መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓም(27-03-2020)
ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ በተከሰተ አደጋ የሰው ልጅ ጭንቅና ብርክ ውስጥ ሲገባ የሚይዝ የሚጨብጠውን ያጣና ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል።ሽብርና መደናገጥ ይከሰታል።ተያይዞም ከገባበት ማጥ ውስጥ ለመውጣት የማይገለብጠው ድንጋይ፣የማያስሰው ምክርና እርዳታ አይኖርም።ለመድሃኒት ፈጠራ ምክንያቱ የበሽታ መከሰት እንደሆነ ሁሉ ለተለያዩ ችግሮችም እንዲሁ ብልሃትና መፍትሔ የሚታሰበው ችግር ሲከሰት ነው።የሰው ልጅ ጠንካራና ደካማ፣ደግና ክፉ መልኩ ጎልቶ የሚታዬውም በዚህ ወቅት ነው።ወዳጅና ጠላትን ለማወቅ ክፉ ቀን ይረዳል የሚባለውም ለዚያ ነው።ክፉ ቀን ፈተናና፣ወንፊት ነው።ማን ከማን የሚለይበት ማበጠሪያ ወቅት ነው።ለሕዝብ ደህንነት የሚያስብና የማያስብ መንግሥት፣ለወገኑ የማይጨነቅና የማይራራ ዜጋ የሚለካውና የሚታወቀው በክፉ ጊዜ ነው።በደህና ጊዜማ ሁሉም ወዳጅ ይሆናል።ባይሆንም ይመስላል።
የመንግሥት አስፈላጊነትና ሚናም ችግርና መቅሰፍቶች ከመከሰታቸው በፊት መከላከልና መጠበቅ ሲሆን ችግሩ ገፍቶ ከመጣም ሕዝብ እንዳይጎዳ መከላከያ የሚሆን ዝግጅትና ለመቋቋም የሚያስችል ብቃት እንዲኖር ማድረግ ነው።በመዘናጋት ወይም ለሥልጣንና ለጥቅም ብቻ ትኩረት በመስጠት ሕዝብ የመቅሰፍቱ ሰለባ ከሆነ በወንጀል ከመጠዬቅ አይድንም።
በሕዝብና በአገር ላይ የሚደርስ አደጋን ለመከላከል አላፊነቱ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱም ዜጋ ሃላፊነት አለበት።እያንዳንዱ ሌላውን ለመታደግ የሚገባውን ሃላፊነት መወጣትና በተግባር መግለጽ ይጠበቅበታል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለማችን ላይ የሰፈነው ኮሮና (Covid-19) የተባለው ወረርሽኝ በመዛመት የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፉዋል፣እዬቀጠፈም ነው።ወረርሽኙ ሃብታምና ደሃ፣ሴትና ወንድ፣ጥቁርና ነጭ፣ወጣትና አዛውንት ፣ጎሳና ዜግነት አይለይም።ሁሉንም ያጠቃል።በዚህ ዓለም አቀፍ የጤና ጦርነት ላይ አብዛኞቹ መንግሥታትና ዜጎች የሚቻላቸውን በማድረግ ላይ ናቸው።የሕክምና ባለሙያዎች ከሚቋቋሙት በላይ ሆኖባቸዋል ፤ህይወታቸውን እስከመስጠት ድረስ ደርሰዋል፤ሆኖም ግን ተስፋ ሳይቆርጡ የሚችሉትን በማድረግ ላይ ናቸው።
የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ብሎም ለማድከም የሕዝብ እንቅስቃሴ ተገድቡዋል፣መስሪያቤቶች፣ትምህርት ቤቶች ፣ተዘግተው እንቅስቃሴና ሥራው ከቤት እንዲሆን ተደርጉዋል።አገሮች ድንበራቸውን ዘግተው መውጣትና መግባት አግደዋል።ሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎቶች፣የየብስ ፣የባህርና የአየር መስመሮች ሙሉለሙሉ በሚባል ደረጃ ቆሙዋል።