ዳግማዊ ጉዱ ካሣ ([email protected])
ሁለት መሠረታዊ ቁም ነገሮችን ላነሣ ነው ከግላዊ የወሸባ (ኳራንታይን) ሥፍራየ ብቅ ያልኩት – እንዲያውም ሦስት ይሁኑልኝ፡፡ እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼና ውድ አንባቢዎች፡፡
ከቦሌ አካባቢ ስለሰማሁት አስደንጋጭ መረጃ ልንገራችሁ፡፡ የሚመለከተው አካልም የእርምት እርምጃ እንዲወስድ በዚህ አጋጣሚ ላስታውስ፡፡ ማንኛውም ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር የሚገባ ሰው ለ14 ቀናት ተገልሎ በህክምና ክትትል እንደሚቆይ በመንግሥት ታውጇል፡፡ ይህ ህግ ደግሞ ማንኛውንም ዜጋ ይጨምራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በጣም ግልጽ ነው፡፡ በሽታው ማንንም ከማንም እንዳለመለየቱና ሁሉንም እንደማጥቃቱ የመከላከል እርምጃውም ሁሉንም ማካተት ይኖርበታልና አንዱን ከአንዱ እየመረጥን አድልዖ ብናደርግ በአንገታችን ላይ ገመድ መጠምጠም ነው፡፡
የአየር መንገድ ሠራተኞች በረራ አድርገው ሲመለሱ በቀጥታ ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱ ነው ከታማኝ የመረጃ ምንጭ የሰማሁት፡፡ ይህ ለምን ይደረጋል? እነዚህ ሰዎች በቫይረሱ ቢያዙ ቤተሰባቸውንና ጓደኞቻቸውን ይበክላሉ፤ ቤተሰባቸው ቢበከል አካባቢያቸውም ይበከላል፡፡ ሥሌቱ ቀላል ነው፡፡ ይህ ነገር ታጥቦ ጭቃ እንደማለት ነው፡፡ በአንዱ አቅጣጫ ለማገድ እየሞከሩ በሌላ አቅጣጫ እንዲዛመት የመፍቀድ ያህል ነው፤ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ገንዘብ ተፈልጎ ጤንነትም ተፈልጎ አይሆንም፡፡ አንዱን መምረጥ ነው፡፡ “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” ነው ነገሩ፡፡ በእስካሁኑ ሁኔታ አንድ ሦስት ያህል ሆስተሶች በቫይረሱ እንደተያዙ ይነገራልና ይታሰብበት፡፡ ቅጥ ያጣ የገንዘብ ፍቅር የሚያስከትለው ችግር ካልታሰበበት መዘዙ ለነተወልደም መትረፉ አይቀርም፡፡
ስለሆነም አየር መንገዱ ባለው ሆቴል ውስጥ ለበረራ የሚልካቸውን ሠራተኞች ለተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ማቆየት ይኖርበታል እንጂ ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ማድረግ አይገባውም፡፡
ሌላው የአደባባይ ምሥጢር የዶ/ር አቢይ መንግሥት የዓለምና በተለይም የኢትዮጵያውያን የትኩረት አቅጣጫና ወቅታዊ ጭንቀት ኮሮና ላይ መሆኑን ከመገንዘብ አኳያ ይመስላል የአማራውን አካባቢ ለተጨማሪ ጭንቀት ዳርጎታል፡፡ ይህ ፋኖን ምክንያት በማድረግ ክልሉን የጦርነት ቀጣና የማድረግ ወቅትን ያልጠበቀ ድርጊት ዓላማው ምንም ይሁን ምን መጨረሻው ግን አያምርም፡፡
