ይድረስ ለክቡር ጠቅላይሚር አብይ አህመድና የማያልፍ ታሪክ ሠርተው ማለፍ ለሚሹ ጓደኞችዎ (ሰዉነት ደሃብ ከሃገረ ስዊድን)

አብይ ተሰማራ – – – አብይ ተሰማራ
እንደ አብርሃም ሊንከን – – – እንደ ቼጉቬራ
ከገፊዎች ሳይሆን – – – ከተገፉት ጋራ
ሊገፉም ከታጩት – – – ያገር ልጆች ጎራ
ካፍንጫ ሥር ሳይሆን ሩቅ ከሚያልሙ – – – ቀና ልብ ያላቸው ጥቂት ጓዶች ጋራ

 

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ በአሁኑ ወቅት ሃገራችን የገባችበት ሲያዩት ቀላል የሚመስል ነገርግን እጅግ አደገኛ አጣብቂኝ ነው :: አሁን ያለንበት አጣብቂኝ አንድ በሥልጣን ላይ ያለ አካል  ከሚያጋጥሙት ዕድሎች አንጻር ከታየ በጣም በተወሰነ  ደረጃ ከ 1997 ምርጫ ማግስት ጋራ ሊመሳሰል የሚችል ነው :: ከሚያመጣው አደጋ አንጻር ካየነው ግን የአሁኑ እጅግ በብዙ እጥፍ የከፋና ምናልባትም የአመራር መሪዉን ያያዛችሁት ሠዎች በተቻለ ፍጥነት እና ድፍረት የመሃሉን መንገድ ካልመረጣችሁ በሃገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ታሪክ ታላቅ ጠባሳ ጥላችሁ እንደ ምታልፉ ግልጽ እየሆነ በመምጣቱ ነው :: ምክንያቱም ግራዉም ሆነ ቀኙ ገደል የሆነበት መንገድ ላይ ስላላችሁ ነው ::

በ 1997 ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በምርጫው ማግስት በፍጥነትና በድፍረት መወሰን ቢችሉና በወቅቱ ስልጣኑን የማስረከብ ድፍረት ቢያጡ እንኳን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባቀረቡት የመደራደርያ ነጥቦች ለመስማማት ደፍረዉ ቀጣዩን ምርጫ ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ መወሰን ችለዉ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላለንበት ቀዉስ አንደርስም ነበር ብዬ አምናለሁ :: ያንን አድርገዉ ቢሆን የሃገራችንን የፖለቲካ ምዕራፍ ቀያሪ መሆን ብቻ  ሳይሆን በቅድሚያ እሳቸዉና ቤተሰቦቻቸዉ፣ ቀጥሎ ዘመድ አዝማዶቻቸዉ፣ ከዚያም አልፎ ፓርቲያቸዉና ጓዶቻቸው፣ ከፍ ሲልም ሃገራቸዉ ማለትም እኛ ዜጎቹ አንገታችንን ከፍ አድርገን እንድንሄድ የማድረግ ወርቃማ እድል ነበራቸው :: ነገር ግን ያንን እድል በማበላሸታቸው ከዚያ በጣም ወደ ከፋ አረንቋ እንድንገባ ሆነናል ::

በያንዳንዳችን  የህይወት ምዕራፍ ዉስጥ ታሪክ  እራሱ የየራሳችንን አሳዛኝ ወይም መልካም የታሪክ አሻራ እናኖር ዘንድ እጅግ ወሳኝ ዕድል በእጃችን ላይ ያስቀምጣል :: እኛም ታድያ በእጃችን ላይ ያለዉን እድል  በተቻለ ፍጥነት እና ድፍረት በመወሰን መልካም የታሪክ አሻራ ለማኖር ካልተጠቀምንበት ታሪካችንን በአሳዛኝ ምዕራፍ ለመደምደም እንደተስማማን ይቆጠራል :: ክፋቱ ደግሞ ታሪክ ተመሳሳይ እድል የማይሰጥ መሆኑ ነው :: አንዴ ካመለጠ  አመለጠ ነዉና ::  ልክ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የታሪክ እድል ማለት ነው ::