ተአቅቦው ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ ሲሆን የሚራዘምበትም ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።በኤኮኖሚ ደረጃ ካደረሰው ስብራትና ቀውስ በላይ በሰው አእምሮና ባህሪ ላይ ያደረሰው ስብራት በቶሎ የሚጠገን አይሆንም።ዘመድ የዘመዱን መሞት በስልክ ከመስማት ባሻገር ቆሞ መቅበር አልቻለም።ሞቶ መቀበር እንደ ትልቅ ዕድል የሚቆጠርበት ዘመን ላይ ደርሰናል።ቀባሪና የመቃብር ቦታ ጠፍቶ የሰው ልጅ አስከሬን እንደ እንጨት ተሰብስቦ ከሚቃጠልበት ደረጃ ላይ ተደርሱዋል።
ይህ ክፉ ጊዜ የሰውን ልጅ ምንነት ለማዬት የቻልንበትን አጋጣሚ ፈጥሩዋል።
በአውሮፓ ደረጃ እዬተዛመተ በመጣው ወረርሽኝ ሳቢያ የወጡትን የጥንቃቄ መመሪያዎች ከማክበሩም በላይ አንዳንድ ደጋግ ታዋቂ ዜጎች ገንዘባቸውን ብቻ ሳይሆን ያሠሩትን ታላላቅ ሆቴል ሳይቀር ለሕክምና ጣቢያነት እዬዳረጉ ይገኛሉ።በሽታው በአዛውንቶች ላይ ስለሚከፋ ወጣቶችና ጎልማሶች ለአዛውንቶች ገበያ በመሄድ የሚያስፈልጋቸውን ሸምቶ በማቅረብ አብሮነታቸውን ይገልጻሉ።እርዳታ ለማድረግ ወረፋ የሚጠብቀው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ሕዝቡ የጤና ባለሙያዎች ለሚያደርጉት ጥረት አድናቆቱንና ድጋፉን በሙዚቃ፣በግጥም፣በጭብጨባ አልፎ ተርፎም ገጸበረከት በማቅረብ ሲገልጽ ፣መንግሥታትም የኤኮኖሚ ስብራት ላጋጠማቸው የግልና የመንግሥት ተቋማት ድጎማ በማድረግ፣ሁሉም በበጎ ተግባር ላይ ተጠምዶ ይገኛል።በዚህ ክፉ ወቅት ለእኔ ብቻ የሚለው እርኩስ መንፈስ የራቀ ይመስላል።
ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ፊታችንን ስናዞር ሁኔታው ይህን ይመስላል።
የበሽታው መኖር ከሶስት ወር በፊት ቢታወቅም በአገር ውስጥ ገባ ተብሎ የተገለጠውና የበሽተኛው ብዛት ይፋ የሆነው ከቀናት በፊት ነው።በዚህ ደረጃ ወረርሽኙን ለመቋቋም የተሄደበት መንገድና ዝግጅት ሲታይ ከአገሪቱም አቅም ጋር ሲለካ አያድርስ ያሰኛል።የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ዋናው መንገድ ንጽህናን መጠበቅ፣የአካል የቅርበት ግንኙነትን ማሶገድ፣ሲሆን አገራችን ለዚህ የተመቸች መሆኑዋን ስንመረምር ግን የምናገኘው መልስ የሚያሰጋ ነው፤ወረርሽኙን ከመቆጣጠር ይልቅ የሚባዛበት መንገዱ ሰፊ ነው።ንጽህናን ለመጠበቅ የውሃ አቅርቦቱ የተሙዋላ አይደለም።እርቀትን ለመጠበቅ የኑሮ ዘዴው የመኖሪያ ቤቱ፣የመጉዋጉዋዣው፣የአኑዋኑዋር ዘዴው ሁሉ ለበሽታው አጋልጦ የሚሰጥ ነው። የሕዝቡ ንቃተ ህሊና ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሃኪም ምክር ከመስማት ይልቅ የአባይ ጠንቋይ መላ ምትና ፈጠራ ወሬ ቀልቡን ይስበዋል።መድሃኒት ባይኖርም ያለውን ልግዛ ቢልም አቅሙ አይፈቅድለትም።ይህንን ሁሉ ሲያስቡት ልብ ይሰብራል።
