ከይሲነት በመልካሙ መደመር ላይ እያሴረ ነው። – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

መልካም ነገሮችን መደመር፣ኩንን ምግብሮችን መቀነሥ ከሆነ የጠ/ሚ ዶክተር አብይ “የመደመር” ፍልሥፍና
ለማደግ፣ለመለወጥ እና ለመበልፀግ የሚፈልግ፣ግለሰብ፣ቡድን እና በአጠቃላይም የብልፅግና ጥማት ያላቸው ሁሉ፣
ሃሳቡን በብርቱ ይፈልጉታል።በዚህ ብርቱ  ፍላጎታቸውም  መሠለኝ ፣ይህ የመደመር ሃሳብ ከጠ/ሚሩ እንደቀረበ ጥቂት
የማይባሉ ዜጎች  ከጠቅላይ ማኒሥቴሩ ጋር ተደምሬያለሁ። በማለት ሃሳባቸውን በከፍተኛ የሀገር መውደድ ሥሜት
የገለፁት።
መቼም ጠቅላይ ሚኒሰትር  አብይ ከሁለት ዓመት በፊት ወደሥልጣን እንደመጡ የነበረውን ደጋፍ፣አድናቆትና ሙገሳ
አረሱትም።እንዴት ይረሳል?
የመደመርን ሃሳብ ከቅንነት፣ከመልካምነት፣ከእድገት ከብልፅግና  እና ኢትዮጵያን እንጂ ግለሰቦችን ካለማንገሥ
አኳያ አይተው ነው ዜጎች እንደ አንድ ሰው በማሰብ ያኔ ግልብጥ ብለው በመውጣት፣ከጫፍ እሥከ ጫፍ እኔም
ተደምሬለሁ !በማለት  የጠ/ሚ ዶ/ር አብይን  ሥም በሥሜት ተሟልተው ደጋግመው በመጥራት ለዓላማቸው ሥኬት
ከጎናቸው እንደሚቆሙ ዜጎች ያረጋጉጡት።
በአሜሪካ እና በጀርመን የሚኖሩትም ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉላቸውን አቀባበልና ያሳዮቸውን በሥሜት የተሞላ
ፍቅርን ቪዲዮውን በማየት ዛሬም ማሥታወሥ ይቻላል ።
እኔም ተደምሬለሁ በማለት ኢትዮጵያዊው ኢትዮጵያዊነቱን እና ሰው መሆኑን  አውቆ ከጎናቸው መሰለፉን
ያረጋገጠው ፣ጠቅላይ ሚኒሥትሩ ፣የሀገሪቱን ከፍተኛውን ሥልጣን መጨበጣቸውን አሥመልክተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ባሰሙት
ንግግር ፣ድህነትን ኖረውበት የሚያቁና ኢትዮጵያ በደሃ ሥም ሲነገድባት እንጂ ፣ደሃ በቀን ሦሥት ጊዜ ሊበላ
ይቅርና በተጨባጭ  በቀን አንዴ እንኳን ሊመገብ ያልቻለባት ሀገር መሆኗ የሚቆጫቸው እንደሆነ   በንግግራቸው
በማረጋገጣቸው  ነው።
በዜጎች አኗኗር ውሥጥም ሁሉም  መሠረታዊ ፍላጎታቸው   የተሟላላቸው ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውን የተረዱ ና
ሌብነትን የሚጠየፉ ሆነው በመገኘታቸው ነው ህዝብ ከእሳቸው ጋር “ተደምሬለሁ”ያለው።
በውጫ እና በሀገር ውሥጥም ካሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች  ጋር ልዩነታቸው እንደተጠበቀ አብሮ ለመሥራት  ዝግጁ
መሆናቸው፤ እንዲሁም፣ሥንኖር ኢትዮጵያዊ ሥንሞትም ከአፈሯ ጋር ተዋህደን ኢትዮጵያ እንሆናለን፣በማለት ፍፁም ታማኝ
የኢትዮጵያ ልጅ መሆናቸውን በማሳወቃቸው እና የንግግር መደምደሚያቸውንም ሁሉን ቻይ ለሆነው ለፍጥረት ዓምላክ
ምሥጋና በማቅረብ የሚቋጩ እምነት ያላቸው መሪ በመሆናቸው  ነወ “ተደምሬለሁ” በማለት ህዝብ በነቂሥ ወጥቶ
የደገፋቸው።
እነዚህን እውነቶችን በመገንዘብ ነው፣ህዝብ ነገ ቁሥሌን ያክሙልኛል በማለት  አበጀህ!ኢትዮጵያዊው ሙሴ ሲል
