ጥር 20 ቀን 2012 ዓም(29-01-2020)
በተለያዬ አቅጣጫ ወይም በተለያዬ አሰላለፍ ሄዶ የሚፈልጉትን ለማግኘት ወይም የጋራ ዓላማን ለማሳካት የሚከተሉት ስልት የተለመደ ነው።በጦር ሜዳ ጠላቴ ነው የሚሉትን ወገን ለማንበርከክና ድል ለመምታት ከመሳሪያው አይነት ጀምሮ በአሰላለፍ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሚዘምቱ ሃይሎች ጥቃት ማድረስ ወታደራዊ ስልት ነው። በፖለቲካም ትግል እንዲሁ የተለያዬ መፈክርና ስም ይዞ ግን ለአንድ ተመሳሳይ ዓላማ መቆምና መታገል የተለመደ ነው።የህብረተሰብ ክፍል አንድ አይነት ፍላጎትና አስተሳሰብ ስሌሌለው በፍላጎቱ አንጻር ለመሳብ የሚያስችሉ ስልቶችን በመንደፍ፣ድርጅታዊ ሰንሰለቶችን በመዘርጋት፣አነጋገሮችን፣ቅስቀሳዎችን በማካሄድ ከመጨረሻው የጋራ ዓላማ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ዘዴ የመጠቀሙ አሰራር በሌሎቹም አገሮች የተለመደለ ሲሆን አሁን በአገራችን የሚካሄደው የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች እንቅስቃሴ የዚያው አካል እንደሆነ መረዳት ይቻላል።ከነዚህ ውስጥ ጎላ ብሎ የሚታዬው በኦሮሞ ጎሳ ስም የተለያዩ የሚመስሉ ግን ለአንድ የጋራ ዓላማ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች አካሄድ በቂ ምስክር ነው።
ለብዙ ዓመታት ሲወድቅ ሲነሳ የኖረው የኦሮሞ ጎሳን መብት ለማስከበር በሚል ሽፋን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚንቀሳቀሰው ክፍል በተለያዩ ጊዚያት የተለያዩ ስሞች ይዞ መነሳቱ አይዘነጋም።በጣልያኖችና በእንግሊዞች ቅስቀሳ የተጀመረው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዘመቻ ኤርትራንና ጅቡቲን በማስገንጠል ሌሎቹም እንዲነሳሱ አድርጉዋል።ላለፉት ሃምሳ ዓመታት እስከአሁን ድረስ የተለያዩ የሚመስሉ ግን አንድ ዓላማ ያላቸው ቱሉና ሜጫ፣የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ(ኦፌኮ)፣፣የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራቲክ ድርጅት(ኦፒዲኦ)፣የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር(ኦዲግ) ፣የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ(ኦዴፓ)፣ኦነግ ሸኖ…ወዘተ በሚሉ ስያሜዎች ስር በመደራጀት አሁን ካሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