ዛሬ ወቅቱ የጸሎትና የምህላ ነው፡፡ ዓለማችን አይታው በማታውቀው ወረርሽኝ በአራቱም አቅጣጫ ተወጥራለች፡፡ ጭንቀታችን “ይህ ወረርሽኝ ይጨርሰናል ወይንስ በቀላሉ ጎሻሸሞ ይተወናል?” የሚል እንጂ ስለወደፊት ዕቅዶች በሃሳብም ይሁን በግብር የምንዋትትበት አይደለም፡፡ በዚህ ወረርሽኝ ሰበብም የፖለቲካና የግል ፍላጎቶቻችንን ለማሣካት መዳከር አይጠበቅብንም፡፡ አንዳንዴ አእምሯችንን በትክክል ብናሠራው ካላስፈላጊ ትዝብት እንድናለን፡፡ ሰው እንሁን፡፡
በክረምት ወቅት ዐይጥና እባብ ላይነካኩ በደመ ነፍስ ተስማምተው ክፉውን ጊዜ በሰላም ያሳልፋሉ ይባላል፡፡ ክፉ ዘመን ሲመጣ በነፍስ የሚፈላለጉ ባላንጣ ወገኖች ጊዜያዊ የተኩስ አቁም አድርገው የጭንቅ ቀንን ይዘልቃሉ፡፡ የአማራ ጠላቶች ግን ይህን አስከፊ ወቅት እንኳን ሊታገሱ የቻሉ አይመስሉም፡፡ የአማራ መኖሪያ ብለው የፈረጇቸውን ሥፍራዎች ለማተራመስ ይህን ወቅት መርጠዋል፡፡ ይህም የሚጠቁመው አማራው ዕንቅልፍ የማይወስዳቸው ጠላቶች ያሉት መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እንኳን ካላዘኑለት መቼ እንደሚራሩለት መረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡
እርግጥ ነው – በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ መጥፎ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል፡፡ በፋኖ ስም ወንጀል የሚሠሩ ዋልጌዎች አይኖሩም አይባልም፡፡ ግን ግን ይህን መጥፎ ወቅት እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ “ሰሊጥ ውስጥ የተገኘሽ መጭ አብረሽ ተወቀጭ” እንዲሉ የአማራን ደጀን ፋኖን ለማጥፋት መሞከር የዞረ ድምሩ ከባድ ነው፡፡
ሦስተኛው ነገር አሁን በዚህ ወቅት ሳይቀር አዲስ አበባ አካባቢ አማራን ለማፈናቀል የሚደረገው የዕብድ አክራሪ ኦሮሞ ባለሥልጣናት ተግባር ነው፡፡ በአሥራት ቴሌቪዥን እንደተከታተልኩት እነኚህ ተረኛ ነን ባዮች አማሮችን እያሳደዱ ቤታቸውን በማፈርስና ንብረታቸውን በማቃጠል ለወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆኑ እያደረጓቸው ነው – ሊያውም በኦሮምኛ እየዘፈኑ “እዚህ አካባቢ አማራ መጥፋት አለበት!” በሚል መፈክር ታጅበው፡፡ ይህንን ድርጊት የአቢይ መንግሥት አያውቅም ማለት አንችልም፡፡ በሌላም ወገን የአቢይ ታዛዦች በሚያስተዳድሩት የአማራው አካባቢም በአሁኑ ወቅት ቤት እያፈረሱ አማሮችን ለጎዳና ሕይወት መዳረጋቸውንም እየሰማን ነው – ማፈናቀሉና ቤት ፈረሳው በዚያው በአማራው ክልልም መከናወኑን ልብ ይሏል፡፡ ሰው የሆነ ሰው በዚህን ወቅት እንደዚህ ያለ ነገር አያደርግም፡፡ አማራን የማሳደድና የማጥፋት ዘመቻ በወያኔ ታቅዶ ላለፉት 30 ዓመታት ጫፍ በደረሰ መልኩ ተግባራዊ ቢደረግም አሁንም በባሰ ሁኔታ በአዲሶቹ ጌቶች አማራው ስቃዩን እየበላ ነው፡፡ ለበጎ ነው! መከራን ያላስቀደመ ድል የለም፡፡
