በህይወት አበበ መኳንንት
E-mail- [email protected]
አንድን ሰውም ሆነ ቡድን በቋንቋው፣ በዘሩ፣ በእምነቱ ወይም በሌላ አንድ የሚያደርገው መመዘኛ ምክንያት ሌላ ወይም ሌሎች ሰዎች ወይም ቡድኖች ተነስተው፣ የአካላዊና ሞራላዊ ጉዳት ከማድረስ ጀምሮ እስከ ግድያ የሄደ ህገ ወጥ ተግባር የዘር ማጥፋት ወንጀል ተብሎ ይፈረጃል። ማንኛውም በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የሚደርስ የጥፋት ድርጊት ወንጀል ተብሎ የሚፈረጅ ቢሆንም የዘር ማጥፋት ወንጀል ግን በቀጥታ ከጉዳዩ ምንም ግንኙነት የሌላቸው ንፁሃንን ሰለባ የሚያደርግ በመሆኑ ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ ወንጀል መሆኑን በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ አሕጉራዊና ብሄራዊ ህጎች ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል።
ዲሴምበር 9/1948 ዓ/ም ፀድቆ ጃንዋሪ 12/1951 ተግባራዊ መሆን የጀመረው የዘር ማጥፋት ወንጀልን የመከላከል እና ፈፃሚዎችን ለመቅጣት የወጣውን ኮንቬንሽን ፈራሚ ከሆኑ ሃገራት ዉስጥ በቀደምትነት የምትገኘዉ ኢትዮጵያ እንደሆነች ይታወቃል። ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥበቃ የሚያደርጉ የአለም አቀፍ ስምምነቶችን የፈረመች ሀገር እንዲሁም በታሪኳ ከፖለቲካ አመለካከትና በጥቂቱ በአሕመድ ግራኝ ጊዜ ከነበረው የሃይማኖት መልክ ያለው ግጭት ውጭ በዘር ማጥፋት ወንጀል የማትነሳ ሃገር ሆና ብትቆይም ከቅርብ አመታት በኋላ ግን የዘር ማጥፋት ጭላንጭሎች መታየት የጀመሩ ቢሆንም በ2018 ዓ/ም ሚያዚያ ላይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ግን ሰፊ የዘር ማጥፋትና ማፅዳት ወንጀልን የምታስተናግድ ሃገር ለመሆን ተገዳለች።
ሃገራችን ቀደም ሲል በፈረመቻቸው ስምምነቶች መሰረት መንግስት የዜጎችን ሰብአዊ መብት የማክበር፣ የመጠበቅ አና የማስጠበቅ ተቀዳሚ ሀላፊነት አለበት። ይሁን እንጂ መንግስት መሰረታዊና ተቀዳሚ የዜጎችን መብት ከማንኛውም አካላዊና ሞራላዊ ጥቃት የመከላከል ሃላፊንቱን በመዘንጋት በዕለት ተዕለት የታይታ ፖለቲካና የፕሮፓጋንዳ ስራ ላይ በመጠመዱ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተማዎች በርካታ ንጹሀን ዜጎች በብሄራቸዉ እና በሀይማኖታቸው (ኦርቶኦክስ ክርስትያን) ከባድ ጥቃትና ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ወንጀል ሲፈጸምባቸው ዝም ብሎ ከማየት ባሻገር ችግሩን ያነሱና የሞገቱ ሰዎች እንደ ሃሰተኛ የሚይታዩበትን ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ መንግስታችን የወንጀል ተግባርን ባለመከላከልና ሲፈፀምም ባለማስቆም እንዲሁም ወንጀለኛን ተከታትሎ ለፍርድ ባለማቅረብ ሶስት ከባባድ ግድፈቶችን እየፈጸመ ከመሆኑም በላይ በድርጊት ትርጓሜ የወንጀል ተግባር ተባባሪ በሚያስመስለው ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።
ቀደም ሲል በኦሮሚያ ጉጂ ዞን ውስጥ በሚኖሩ የጌዶኦ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ በአከባቢው በሚኖሩ ኦሮሞዎች አማካኝነት ሰፊ የዘር ማጥፋት ግድያና ጥቃት ደርሷል። የአንድ ዓመት ህፃናት ሳይቀሩ በዘራቸው ምክንያት በቢላዋ አንገታቸው እየታረዱ ተገድለው በየጥሻውና በየበረሃው የአውሬ እራት እንዲሆኑ ሲጣሉና ቀሪዎቹም ህይወታቸውን ለማዳን በየጫካው ሲደበቁ በወቅቱ መንግስት ችግሩ የሌለ በማስመሰልና በመደበቅ ሊያፍነው ቢሞክርም በጠንካራ የሃገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች ጥረት ዓለም እንዲያውቀው ቢደረግም የኢትዮጵያ መንግስት ግን የችግሩን ምንጭ ከመነሻው ለማድረቅ የሰራው ስራ የለም። በጌዶኦ የዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ ተሳታፊ የነበሩት ወንጀለኞች ወደ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ አልታየም፣ አሁንም ችግሩ ሳይቀረፍ በጊዜያዊ ሽንገላና ማባበል ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ቢሞከርም ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛዎቹ በየበረሃው እንደተበተኑ መንግስት እንደሌለው ሃገር በስጋትና በፍርሃት ይኖራሉ።