በገ/ክርስቶስ ዓባይ
ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ/ም
ፖለቲካ ማለት የሕዝብ አስተዳደር ማለት ነው። እንግዲህ ‘ሕዝብን ማስተዳደር የሚገባን እኛ ነን’ ብለው የተለያዩ አማላይ አስተሳሰቦችን በመያዝ ሰውን የሚሰብኩ ደግሞ ፖለቲከኞች ሲሆኑ፤ እንደዚህ ያሉትን ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸውን ‘ፖለቲከኞች ነን’ ባዮችን በማሰባሰብ በፓርቲ አደራጅቶ የሚመራው ሰው ደግሞ ፖለቲከኛ ይባላል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ጄኦግራፊ ያጠና (የሚያጠና) ሰው በመንግሥታት አንድም ከፍተኛ ሥልጣን ይሰጠዋል፤ አልያም መንግሥትን ይቀናቀናል በሚል እጅግ የሚፈራና ዓይን የሚጣልበት ሰው ነበር። ምክንያቱም የጂኦግራፊ ምሁር የሆነ አንድ ሰው ስለአንድ አገር ጉዳይ አብጠርጥሮ ያውቃልና። የአገሪቱን ቅድመ ታሪክ፤ የድንበር ሁኔታ፤ የሕዝቦችን የቋንቋ፤ አሰፋፈር፤ ባህልና የኑሮ ሁኔታ፤ የአገሪቱን መልክአ ምድርና ካርታ፤ ከአጎራባች አገሮች ጋር ያላትን የድንበርና የወሰን ግንኙነት፤ የከባቢ አየር ጠባይ ሁኔታ፤ አገሪቱ ያላትን የከርሰ ምድር ሀብት፤የመንግሥቱን የአስተዳደር ዘይቤ እና ኢኮኖሚው የተመሠረተበትን ሁኔታ እንዲሁም ከውጭ አገር ጋር ያላትን ስትራተጂካዊ ጠላትነትና ወዳጅነት አስመልክቶ ሠፊ ዕውቀት አለው።
በአሁኑ ወቅት ይህ ውቅያኖስን የሚመስለው የዕውቀት ዲሲፕሊን፤ ቀስ በቀስ በየጊዜው በርካታ ዘርፎች ወጥተውለት፤ ምሁራን በጥልቀት እያጠኑት እስከ ዶክትሬት በሚደርስ ደረጃ ተመርቀውበታል። ፖለቲካል ሣይንስ፤ጄኦሎጂ፤ ኢኮኖሚክስ፤ ሶሲዮሎጂ፤ ሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት (ኮሙኒቲ ዲቨሎፕመንት)፤ የሕዝብ አሠፋፈርና ቆጣራ (ዴሞግራፊ) የአካባቢ ደንና አራዊት ጥበቃ፤እና ሌሎችም ይገኙበታል። ከዚህ ዓነስተኛ ገለጻ ተነስተን ስንመለከተው የጂኦግራፊ ዕውቀት ምን ያህል የሰፋና የጠለቀ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
ታዲያ እንዲህ ያለውን የአገር መሠረታዊ ዋልታና ምሰሶ፤ በፖለቲካ ብቻ በመወሰን የሥልጣን ከርቻ ላይ ለመውጣት ሲባል የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ዙፋኑ ላይ ለመቀመጥ የሚያስችል አቋራጭ መንገድ መጠቀም፤ የፖለቲከኞች ሚና ሆኖ ይታያል። አንዳንዶቹ በተፈጥሮ ያገኙትን የመናገር ችሎታና አንደበተ ርዕቱነት ሕዝብን በማማለል፤ የሕልም እንጀራ እያሳዩ አእምሮውን ይሰልቡታል። ይህንኑም እውነት እንደሆነ አድርገው ለሕዝብ የሚያረጋግጡ አስመሳይ ካድሬዎች አሉ። ካድሬዎች የአንድን መሪ ሐሳብ እንደ በቀቀን እያስተጋቡ ሕዝብን በመስበክ ሥልጣን የሚያደላድሉና ከሚገኘው ጥቅም እኛም እንቋደሳለን በማለት ሌት ተቀን የሚጥሩ ናቸው። ሁኔታዎች ፈቅደውና ተሳክቶላቸው መሪያቸው ሥልጣኑን በእጁ ባስገባ ጊዜ ደግሞ ተገልብጠው ተቃዋሚም ይሁን ደጋፊውን ሕዝብን ሳይቀር እያሳደዱ የሚያንገላቱ፤ የሚአስሩና የሚገድሉ ርህራሄ የሌላቸው ጨካኞች ናቸው።