የዚሁ ስብስብ አካል የሆነው ኦፒዲኦ አሁን ኦዴፓ በመባል በሥልጣኑ ላይ የተቀመጠው ቡድን መንግሥታዊ ሽፋን ተላብሶ የኦሮሞን የበላይነትና ጥቅም በማስከበር ብሎም ለወደፊቱ የኦሮሞ አገር ምስረታ ሂደትን በማመቻቸት ላይ ይገኛል።የጎሰኞች ክለብ የሆነውን ኢህአዴግን ብልጽግና ፓርቲ የሚል ጭንብል አልብሶ በሚያደርገው የማጃጃል ፕሮፓጋንዳ ሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲዘናጋ አድርጎታል።ሌሎቹም የኦሮሞ ጎሳ ድርጅቶች በስልጣን ላይ የተቀመጠውን ቡድን እነሱን የሚቃወምና ለኢትዮጵያ አንድነት የቆመ በማስመሰል በስከጀርባ የሚያገኙትን መንግሥታዊ ድጋፍና ከለላ እዬተጠቀሙ በሌላው ላይ ጉዳት እያደረሱ እራሳቸውን በማጠናከር ላይ ናቸው። ሌላው ኢትዮጵያዊ ውስጣዊ ትስስራቸውን ካለመረዳት አንዱን ጠላት ሌላውን ወዳጅ አድርጎ እያጨበጨበ ከማጫፈር በቀር ሊነቃ አልቻለም።ተፎካካሪ በሚል ስም ተጎታች ሆኖ አገሩን ለጥፋት አጋልጦ ለመስጠት ይረባረባል።
የነዚህ በተለያዬ ስም ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻ የሚያካሂዱት የኦሮሞ ድርጅቶች በመንፈስ የተሳሰሩ የኦነግ ቤተሰቦች መሆናቸውን ለማወቅ ጠንቋይ መሆን አይጠይቅም፤የሚሰሩት ሥራ አመላካች ነው።እንደኦዴፓ ያሉትን የኦሮሞ ድርጅቶች ለአንድነት የቆሙ ሃይሎች ናቸው እያሉ መጃጃልና እራስንና አገርን ለአደጋ ከማጋለጥ ይልቅ ሃይልን አሰባስቦ በመጡበት መንገድ መክቶ ለመመለስ መደራጀት ነገ የማይሉት ተግባር ነው።ትናንትና ለኢትዮጵያ አንድነት ቆመናል የሚለው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ መሪ መረራ ጉዲና የተባለው ይሉኝታ ቢስ ግለሰብ በድፍረት፣ “ትግላችን ከአምስት መቶ ዓመት በፊት የተነጠቅነውን የኦሮሞ አገር ለማስመለስ ነው” ሲል በአደባባይ ተደምጥዋል። ትናንትና ለይስሙላ ሲያወግዘው ከነበረው ጁዋር ሞሃመድ ከተባለ አሸባሪ ጋር ለብዙ ዓመታት አብሮ ሲሰራ እንደነበረ ዛሬ እጅ ለእጅ ተያይዞ የዓላማ አንድነቱን ግልጽ አድርጉዋል።የጊዜ ጉዳይ ነው ሌሎቹም አንድነታቸውን ይፋ ያደርጋሉ።ወይም የምርጫው ውጤት አንድነታቸውን ያጋልጣል።
ምርጫ የተባለው ዝግጅት የጉልበት መፈተኛ ከመሆንም ባለፈ የነገውን ሂደት የሚያበስር ለመሆኑ አሁን መሬት ላይ ያለው እውነታ ያረጋግጥልናል። ከሌሎቹ ድርጅቶች በላቀ ደረጃ እርስ በርሳቸው እዬተናበቡና እዬተጋገዙ፣ከውጭም አስፈላጊው ድጋፍ እዬተቸራቸው በሎጅስቲክስ፣በገንዘብ፣ በድርጅት መዋቅር የበለጠ ጥንካሬ ያላቸው እነዚሁ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (የኦነግ) የመንፈስ ልጆች የሆኑት የኦሮሞ ጎሳ ድርጅቶች ናቸው።የፈለጉትን ጥቃትና ወንጀል ሲፈጽሙ በሥልጣን ላይ የተቀመጠው አጋራቸው እርምጃ መውሰድ ቀርቶ እንደ መንግሥትነቱ ለማውገዝ እንኳን አልደፈረም።በዝምታ ተባብሩዋቸዋል።የምርጫ ጊዜ ሳይደርስ በፈለጉበት ቦታ ተዘዋውረው ቅስቀሳ እንዲያካሂዱ ብቻ ሳይሆን በአገር ወዳዱ ላይ ነጻ እርምጃ እንዲወስዱ የስነልቦና ስብራት እንዲያደርሱበት ፈቅዶላቸዋል።መጠነ ሰፊ ወንጀል ሲፍጽሙ አይቶ እንዳላዬ፣ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኑዋል።የሕግ የበላይነትን ማስከበር ተስኖታል።ወትሮስ ለሕዝብ ደህንነት የተነደፈ ሕግ መቼ አለና!ሕጻናት በአሸባሪዎች ታግደው ስቃይ ሲደርስባቸው አልደረሰላቸውም
