቀን እንኳ በኀላፊነት ወንበራቸው ላይ እንዲቆዩ እድል የሚሰጣቸው አልነበረም፣ አይደለምም፡፡

ሰውየው በሞቅታ ስሜት ተነሳስተው በማን-አህሎኝነት እየተወራጩ ኦሮሚፋ እያደገ ሲሄድ የአማርኛ ቋንቋ ግን በሞት አፋፍ ላይ ነው፡፡ በማለት ራሳቸው ለራሳቸው ሲያውጁ በመገረም አዳመጥናቸው አይደል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት ዘመቻ የዜጎችን ፊርማዎች ለመሰብሰብ! - ግርማ ሞገስ

ለነገሩ ቀድሞም ቢሆን አቶ ሺመልስን ስናውቃቸው ማለፊያ አማርኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ፤ ሆኖም ሰሞንኛ መነጋገሪያ ሆኖ ከቀጠለው ዲስኩራቸው ለመገመት የሚቻለው ለተጠቀሰው ልሳንና ለፈረደበት የአማራ ህዝብ ያላቸው ጥላቻ የመረረና ወደር የማይገኝለት መሆኑን ነው፡፡

የርሳቸውን ቃል በጥሬው መቀበሉና ለዚህ የተንጋደደ አስተያየታቸው በዋቢነት የተጠቀሙበትን ጥናት ማረጋገጡ ለጊዜው ቢከብድም በአሁኑ ወቅት “እንደቤኒ-ሻንጉል-ጉምዝ  ባሉት የሀገሪቱ ክልሎች በአማርኛ ቋንቋ ኪሳራ ኦሮምኛ በመስፋፋት ላይ ሲሆን አማርኛ ግን በተቃራኒው ቁልቁል ወደእንጦርጦስ እየወረደ ነው” ሲሉ በሰፊው ተሳልቀዋል፡፡

በርግጥ እኛ እርሳቸውን አይደለንምና የኦሮምኛ ቋንቋ ከተባለውም በላይ በሀገራችን ተስፋፍቶ ብናየው ደስታውን አንችለውም፡፡ ለዚህ ግን የግድ የአማርኛን ግብአተ-መሬት መመኘት ለምን እንደሚያስፈልግ በጣሙን ግር ያሰኛል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ “እንደአፋን ኦሮሞ ሁሉ ለምሳሌ አፋርኛና ሶማልኛ ተጨማሪ የፌደራሉ መንግሥት የስራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ አጥብቀን የምንወተውተው እኛን ጨርሶ በማያገባን ጉዳይ ያን ያህል ለነርሱ አስበንና ተጨንቀን ሳይሆን ሰሜነኞቹ የአማርኛና የትግርኛ ቋንቋዎች እስከዛሬ ድረስ ያሳደሩብንን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቀነስ አቅደን ነው” ሲሉ በስም የጠቀሷቸውን ታዳጊ ክልሎች የቱን ያህል እንዳታለሏቸውና በንቀት እንደሚመለከቷቸው ለወዳጆቻቸው ያለይሉኝታ ነግረዋቸዋል፡፡

ሰውየው መቸ በዚህ ብቻ በቅቷቸው፡፡

“በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ፍርስራሽ ላይ እንደአዲስ የተገነባው የብልጽግና ፓርቲ መሪና አውራ ድርጅት በመሆኑ በርሱ አማካኝነት የሀገሪቱን ፌደራላዊ የመንግሥት ሥልጣን መዋቅር እንደተሰናባቹ የህ.ወ.ሀ.ት ቡድን በብቸኝነት ይዘን መቀጠል አለብን”፤ “ለውጡን በብቃት መርተን ለዚህ ያደረስነውና ድሉን ያመጣነው በዋነኝነት እኛ መሆናችን ከወዲሁ መታወቅ አለበት”፤ “ህ.ወ.ሀ.ት በቀደመው ዘመን ጨቁኖና ረግጦ በተላላኪነት የገዛንን ያህል እኛም በተራችን በሌሎች ላይ መሰልጠን ይኖርብናል”፤ ቀድሞውኑ  “ብልጽግናን አቅደን የጠነሰስነውና ያደራጀነው ለዚሁ አላማ እንዲያመች አድርገን ነው”፡፡፤ ባንኩም ሆነ ታንኩም ከ150 ዐመታት በኋላ የኛ የኦሮሞዎቹ ሆኗልና በዚሁ አቅጣጫ ተግተን መረባረብ ይኖርብናል”  በማለት አብዝተው ሲመጻደቁ ተደምጠዋል፡፡

ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል እንዲሉ አቶ ሺመልስ ከዚህም በላይ ሁለት ዓመታት ያህል የኋሊት ተጉዘው ዝነኛውን የኦሮ-አማራ ፕሮጀክት ሲተቹ “የአባይን ወንዝ በመሻገር ገሚሱን አሳምነውና ቀሪውን ደግሞ አደናግረው” ከባህርዳር በድል አድራጊነት እንደተመለሱ በሽሙጥ ካስታወሱን በኋላ በህ.ወ.ሀ.ት እግር ለመተካት የነበራቸውን ምኞት በቀላሉ ለማሳካት መቻላቸውን እስከማስተጋባት ደርሰዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቃለ ምልልስ.... በሊባኖስ ከ4ኛ ፎቅ ከወደቀችው ከእህት ብርቱካን ጋር

ሰውየው ከፍተኛ አጽንኦት በመስጠት ያነሱት ሌላው አቢይ ነጥብ የሀገሪቱን መዲናና የፌደራሉን መንግሥት መቀመጫ ይመለከታል፡፡ “የአዲስ አበባን ዴሞግራፊ በሕግም ሆነ በግድ እንደሚቀይሩት” ዝተው ይህኛው ፕሮጀክትም ቢሆን አስቀድሞ የተጀመረ መሆኑን ለእድምተኞቹ ሳያፍሩ ገልጸዉላቸዋል፡፡

እንደእውነቱ ከሆነ ፕሬዚደንት ሽመልስ ለእንዲህ ያለው መረን የለቀቀ ዲስኩር ያን ያህል እንግዳ እንዳልሆኑ ይህ ጸሃፊ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የአሁኑን ንግግራቸውን ምናልባት ልዩ የሚያስመስለው ከመጋረጃ በስተጀርባ የተደረገና በምስጢር ሾልኮ ከወጣ በኋላም ወደባላንጣዎቻቸው እጅ ሳያስቡት ተሸጋግሮ ለህዝብ በመሰራጨት ላይ ያለ መሆኑ ብቻ ነው፡፡

አፈሩ ይቅለላቸውና የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚደንት መሀመድ ሙርሲ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውንና ከፍተኛ የጦር መኮንኖቻቸውን ይዘው በመገንባት ላይ ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከካይሮ ሰማይ ተወርውረው በቦንብ ሊያጋዩት እንደሚችሉ በዛቱበት መድረክ ከፈቃዳቸው ውጭ ለመላው አለም በድብቅ ቴሌቫይዝ እንደተደረገው ስብሰባ መሆኑም አይደል?

በርግጥ በወጣት የእድሜ ክልል የሚገኙ የሚመስሉት ኦቦ ሺመልስ ያልበሰሉ ካድሬ እንጂ ብቁ ፖለቲከኛ ናቸው ለማለት ፈጽሞ አያስደፍርም፡፡ ከየወቅቱ ሁኔታዎች ጋር ለመለዋወጥ በሚቀናውና ያን ያህል እምነት በማይጣልበት አቋማቸው ሳቢያ ሀገራቸውን ይቅርና ራሳቸውን እንኳ በቅጡ መምራት እንደሚሳናቸው በበርካታ አጋጣሚዎች ተስተውሏል፡፡

ስለሆነም በውል ያልተገራው አንደበታቸው በየደረሰበት ከሚረጨው መርዝ እንዲታቀብ ጠበቅ ያለ ልጓም ሊበጅለት ይገባል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግሥትም ቢሆን የምልአተ-ህዝቡን ድጋፍና ቅቡልነት ጨርሶ ከማጣት ብልህነት የማይታይባቸውን አንድ ደመ-ሞቃት የፖለቲካ ብላቴና መገሰጽ፣ ብሎም በልበ-ሙሉነት መቅጣቱ ይሻለዋል፡፡

ይህንን ጸሀፊ አብዝቶ የሚያስገርመው አቶ ሽመልስ ራሳቸውም ሆኑ የብልጽግና ፓርቲ በሰውየው ላይ ለተሰነዘረው ለዚህ ብርቱ ወቀሳ እስከዛሬ ድረስ ይህ ነው የሚባል ይፋዊ ምላሽ ወይም ማስተባበያ ሊሰጡ እንኳ አለመሞከራቸው ነው፡፡ ይልቁንም በህቡእ ተደረገ የተባለውን የዚያን ዲስኩራቸውን መጋለጥና ወደአደባባይ መውጣት ተከትሎ አንዳንድ ወገኖች ይህ የፕሬዚደንቱ ያፈነገጠ አቋም የግላቸው እንጂ የፓርቲያቸው እንዳልሆነ እየተሽኮረመሙም ቢሆን ሽንጣቸውን ገትረው በአደባባይ ሲሟገቱላቸውና ገሃድ የወጣውን እውነት ሊሸፋፍኑላቸው ሲጣጣሩ ታዝበናል፡፡ ሆኖም እነዚህ ወገኖች ይህንኑ ጥብቅናቸውን በውል የሚደግፍ አንዳች የረባ አመክንዮ አያቀርቡልንም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዘረኝነትን የማውደሚያ ጊዜ አሁን ና ዛሬ ነው - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