ፖለቲከኞች ሥልጣን ፈላጊዎች በመሆናቸው፤ አገሪቱ በአላት የቴክኖሎጂ ዕድገትና የኢኮኖሚ አቅም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሆን የማይቻለውን ሁሉ እናደርጋለን በማለት ምለው ተገዝተው ቃል ይገባሉ። ልክ አንድ ወያላ ተሣፋሪን ለምኖና አግባብቶ ከአሳፈረ በኋላ መጨረሻ ላይ ተሳፋሪውን አንድም ሳይደርስ ወይም ደግሞ ከመውረጃው አሳልፎ ገፍትሮ እንደ እሚያወርደው ሁሉ፤ ፖለቲኞችም እንዲሁ በጥሩ ሥነ ምግባርና መለማመጥ ‘እኛን ምረጡ!” በማለት ሲለምኑና ሲወተውቱ ይቆዩና የመሪነቱን ቦታ ሲቀዳጁ ግን ‘ሁልህም አርፈህ ቁጭ በል!’ በማለት የሕዝብን አጀንዳ ወደጎን በመተው የራሳቸውንና የተከታዮቻቸውን ፍላጎት ብቻ በማሟላት የሥልጣን ጊዜያቸውን በኃይልና በአፈና ለማስረዘም ይጥራሉ።
በተለይ በታዳጊ አገሮች የሚታየው የፖለቲከኞች ልምድ ተመሳሳይ ነው። አንዴ ሥልጣን ከእጃቸው ከገባ በምንም ተዓምር ከእነርሱ እንዳይወጣ የተቻላቸውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይድረሰውና የዓለም አገሮችን አስተዳደርና የሰብአዊ መብት ጥበቃ የሚከታተሉ ከ25 የማያንሱ የሲቪክ ድርጅቶች እንደሚገኙ ሲታወቅ፤ በሁሉም የሰብአዊ መብቶች ዘርፍ አገሮችን በማወዳደር የሚገመግሙና ደረጃም የሚያወጡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሲቢክ ማኅበራት ተቋቁመው ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ በጠንካራቱና በዓለም ያለው ተቀባይነት ጎልቶ የሚታየው አምነስቲ ኢንተርናሽናል አንዱ ነው። የአውሮፓ ኅብረትም የታዳጊ አገሮች፤ ለሰብአዊ መብትና ለዲሞክራሲ ዕድገት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ በተለይ ለፖለቲካዊ ምርጫ የሚያስፈልገውን የኅትመት፤ የሰው ኃይል ሥልጠና እና የሎጅስቲክ ወጭዎችን ከመሸፈን ጀምሮ ምርጫው ፍትሐዊና ያልተጭበረበረ መሆኑን ወኪሎቻቸውን በመላክ ይታዘባሉ።
ነገር ግን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በፈቃደኝነት ለመልቀቅ ከሚያደርጋቸው ቁርጠኝነት ይልቅ የምርጫው ሁኔታ ለይስሙላ እንዲደረግና በተቻለ ዘዴ አንድም የገዥው ፓርቲ ታማኞችን፤ በየምርጫ ጣቢያው በመመደብ ቆጠራውን ለእነርሱ በሚጠቅም መልኩ በማስተካከል፤ ወይም በምስጢር የምርጫ ሣጥን የመገልበጥ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ጊዜያቸውን ማራዘም ይመርጣሉ።
እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ የሚከሰተው ከመሪው ብቻ ሳይሆን ከበታች ሹማምንትም ጭምር ነው። ምክንያቱም እያገኙ ያሉት ጥቅምና የቅምጥል ኑሮ እንዳይጓደልባቸው የሆነ ምስጢራዊ ዘዴ ተጠቅመው በያዙት ሥልጣን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ስለሚፈልጉ መሪያቸውንም በተንኰሉ እንዲገፋበት ከፍተኛ ማደፋፈር ያደርጋሉ። እንዲህ በሚደረግበት ወቅት ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲ ዓባላትም ሆነ አንዳንድ በራስ መተማመን ያላቸውና ለኅሊናቸው ያደሩ የውስጥ ዓባላትም ‘የሕዝብ የምርጫ ድምፀ ውሳኔ መከበር አለበት!’ የሚል አቋም በመያዝ በተፃራሪነት የሚቆሙ ከሆነ በስውር እንዲወገዱ ይደረጋል። እንዲህ ዓይነቱን የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ደግሞ የሠራ ባለሥልጣን በሌላ ኃይል የሚተካ ከሆነ እስር ቤት እንደሚገባ ስለሚያውቅ ወደደም ጠላም ያለው አማራጭና ለኅልውናው ዋስትና የሚሆነው፤ በሥልጣን ላይ መቆየቱ ስለሆነ በሕዝብ ተመረጠም አልተመረጠ ወንበሩን መልቀቅ አይፈልግም።
እንግዲህ አንድን ወንጀል ለመደበቅ ሌላ ወንጀል ይሠራል፤ ያንንም ለመደበቅ ወይም ለማፈን ሌላ ተጨማሪ እያለ፤ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ሊቋቋሙት ወደማይቻላቸው ከፍተኛ የሰላምና የደኅንነት ሥጋት ላይ ይወድቃሉ። በዚህ ጭንቀት ወቅት ሥራ ይበደላል፤ የአገሪቱ ዕደገት ይጓተታል፤ታላቅ የኢኮኖሚ ኪሣራም ይደርሳል። ሁሉም ነገር ማለት የመንግሥት መዋቅሮች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎትና ቁጥጥር ማድረግ ስለማይችሉ በአብዛኛው የንግዱ አንቅስቃሴ አዝጋሚ በመሆን መሽመድመድ ይጀምራል። እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በመጠቀም የውጭ ኃይላትና አንዳንድ ታላላቅ ኩባንያዎችም ከመጠን ያለፈ ትርፍ ለማግበስበስ መሞከራቸው አይቀሬ ነው። በመካከሉ የሚጎዳው የእለት ተዕለት ጉርሱን ለማግኘት ላይ ታች የሚለው ድሀው የኅብረተሰብ ክፍልና፤መካከለኛ ገቢ ያለው የመንግሥት ሠራተኛ፤ በዋጋ ንረት ምክንያት ያልተጠበቀ የኑሮ ጫና ይወድቅበታል።
እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት አንድ ዓቢይ ጉዳይ ስላለ ይህንን ማስገንዘቡ ጠቃሚ እንደሚሆን ይገመታል። በሥልጣን ላይ የሚገኙት የወቅቱ ጠ/ሚንስትር ‘በምርጫ ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ ነገር ግን በሌላ መንገድ ከሆነ በግልጽ ጦርነት እንገባለን’ በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገሩ ስምተናል። በዲሞክራሲያዊ አሠራር ወደዱም ጠሉም በምርጫ ከተሸነፉ መልቀቅ እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ነገር ግን ይህ አባባል አንድ ነገር ያስታውሰናል።
‘አንድ አንበሳ ዛፍ ላይ ያለችን አንዲት ጦጣ ሽቅብ አንጋጦ እየተመለከተ ‘ነይ ውረጅና እንጫወት አልበላሽም’ ቢላት ‘ነገሩ ጥሩ ነበር ነገር ግን አልበላሽምን ምን አመጣው?’ አለችው ይባላል። ከዚህ የምንረዳው ታላቅ ፍሬ ነገር አለ። ይኸውም ጠ/ሚንስትራችን ምርጫ ተደረገም አልተደረገ ሥልጣናቸውን እንደማይለቁ ግልጽ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ሌላው ቢቀር እንኳ እጃቸው በደም ተጨማልቋልና በሕግ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ በምርጫ ለመልቀቅ ወኔው ሊኖራቸው አይችልም።
እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ጊዜ የማይሰጥ ስለሆነ ሕዝቡ አፍ አውጥቶ ባይናገርም ልብ ለልብ ግን አስተሳሰቡ ተመሳሳይነት ይኖረዋል። በተለይ ዘመን ያመጣውን የሶሺያል ሜዲያ በመጠቀም በስፋት መወያየቱን ይጀምራል። ይህንን አስመልክቶ ቱኒሲያዊው ዜጋ ሞሐመድ ቡአዚዚ በመንግሥት ወታደሮች በተደጋጋሚ የደረሰበትን የሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት በማድረግ እ.ኤ.አ. ታህሣሥ 10 ቀን 2010 ዓ/ም በራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ በእሳት በማቃጠሉ፤ የዓረቦችን መነቃቃት (Arab Spring) ማስከትሉና የብዙ ዓረብ መንግሥታትን በሕዝብ አመጽ እንደለወጠ የምናስታውሰው ነው። ይህ ጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ሰደድ እሳት የተዛመተው በሶሺያል ሜዲያ አማካይነት እንደነበር ማስተዋል ተገቢ ይሆናል።
በዚያን ወቅት በጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ የሚመራው የኢሕአዴግ መንግሥትም ከፍተኛ ውጥረት ላይ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም ሁኔታውን ለማስቀየር ሲባል በአራት ወራት ልዩነት በድንገት እ.ኤ.አ በሚያዝያ 2011 ዓ/ም የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ እንዲቀመጥ ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሶሺያል ሜዲያን እንዳይጠቀም ለመግታት ሲባል የቴሌኮም ታሪፍ ጣራ እንዲነካ በመሆኑ የቴሌፎን አገልግሎት በአፍሪካ ውድ የሚባል ሲሆን የጥራት ደረጃውም ከሶማሊያ እንኳ ያነሰ እንደሆነ በዘርፉ የተሠማሩ አጥኚዎች ይመሰክራሉ።
ከለውጡ ወዲህ እንኳ አሁንም፤ ተገቢው ማሻሻያ ስላልተደረገበት የኢትዮጵያ ቴሌኮም ‘በኪስ አውላቂነት’ ከሚመደቡት የመንግሥት ተቋማት አንዱ እንደሆነ ይነገራል። እንዲህ ያለው እርምጃ የአገርን ዕድገት ከማቀጨጭ የተለየ ሆኖ ሊታይ አይችልም። በራስ መተማመን የሌለው መንግሥት፤ የሚያስተዳድረው ሕዝብ ሶሺያል ሚዲያን ሁል ጊዜ ለፖለቲካ ተግባር ብቻ የሚጠቀምበት አድርጎ ይወስደዋል።
ለመማሪያና ለመረዳጃ እንዲሁም ለግብይት አገልግሎት መጠቀም ስለሚቻል ሥራን በጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቀላጠፍ የሚያደርግ መሆኑን ከግምት ውስጥ አያስገባም። የኢትዮጵያው ቴሌኮም በአራተኛው ጄኔሬሽን ፈጣን አገልግሎት እየሰጠን ነው የሚል ቢል ቦርድ በየቦታው ማቆሙን ሰምተናል፤ ይሁን እንጂ ተጠቃሚዎቹ አንድ መቶ ብር ከፍለው የሚፈልጉትን ሳያገኙ ገንዘቡ ግን እንደሚያልቅ በምሬት እየተናገሩ ናቸው። ከዚህም በላይ አገልግሎቱ በሁሉም አካባቢዎች እኩል እንዳልሆነ በዘርፉ የተሠማሩ ቴክኒሺያኖች አረጋግጠዋል።