በጎሳ ያልተደራጁ ድርጅቶች በአገር ውስጥ ፣ከክፍለሃገር ክፍለሃገር በነጻነት ተዘዋውረው ቅስቀሳ ማካሄድ ቀርቶ በሚኖሩበት ከተማም በከፈሉበት አዳራሽ የመሰብሰብ ነጻነታቸውን ገፎ ለተገንጣዩ ኦነግ ግን በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ በተሠራው የሚሊኒዬም አዳራሽ ውስጥ እንዲምነሸነሽ ፈቅዶለታል። ምርጫው እንዲካሄድ የሚወተውቱት እነዚሁ ድርጅቶች ሌላው ባልተዘጋጀበት ሁኔታ እንደሚያሸንፉ በመተማመን ነው።የውጭ ሃይሎችም ምርጫው እንዲካሄድ የሚወተውቱት ለዚያው ግብ ነው።
በዚህ መልክ ምርጫው ቢካሄድ በፓርላማ ተብዬው ውስጥ የሚጠቀጠቁት በልዩ ልዩ ስም ቅስቀሳ አድርገው የሚመረጡት ሙሉ ዝግጅት ያደረጉት የኦሮሞ ድርጅቶችና በነሱ መልክ በጎሳ የተደራጁ ድርጅቶች ተወካዮች ይሆኑና የጎላ ድምጽ ይኖራቸዋል።ያንን ዕድል ካገኙ ደግሞ ባለው መልክ ኢትዮጵያን በመቆጣጠር የበላይ ሆኖ ለመቀጠል ከፈለጉ ይቀጥሉበታል ፤አለያም የጋራ ዓላማቸው የሆነውን ኢትዮጵያን አፈራርሰው በታሪክ ያልነበረ ኦሮሚያ የሚባል አገር ፈጥረው አሁን የገነቡትን የጦር ሃይል ተጠቅመው የእኛ ነው የሚሉትን አካባቢ ለምሳሌም ደቡብና ምስራቅ ወሎን፣ግማሽ አፋርን፣ የኦጋዴን፣ደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያን፣ጋምቤላና ቤንሻንጉልን፣ሸዋን፣ጎጃምን በጉልበት በመዋጥ ክልላቸውን ያሰፋሉ።ይህን ካጠናቀቁ በዃላ ኦሮሚያ የሚል አገር መመስረታቸውን ይፋ ከማድረግ የሚያግዳቸው አይኖርም።የውጩም ተባባሪዎቻቸው ፈጥነው እውቅና ይሰጣሉ።በዚህ መልክ ኢትዮጵያን ካጠፉ በዃላ ወደ ቀጣዮቹ የአፍሪካ አገሮች ዘመቻቸውን ይቀጥላሉ። ይህንን አያደርጉትም ብሎ መጠራጠር ከጅልነትም በላይ ጅልነት ነው።ለዚያ ማስረጃው በአዲስ አበባ የሚከናወነው የሥልጣንና የቦታ ቅርምት ብሎም በተለያዩ ቦታዎች ለምሳሌም በከሚሴ፣በድሬዳዋ፣በሓረር፣በጅማ፣ በወለጋ፣በባሌ፣በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚያካሂዱት የማፈናቀልና የሽብር ዘመቻ በቂ አመላካች ነው።ይህ ስትራተጂ በኦሮሞ ነን ባዩቹ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን የሌሎቹም በጎሳ ማንነት የተደራጁት ቡድኖች ፍላጎት ነው።አሁን በዬጎሳው የሚነሳው ክልል የመሆን ጥያቄ ዓላማው አገር የማፈራረሱ ሂደት ቢሳካ ሁሉም የእኔ ነው የሚለውን መሬት ቦጫጭቆ ለመያዝ ያለውን ፍላጎት ያመላክታል።በሰላም እንደማይኖር ግን ዘንግቶታል።
