ውረዱ ደፍራችሁ (ዘ-ጌርሣም)

የዘር ፖለቲካ እያራመዳችሁ
ተንኮልና ሴራን እያላመጣችሁ
በተቃዋሚ ስም የተሰለፋችሁ
የወገንን ጆሮ ያደነቆራችሁ
የህዝብ ብሩህ ተስፋ ያደበዘዛችሁ
በአንድነት መቆሙ ያስበረገጋችሁ
ከሥልጣን በስተቀር ሌላ ያልታያችሁ
እስከ መቸ ድረስ አለን ትላላችሁ
ወጣቱን ተኩና ውረዱ ደፍራችሁ
ህዝቡንም አክብሩ እንዳከበራችሁ

ነገር ከሚበላሽ ከዚያው ተጣብቃችሁ
ጉልበታችሁ ደክሞ እናንተ አርጅታችሁ
እስከ መቸ ድረስ አለን ትላላችሁ
ወጣቱን ተኩና ውረዱ ደፍራችሁ
ህዝቡንም አክብሩ እንዳከበራችሁ

ምን አረገ ህዝቡ በፍቅር የኖረው
ተዋልዶ ተካብዶ ለፍሬ የበቃው
ደስታና መከራን አብሮ ያሳለፈው
እንደ ዱር እንስሣት ከምታጫርሱት
ምናለ ቢበቃ እናንተ ብተውት ???
እስከ መቸ ድረስ አለን ትላላችሁ
ወጣቱን ተኩና ውረዱ ደፍራችሁ
ህዝቡንም አክብሩ እንዳከበራችሁ

በቃ ተውን ብሎ እየለመናችሁ
አትለያዩን ብሎ እየነገራችሁ
በማያውቀው ሴራ ደም ታቃባላችሁ
ከትናንቱ ስህተት ምን ተፀፀታችሁ ?
እስከ መቸ ድረስ አለን ትላላችሁ
ወጣቱን ተኩና ውረዱ ደፍራችሁ
ህዝቡንም አክብሩ እንዳከበራችሁ

ኢትዮጵያስ ብትሆን ምን በደለቻችሁ
የምታሟርቱት ትበተን ብላችሁ
ሥልጣኑን ለናንተ ማነው የሰጣችሁ ?
ፈላጭና ቆራጭ አርጎ የሾማችሁ ?
እስከ መቸ ድረስ አለን ትላላችሁ
ወጣቱን ተኩና ውረዱ ደፍራችሁ
ህዝቡንም አክብሩ እንዳከበራችሁ

በየትኛው ቋንቋ
በየትኛው ባህል
በየትኛው ዕምነት
በየትኛው ዳኛ
በማን መስካሪነት
በማን ፈራጅነት
በማን ጠበቃነት
በነማን ህግጋት
በየትኛው አንቀፅ
ይታይ ጉዳያችሁ
እስከ መቸ ድረስ አለን ትላላችሁ
ወጣቱን ተኩና ውረዱ ደፍራችሁ
ህዝቡንም አክብሩ እንዳከበራችሁ

ሂዱ ጥፉ እንዳልል ወገኖቸ ናችሁ
ዝም እንዳትባሉ ታሳፍራላችሁ
ላም አለኝ በሰማይ ዘለዓለም ሁናችሁ
እስከ መቸ ድረስ አለን ትላላችሁ
ወጣቱን ተኩና ውረዱ ደፍራችሁ
ህዝቡንም አክብሩ እንዳከበራችሁ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሆድ ስንቱን አስከዳህ! - በላይነህ አባተ

ሥልጣን በማምታታት የሚገኝ መስሏችሁ
ጠብታ እንኳን ሳይኖር ዐርባ ዓመት ሞላችሁ
ከዕንግልት በስተቀር ምን አተረፋችሁ ?
አሁንስ ምንድነው ቀጣይ ዕቅዳችሁ
እስኪ ተናገሩ ዛሬስ ምን አላችሁ ?
እስከ መቸ ድረስ አለን ትላላችሁ
ወጣቱን ተኩና ውረዱ ደፍራችሁ
ህዝቡንም አክብሩ እንዳከበራችሁ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share