ትሕነግ እና ጦር አውርድ ጉዞው (በሙሉአለም ገ.መድህን)

“ትግራይ እንደ ክልል ሳይሆን፣ እንደ ሃገር የኔ የምትለው ጠንካራ ሠራዊት እንዲኖራት፣ …ዓለምን እሚያስደምምና እሚያስደነግጥ ሰራዊት እንዲኖራት ነው እየሰራን ያለነው ”

ይህን የተናገረው ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ ነው። የሰውየውን ሚና ከትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ “ኢታማዡር” በለው።

ትህነግ ከነፃ አውጭነት ባህሪው ሳይወጣ ሃያ ሰባት ዓመታትን በቤተመንግሥት ቆይቷል። “አጋር” ብሎ ያቀረባቸው ሁሉ በገቢር ‘ገባር’ ከማድረግ ባሻገር ስለፍትሃዊ ተጠቃሚነት አሳስቦት አያውቅም። ከዐድዋ ፊውዳል የሚመነጨው የጠባብ ቡድንተኝነት መቆሚያ የሌለው የፖለቲካ ፍላጎቱ፣ በፌዴራሊዝም ስም ሲነገድበት ኑሯል።

ዛሬ 1983 አይደለምና የትላንት ብልጠቱንና ሃሳዊነቱን የተረዱ “አጋሮች” ሰልፋችን አንተ ዘንድ አይደለም ብለውታል። ቀዳሚነትን እና የበላይነት መለያው ያደረገው ይሄ ኀይል በአዲስ ጦረኝነት ቢቻለው ወደመሀል ፖለቲካው መመለስ ካልሆነለት ደግሞ አገሪቱን አፍርሶ በደካሞች የተከበበች ጠንካራ ትግራይን የመፍጠር ፍላጎት አለው።

በወታደራዊ ዝግጅቱ ሙሉ ጦርነት ለማካሄድ በሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል። በሁሉም ዞኖች ስር ባሉ ወረዳዎች የሚሊሻ ስልጠናዎች ከስምንት ዙር በላይ ተሰጥተዋል። ‘ፀለምት’ ፣ ‘አግበ’ እና ‘አዲ ጎሹ’ የኮማንዶ ስልጠናዎችን ጨምሮ የልዩ ኀይል ማሰልጠኛ ካምፖች አሉ። ዛሬ የትሕነግ ጦር በኮማንዶ ደረጃ የተዋቀረ ሆኗል። ሁለተናዊ ቁመናው የልዖላዊት ሀገር እንዲሆን እየተሰራበት ስለመሆኑ ሌ/ጄኔራል ታደሠ ወረደ በአደባባይ ነግሮናል።

አፈር ገፊው የትግራይ አርሶ አደር ምንም በማያውቀው ሁኔታ ‘ጠላት ከሸዋ ሊመጣብህ ነው፣ አማራ ሊወጋህ እየመጣ ነው፣ ሻቢያ ተነሳብህ’ በሚል trauma ውስጥ ከቶታል።

የልዩ ኀይል አደረጃጀቱ በይዘት ደረጃ በክፍለ ጦርና በሬጅመንት ደረጃ የተደራጀ ነው። የሻለቃና የሻምበል አመራሮች ቢኖሩትም በጋንታ ደረጃ ያለው ትጥቅ ሲገለፅ :-

አንድ ጋንታ አስራ ስድስት የሚደርሱ አባላት ሲኖሩት፣ አስሩ ክላሽ፣ አራቱ የእጅ መትረየስ፣ ሁለቱ ስናይፐር እንዲታጠቁ ተደርጓል። ይሄ የታችኛው አደረጃጀት ሲሆን፤ ከጋንታ እስከ ሬጅመንትና ክፍለ ጦር እያደገ የሚሄድ አደረጃጀት አለው። የጸጥታ ኀይል ስምሪቱ የተደራጀና ማዕከላዊ [command and control ] ያለው አደረጃጀት ነው። ከመከላከያም ሆነ ከፌዴራል ፖሊስ አኩርፈውም ይሁን በጡረታ የወጡ (የትህነግ) መኮንኖችን በጦር አውርድ ዝግጅት ተጠምደዋል።

ዋና አዛዦቹ ጌታቸው አሰፋ እና ሌተናል ጀኔራል ታደሠ ወረደ ናቸው። ታዴ ነብሴ ከባህር ዳር ሳይቀር መረጃ ያገኛል፣ ፖሊስ ኮሚሽኑ ውስጥ ጥሩ ወዳጅ እንዳለው ነው የሰማነው።