‘ድመት መንኩሳ ዐመሏን አትረሳ’ እንዲሉ፤ጠ/ሚንስትሩ የኢንሳ ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት ይሠሩት የነበረውን እያስታወሱ በዚያው የአፈና ሥርዓት እንደቀጠሉበት ለመረዳት አይከብድም። ይህ ብቻም አይደለም፤በራስ መተማመን የሌለው መንግሥት ሁኔታውን በመረዳት ተጨማሪ አፋኝ ኃይል በመቅጠርና በማሠልጠን በጉልበት ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረጉ አይቀሬ ነው። ነገር ግን ችግሩ ለጥቂት ጊዜ የታፈነ ቢመስልም ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ይቆይና አንድ ቀን፤ እየተጠቃ ያለው ሕዝብ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ቅስቀሳ ተገፋፍቶ አደባባባይ መውጣቱ አይቀርም።
ያኔ የመግሥት ኃይሎችም ከበላይ የሚሰጣቸውን መመሪያ ለማስፈጸም ሲሉ በተቃዋሚው ሠልፈኛ ላይ ያመረረ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ዞሮ ዞሮ የሕዝብን ድምፅ በመቀማት ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ያልሆነው መንግሥት ከዝቅተኛ ወንጀል ወደ ላቀ ወንጀል፤ ከጥፋት ወደ ከፍተኛ ጥፋት እየተሸጋገረ መጨረሻው አያምርም። ጉዳዩ በዓለም መድረክ እየታወቀ ሲሄድም መጥፎ ተግባሩን የሚሸፍንበት አንዳችም ከለላ ስለማይኖረው እርቃኑን ይወጣል።
መጨረሻውም ግልጽ ነው፤ የመንግሥት ሥልጣን ያለሕዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ፤ ዘለዓለማዊ ሊሆን አይችልምና በከፍተኛ ቅሌት መዋረዳቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የሕዝቡን የድምፅ ውሳኔ በማክበር በፀጋ ተቀብለው ለተተኪያቸው በፍቅር የሚያስተላልፉ፤ በበለጸጉት አገሮች ካልሆነ በስተቀር በታዳጊ አገሮች ፈጽሞ የተለመደ አይደለም። ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት በሥልጣን በነበሩት ወቅት በቅንነትና በታማኝነት ኃላፊነታቸውን ስለማይወጡና ኃይላቸውን ያለአግባብ በመጠቀም የተለያዩ ወንጀሎችን በመሥራት በሙስና የተዘፈቁ ስለሚሆኑ፤ ‘ከሥልጣን ብወርድ በሕግ ልጠየቅ እችላለሁ’ ብለው ስለሚሰጉ እንደሆነ መገመት አይከብድም።
ነገር ግን ሥልጣናቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙ በሀገር ዕድገትና ልማት ላይ ብቻ፤ ቢያውሉት ግን በምርጫም ወቅት ምንም የሚያሰጋቸው ጉዳይ አይኖርም። ምክንያቱም ሠፊው ሕዝብ እንዲህ ያለውን ታማኝ መንግሥት ትቶ አባቱን፤ ወንድሙን፤ ወይንም ጓደኛውን እንደማይመርጥ በግልጽ ይታወቃል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ለአገራችን ለኢትዮጵያ የሚበጃትና የሚስማማት የዘውድ አገዛዝ ነበር። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ማለት መላዋ የአፍሪካ አህጉር ነበረች። እንግሊዞች ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ለማጥፋት ‘አቢሲኒያ’ የሚል ስም በመስጠት በዓለም መንግሥታት ዘንድም ተቀባይነት እንዲያገኝ በማከታተል በርካታ መጻሕፍትን በማሳትም አሥራጭተው ነበር። ነገር ግን በዘውዱ አስተዳደር፤ በኦርቶዶክስ ሃይማኖትና በእውነትኛ ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች አማካይነት ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም። ኢትዮጵያን በዓለም ገናና አድርጎ ያቆያትም የዘውድ አገዛዝ እንደሆነ የሚካድ አይደለም።
ይህንን ወዳጆቻችን ብቻ ሳይሆኑ ጠላቶቻችንም ጠንቅቀው ያውቁታል። ነገር ግን ምቀኞችና ቀናተኞች ይህንን ታላቅ የአስተዳደር ዘይቤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲወገድ አድርገዋል። በዓለም ላይ በዘውድ አስተዳደር የሚገኙ ሀገራት ድምጻቸው አይሰማም። ስዊድን፤ኖርዌይ፤ዴንማርክ፤ ቤልጅየም፤ታይላንድ፤ጃፓን እና የመሳሰሉት በቴክኖሎጂ ዕድገት፤ ወይንም በሰብአዊነት እርዳታ ለጋሽነት (Humanitarian Aid) ካልሆነ በስተቀር በሌላ ነገር ስማቸው አይነሳም።
በዘውዱ አገዛዝ እንግሊዝም አለችበት፤ ንግሥት ኤሣቤጥ አሁንም የካናዳ፤የአውስትራሊያ እና የኒውዚላድ አገሮች የበላይ ናቸው። ነገር ግን እንግሊዝን ከሌላው አገር የሚለያት የዘውድን አስተዳደር ከእነርሱ በስተቀር ሌላው አገር እንዲጠቀምበት አይፈልጉም። ስለሆነም የብዙ አገሮችን ንጉሣዊ አገዛዝ በማፍረሱ በኩል በስውር ተባባሪዎች ሆነዋል።
ኢትዮጵያ ለከፍተኛ የነፃነት ክብርና ጀግንነት የበቃችው በንጉሣዊው ሥርዓት እንደነበረ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ንጉሥ ማለት ‘ሥዩመ እግዚአብሔር’ ማለት ነው። ስለሆነም የሕግ የበላይነትን ያስከብራል። ፍርድ እንዳይጓደል፤ ደሀ እንዳይበደል ተግቶ ይሠራል። በዘር እና በሃይማኖት ልዩነት አያምንም፤ ምክንያቱም ሁሉም የሰው ዘር እኩል እስከሆነ ድረስ ‘አገር የጋራ ነው፤ ሃይማኖት ደግሞ የግል ነው!’ ብሎ ያምናልና።
ኢትዮጵያን ከሌላው አገር ልዩ የሚያደርጋት የራሷ ፊደል ያላት ጥንታዊ አገር ስትሆን ታሪኳንም ጽፋ የያዘች በዓለም ካሉ ጥቂት አገሮች አንዷ መሆኗ ነው። ሌላው ደግሞ ሕዝቡ እጅግ እግዚአብሔርን የሚፈራና እንግዳ ተቀባይ መሆኑ ነው። ከዚህም የተነሣ የክርስቲያን አገር የነበረችው ኢትዮጵያ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የመጀመሪያዎችን የእስላም ስደተኞች (First Hijira) በደስታ ተቀብላ ያሠፈረች ባለውለታ አገር መሆኗን ልብ ይሏል።