ከዛም በተረፈ በኢትዮጵያ ዙሪያ ከበባ ያደረጉት የውጭ አገሮች የጦር ሃይሎች ግብግብ አፍሪካን ለመቀራመት ለሚያደርጉት ዘመቻ መሰናዶ እንጂ ለከባቢው ሰላም ብለው አይደለም። ይህ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ፍላጎት ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑት አገር በቀሎቹ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑት የውጭ አገር መንግሥታትና የፖለቲካ ሃይሎችም ጭምር ነው።ከወረራ እራሱዋን ተከላክላ በመቆዬት እንኳንስ ለራስዋ ለአፍሪካ ነጻነት ቀናኢ የሆነችው አገር በዚህ መልኩ እንድትጠፋ በልዩ ልዩ መልክ ሰርገው በመግባት ያላደረጉት ተንኮል የለም ።ታሪካዊ ወደቦቹዋንና በግዛት ድንበሩዋ ውስጥ የነበሩትን ኤርትራና ጅቡቲን እንድታጣ አድርገዋታል።አሁንም ተገንጣዮቹ በተለይም የኦሮሞ ጎሳ ድርጅቶች እንዲጠናከሩ አንዱ የሆነውን ኦፒዲኦን ለሥልጣን እንዲበቃ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ለወደፊቱ አገር ምሥረታ ብቃት እንዲኖራቸው አስፈላጊውን የገንዘብ፣የፖለቲካ ድጋፍ እንዲሁም፣ስልጠና በመስጠት ላይ ናቸው።ለዚያ መንደርደሪያ እንዲሆን ኢዴሞክራሲያዊ መሆኑን ቢረዱም ምርጫው እንዲካሄድ አጥብቀው ይሻሉ።በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብም እያፈሰሱ ነው። ሕጻናት፣ አዛውንት ወጣትና ሴቶች ሲታገቱ፣ሲረሸኑ፣ሲፈናቀሉ ግን ድምጻቸውን አላሰሙም፤ምንም እንዳልተደረገ በዝምታ አልፈዋል።ዓለም አቀፍ ግዴታቸውን አልተወጡም።ይባስ ብሎ ተጠያቂ የሆነውን የመንግሥት መሪ የዓለም የሰላም ምልክት አድርገው የኖቤል ተሸላሚ አድርገውታል።
ለኢትዮጵያ አንድነት ብሎም ለራሱ የመኖር ህልውና የሚቆረቆረው ወገን ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው።ያም በልዩ ልዩ ስም ተነጣጥሎ የተበታተነ ደካማ ትግል ከማካሄድ እንደ አያት ቅድመአያቶቹ በአንድ የአገር አድን የአርበኞች ጣራ ስር ፣ሃይሉንና እውቀቱን አሰባስቦ ትግሉን ማካሄድ ነው። ኢፍትሃዊ በሆነው በምርጫው ዙሪያ መረባረብ ሳይሆን ሁሉንም ያካተተ ግን ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያን አንድነት የተቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የሲቪክ ማህበራትና የህብረተሰብ ክፍሎች፣የእምነት ተቋማት፣የሙያ፣የሴቶችና የወጣት ድርጅቶች የሚሳተፉበት የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም፣ሕዝብ የተሳተፈበትና የተቀበለው ሕገመንግሥት እንዲረቅና በሥራ ላይ እንዲውል በሚያበቃው ትግል ላይ መረባረብ መሆን ይገባዋል።ይህንን ካረጋገጡ በዃላ ምርጫ ቢካሄድ አስተማማኝ ይሆናል። አሁን በተወጠነው የምርጫ ዝግጅት መሳተፍና ያለውንም “ሕገመንግሥት” ተሸክሞ መጉዋዝ እራስንና አገርን ለጥፋት አሳልፎ መስጠት ነው።ለእርድ የሚነዳ ከብት መሆን ማለት ነው።