ከሁሉም በላይ ግን ይህንን ክፉ ቀን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረገው ውድድርና ሽሚያ በመንግሥትና በነጋዴው ዙሪያ የሚካሄደው ዘረፋ ሰው መሆንን ያስጠላል።ነጋዴው በሸቀጡ ላይ እጥፍ ዋጋ በመጨመር በተጠቃሚው ላይ ከበሽታው የበለጠ በሽታ ሆኖበታል።መንግሥት የሕዝቡን ጤንነት ከማስጠበቅና ከመንከባከብ ይልቅ ወረርሽኙን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሲያደርገው ማዬቱ ተስፋ ያስቆርጣል።ሌሎቹ አገሮች የመጉዋጉዣ መስመሮችን ሲያግዱ፣የኢትዮጵያው ግን በሽታ ከተዛመተበት አገር ሳይቀር የአዬር በረራውን ቀጥሎበታል፤እንዳይገባ ሲታገድም ለምን የሚል ጥያቄ ያነሳል። ከውጭ አገር የሚገቡ ዜጎችን ለሁለት ሳምንት ለይቶ ማስቀመጥ በሚለው ሰበብ ለአስራ አራት ቀናት በጣም ውድ በሆነው በቀን ከ$150 ዶላር በላይ በሚያስከፍለው አዬር መንገዱ ባሰራው ስካይ ላይን ሆቴል(Sky Line Hotel) ውስጥ በራሳቸው ወጭ እንዲሰነብቱ ያስገድዳል።መክፈል አልቻልንም፣ዝቅተኛ ሆቴል ውስጥ እንረፍ የሚሉትን ከአረብ አገር የሽቀላ ኑሮ የተመለሱትን ምስኪኖች ሰብስቦ ውሃና መጸዳጃ በሌለው ፣የምግብ አቅርቦቱ ባልተሙዋላ፣የትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ አስራና አስራአምስት ሆነው ህጻናትና አዋቂ ሳይለዩ እፍግፍግ ብለው የሚያድሩበት ማጎሪያ አዘጋጅቶ እንደ ወንጀለኛ በፖሊስ ከቦ እያሰቃዬ ይገኛል። ይህ ነው ነጋዴው በዋጋ ጭማሪ፣ መንግሥት ደግሞ በማስገደድ ደሃ ዜጎችን የመዝረፍ ዘመቻው፣ይህ ነው ግርግር ለሌባ ያመቻል ማለት!
በሌላም ዙሪያ ማህበራዊ ስብሰባዎችና ዝግጅቶች እንዳይካሄዱ መመሪያ ወጥቶ ሳለ ገዢው መንግሥት ግን የፖለቲካ ቅስቀሳ ለማድረግ በማስገደድ አዳራሽ ሞልቶ ድጋፍ ይሰበስባል።ድጋፍ ያላደረገው በዚህም በዚያም ተብሎ የሚደርስበት በደል አያድርስ ነው።ከሥራው ይወገዳል፤ንብረቱን ይቀማል፣በስበብ ባስባቡም ወደ እስር ቤት ይወረወራል —ወዘተ ወዘተ!በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚያተራምሰውና ሰላም ካሳጣው የሥልጣኑ ባለቤት ከሆነው ከጎሳ ቫይረስ ሳይወጣ ዓለምን በበከለው ለኮሮና ቫይረስ ተጋልጦ ይገኛል።በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ! ሁለቱንም ቫይረሶች ለማሶገድ የሕዝቡ አንድነትና ቁርጠኛነት ወሳኝ ነው።
ከላይ እንደተገለጸው የሰው ልጅ የሚመዘነው በመከራ ቀን በመሆኑ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከመጥፎው ጎን ለጎንም የሚያበረታታና የሚያኮራ ተግባርም በመታዬት ላይ ነው።በተለይም የአዲስ አበባ ወጣቶች ለሚያደርጉት ሰብአዊና በጎ አድራጎት ተግባር የሚተባበሩ ዜጎች መኖራቸው አገራችን የሌቦችና የዘራፊዎች አገር ብቻ ሳትሆን ወገን ወዳዶችና በሰብአዊ ምግባር የታነጹ ደጋጎች እንዳሉዋትም አመላካች ነው። ቁጥራቸው ይብዛልን!!