ስለአማራነት ትንሣኤና ተዛማጅ ጉዳዮች አሁን ጭንቅ ላይ ሆነን ምንም ማለት አልፈልግም፡፡ ግን በተስፋ ልለያቸሁ ወደድኩ፡- ይህ ወረርሽኝ ያደረገውን አድርጎ ያልፋል፤ ሁሉም ወገን ደግሞ የሥራውን ያገኛል፤ ተንጋለህ የተፋኸው ካንተው ውጪ ወደየትም አይሄድም፡፡ አማራው ጋር ጠብ ያላችሁ ወገኖች ግን ወደ ቀልባችሁ ተመለሱ፡፡ ገድላቸሁ የማትጨርሱትን ኃይል ለመግደል መሞከር ጣጣው ብዙ ነውና ለጊዜው ኮሮና ላይ አተኩሩ፤ እናተኩር፡፡ ደግሞም በአንድ ወገን ጸሎት በአንድ ወገን ጦርነት ትራጂ-ኮሜዲ ዓይነት ቧልታይ ድንቃይ የፋርስ ትያትር ነውና በመከራ ወቅት ልታስቁን አትዳዱ፡፡ ያዋጣል ካላችሁም መንገዳችሁን ጨርቅ ያድርጋላችሁ – የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም፡፡ እኔ ግን ተናግሬያለሁ – የተናገርኩትም ለማንኛውም አማራ ጠል አክራሪ እንጂ ለእገሌ ወይ ለእገሊት እንዳልሆነ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ መልካም የhibernation ዘመን! ዘመነ aestivation ደግሞ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ያኔ ግን ብዙ ግሳንግስ ተወግዶ … ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል… ለምንደርስ ብዙ መልካም ዜና ነበረኝ… ግዴለም … ብቻ ያድርሰንማ፡፡
የነጃዋርን ትዕቢት፣ የነበቀለ ገርባን ዕብሪት፣ የነዶ/ር ገመቹን ትምክህት፣ የነፕሮፌ. መረራን እስስታዊ ባሕርይ፣ የነዳውድ ኢብሣን ጎጠኝነት … የነእስራኤል ዳንሣን “ተዓምር ሠሪነት”፣ የነ “ንግሥተ ነገሥታት እህተ ማርያም” ስንዱንና መሰል ሥራ ፈት የሰይጣን ባርያዎችን አጋንንታዊ መተት አፈር ደቼ አብልቶ ሁሉንም በየጓዳው የወተፈና ዶሮ ጠባቂ ያደረገ አምላክ ክብሩ ይስፋ፡፡ እርሱ ጠፍጥፎ የሠራው ይመስል “ከክልሌ ውጡልኝ!” ይል የነበረን ጎጠኛ ሁሉ ደጁ ሳይቀር እንዲናፍቀው ያደረገ አምላክ ምሥጋና ይድረሰው – (ኮሮናዬም ልጅ ይውጣለት!)፡፡ ደግሞም ገና ምኑ ተነካና! ከዚህች 4 በመቶ እንኳን የመግደል አቅም ከሌላት ትንሽዬ ቁንጥጫ ወደ 80 እና ከዚያ በላይ የመግደል ኃይል ወዳለው መቅሰፍት እንሸጋገራለን – የላይቴ ላይ በል ያለኝን አልኩ፡፡ መትረፊያው አሁን ለኮሮና የሚነገረውና በተወሰነ ደረጃም እውነት መሆኑ ሊካድ የማይገባው ውኃና ሣሙና እና አካላዊና ማኅበራዊ መራራቅ ብቻ እንዳይመስልህ፡፡ ንስሃና ጸጸት ብቻ ነው፡፡ ያ ከሰው ልጅ ሥልጣኔ በላይ የሆነ ቀን ጅማሬው በጉልኅ እየታዬ ነው፡፡… ልብንና ኩላሊትን የሚቀይር የዘመናችን ሥልጣኔ በቤተ ሙከራ ራሱ የፈጠረውን ተራ ጉንፋን ማከም አልቻለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም – ለሌሎች የፈጠረው ወረርሽኝ በራሱ ጓዳ ግዘፍ ነስቶ ሽዎችን በየቀኑ ሲያጭድ ፈዝዞ ከማየት ውጪ አንድም አልፈየደም – ቀን አይጥልም አንበል፤ ይጥላል፡፡ አዎ፣ የማይታመነው ትያትር መሰል የዓለም ፍጻሜ በሙሉ ግርማ ሞገሱ ጀምሯል!!