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ወንጀልንና የፖለቲካ መቻቻልን ለያይቶ ማየትና እንደየባህሪያቸው የማስተናገድ ብቃቱ አነስተኛ ወይም እጅግ በጣም ደካማ ስለሆነ እንዲህ ያለ የህግና የፍትህ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች ሲኖሩም “መታገስ አለብን” የሚል አሳዛኝና መታመን የማይችል መልስ በመስጠት ወንጀለኞች በነፃነት ሰላማዊ ሰዎች ደግሞ በፍርሃትና በጭንቀት ውስጥ የሚኖሩበት ስርአት እንዲሰፍን የራሱን አስተዋፆኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ቀደም ሲልም እንደዚሁ በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል መካከል ተፈጥሮ በነበረው ዘር ተኮር ግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከየቀያቸው ተፈናቅለዋል በርካታዎች በዘራቸው ምክንያት ብቻ ተገድለዋል። መንግስትም ወንጀለኞችን ይዞ ለፍርድ በማቅረብ ችግሩ ደግሞ እንዳይከሰት በማድረግ ፈንታ የማስታረቅ የሚመስል ስራ በመስራትና ችግሩን የሚያሳዩት ሰዎችንና ድርጅቶችን በመውቀስ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደ ወንጀል እንዳይታይ በማድረግ በየአከባቢው በዚሁ ወንጀል የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር የራሱን አስተዋፆኦ እያደረገ ነው።
በመቀጠልም አማሮች፣ ትግሬዎችና የጋሞ ብሄረሰብ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ በቄሮ ስም የተደራጁ የኦሮሞ ወጣቶች ቡራዩ ከተማ ውስጥ ገብተው፣ የድብደባ፣ የዘረፋ፣ የሴቶች መድፈርና ግድያ በማከናወን ቤታቸን በማቃጠልና ከአከባቢው ውጡልን በማለት ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈፅሙ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ጠቅላይ ሚኒስትርና መንግስቱ ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል ተጠምዶ ነበር።
በመቀጠልም ኦክቶበር 23/2019 የኦሮሞ አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ጠባቂዎቹ በሌሊት ትተዉት እንዲሄዱ መንግስት ያስተላለፈላቸውን መልዕክት በመግለጽ የኦሮሞ ቄሮዎችን ድረሱልኝ በማለቱ በዚሁ ሳቢያ በተነሳው የኦሮሞ ቄሮ ቁጣ ከ89 በላይ ንፁሃን ዜጎች ዘራቸው አማራ የሆኑት እየተመረጡ እንዲገደሉ ሲደረግ፣ በየቤተክርስቲያኑ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሲገደሉ፣ ሲቃጠሉና ሬሳቸው በመኪና ሲጎተት የመንግስት ፖሊሶች ድርጊቱን እንደ ድራማ ቆመው እያዩ እንደነበረ ከዚሁ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተአምር ያመለጡ ሰዎች በተለይም አማሮች ተናግረዋል። ማስረጃዎችም በተለያዩ ሚዲያዎች በፎቶና በቪዲዮ ተደግፈው ቀርበዋል። ይሁን እንጂ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ አንዳቸውም ነፍሰ ገዳዮች ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አልተደረገም።
