…ካዛሬ 21 ዓመታት በፊት፣ ወደ ግብጽ ሀገር ሄጄ ነበር። በዚያም ጉዞዬ፣ የአባይን ዳርቻ ተከትዬ እስከ አሌክሳንድርያ ከተማም ድረስ ዘልቄ የአባይን መጨረሻ እስከ ሜድትራንያን ባሕር ለማየት ችዬ ነበር። የግብጽ ቆይታዬን ስጨርስ፣ በካይሮ ከተማ ላይ ከተነጣለለው የአባይ ወንዝ በአንዱ ዳርቻ ተቀምጨ፣ በቁጭትና በሮሮ ስሜት ውስጥ ሆኜ ይህቺን “እንደምነህ አባይ“ የምትለዋን ግጥም ጫርኩኝ። በወቅቱ ከአንድ በውጭ ሀገር ካገኘሁት ያገሬ ልጅ ጋር እንደማወራው አይነት፣ ከምሬ አባይን ፊት ለፊት እያየሁ፣ “እያወጋሁት” ነበር ግጥሟን የጻፍኩት። (ግጥሟም በዚያን ጊዜ በእጅጉ ታዋቂና ተወዳጅ በነበረችው በጦቢያ መጽሔት ላይ ለንባብ በቅታም ነበር።) አባይ ወጌን ከጠረቅሁለት ከ21 ዓመታት በኋላ ቀልብ ገዝቶ፣ በእናት ሀገሩ ምድር ላይ ተዐምር ሊሰራ ተዘጋጅቷል። እኔም ውሳኔውን በአድናቆት፣ በደስታና በጸጋ ተቀብዬ፣ በማንኛውም ረገድ ከጎኑ ልቆም ቃል ገብቻለሁ። ኢትዮጵያውያን ሁሉም፣ በያሉበት በመተባበር የአባይን ተልዕኮ ከዳር ያደረሱ ዘንድ፣ እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ በአክብሮት ለማሳሰብ ወደድኩ።
…እነሆ ታሪክ ሊሆን የተቃረበው የቆየ ወጋችን ከአባይ ጋር፦
እንደምነህ አባይ?!
ሁሌም እየቆጨኝ፣ ያኗኗርህ ዕጣ፣ የጉዞህ ፍጻሜ፣
ወንድሜ የናቴ ልጅ፣ ልጠይቅህ መጣሁ፣ ወሬህን ቃርሜ፤
እንዴት ነህ ባያሌው? ተስማማህ ወይ ኑሮ?
በሀገረ-ምሥር፣ ከተማ ካይሮ!
ከዚያ ሰላም ምድር፣ ከዚያ ሰላም አምባ፣ ስትደነፋ መጥተህ፣
የመኪናው መዐት፣ የጡሩምባው ጩኸት፣ የሰዎች ትርምስ…
እንዴት ሰላም ሰጠህ?!
እንደምነህ አባይ?!
የዘር ግንዴ ክፋይ።
የናታችንን ሃብት፣ ቅርሷን አግበስብሰህ፣
ፋታ ሳትሰጣት፣ በኃይል ደንፍተህ፣
ሸክምህን ሁሉ፣ ለባዳ አራግፈህ፣ ጸጥ-ለጥ ብለህ፣
ገራም ሆነህ ሳይህ፣ ካይሮ ተኝተህ፣
ባጣሙን ተገረምኩ..!
ለካስ ለዚህ ኖሯል፣ ያ! ሁሉ ችኮላ?
አወይ አባይ ሞኙ፣ የኛው ጉድ ተላላ።
እንደምነህ አባይ? የጣና ባህር ልጅ፣ የኢትዮጵያ ሸጋ፣
በናት ሀገር ምድር ፣ ባያጋጣጥምን ከቶ ባይሳካ፣
እስኪ በሰው ሀገር፣ እስቲ በሰው ምድር፣ ቁጭ ብለን እናውጋ!
…ከጣና ወደ ካርቱም…፣ ከካርቱም.. አስዋን…
ከአስዋን. ካይሮ … ሜ – ድ – ት – ራ – ን – ያ – ን!
ይሄ ሁሉ ጉዞ፣ ይሄ ሁሉ ድካም፣ ኧረ ለምን ይሆን?!
እንደምነህ አባይ? የወንዜ ልጅ ወንዜ፣
ሃሳብ ይዞኝ ጭልጥ… ሳይህ በትካዜ፤
ለዚህ ነበር እንዴ? ያ! ሁሉ ድንፋታ፣
ያ! ሁሉ ሁካታ፤
ግርማህን ተገፈህ፣
እርቃንህን ቀርተህ፣
ለማሳመር ኖሯል? የበረሃ ገላ፣
አንተ ሞኝ! ተላላ!
ምንስ አግኝተህ ነው? እንዲያው አዲስ መላ
ሰውን ያስከተልከው፣ በስደት ከኋላ፤
አህዛቡ ሁሉ አንተን ተከትሎ፣
ወጣ እኮ ኮብልሎ፤ እናት ምድሩን ጥሎ፤
እንደምነህ አባይ? ያገር ልጅ ናፍቆቴ፣
አተኩሬ ሳይህ፣ ራደ ሰውነቴ፤
እንዴት አምሮብሃል? በጀርባህ ተዘርረህ፣
መርከብ፣ ጀልባ… አሳፍረህ፣
ድልድይ አሰርተህ…፣
ልምላሜ ውበት፣ በጸዳል ተከበህ፣
የእንቁ ቁልፍ፣ ክቡር፣ የግብጽ ህይወት መፍቻ!
“ኮርኒሽ ኤል-ኒል”- ያባይ ወንዝ ዳርቻ፤
እንደምነህ አባይ?!
“የሀገር ሃብት የባዕድ ሲሳይ”፤
እስኪ እንነጋገር፣ አታውቀኝም እንዴ..?
ጥቁር ያገርህ ልጅ፣ አኔም ስደተኛ፣
በናፍቆት፣ በጸጸት…፣ እንቅልፍ እማልተኛ፣
ወጥቼ የቀረሁ፣ (እንዳንተው) የሌሎች አገልጋይ፣
ጉልበቴን… እምሽጥ፣ ላባዕዳን ሲሳይ፤
አንተን ልውቀስ እንጂ ግብራችን አንድ ነው፤
የራሳችን አሮ፣ ሌላ እምናማስል፣
ለለምጽ በሽታችን፣ እማንፈልግ ጸበል፣
ራሳችንን ልንሆን፣ ያልቻልን ከርታታ፣
የተጸናወተን፣ የመምሰል በሽታ፤
እንደምነህ አባይ?
የዘር ግንዴ ክፋይ!
አለን እኮ ምስጢር፣እኔና አንተ የጋራ፣ እምንካፈለው፣
ትውልድ ያስቆጠረ፣ ረቂቅ ማተብ ክታብ፣ ዘመን የሸፈነው፤
በየልባችን ውስጥ፣ እስኪ እናስብበት፣
ከእለታት አንድ ቀን እግዚአብሔር ያለ ዕለት፣
በቃ-ብሎ አክትሞ፣ የስደት ኑሯችን ፣
አኔም ተመልሼ፣ አንተም ቤትህ ረግተህ፣
“ኢንሽ አላህ”! “ኢንሽ አላህ”!
እስኪዚያው ድረስ ግን…
ደህና ሁን! ደህና እንሁን! አሜን!
ጌታቸው አበራ
(ካይሮ-ግብጽ “ኮርኒሽ ኤል-ኒል”- ከአባይ ወንዝ ዳርቻ)
ጥቅምት 1991 ዓ/ም
(ኦክቶበር 1998)