እዚህ ጋር መታወስ ያለበት ፍሬ ጉዳይ ቢኖር በመግቢየዬ ላይ ለማሳሰብ እንደሞከርኩትና በታሪክ እንደምናዉቀውም ዘመዶቻቸዉ ከሚፈጽሙት ኢሠብዓዊ ድርጊት ጎን ሳይሆን ከተጨቆኑት ጥቁሮች ጎን በመቆም የተሰጣቸዉን የታሪክ እድል ሳያባክኑ በአግባቡ ለመጠቀም በፍጥነትና በድፍረት መወሰን በመቻላቸው መልካም አሻራቸዉን እዳኖሩት እንደ አሜሪካዊዉ ፕሬዚደንት ልክ እንደ አብርሃም ሊንከንና ጓዶቻቸው አሊያም እንደ ቦሊቪያዉ የነጻነት ታጋይ እንደ ቼጉቬራ ሁሉ ከአግላዮች ወይም ከሃሰት ጎን ሳይሆን ከእዉነትጋር መቆም ያለባችሁግዜ ላይ እንዳላችሁ ይሰማኛል :: በመሆኑም በእጃችሁ ላይ ያለዉን የታሪክ ዕድል በአግባቡና በወቅቱ በመጠቀም መልካም የታሪክ አሻራ ለማኖር በፍጥነትና በድፍረት  ለመወሰን ግዜ ባታባክኑ ይመረጣል ::

እንደ መልዕክቴ መቋጫ ወይንም እንደ መዉጫ በፍጥነትና በድፍረት ሊወሰኑ የሚገባቸዉን በሚመለከት የሚከተሉትን የመፍትሄ ሃሳቦች ለመሰንዘር ወደድኩ :: የመፍትሄ ሃሳቦቹን እኔ ጠቅለልና አጠር ባለ መልክ ላቅርባቸው እንጂ ከሞላ ጎደል በተበጣጠሰ መንገድም ቢሆን በተለያየ መንገድና በተለያዩ መድረኮች የሃገራችን ልሂቃን ሲያነሷቸዉ የነበሩ መሆናቸዉን ላሰምርበት እወዳለሁ :: ልዩነቱ  ሃገራችን አሁን ላለችበት እጅግ አደገኛ አጣብቂኝ በእኔ አረዳድ ትክክለኛ መፍትሄ በትክክለኛዉ ሰዓት ሆነዉ ስለታዩኝ ነዉ :: እስካሁንም ሃሳቦቹ ጆሮ ያላገኙት በትክክለኛ ወቅት ስላልቀረቡ ይሆናል ብዬ ሳላመንኩኝም ጭምር ::

 

የመፍትሄ ሃሳቦች

1ኛ/  በሃገራችን እንደ ፖለቲካ  ፓርቲ በዘር ወይንም በሃይማኖት የመደራጀት መብትን በህግ መገከልከል

    ምክንያቱም

  • በአንድ በኩል የዚህን መብት አሉታዊ ዉጤት በርስዎ የስልጣን ዘመን እንኳን በተደጋጋሚ አይተነዋል
  • ከዚያ ባለፈምም ከዚህ በኋላ የሚመጣው የመብቱ ዉቴት ደግሞ እንደ ሃገር ሳያጠፋን ለመመለሱ ምንም ዓይነት ዋስትና የለንምና

2ኛ/  ፌዴራሊዝምን ወይንም የህዝብን ራሱን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲሁም ባህልንና ቋንቋን
         የማሳደግ መብትን በማይጎዳ መልኩ አሁን ያለዉን የአስተዳደር ወሰን ወይንም የክልል አደረጃጀት
         ማሻሻል

ለምሳሌ ኦሮሚያና አማራ ልክ እንደ ደቡብ ሁሉ ሰፋፊ ክልሎች ናቸዉ :: ስለዚህ የኦሮሚያንና የአማራን የክልል  ወሰን ማሻሻል ይህም ማለት ወለጋን ራሱን የቻለ ክልል፣ አርሲን  ራሱን የቻለ ክልል፣ ጅማን፣ ጎጃምን፣ ሸዋን፣ ወሎን፣ ጎንደርን እያልን የሁሉንም ህዝብ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የህዝብ ብዛትን፣ ለአስተዳደር ወሰኑ ያለ ቅርበትን፣  ወዘተረፈ ባካተተተና በባለሞያዎች በተጠና  እንዲሁም የሊሎች ተመሳሳይነት ያላቸዉ ሃገሮችን መልካም ተሞክሮ ከግምት ባስገባ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ይቻላል፣ ይገባልም::

ምክንያቱም በዚህ የሚጎዳ ህዝብ ደግሞ አይኖርም :: ካለም የግል ጥቅም የሚያጡ ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች ናቸዉና ::

ለምሳሌ ይህ በመደረጉ የወለጋ ህዝብ በተሻለ መልኩ ራሱን በራሱ የማስተዳደርና የኔ የሚላቸዉን ዕሴቶች የማጎልበት ዕድል ይኖረው ይሆናል እንጂ የሚከለክለዉ ነገር ስለማይኖር :: የሌላዉም ህዝብ እንዲሁ ::

