ያለ ይመስለኛል የጎደለን ነገር
በታሪክ አውድ ላይ ቆይቶ የሚዘከር
የምድር ልሂቃን ገና ያላገኙት
በምርምራቸው ያልተወያዩበት
ከእህል ከመጠጡ ከምንመገበው
ወይም ከአየሩ እንደሁ ከምንተነፍሰው
የዕድሜ ገደብ ሳይለይ ሁሉን አደንቁሮ
ከፍቅር አብልጦ መርጧል አምባጓሮ
እኛ ስንባላ ዓለም እየሳቀ
ንብረታችን ወድሞ ህዝባችን አለቀ
በደንብ ላስተዋለ ይህ የጤና አይደለም
ቢኖር ነው ጎደሎ ሁሉን የሚያስገርም
ያለ ይመስለኛል የጎደለን ነገር
በታሪክ አውድ ላይ ቆይቶ የሚዘከር
የሰው ልጅ ተራቆ ሰማይ ላይ ሲወጣ
እኛ እንታያለን ራስን በእጃችን መልሰን ስንቀጣ
ይመርመር ደማችን አጥንታችን ጭምር
በአግባቡ ይታወቅ የጎደለን ነገር
ሥነ ልቦናችን አንጎላችን ሳይቀር
ምልክት ቢያሳዩ ለጎደሎው ምስጢር
ያለ ይመስለኛል የጎደለን ነገር
በታሪክ አውድ ላይ ቆይቶ የሚዘከር
ብርሃን ሲመጣ የምናደበዝዝ
ሙቀት መጣ ሲባል የምናቀዘቅዝ
ምን ተውሳክ ቢኖር ነው ተጣብቶን የኖረ
ሁሌ የሚያያጋጨን እያደናበረ
ያለ ይመስለኛል የጎደለን ነገር
በታሪክ አውድ ላይ ቆይቶ የሚዘከር
እስኪ አንዴ ቆም እንበል
ነገር እናስተውል
ጉድለቱን ተረድተን እራስን ለማወቅ
ምንድን ነው ጎደሎው
ከእኔ ጋር የሌለው
በማለት እንጠይቅ
ካልቻልን እናስጠይቅ
ጎደሎ መኖሩ ግልፅ ነው ይታያል
ክብደቱ አመዝኖ ባዶነት ያሳያል
ያለ ይመስለኛል የጎደለን ነገር
በታሪክ አውድ ላይ ቆይቶ የሚዘከር