****
ያ ሟች ሰውየ (ጀኔራል አብርሃ ወ/ማርያም) በከባድ ህመም እየተሰቃየ “ከመሞቴ በፊት የአማራን ትምክህት ካልሰበርኩ” ሲል እንደነበር በጠገዴ በኩል ኮብልሎ የመጣ አንድ የሻለቃ አመራር ቃሉን ሲሰጥ፣ መናገሩን ከአንድ መርማሪ ሰምተናል። በነገራችን ላይ ወደ አማራ “ክልል” ኮብልለው ከሚመጡት የትሕነግ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት (በተለይ በአመራር ደረጃ ያሉትን)።

ሱዳን ውስጥ ‘አላምያ’ የተባለ ቦታ ላይ ሲሰጥ ስለከረመው ወታደራዊ ስልጠና ቢጠየቁ ብዙ የሚናገሩት ጉድ አለ። የደምሒት ወጣቶች ከጽንፈኛው የቅማንት ኮሚቴ ጋር ሆኖ ጎንደርን እንዲያነድ የከተማ ሽምቅ ውጊያ ስልጠና በሁለት ዙር ስለ መሰጠቱ መረጃዎች አሉ። እያገባደድነው ባለው በዚህ ዓመት ብቻ ከመስከረም 16- ጥር 05 ድረስ አምስት የመደበኛ ውጊያ ይዘት ያላቸው ግጭቶች (ጭልጋ፣ አይምባ_ጓንግ፣ አዘዞ፣ ደፈጫ ኪዳነ ምህረት፣ ቁስቋም) በግንድ መጣያ እና በመተማ መስመር ከአስር ጊዜ በላይ የደፈጣ ጥቃቶች፣ ከሃያ ስድስት በላይ እገታዎች (የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች፣ የመንገደኛና የታዳጊ ህፃናት እገታዎች) ሲፈፀሙ ዋና ግቡ አካባቢው ላይ Social unrest በመፍጠር ሕዝቡ መንግሥት ላይ እንዲያምጽ፣ የክልሉ መንግሥትም በተደጋጋሚ ትንኮሳ ተበሳጭቶ ያልሆነ እርምጃ እንዲወስድ ነበር።

ያም ሆኖ ጥይት ሲዘንብበት የከረመው ሕዝባችን (በተለይም የከተማ አደረጃጀት የፈጠረው ወጣቱ) ራሱን ተከላከሎ፣ ልዩ ዒላማ የነበረችውን መናገሻ ጎንደርን ከጥቃት አዳነ እንጅ የሚመራውን መንግሥት ሊወጋ አልተነሳም። በመቶዎች የሚቆጠሩ የአላምያ ሰልጣኝ የሆኑ ሰርጎ ገቦች በየ ቁጥቋጦው ወድቀው ቀርተዋል። በተለይም ከመስከረሙ በአይከል ከተማ የልዩ ኃይላችን ካምፕ ውስጥ ከተፈፀመው የከተማ ሽምቅ ውጊያ (ማርጌላይዝም) በኋላ፣ የተወሰዱት የአፀፋ እርምጃዎች የትሕነግን የተራዛሚ ግጭት ምኞት ያከሸፉ ቆራጥ እርምጃዎች ነበሩ። በዚህ ረገድ ከሰቀልት ይዞ ወዲህ በአይምባ እስከ ጓንግ ድረስ በነበረው ኦፕሬሽን የደምቢያ ፋኖ ልዩ ክብር ይገባዋል። በእነርሱ መስዋዕትነት የአማራ የማሸነፍ ስነ-ልቦና ቀጥሏል፣ እንጅማ በትሕነግ በኩል የተደገሰልን የሞት ድግስ ብዙ ነበር።

ወደ ትሕነግ ወታደራዊ አደረጃጀት ጉዳዮች ስንመለስ
*****
በወልቃይት እና በሁመራ [ምዕራባዊ ዞን ይሉታል] በኩል ያለውን ቀጣና (ግንባር) መቀመጫውን ሽሬ አድርጎ ብርጋዴየር ጀኔራል ምግብ ኃይሌ ይመራዋል።