3ኛ/  ብዙሃን በሚኖሩበት ክልል ዉስጥ የሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሌሎች የህብረተሰብ  ክፍል  አባላት
        መብትን እንደዜጋ በተገቢዉ መንገድ ለማክበር እና ለማስከበር የሚያስችል ጠንካራ ህግ ማዉጣት::

ብዙሃኖች ባህልና ቋንቋቸዉን ለማሳደግ በሚሄዱበት ርቀት የህዳጣንን ወይንም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሌሎች የህብረተሰብ ክፍል አባላትን መብት እንዳይጨፈልቁ ማድረግ ይቻላል:: ምክንያቱም በሃገሪቱ  ብዙሃን በሚኖሩበት የተለያዩ የአስተዳደር ወሰኖች ወይንም ክልሎች ዉስጥ የሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሌሎች የህብረተሰብ ክፍል አባላት በከፍተኛ ሁኔታ ሰለባ እየሆኑ ሲሆን ይህንን በማድረግ እንደ ዜጋ የመኖር፣ ሃብት የማፍራትና ሰብዓዊና  ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ሊከበርላቸዉ ይችላል፣ ይገባልም::

ለምሳሌ ድሬዳዋ ዉስጥ ያሉ የሁሉንም ህዝቦች መብት በተገቢዉ መንገድ ሊያስከብር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ማበጀት :: በሌሎቹም የአስተዳደርወሰኖች ወይንም ክልሎች  ዉስጥ ለሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሌሎች የህብረተሰብ ክፍል አባላትም እንዲሁ ::

4ኛ/  የክልል ልዩ  ሃይል አባላት በሚል ስያሜ በየክልሉ እየተሰጡ ያሉ ስልጠናዎችን  ማስቆም ብቻ ሳይሆን
        ከዚህ ቀደም  የሰለጠኑትንም ቢሆን በመንግስትም ሆነ በህዝብ ላይ አደጋ በማያስከትልና ዉጤታማ
በሚያደርግ መንገድ እንደገና ማደራጀት

 

ምክንያቱም

እነዚህ አካላት አሁን ባላቸዉ አደረጃጀት ወደፊት በህዝብና መንግስት ላይ ሊከሰት የሚችለዉን አደጋ በማባባስና በማፋጠን ረገድ የበኩላቸዉን ሚና ለመጫወት የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው::  ስለሆነም በትኩረት ሊታሰብበት ይገባል ::

በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች ወሳኝ ሊባሉ የሚችሉ አፍንጫ ሥር ሳይሆን ሩቅ የሚያልሙ ግቦችን ለማሳካት በርስዎና በጓዶችዎ በኩል ርምጃዎችን ለመዉሰድ በፍጥነትና በድፍረት መወሰን የምርጫ ጉዳይ አይደለም :: በዚሁ መሠረት መወሰን ከቻላችሁ የሃገራችንን የፖለቲካ ምዕራፍ ቀያሪ መሆን ብቻ ሳይሆን በቅድሚያ እራሳችሁንና ቤተሰቦቻችሁን፣ ቀጥሎ ዘመድ አዝማዶቻችሁን፣ ከዚያም አልፎ ፓርቲያችሁንና አባሎቻችሁን፣ ከፍ ሲልም ሃገራቸሁን ማለትም እኛን የሃገሪቷን ዜጎች አንገታችንን ከፍ አድርገን እንድንሄድ የማድረግ ወርቃማ እድል ምናልባትም የመጨረሻ  እድል እንዳላችሁ ይሰማኛል :: በርግጥ ቀላል አይደለም :: ምክንያቱም አሁን  ያልገባቸዉና አፍናጫቸዉ ሥር ብቻ የሚያስቡ ብዙዎች ሊቃወሟችሁና ዉጉዝ ከመ አሪዎስ ሊሏችሁ ይችላሉና :: ሆኖም ግን ልክ እንደ አብርሃም ሊንከንና ሌሎች የአለማችን የታሪክ ፈርጦች ሁሉ ለወጀቡ ሳትንበረከኩ ወደፊት ከተጓዛችሁ የናንተ ብቻ ሳይሆን የኛም የልጅ ልጆች፣ ከዚያም አልፎ የሌሎች ሃገር ሰዎችም የልጅ ልጆች ሃዉልታችሁ ሥር ፎቶ ለመነሳት የሚሽቀዳደሙባችሁ ባለ የመልካም ታሪክ አሻራ ባለቤቶች እንደምትሆኑ ዕምነቴ የጸና ነው :: ማለትም በፍጥነትና በድፍረት መወሰን ከቻላችሁ :: አይ ብላችሁ ፈራ ተባ  ስትሉ ፊታችን የተጋረጠዉ አደጋ እናንተን ከቀደማችሁ ወይንም ደግሞ አፍንጫችሁ ሥር ብቻ  ማሰብ ከመረጣችሁ የሃገሪቱን ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆን የስከዛሬ ታሪካችሁንም በዜሮ እንደማጣፋት ይቆጠራል :: ምክንያቱም የታሪክ ዕድላችሁን በማበላሸታችሁ በተለየዩ ወቅቶች በተለያዩ ሃገራት አሊያም አሁን በቅርብ እንኳን በኛዉ ሃገር እንደተከሰተዉና እንደተመለከትነዉ ሁሉ ሃዉልታችሁ በቀጣዩ ባለተራ የሚፈርስና  መሬት ላይ የሚጎተት፣ የገነባችሁት ሁሉ የሚናድ፣ የጻፋችሁት ሁሉ የሚቀደድ ከመሆን አይድንም :: ከናንተ የቀደሙቱ የነበራቸዉን እድል በማበላሸታቸው የራሳቸዉን እድል ከማበላሸት አልፈዉ አሁን ወደ አለንበት ከዚያ በጣም የከፋ አረንቋ ዉስጥ እንድንወድቅ አድርገዉናል::