በሽታውን ለመቋቋምና ወገኖቻችንን በመርዳቱ ዙሪያ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም በውጭ አገር የሚኖረው ሃይሉን አስተባብሮ የሚችለውን ለማድረግ መነሳት አለበት።የሚሰጠው እርዳታና ድጋፍ በአደራ በሌዎች እጅ ውስጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ ማድረጉም አንዱ ተግባር መሆን አለበት።ምንም እንኳን መቶ በመቶ አስተማማኝ ባይሆኑም ምክንያቱም ብልግናው ያልበከለው አካል መኖሩ አጠራጣሪ ነውና እርዳታው በእምነት ተቋማት በኩል ቢሆን የተሻለ ይሆናል።በዬቦታው የተለያዩ ስብስቦች የሚያደርጉት የእርዳታ ማሰባሰብ ጅማሮ ቀና ቢመስልም ወደ አንድ ብሔራዊ አሰባሳቢ ተቋም ቢጠቃለል ለቁጥጥር ያመቻል።ለዚህ ተግባር የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልም አንዱ አማራጭ ነው። በተረፈ ግን እርዳታ ማሰባሰቡ ለመንግሥት እጅ መንሻ እንዳይሆን መጠንቀቁ መልካም ነው።
አገራችንንና ሕዝቡዋን ከገጠማት የጎሳና የኮሮና ቫይረስ ፈተናና ውድመት ይጠብቃት!!
ተጨማሪ ማሳሰቢያና ጥሪ
በአሸባሪዎች ታፍነው ከሶስት ወር በላይ የደረሱበት ያልታወቀውን ወጣት ተማሪዎች ጉዳይ ትኩረት ሰጥተን የሚመለከተውን የመንግሥት አካል ከመጠዬቅ እንዳንቦዝን አደራ እላለሁ።በተጨማሪም ለዓለም ማህበረሰብና የሰብአዊ መብት ተቋማት ጉዳዩን በማስረዳት ክብደት እንዲኖረው ለማድረግ መንቀሳቀስ እንዳለብን ለማስታወስ
እወዳለሁ።ስለሆነም የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ አቋቁመው ወጣቶቹ እንዲለቀቁና አጋቾቹም በሕግ ፊት እንዲቀርቡ እንቅስቃሴ ያደርጉ ዘንድ መገናዊ ጥሪ አደርጋለሁ።ጉዳዩን በታፈኑትና በወለዱዋቸው ወላጆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው ቦታ ሆነን እንድናዬው ይሁን! ግር ግር ለሌባ ያመቻልና የኮሮና ወረርሽኝ ይህንን ትልቅ ነፍስ አድን ዘመቻ ከማድረግ እንዳይከልለንና እንዳንዘናጋ እንጠንቀቅ!! ችግርን እንዳመጣጡ ለመመለስ ዘርፈ ብዙና ብቃት ያለው ጠንካራ ድርጅት መፍጠር ዋስትና ይሆናል።ለመቶ ሚስማር አንድ መዶሻ እንዲሉ!!
አገሬ አዲስ