በማወደሥ ፤ከአንተ በፊት እኛ እንሰዋለን በማለት በመሥቀል አደባባይ ፍቅሩን የገለጠላቸው ።
እርግጥ ነው፣  ጠ/ሚ አብይ አህመድ(ዶ/ር)  ሌብነትን ከተጠየፉና ሌቦችን የማይታገሱ ከሆኑ ደግሞ ፣ይህ
ህዝብ የበይ ተመልካችነቱ ያከትማል።እናም ህዝብ ተሥፋን ሰንቆ   ታላቅ ደጋፉን ፣ክብርና አድናቆቱን ሳይሰስት
መሥጠቱም ለዚህ ነው።ይሁን እንጂ አንድ እጅ ብቻውን ማጨብጨብ እንደማይችል ህዝብ የተገነዘበው ከአንድ አመት
በኋላ ነው።
እንደዚህ ፀሐፊ የመጀመሪያ የአድናቆት ፅሑፍ ሃሳብ (በጎልጉል ድረ ገፅ የፃፈውን ያሥታውሷል) ጠቅላዩ አዲሥ
ፓርቲ እሥካላቋቋሙ ድረሥ ኢህአዴግን አሁን ባለው አቋሙ ይዘው የኢትዮጵያን ህዝብ ድምፅ  ለማግኘት እንደማይችሉ
እና  አባላቶቻቸውን   በንሥሐ አጥምቀው አዲሥ ፖርቲ  ማቋቋም እንዳለባቸው   ምክረ ሃሳብ መለገሤን
አሥታውሳለሁ።
እናም ዓባላቶቻቸው ምን ያህል በንሥሐ ፀበል መጠመቃቸውን ባላውቅም፣አብዮት ብሎ ዴሞክራሲን ከህሊናቸው
በማሶገድ   በአዲሥ መልክ “ብልፅግና” የተሰኘ ፓርቲ መሥርተዋል።
እናም በመጪው ብሔራዊ ሀገር አቀፍ ምርጫ ፣ይህንን    የሥምንት ክልሎች ጣምራ  ፖርቲ የሆነውን ብልፅግና
የተሰኘ ፓርቲ  አሸናፊ አድርገው  በምርጫ የሁሉም ክልሎች ጠ/ሚ በመሆን ህዝብን ወደብልፅግና የሚያሻግር ተጨባጭ
ለውጥ እሥካላመጡ ጊዜ  ድረሥ ፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያደርጉት ጥረት በፈተና የተሞላ ይሆናል
ብሎ ይህ ፀሐፊ ያምናል።ምክንያቱም በመደመር ፍልሥፍናቸው ፍየል ከነብር፤ድመት ከአይጥ፤ዶሮ ከሸለምጥማጥ
ወዘተ።ሊደመር ይችላል ብለው ሥለማያሥቡና፣አንድ ዓይነት ፣አሥተሳሰብ ና የጋራ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ና
ፓርቲዎች በመቀናጀት ፣የተለየ ሃሳብ ያላቸውም ለሀገሪቱ ህዝብ የሚጠቅም ተደማሪ ሃሳብ በማዋጣት፣ ባለፈው የሀገር
መልካም ሥራ ላይ ተንተርሰው ፣ታላቅ ሥኬት ሊያሥመዘግቡ ይችላሉ፣የሚል “መልካም የመደመር” ሃሳብ ሥላላቸው ነው።
ይሁን እንጂ ገና ከወዲሁ ከፓርቲያቸው ያፈነገጡ “ኢህአዴግ ወይም ሞት” ያሉ ፣ከቀድሞው ኢህአዴግ መታረም ያለበት
አሥተሳሰብ  ጋራ የተጣበቁት፣አብዛኛዎቹ የሚያምኑት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ በመሆኑ ፤እነዚህኞቹ ደግሞ የሚከተሉት
በአብዮት የተቀባባ ዴሞክራሲ ከመሆኑም ባሻገር  ፣ከአብዮታዊነት ይልቅ በጥቅመኝነት የተደመሩ አንድ ዓይነት
አስተሳሰብ ያላቸው በመሆናቸው እነዚህ ከጎሰኞች፣ከወንዘኞች፣ከቋንቀኞች ጋር ተደምረው፣ ፣”የመልካሙን  መደመር
ፍልሥፍና” ሥኬት ሊያደናቅፉ ይችላሉ።
በጥቅም የተቧደኑ ፣ የጋራ ህልምና ሃሳብ ያላቸው፣ ቡድኖች  “በህዝብ ሥም ፣ያለአግባብ ያከማቸነው ሀብት
ነገ በብልፅግና ፓርቲ አደጋ ላይ ይወድቃል።” ብለው በማሰብ ነው ለብቻቸው  አብዮታዊነትን በመምረጥ በህዝብ ሥም