ሰውን በዘሩ እየለዩ የገደሉ ሰዎች አለመያዝና ለፍርድ አለመቅረብ ወንጀለኞችን የልብ ልብ ሰጥቷቸው እንደገና በሰኔ 29/2020 አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከተሎ በኦሮሚያ አርባ ወረዳዎች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣ አማራ የሆኑት እየተለዩ ተጨፍጭፈዋል፣ ንብረታቸው ተቃጥሏል፣ ሬሳቸው በመኪና ተጎትቷል። ይህ የሆነው አማራና ኦርቶዶክስን በመለየት ሲሆን መንግስት 239 ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ በሚዲያው ቢነግርም አንዳንድ ሚዲያዎች ግን መንግስት ቁጥሩን ደብቆታል እንጂ ከተባለው በላይ ሞቷል ብለዋል። ይሁን እንጂ አንድም ንፁህ ሰው በዘሩና በሃይማኖቱ ምክንያት በወንጀለኞች እየታደነ እንደ አውሬ በገጀራ ተጨፍጭፎ ሲገደል መንግስት ምንም ሳያደርግ በቸልታ እየተመለከተው እንደነበር ከአካባቢዎቹ የደረሱ ማስረጃዎችና በህይወት የተረፉ ሰዎች ምስክርነት ያስረዳል። በተለይም በዴራ፣ በአጋርፋ፣ በሻሸመኔና በአርሲ ነገሌ ላይ ክርስቲያኖችና አማሮች ለስምንትና ዘጠኝ ሰዓታት ወንጀለኞች እየዞሩ ሲገድሏቸውና የመንግስት ፖሊስም ሆነ የመከላከያ ሃይል እንዲያድናቸው ሲማፀኑ “ከበላይ አካል እርምጃ እንድንወስድ ትዕዛዝ ስላልተሰጠን ምንም ማድረግ አንችልም” በማለት የንፁሃን መጨፍጨፍና የህፃናትን ሞት ለመታደግ ምንም ጥረት ሳያደርግ ቀርቷል። እነዚህ ዜጎች የሚረዳቸው አጥተው ወይም በሌለበት ሳይሆን የመንግስት ፖሊስና ሰራዊት ለመርዳት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ለዘር ማጥፋት ወንጀል አጋልጦ ስለሰጣቸው ለአካላዊ፣ የሞራልና የህይወት አደጋ አጋልጧቸዋል።
እንዲህ ያለ ወንጀል ሲፈፀም መንግስት ዜጎቹ ያቀረቡለትን የአድኑን ልመና ከቁብ ሳይቆጥር እሱ ስልጣኑን እንዴት አድርጎ ማራዘም እንደሚችል ብቻ እያሰበ ሰዎችን ያረዱና ያሳረዱ የመንግስት ሃላፊዎችን ትቶ በአዲስ አበባ ላይ በሰላማዊ መንገድ ሲቃወሙ የነበሩት ሰላማዊ የፖለቲካ ሰዎችን ማሰር ሲጀምር ሃገራችን በአምባገነን መንግስት ቀንበር ስር መውደቋን ያረጋገጣል።
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ እነዛ በወንጀለኞች ሳቢያ ከዘር ጭፍጨፋው አምልጠው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች አያያዝ ጉዳይ ነው። የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ተከትሎ ከተደረገው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አምልጠው በየቤተክርስቲያኑ የተደበቁና የተጠለሉ ሰዎች ምንም ዓይነት ዕርዳታ አላገኙም አሊያም እዚህ ግባ የማይባል የማስመሰል ፕሮፓጋንዳ እየተፈፀመባቸው ይገኛል። በኦሮሚያው የዘር ማጥፋት ወንጀል መሪ ተዋናዮቹ ዶክተር ዓብይን ወደ ስልጣን ለማምጣት ተደራጅተው መንገድ ሲዘጉና ዓመፅ ሲያስነሱ የነበሩ ቄሮ የተባሉ አሸባሪዎች ናቸው። እነሱ በዚህ መንግስት ማንንም ቢገድሉም ሲታሰሩና ሲጠየቁ አይታዩም። ይህ ማን እንደፃፈው ያልታወቀ የቄሮዎች ያለመያዝና ያለመጠየቅ መብትም ሌሎች ቄሮዎች በየቦታው በአማራውና በሌሎች ብሄሮች ላይ ጥቃት በመፈፀም ንብረታቸውን ዘርፈው፣ ልጅቻቸን ደፍረውና ገድለው በሰላም እየኖሩ ይገኛሉ።
አሁንም ኢትዮጵያን መንግስት በወንጀለኞች ላይ አስፈላጊና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ በአፅንኦት ቢማፀኑም መንግስት ግን ለፖለቲካ ፍጆታ እዚያና እዚህ ከሚያደርገው ርካሽ የፕሮፓጋንዳ ስራ ባሻገር ጠብ የሚል ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም። ከአርቲስ ሃጫሉ ሁንዴሳ መግደል በኋላ በተደረገው የዘር ማጥፋት ወንጀል አብዛኛዎቹ ተጠቂዎች የአማራና ኦርቶዶክስ ክርስትያን የሆኑ የሌሎች አናሳ ብሄረሰቦች ተወላጆች ናቸው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመላው ዓለም የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን በመንግስት ላይ ያላቸውን ተስፋ መቁረጥ በየአከባቢው በከፍተኛ ቁጣ ወጥተው ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። በሁሉም ሰልፎች ላይ ካለልዩነት ከተነሱት ነጥቦች ዋነኛው መንግስት የህዝብ ደህንነት ያስጠብቅ የሚል ይገኝበታል።