በአላማጣ እና ራያ በኩል [ደቡባዊ ዞን] ያለውን ቀጣና ብርጋዲየር ጀኔራል ኃይለሥላሴ ይመራዋል። ከማይጨው የሚነሳ ቢሆንም የአካባቢው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኃይለሥላሴ ዕዝ ስር ነው።

የኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ያለው አሰላለፍም መሰል አደረጃጀት አለው። በተለይ በተከዜ በኩል እና ከሱዳን ሐምዳይት ጫፍ አንስቶ ያለው መስመር threat zone ተብሎ ተለይቷል።

ትህነግ ከጊዜ ጋር ትንቅንቅ ውስጥ የገባ ቡድን በመሆኑ፣ ከፖለቲካ እንቅስቃሴው ጎን ለጎን ወታደራዊ አማራጭ ሌላኛው የሙከራ በሩ ነው። ጦረኛ የአፈጣጠር ባህሪው ከብዕር ይልቅ ለብረት እንዲታመን አድርጎታል። ዝግጅቱ የሙሉ ጦርነት ቢሆንም ራሱ ደፍሮ አይጀመረውም። ሊመጡ ይችላሉ የሚላቸውን ስጋቶች በመለየት ቀድሞ ማምከን ቀዳሚ ግቡ ነው።

በመሠረታዊነት ሦስት ጠላት ለይቷል። የፌዴራሉ መንግሥት፣ የአማራ መንግሥትና የኤርትራን መንግሥት። ሦስቱም ኀይል ባሉበት ተዳክመው እንዲወድቁ ማድረግ ቀዳሚና ተመራጭ ፖለቲካዊ ግቡ ነው። ለዚህ ደግሞ የውጭ ግንኙነቶችን ማበላሸት ጨምሮ በአገር ውስጥ Deep state, Insurgency, Proxy war, Economic sabotage, etc ግራንድ ስትራቴጂዎችን በመለየት ዓመቱን ሙሉ በአውዳሚ ተልዕኮ ላይ ተጠምዶ ከርሟል። የዚህ ተልዕኮ ዋነኛ ዓላማ በተቻለ መጠን ጦርነቱ ወደ እርሱ እንዳይመጣ ሦስቱ ወደረኞቹ ባሉበት ተዳክመው እንዲወድቁ ማድረግ ነው።

በዚህ ሁሉ ሂደት በአንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ይቻላል።

ትህነግ የውክልና እንጅ የግንባር ጦርነት አይገጥምም። የጦርነትን ዋጋ ያውቀዋል። በዚህ ሰዓት ጦርነት ውስጥ መግባት ትግራይን ወደ ቅድመ 1983 ድኀነቷ መመለስ እንደሆነ ከሱ በላይ ማንም አያውቅም። ጦርነት መሸከም የሚችል የምርትም ሆነ የምጣኔ ሃብት አቅም የለም። በቀጣይ ኢፈርትን ታርጌት ያደረገ የኢኮኖሚ ጦርነት እንደሚጠብቀው ያውቃል።

ይህ በገዛ ፍላጎቱ ላይ ማመፅ ያልቻለ፣ የቁስ ሰቀቀን ውስጥ የወደቀ ቡድን የአፍሪቃ ቀንድ የሠላምና ደኀንነት ስጋት ነው። የፊታችን ዕረቡ የሚያካሂደው ሕገወጡ ምርጫም በቀጣናው ‘ሽብር መር ንዑስ መንግሥት’ ሆኖ እንዲቀጥል የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል። ‘ተመርጫለሁ፣ ሕጋዊ ነኝ’ በሚል የፕሮፖጋንዳ ጋጋት ጦር አውርድ ሆኖ መቀጠል ይፈልጋል። ከአዳራሽ የወጣው የዚህ ቡድን ፖለቲካ ወደ አዳራሽ የመመለስ ዕድል የለውም። ጊዜው ረፍዷል። ለዚህም ነው በአደባባይ ጦር አውርድ ባህሪ ሲያሳየን የሚውለው።

በርግጥ፣ ‘የግንባር ጦር ፈሪ፤ የውክልና ጦር ፈጣሪ’ ስለመሆኑ ዐቢይ አህመድም፣ ኢሳያስም ሆነ ተመስገን ጥሩነህም በሚገባ ያውቃሉ። ጨንቆት ያለውም ይሄው ነው።

2013 ማን እንደሚሻገራት አብረን እናያለን!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.