የተሸጎጡት ።ቆመንልሃል፣እና በለፅግሃለን እያሉ “ዶሮ ማታ “ የሚሉት ህዝብ ግን የራሳቸውን ብልፅግና ነው እንጂ
የእርሱን  ብልፅግና ከቶም እንደማይሹ ያውቃል።
የመላው ሀገርን እና የህዝብን ብልፅግና የሚሹ ፣ግለሰቦች፣ቡድኖች ና ፓርቲዎች ሃሳባቸው ሊደመር እና ህዝቡ
ራሱ፣ ለዓላማቸው ትልቅ ጉልበት ሊሆናቸው  እንደሚችል ይታወቃል።ይህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት
ውሥጥ ግን እብዛም አይታይም።ምክንያቱም ብዙዎቹ የፓርቲ አባላቶች ለራሳቸው ከርሥ የሚውል   ዳቦ ፍለጋ እንጂ
ለፓርቲው ራእይ፣ዓላማ፣ግብና ሥኬት አያሥቡም።ይህንንም ትላንት “የኢህአዴግ ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው።”
በማለት የዓመታት ሥንቃቸውን ቶሎ፣ቶሎ በማከማቸት ሲከብሩ  አሥተውለናል።
የኢህአዴግንም ሆነ የሌሎቹን ፓርቲዎች አደረጃጀት ብንፈትሽ በመጠን ይለያይ እንጂ በጥቅም ንቅዘት
የተሞላ፣በወንዝ ልጅ የተገነባ ሆኖ እናገኘዋለን።አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ሰውን ሳይሆን ቋንቋን ሲደምሩና ሲቀንሱ ነው
የሚሥተዋሉት።
ዛሬ በኢትዮጵያ አብዛኽኛዎቹ ሰዎች   የፓለቲካ ፓርቲ የሚያቋቁሙት እንወክለዋለን ለሚሉት ህዝብ ብልፅግና
ለማምጣት አይደለም። ወይም ደግሞ የመንግሥትን ሥልጣን በምርጫ ከያዝን ኢትዮጵያና ህዝቧን በተሰጠን የሥልጣን
ገደብ ውሥጥ በብልፅግና ጎዳና በፍጥነት እንድትራመድ የሚያበቃ ከሌሎች ፓርቲዎች የተሻለ ፖሊሲዎችን በተጨባጭ
አርቅቀናል እንካችሁ።ፍረዱን ።  በማለት ህዝብን አሳምነው አይደለም። በዙዎቹ የአንድ ቋንቋን ተናጋሪ የሆኑ
ዜጎች   ምንጅላቶች  ጭቆና እና በታሪክ አጋጣሚ ግለሰቦች የፈፀሙባቸውን  ግፍ፣ ህዝብ እንደፈፀመ አድርገው
በመተረክ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብን ከሌላው ቋንቋ ተናጋሪ  ህዝብ ጋር በሐሰተኛ ትርክት እንዲቃቃር
በማድረግ፣ብዙም  ሳይደክሙ ፣በጥላቻ ና በማናከሥ ፓለቲካ ተሰሚነት አግኝተው ባልተራዘመ ጊዜ የተትረፈረፈ እንጀራ
በህዝብ ሥም  ለማግኘት ነው፣ ሌት ና ቀን የሚጥሩት። እነዚህ የኢትዮጵያ የዜጎቿ ጠላቶች በመሆናቸው ምንጊዜም
ግጭት እንዲኖር የሚፈልጉ ፣በህዝቧች እርሥ በእርሥ መተላለቅ  ለማትረፍ እና የቅንጦት ኑሯቸው እንዳይቋረጥ  ያለ
እንቅልፍ የሚዳክሩ ናቸው።ይህንን እውነት ደግሞ   የባነነው እና ያለሰው ምርኩዝ እየተራመደ ያለው ወጣት በሚገባ
ይገነዘባል።
ይህ “ የባነነ ነቄ ተውልድ” ፣ በወንዝ እና በጎሳ ጓደኝነት ተቧድነው ፣ህዝብን የሚያማልል ሃሳብ በየፈርጁ
የሚሰብኩ ካድሬዎችን  ከቀበሌ ጀምሮ በመመልመል አሪፍ የፖለቲካ ተዋናያንን  በየዘርፉ በማፍራት፣ለህዝብ ቀጣይነት
ያለው ልብ አንጠልጣይ ፖለቲካዊ ድራማ በአሥፈላጊ ጊዜ ሁሉ በማሣየት  ፣ በህዝብ ሥም የበዛ ዳቦ ለማግኘት
የሚጥሩትን በመገረም እያሥተዋላቸው ነው። የሚያራምዱትም ፖለቲካ የሴሬ እና የጠልፎ ማሥወገድ ፓለቲካ እንደሆነም
በሚገባ ተረድቷል።
እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ለኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ብልፅግና አያሥቡም።እኔ ለዚህና
ለዛ ቋንቋ ተናጋሪ ምን አገባኝ?ለምን “አራት እግሩን አይበላም” ባዮች ይበዙባቸዋል።
ሥለሆነም   መልካም ነገሮች የላቸውምና እንዴት በመልካም ነገር ላይ ሊደመሩ ይችላሉ? የሚደመሩት እኳ
መልካም፣የፓለቲካ እና የፈጠራ  ሃሳቧች፣ ናቸው።የሚደመሩት እኮ መልካሞቹ እሴቶቻችን ናቸው።የሚደመሩት እኮ
መልካም  ባህሎች እና ማህበራዊ ክልከላዎቻችን ናቸው።የሚደመሩት እኳ ቀና አመለካከቶቻችን እና አሥተሳሰቧቻችን
ናቸው።የሚደመሩት እኳ የተፈጥሮ እና የግል ሀብቶቻችን እኳ ናቸው።… እነዚህ ሁሉ በዜጋው የታመነባቸው ቅን
እና መልካም ሃሳቧች ሲደመሩ ብቻ ነው በአንድ ሀገር ውሥጥ ተጨባጭ የሀገር ታላቅነት የሚፈጠረው።
በአንድ ሀገር ላይ ትልቅ ለውጥ ሊፈጠር የሚችለውና ሀገር ታላቅ የምትሆነው፣መልካም ነገሮች፣ ሲደመሩ እና
ከይሲ ሃሳቧችና ተግባሮች ሲወገዱ ነው።
ከይሲ ሃሳብ እና ተግባር ፣ ጠቃሚና ገንቢ ሃሳቦችን እና የእድገት መሠላል የሆኑ ጅምር ድርጊቶችን  መልካም
ሥራዎችን ሁሉ የማያጠፋ ነው።መልካሙ  መደመር አውዳሚ እና ፀረ እድገት ከይሲ ሃሳቦችን አይደምርም።፣ፀረ
ፍትህ፣ፀረ፣  ልማት ኃይሎችንም አያካትትም።መልካሙ መደመር ለእድገታችን የሚጠቅም ነውና ፣ሁሌም ሸኩቻ
ከማይጠፋበት በአብዮት ከተሞላ  ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ይልቅ፣ለሥራ፣ለእድገት፣ለልማት፣ለፍትህ፣ለእኩልነት፣ለዜጎች
ሁሉ ነፃነት፣ለዴሞክራሲ ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚበጅ ሃሳብን ሁሉ ደምሮ  የሚጎዝ በመሆኑ በዚህ መንገድ
የለውጥ ኃይሉ ቢጓዝ ይበጀናል በማለት ነው ፣ድጋፉን ህዝብ ከጅምሩ የሰጠው።
ዛሬ ግን ከይሲነት በመልካሙ መደመር ላይ እያሴረ ነው።ይህንን በመገንዘብ የኢትዮጵያን የሀገር መከላከያ
ሠራዊት  ፣ምንጊዜም ነቅተህ እንደሥምህ ሀገርህን ኢትዮጵያን ጠብቅ፣ለሀገርህ ክብር፣ለህዝቧ ነፃነት ፣ደህንነትና
ሠላም ትላንት፣በክብር ተሠውተሃል።ደምተሃል።አካልህን ገብረሃል።ዛሬም የዚህ ህዝብ አለኝታ አንተ ነህና ፣ሥልጣንን
በኃይል ለመያዝ በሚያሴሩት ላይ ሁሉ፣የሀገርህን ሉአለዊነት ለማሥደፈር እና ህዝቧን በባርነት ለማሥገዛት
የሚጥሩትን ሁሉ ችላ አትበል።በእኔም ካቢኔ ውሥጥ የሀገርን ክብር እና የህዝቧን አንድነት የሚሸረሽር ተግባር
ካየህ አትታገሥ ፣አንተ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ነህና!በማንም ፖርቲ የውሥጥ መተዳደሪያ አትገዛም።የምትገዛው
ለህገመንግሥቱ እና ለራሥህ ፕሮፌሽን ነውና! በማለት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሥቴር አብይ አህመድ ለሠራዊቱ ጠቃሚ
መልዕክት አሥተላልፈዋል።
