ደህና ሁን ጨለማ – በላቸው ገላሁን

ደህና ሁን ጨለማ – ደህና ሁን ጥልመት
ከዐባይ ውሃ ማማ – መጣብህ መብራት
ከሰል ክረም ደህና – ጭራሮ እንጨት ችቦ
ሊተካህ ነውና – የኤሌክትሪክ ሽቦ፤
ኩራዝ ሰንብች ደህና ¬– ሻማና ፋኖስ
ፈንጥዢ ኩሽና – በኖ ይጥፋ ጭስ
ግብስብሱ ቅጠል – የኩበት ጥፍጥፍ
አይብላህ ነበልባል – ይብቃ የእሳት ግርፍ፤
አገሬም ተግ በይ – መንደሬም ድመቂ
አሻቅቢ ወደ ላይ – ከሽልብታሽ ንቂ
ተማሪ ነጋዴው – ተደሰት ገበሬ
ሲገፈፍ ጨለማው – ጠሐይ ሲሆን ዛሬ
ዘምሩ አእዋፍ ¬– አራዊት ጨፍሩ
የጥልመት ጊዜ ሲያልፍ – ብሩህ ነው አገሩ።
ያኔ ታዲያ . . .

ያ ሃሳበ ስንኩል – ያ የጨለመበት
ትቶ ወደ ፊትን – የሚጓዝ የዃሊት
ያኔ መብራት ሲሆን – ሲፈካ እንደ ጣሐይ
ሲመለክት ጎኑን – ዙርያ ገባውን ሲያይ
የጦቢያዬን ስፋት – ድንበር የለሽ አጥር
የቀለሟን ውበት – የህዝቦቿን ማማር
በብርሃኑ ግለት – በረጅሙ ጮራ
ከሩቅ ሲመለከት – ሜዳና ተራራ
ምንናልባት ምናልባት – ቀልቡን ይገዛና
ካለፉት ዘመናት ¬– ደዌው ይድንና
እሱባኤ ገብቶ – እፍኝ ጥሬ በልቶ
ከኩነኔው ነጥቶ – ከወገን ተስማምቶ
መሆኑን ተምሮ – የአብራኳ ክፋይ
ባሻው ቦታ ኖሮ – ያለምንም ከልካይ
እንደዚያ ነው መግዘፍ – እንደዚያ ነው መድመቅ
እየኖሩ ማለፍ – እያለፉ መፅደቅ።

በላቸው ገላሁን
ሰኔ ፳፯ ፳፻፲፪ ዓ. ም

ፒትስበርግ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.