ለነገሩ አሁን በአገራችን የበቀሉት የበሉበትን ወጭት የሚሠብሩ እስላም አክራሪዎች፤ በቁራን ስለተጻፈ እንጂ ይህንኑም ከመካድ ወደ ኋላ አይሉም። ምክንያቱም የክርስትና ሃይማኖት የታደጋቸው ባለውለታ ሳይሆን ጠላት እንደሆነ ተደርጎ ስለተነገራቸው፤ ያለአግባብ ዘግናኝ እርምጃ ለመውሰድ ይሞክራሉ። ከአርቲስት ሃጫሉ የግፍ ግድያ በኋላ በዝዋይ፤ በሻሸመኔና፤ በአርሲና በባሌ እንዲሁም በሐረር የታየው ዘር ተኮር ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት፤ ከመሠሪ የኢትዮጵያ ጠላቶች የታቀደውን ዓላማ ማስፈጸሚያ እንደሆነ አጠራጣሪ ሊሆን አይገባም።
እንግዲህ ፖለቲከኞች ደካሞች ከመሆናቸው የተነሳ እንዲህ ያለውን የዘር ክፍፍልና ልዩነት እንደ ጀብድ በመቁጠር ሕዝብን በማስተባበር ሳይሆን በመከፋፈልና እርስ በእርሱ በማናቆር የግል ጥቅማቸውን የማስከበሪያ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። እንዲህ ያሉት ለግል ጥቅማቸው የቆሙት ፖለቲከኞች ደግሞ በገንዘብ ተገዝተው የኢትዮጵያ ጠላቶችን አጀንዳ አንግበው ደሀውን እየሰበኩ በመንጋ በማሰለፍ በግምባር ቀደም መሪነት አስፈጻሚ ሆነው ይታያሉ።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ኅብረ ቀለም ያለው መጋረጃ እና ጥሩ ስጋጃ ምንጣፍ ፊት ለፊት እያሳዩ ከመጋረጃው ጀርባ ግን የሕዝብን ሳይሆን የራሳቸውን የግል አጀንዳ እያካሄዱ መሆናቸው ይታወቃል። ሕዝብ በአንድ አቅጣጫ የሚያየውንና የሚሰማውን ብቻ ሳይሆን ከአድማስ ባሻገር ያለውን የፖለቲከኞች አጀንዳ ራዕይ፤ ከተቀናቃኞቻቸው የሚሰጠውንም ትችት፤ በአንክሮ በመከታተል የራሱን የኅሊና ግንዛቤ በመጨመር ትክክለኛውን ለይቶ ለማወቅ መጣር ይኖርበታል። ካልሆነ ግን ‘በሬ ከአራጁ ጋር ይውላል’ ማለት እንደሚሆን መረዳት ተገቢ ነው እንላለን።
በቁመና፤ በዘር፤ በቋንቋ፤ ወይንም በአነጋገር ብልጣብልጥነት አገር ልትገነባ እንደማትችል ማጤን ብልህነት ነው። በአብዛኛው ፖለቲከኞች፤ በሃይማኖት አያምኑም፤ ስለሆነም ፈጣሪ አምላክ የሚባል ነገር የላቸውም። አለን ቢሉም ከማስመሰል የዘለለ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲ ስብስብ ደግሞ ለአገርም ሆነ ለወገን የሚጠቅሙ አይደሉም። ሰውን የሚያዩት እንደ ባዮሎጂካል ቁስ አካል እንጂ በአርአያ ሥላሴ እንደተፈጠረ አይደለም። ይህም ማለት አንድን ሰው ለራሳቸው የሚጠቅም የፈለጉትን አጀንዳ ከአሥሩት በኋላ እንደ ሲጋራ ቁራጭ፤እንደ አረጀ ጎማ ወይንም ደግሞ እንደ ተላመጠ መስቲካ አውጥተው ይተፉታል።
እነርሱ ሰውን የሚያስቡት እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ግዑዝ አካል ነው። የሰጡትን ትዕዛዝ በሚፈጽምበት ጊዜ ቢሞት ወይንም ለዘለቄታው አካለ ስንኩል ቢሆን ዞረው አያዩትም። ወያኔ ሕወሃት ያደረገውን ማስታወስ ተገቢ ነው። ብዙ የትግራይ ልጆች በፍላጎትም ይሁን ተገደው በትግል ላይ ከቆዩ በኋላ ብዙዎቹ ሲሞቱ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ለዘላቄታዊ የአካል ጉዳት ተዳርገው ሳለ፤ ወያኔዎች ሥልጣን ከያዙ በኋላ ምንም ዓይነት ተገቢውን ዕርዳታና እንክብካቤ ሊያደርጉላቸው አልፈቀዱም። በዚህም ምክንያት ግማሾቹ በንዴት ሕይወታቸውን ሲያጠፉ ግማሾቹ ደግሞ በልመና እየተሠቃዩ እንደሆነ እየሰማን ነው።