እኔ በበኩሌ ሰውየው ካልታሰበ የምላስ እንሽርት የተነሳ ስላመለጣቸው ድንገት አፈትልኮ የወጣ ሳይሆን በጥብቅ የሚያምኑበትንና ጓዶቻቸው ጭምር የሚጋሩትን ተምኔት በሀኬት እንዳስተጋቡ ነው የሚሰማኝ፡፡ ከዚያ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የኢሬቻን በአል አዲስ አበባ ላይ እንዲያከብር የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን ጨምሮ በበርካታ ተሽከርካሪዎች እየተጫነ ከአራቱም የመዲናዋ መአዘናት በካድሬዎች ቅስቀሳ ተጓጉዞ በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰበው ብዝሀ-ኦሮሞ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም ባሰሙት ታሪካዊ ዲስኩር የነፍጠኛውን ስርአት አንኮታኩተነዋልና አቦ ይመቸን ሲሉ አያሌዎችን በመሬት አንቀጥቅጥ ጭብጨባ ያስፈነደቁበትና ጮቤ ያስረገጡበት ድንፋታ ጨርሶ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ያ የተወላገደና የተረኝነት ደዌ የተጠናወተው አቀራረባቸው በጊዜው ራሱን የኦሮሞን ማሕበረ-ሰብ ጨምሮ ብዙኃኑን ዜጎች ክፉኛ እንዳበሳጨና ልባቸውን እንዳደማ በምሬት የምናስታውሰው ጉዳይ ነው፡፡ በወቅቱ ሳይታረም በመታለፉም እነሆ ሰውየውን ለዳግመኛ ስህተት ዳርጓቸዋል፡፡

በመሰረቱ የዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ቀኖና እንደኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ሁሉ ብልጽግና ፓርቲም ቢሆን በጥብቅ የሚከተለው ሀይማኖት እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ የቱንም ያህል የግል ነጻነት ቢኖራቸው ፕሬዚደንቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ፓርቲያቸው በይፋ ከሚያራምደው የተለየ አቋም ይኖራቸዋል ተብሎ በጭራሽ አይታመንም፡፡

እንግዲሕ እስካሁን እንደሚስተዋለው ሕግ ፊት መቅረብና መጠየቃቸው ይቅርና በህቡእ የተሳለቁበትን ህዝብ ይቅርታ ለመጠየቅ እንኳ ግድ ሳይሰጣቸው ሰውየው በዋዘኝነት የሚታለፉና በያዙት ቁልፍ ኀላፊነት እንደተደላደሉ ይቀጥሉ ዘንድ የሚፈቀድላቸው ከሆነ በቀላሉ ከሚታረሙ ይልቅ በስህተቱ እንደሚገፉበት ጥርጥር የለውም፡፡ አሉታዊ ምሳሌነታቸውም ቢሆን ወደሌሎች አጋሮቻቸው በቀላሉ ሊጋባ እንደሚችል እየታዘብን ነው፡፡

የርሳቸውን ዲስኩር ወደአደባባይ መውጣት ተከትለው የኦሮምያ ክልልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች በሕግ ከተሰጣቸው ማንዴት ውጭ በፌደራሉ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 90 ንኡስ አንቀጽ (2) ስር የሰፈረውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ የገዳ ስርአትን በመደበኛው ትምህርት  ውስጥ አካቶ ለማስተማር መነሳሳታቸውንና የፕሬዚደንቱን ተምኔት ወደመሬት ለማውረድ ይፋዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር እስከማወጅ መድረሳቸውን እዚህ ላይ ማንሳቱ ትዝብታችንን ሊያጠናክረው ይችላል፡፡

እነዚህ የመንግሥት አካላት በጠራራ ጸሀይ የሚጥሱትና ከፍ ብሎ የተጠቀሰው የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ እንዲሕ ይነበባል፡-

 

ትምህርት፣ (መደበኛ ትምህርትን መሆኑ ነው)፣ ከሀይማኖታዊ ቅኝት፣ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነትም ሆነ ከባህላዊ ተጽእኖ ነጻ በሆነ መንገድ መሰጠት ይኖርበታል፡፡

አበቃሁ፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.