ምርጫ ቦርድ ተብዬው የመንግሥት ተቋም ለምርጫ ብቃት መመዘኛው ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያን አንድነት መቀበል መሆን እንደሚገባውም አብስሮ መጠዬቅ ይገባል።በኢትዮጵያዊነቱና በኢትዮጵያ አንድነት የማያምን ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ እንኳንስ በአገራዊ ምርጫ የመካፈል በአገር ውስጥ የመኖር መብት ሊኖረው አይገባም።ሰላምና አንድነትን በሚያናጋ በግልጽና ድብቅ ሴራ የተሰማራ በሥልጣንም ላይ ያለ ቢሆን ለፍርድ እንዲቀርብ ማድረግ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ ነው።
የዶክተር አብይ መንግሥት እውነት ለኢትዮጵያ አንድነት የቆመ ከሆነ ያለው ምርጫ ሥልጣኑን ለተውጣጣ ሕዝባዊ ጊዜያዊ መንግሥት ማስረከብ ነው።እንዳለፉት መንግሥታት ይህንን አልቀበልም ብሎ በያዘው መንገድ መጉዋዝ ከመረጠ የእሱም ያገራችንም አወዳደቅ አያምርም።በአገር ውስጥ ከሃይለሥላሴ፣ከመንግሥቱ ሃይለማርያም፣ከመለስ ዜናዊ፣ከሃይለማርያም ደሳለኝ ከውጭ አገር አምባገነን መሪዎችም አወዳደቅ ጭምር ትምህርት ቢወስድ ይጠቅመዋል። ሥልጣኑን ያስረክብ ሲባልም በእልህና አላፊነት በጎደለው መልክ አዝረክርኮ መሄድ አይደለም።ወይም ሥልጣኑን ለነውጠኞች በሚያመች መንገድ አሳልፎ መስጠት ማለት አይደለም።እሱም አካል ለሚሆንበት የሽግግር መንግሥት አላፊነቱን ይስጥ ማለት ነው።
የአንድነት ጎራው ልብ ይግዛ!በአንድ የጋራ ግንባር ጣራ ስር ተሰባስቦ እራሱንና አገሩን ከጥፋት ያድን!!አገር ሳይኖር ሥልጣን እንደማይኖር ይገንዘብ!!ጎሰኝነት የሰው ልጆች ጸር የሆነ ቫይረስ ነው።ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶችና ከዚያም በዃላ ለተከናወኑት ግጭቶችና አገር የመበታተን ውጤት ለሆኑት የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ለህዝብ መፈናቀልና መሰደድ ምክንያቱ ዘረኝነትና የዘራፊዎች እራስ ወዳድነት ነው።ከዚያ አደጋ ለመዳን ያለው አማራጭ የጋራ አመራር ፈጥሮ መሰለፍ ብቻ ነው። መከፋፈል ምን እንደሚያስከትል ከየመን፣ከሶማሊያ፣ከሊቢያ፣ከሶሪያ፣ከሩዋንዳ፣ከዩጎዝላቪያ ተመክሮዎች መማር አለብን።አሁን ያለንበትንም ሁኔታ እናጢን።
ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በጎሰኞች ተበታትና የነበረችውን አገር በማሰባሰብና ከውጭ ገፍቶ የመጣን ወራሪ አሳፍረው የመለሱትን ጀግና ኢትዮጵያውያን ገድል ከመዘከር አልፈን አሁን የገጠመንን ተመሳሳይ ሁኔታ ለማሶገድ ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል።የአድዋን ጀግኖች ስንዘክርና ስንኮራባቸው የዘመናችንን አድዋ ግዳጅ መዘንጋት የለብንም።ጎሰኞች ለአንድ አገር የማፈራረስ ዓላማ በመተባበር ሲነሱ እኛ አገራችንን ለማዳን በጋራ የማንነሳበት ምክንያት ሊኖር አይገባም።የግልና የቡድን ጥቅም ሊከበር የሚችለው አገር ሲኖር ነው።ትልቁ ጥቅም ደግሞ እንደልብ ተንቀሳቅሰው በሰላም የሚኖሩበት፣ከአያት ቅድመ አያት የወረሱት የሚከበሩበት ነጻ አገር ባለቤት መሆን ነው። ለዚያ የጋራ ዓላማ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንነሳ!!
አገሬ አዲስ