ከዚህ የምንረዳው ፖለቲከኞች በሚያስቀና ሁኔታ፤ ዛሬ እንደ እናት ልጅ ወንድም፤ ወይም እንደ ትግል አጋር ጓድ ያደረጉትን ጓደኛቸውን፤ ሁኔታው ከተመቻቸላቸው በኋላ፤ ወይም የሚወዳደራቸው ከመሰላቸው ደግሞ እንደ ዋነኛ ጠላት አድርገው በፍጥነት መፈረጁን ያውቁበታል። ለዚህም ማስረጃ ይሆን ዘንድ የተለያዩ ክስተቶችን መጥቀስ እንችላለን። የሩሲያ መሪ የነበረው ጆሴፍ እስታሊን የትግል አጋሩ የነበረውን ትሮትስኪን አሳዶ እንዳስገደለው፡ በአገራችንም ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሻለቃ አጥናፉ አባተን እንዳስገደሉ፤ መለስ ዜናዊ ታምራት ላይኔን እና እነ ስዬ አብርሃን ዘብጥያ እንዳወረዷቸው፤ ክንፈ አብርሃንና ሃየሎም አርአያን እንዳስገደሏቸው፤ አሁንም ሌላውን እንተወውና በዶ/ር ዓቢይ አህመድ እና፤ የመከላከያ ሚንስትር የነበሩትን የአቶ ለማ መገርሣን ጉዳይ ማየቱ ይበቃል።
እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ታላቅ ክብርና አመኔታ የነበራቸው ሰዎች እንኳ ኅሊናቸውን ለጊዜያዊ ጥቅም ሸጠው ፍርፋሪ ለመልቀም እየተርመጠመጡ ሲታዩ በጣም ያሳፍራል። ‘ፖለቲካ ህሊናን ያውራል!’ ኅሊና ሲታወር ደግሞ የፈጠረንም አምላክ ያስረሳል። አፍቅሮ ንዋይና የሥልጣን ጥማት፤የሰይጣን መንገድ መሆኑ ተሰርውሮባቸዋል። በአንድ ወቅት የሰላ ብዕር አላቸው የሚባሉት፤ዓለምን እየዞሩ ያስተምሩ የነበሩ ዝነኛ ሰዎች ሁላ አፋቸው ተሸብቦ፤ ብዕራቸው ነጥፎ፤ የሚሰሙትንና የሚያዩትን እንዳላወቁ ሆነው በገንዘብ ተጠልፈውና ደንዝዘው ሲወድቁ ማየት እጅግ ያሳዝናል። ዓለም አውጥታ አውጥታ ከላይ ታደርስና አውርዳ ማፍረጡን ታውቅበታለች። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች እናንተን እንምከር ሲሉ የነበሩ ሲሆኑ አሁን እነርሱን ማን ይምከራቸው? ኅሊናቸውን ስለሸጡት ፈጣሪያቸውንም እረስተዋልና!
ስለዚህ ወገኔ ንቃ! ኅሊናህን ተጠቀም እንጂ በብልጣብልጥ ፖለቲከኛ እንዳትታለል። ፖለቲከኛ የልብ ጓደኛውን እንኳ ወቅት ጠብቆ ጭዳ የሚደርግ አረመኔ መሆኑን በመገንዘብ ሁልህም ነቅተህ በኅሊናህ ተመራ። ለጓደኛው ያልሆነ ለማንስ ሊሆን ይችላል ብለህ ታስባለህ? ከሁሉም የከፋው ደግሞ የሰው መሣሪያ በመሆን ምንም ዓይነት በደል ያልፈጸመብህን ሰው፤ ሕይወትና ንብረት፤ ማውደም ቂልነት እንጂ ብልህነት ሊሆን አይችልምና ቆም ብሎ ማሰቡ ከኅሊና ጸጸት ያድናል።
ስለዚህ ጽሑፍ አስተያየት ለመስጠት ወይም ለመተቸት የምትፈልጉ አገርንና ወገንን ከጥፋት ለማዳን ከሚደረገው ትግል የተሻለ ነገር የለምና፤ በ [email protected] ኢሜል ብታደርጉልኝ በደስታ የምቀበል መሆኔን በትህትና እገልጻለሁ። በጽሑፉ ከረካችሁ ለጓደኞቻችሁና ለምታውቋቸው በማካፈል፤ ያላዩት እንዲያዩት ተባበሩ፤ ይህም አገርን የመታደግ አንዱና ዋነኛው የትግል ዘዴ መሆኑን አትርሱ!