እንግዲህ ጠቅላዩ፣ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ተገቢ መልዕክት ሲያሥተላልፉ፣ በሙሥና የተወሳሰበውን የፊደራልም
ሆነ የክልል ተቋም አሥተውለው ይመሥለኛል።ይህ ህዝብ እሥከመቼ እንደሚነገድበት አይገባኝም ። ፍትህ ለሁሉም መቼ
እኩል እንደምትሆንም ሳሥብ ይጨቀኛል።በሀገሬ ህግ የሁሉም ሰው የበላይ ሆኖ ሁሉም ሰው የህግ ተገዢ የሚሆንበትን
ቀን ለማየት እናፍቃለሁ።
ማጠቃለያ
እንግዳህ መደመር፣ማከማቸት፣መሠብሰብ፣ማካበት ከሆነ ትርጉሙ፣የምታካብተው ምንድነው?የምታከማቸው
ምንድነው?የምትሰበሥበውሥ ምንድነው?ይህን ጥያቄ በወጉ አጢኖ  መመለሥ  የሚገባ ይመሥለኛል ።
ይሆ ብቻ አይደለም ጥያቄው ።የምትደምረውን በውል ታውቃለህ ወይ?የምትደምረውን የሚቀንሥ፣የሚያጠፋ ና
የሚያወድመውንሥ እንዴት እያሥተናገድከው ነው?  ከአጥፊው እጥፍሥ ዓልሚ ወይም ደማሪ አፍርተሃል ወይ?የወቅቱ
ጥያቄ  ይህ ነው ?
ዛሬ መለሥ ብለን የወቅቱን የዓለምን እና የራሳችንን ሀገር  ነበራዊ እውነት ማየት ያሥፈልገናል።እየኖርን
ያለነው ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ባሉ የቆዳ ማዋደድ ትርክቶችና የነፃ አውጪ ሃሳቧች ነው ፣ወይሥ በ21 ኛው ክ/ዘ
የአብሮነት ቱሩፋት?በጋራ የመበልፀግ ራእይ ?ወይሥ ዛሬም ያለነው  በሌብነት፣”በአዛኝ ቅቤ አንጓች
ፓለቲከኝነት…?”
እውን ዛሬም አዛኝ ቅቤ አንጓቾችን እያቆላጰላጠሥን ነው? ወይሥ ጉርጥ አደፈጠም ዘለለ ያው ጉርጥ ነው እያለን
ነው?እንዳህ ብለን ሥናበቃሥ የህግ የበላይነትን አሥከብረናል ወይ?
እሥቲ እኛ የለውጥ ሃይሎች ነን  ያልነው ቆም ብለን ራሳችንን እንገምግም።እንጠይቅ።እንፈትሽ።እንወቅ።እኛ
ማነን? በመልካም ነገር መደመር ውሥጥ፣ ትላንት ተደምረናልን? ወይሥ።መደመር የምንፈልገው መጥፎ ነገሮችን ነውን
ማለትም ጎሰኝነትን፣ዘረኝነትን፣የወንዝ ልጅነትን፣መንደርተኝነትን፣ቆዳ ማዋደድን፣ሆዳምነትን፣ሥግብግብነትና
ጨካኝነትን፣ግብዝነትናት ትምክህተኛነትን ፣ሌብነትና ዘረፋን ወዘተ። ከሆነ እነዚህ የሚያወድሙን እንጂ የሚያለሙን
እንዳልሆኑ ከወዲሁ መገንዘብ አለብን።
ከዚህ እውነት አነፃርም መንግሥት እንደመንግሥት፣የህግ የበላይነት እንጂ በህግ ላይ የበላይ የሆነ ሥውር
የግለሰብ መንግሥት እንዳይኖር ለማድረግ እና የህዝብን ሠላምና ደህንነት የሀገሪቱን አንድነት ለማሥጠበቅ  ሲል
ሳይዘገይ ጠንካራ እርምጃ ካልወሰደ ከተደማሪው ይልቅ ተቀናሹ ህዝብ እንደሚበዛ እና ሀገሪቲ ተመልሳ ወደግጭት
አዙሪት ውሥጥ ልትገባ እንደምትችል ከወዲሁ ማሰብ ይጠበቅበታል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አባይን እነማን መቼ ይገድቡት?

1 Comment

  1. 27 አመታት የደፈረሰና የጨቀየን ወንዝ ለማጥራት የተረጋጉ ብዙ አመታት ይፈልጋሉ:: ህውሀት ሀገር በትኖ ዘርፎ ወደ ሞት ጎዳና ላይ ይገኛል:: ለማስተካከል ብዙ ጊዜ ይፈልጋል

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.