የዓብይ መንግስት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሃገራችንን ወደ አደገኛ የፖለቲካ ማዳለጥና ወደማይጠገን የማህበራዊ ቅውስ እየገፋት ይገኛል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ሃገራችን ረዥም ለመሄድ የምትችልበት ጉልበቱም ሆነ አቅሙ የላትም። አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት እንደ መንግስት ስራውን በትክክል መስራት ካልቻለ በኢትዮጵያ ከባድ የሆነ የዘር ግጭትና ኣልቂት ሊፈጠር እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም።
መንግስት ዜጎቹን ከግድያና ካፈና ካላዳነ ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት በገዛ ሃገራቸው በሰላም የመኖር ዋስትናቸው ተጠብቆ መኖር ካልቻሉ የመንግስት በስልጣን ላይ መኖር ምን ጥቅም አለው? ጁን 22 ቀን 2019 በአንድ ቀን የአማራ ክልል ፕሬዝደንት፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ፣ የፕሬዝደንቱ ረዳት፣ የሃገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና ሌሎች ከፍተኛ የመከላከያ ጀነራል በቢሮአቸውና በቤታቸው ሲገደሉ ማን እንደገደላቸው እንኳ ማጣራትና ህዝቡን ማሳወቅ የማይችል መንግስት እንዴት አድርጎ ነው ኢትዮጵያን አልምቶና አረጋግቶ ወደተሻለ ምዕራፍ ሊያሻግራት የሚችለው? ከስምንትና ዘጠኝ ወራት በፊት በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩት የአማራ ክልል 17 ሴት ተማሪዎች ባልታወቁ ሰዎች ታፍነው ተወሰዱ ከተባለ በኋላ መንግስት በሃሰት ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲመለሱ አድርገናል ቢልም ወላጆች የልጆቻቸውን ዱካ ማግኘት ባለመቻላቸው ጉዳዩ እስካሁን ምንም መፍትሄ ሳያገኝ እንደጠፉ ቀርተዋል።
በያዝነው ሳምንት ማለትም በሃምሌ ወር 2020 መጨረሻም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያልታወቁ ታጣቂዎች አማራ ገበሬዎችን ብቻ ለይተው አስራ አራት ገድለውና ብዙ አቁስለው ሳይበቃቸው ከትናንት ወዲያ ደግሞ ሶስት የአማራ ብሄር ተወላጆች ታፍነው ሲወሰዱ መንግስት ምንም ማድረግ አልቻለም አልፈለገምም። አሁን ያለው የኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትክክለኛ ማንነት በመደበቅና በጥቅም ባሰማራቸው ሚዲያዎቹና አንዳንድ የጥቅም ተጋሪ በሆኑ ምሁራኖች በኩል ምዕራባውያንን በማታለልና በማሳሳት የሰላም ኖቬል ሽልማት ቢሸለምም ትክክለኛ ገፅታው ግን እንኳንስ ለኖቬል ሽልማት ላለበት ስልጣን የማይመጥን፣ ዕውነትን የማይናገር፣ ምክርና ውይይትን የማይደግፍ፣ እርሱን እንደ ዕውቀት መጨረሻ የሚያይ ሰው በመሆኑ ሃገራችንን ወደ አምባገነናዊ፣ ፀረ ዲሞክራሲና ስርዓት እየወሰዳት እንደሆነ ለመገንዘብ የግድ የፖለቲካ ሰው መሆን አይጠይቅም።
በሃገራችን በአማራዎችና በሌሎች ብሄሮች ላይ እየደረሰ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ባፋጣኝ እርምጃ ተወስዶበት እንዲቆም ካልተደረገ ነገ ሲበዛ ልጆቹንና ቤተሰቡን ለመከላከል ሲል ተበዳዩ ህዝብ በሚወስደው እርምጃ ሃገሪቱ ማባሪያ ወደሌለው ግጭትና ጦርነት ገብታ ከናካቴውም እንዳትበታተን ያሰጋል። በሰላምና በፍትህ የምናምን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተነስተን በሁሉም መስክ ሃገራችንን ለማዳን ትክክለኛ ሰላማዊ እርምጃ ዛሬውኑ መውሰድ ካልቻልን ሃገራችን ከገናናነትና የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ ወደ ፍርስራሽነት እንዳትቀየር የሚይድናት አንድም ሃይል አይኖርም። እኛ ልጆቿ በዚህ ዘመን ልንደርስላትና ህዝብን ከዕልቂት ሃገራችንን ደግሞ ከመበታተን ልናድን ካልቻልን ሌላ ሃይል መጥቶ ሊያድናት አይችልም። ይህ ዕውነት ነው።