እኔ አበቃሁ

  • ምርጫዉ የናንተ ነው እንደ እኔ እምነት ግን ከቀደሙቱ ተምራችኋል ብዬ ስለማምን ብቻ ሳይሆን በዚህ በቴክኖሎጂና በመረጃ ዘመን እየኖራችሁ ይህንን እድላችሁን ታባክኑታላችሁ ብዬ ስለማላስብ ነዉ ይህንን ለመጻፍ የተነሳሳሁት ::

ስለ እኔ

  • በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሃገሪቷ ያፈራቻቸዉን የየዘርፉ ልሂቃን አቅም ለመጠቀም ለጀመራችሁት በጎ ጅምር አክብሮት መስጠት ከሚሹትና ፈጣሪ በጎዉና ቀናዉን መንገድ ይመራችሁ ዘንድ ከሚመኙት ዜጎች አንዱ ነኝ ::

ሰዉነት ደሃብ
ከሃገረ ስዊድን

ሃምሌ 2012

1 Comment

  1. መልካም አስተውለዋል ሰውነት ደሀብ ሆይ!

    ግርማዊ ጃንሆይ ይመሩት የነበረውን አስተዳደር በ አስራ አራት ጠግዛት የተከፈለው የነበረው ይህን የጎሣ አባዜ በጣም ቀርፎ ነበር ምንም እንኳ አስተዳደሩ ላይ ብዙ ስህተትም ቢኖርበት። የዘመኑ ትውልድ በተለይም ከአብዮቱ በሁዋላ ተመሰቃቅሎበት እንጅ የደርግን ክፍላተሀገራት የየክፍለሀገሩ ኦቶኖመስ አስተዳደር ቢፈጠርና አስራ አራት ክፍለ ሀገራት አድርጎ አስራአምስተኛውን የሲዳማና ሌሎች አስተዳደር፣ ሸገርን ለብቻ እራሷን የቻለች ልክ እንደ ዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ የአዲስአበባ አስተዳደር ብትሆን (ድንገት ሌሎች የደቡብ ወገኖቻችን የዛሬውን የጎሣ ብልጭታ አይተዋልና የመድልኦ እንዳይመስል ኦቶነመስ አርጎ ልክ እንደአዲሳባ ዲስትሪክት ኦፍ ወላይታ፣ ጋሞ እያልን) አስተዳደሩን ወደ 20 ብንገፋ እንዴት ቀና ዴሞክራሲ ባሰፈን። ሆኖም አሁን እርስዎ የመከሯቸውን ለመተግበር ሰውዬው ማንን ይዘው ነው ያስብላል። ለ30 አመታት የተዘራውና አሁን የተምች አዝመራውን የምንበላው ዜጎች በጎሣ ተሸንሽነናልና ምናልባት ከመጪው ምርጫ ማግስት አቢይ ቢያሸንፉ ይህን ለማድረግ ወደሁዋላ እንደማይሉ ስራቸው ይነግረኛል። ለምን? ማንዴቱ ይኖራቸዋልና፣ በዴሞክራሲ ተመርጠዋልና። ብዙ አገራዊ ራእይ ሰንቀዋልና። እንኳንስ እርስዎ ያሳሰቡትን ለመተግበር ይቅርና በብቃትና በዜግነት ብቻ የመንግስት መ/ቤቶችን እንኳ ዛሬ ለመሙላት እንመኘው እንጅ አይቻላቸውም። ለምን? በጣም በዚህ ጎሣ ልክፍት አገሪቱ ተቀፍድዳለችና። ወጣቱ ትውልድ ጥርስ ነቅሎ ጨፈቃ ይዞበታልና። ይህው ነው ሀቁ። ውስጣቸው የተሰነጉት ስንት የጎሣ በሽተኛ እያለ በፈለገው ስሌት ዛሬ ላይ ተሁኖ እርስዎ ይሁኑ እኔ የምንመኘው የዴሞክራሲ እሳቤ ጨርሶ አይችሉትም። ይልቅ ወገን ኢትዮፕጵያዊ/ዊት የሆነ ሁሉ አቢይን እንደ ሊንከን ይሁን ቼጉቬራ ለማጀገንና እዚያ እንዲያደርሱን በጉልበትም፣ በእውቀትም እርስዎ እንዳነሱት በሀሳብም፣ በሰልፍም ካስፈለገም በነፍስም ደጀን እየሆን ይህን ከፍጻሜ እንዲያደርሱልን መታገል ነው። እነዚህን የጽልመት ሎሌ ህውሀቶችን ሰው በቀላሉ ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ገንዘቡ በብርም ፣በዶላርም ፣ በዩሮም፣ በቻይናም በጃቸው ነው። ዴሞክራሲን ለማምጣት የፈንቅል ልጆች እንደሚነግሩን፣ እኔም እንደማምንበት ድራሻቸውን ማጥፋት ነው። በልመና አልተቻለንምና። ታድያ በህብረታችን ነው። ሁሉም የበኩሉን ይወጣ። አገር በምኞት አትገነባምና። የእርሶን አይነቱን ቀና ወገን ያበራክትልን። ደጋግመን እንዲህ አይነቱን የአስተዳደር ፍላጎቱን ወገን ቢያሳውቅ የሁዋላ ሁዋላ ምኞታችን ይሳካ ይሆናል።

    የእኔ የግሌ ምኞት የየክፍላተ ሀገራት እራሱን የቻለ ኦቶኖመስ አስተዳደር ሆኖ ፕሬዚደንታዊ ይሆናል። የኦፊሴል ቋንቋን ዖሮሚፋንና አማርኛን ማድረግ። ድንገት የህዝቡን ፍላጎት አይቶ የእንግሊዝ አይነት ፓርሌመንትሪ ከሆነም በሪፈረንደም መጠይቅ። አንድ ትውልድ በነዚህ ከይሲ ወያኔዎች አልቆብን እንጅ የዘውድ ምክርቤት ከላይ ሆኖ ልክ እንደ እንግሊዞቹ በጠ/ሚር ብንተዳደርና ክፍላተሀገራችንን በዴሞክራሲ ብናድስ ለአንድነታችን እንዴት ባማረ። አሁን ያሉቷ ፕሬዚደንታችን ያው ከላይ ቁንጮ ሆነው ለሲንቦልነት አይደል ያሉት? ክራውን ፕሪንስ በህይወት ያሉት ቢሆኑ ምን ልዩነት አለው? ምንስ ክፋት አለው? ያው ጨለምተኞቹ ከማለቃቀስ በቀር? እንደውም ፈጣሪ ምናልባት ጃንሆይን በግፍ ስለሆነ የገደልናቸውና ማካካሻ አርጎልን በቸርነቱ ይምረን ይሆናል። መንግስቱ ነው ወይስ መለስ ነው የጃንሆይን ያህል የደከመው ለኢትዮጵያ? የአቢይ እንኳ ገና አንድ ፍሬ አስተዳደር ነው ሆኖም ከሁለቱ ደግሞ ያስንቃል። ይበሉ ደግሞ እራሱን አያውቄ ሁላ አድሀሪም ይባልልኝ ይሆናልና በዚሁ ልሰናበትዎ። ገና ነው መከራችን እንደሀገር። እኔ በበኩሌ ይቺን የመከራ ጊዜ እንለፈው ብዬ እንጅ በአደባባይ ይህን ማቅረቤ አይቀርም ። የጎጥ ፖለቲካ ለማንም አገር ህዝብ አይበጅም። ሊበጅም አይችልም ።ይህው ነው። ይበርቱ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.