ይህች ከትግርኛ የተወሰደች ተረታችን በጣም ገላጭ ናት፤ እወዳታለሁ፡፡ “ስለምጣዱ ሲባል ዐይጧ ትለፍ” ትባላለች ወደ አማርኛ ስትጠለፍ፡፡ ግን ታዲያ ሁሉም ነገር ገደብ አለው፤ በተለይ የጊዜና የትግስት፡፡
አማራው ዐይጧ ከምጣዱ እስክትወርድለትና ብቻ ለብቻ እስኪገናኙ ከሚገባው በላይ ታግሷል፡፡ ምናልባት ከ50 ዓመታት ለማይተናነስ ብዙ ዘመን፡፡ እንዲያውም ይህ ትግስቱና አርቆ አሳቢነቱ እንደፍርሀት እየተቆጠረ በጠላቶቹ ቤት ሳያስንቀው አልቀረም፡፡ እንጂ ለጀግንነቱማ የሸንኮራውን አስማረና የጎጃሙን በላይ ዘለቀ ነፍሳት በሙት መንፈስ ጠሪ ጠንቋዮቻቸው አስጠይቀው መረዳት ይችላሉ፡፡ ሞት ሲዘገይ የቀረ መምሰሉ ዐይናቸውን ካልጋረደባቸው የአማራ እናት እነስንዴውንና አሣምነውን ብቻ ወልዳ እንደማታቆም ደግሞ በቅርቡ እንደሚያዩት እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለነገሩ ጥጋብ እኮ መጥፎ ነው – ርሀብን ያስረሳል፡፡ ለዚህም ነው “ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ” እና/ወይም “የዱባ ጥጋብ ካለስንቅ ያዘምታል” መባሉ፡፡
አሁን አሁን አማራ ትግስቱ እየተሟጠጠ ነው፡፡ እግዚአብሔር አይበለው እንጂ አማራው ነሸጥ አድርጎት ይህችን ጥፍራም ባለጌ ዐይጥ ምጣዱ ላይ ቁብ እንዳለች በያዘው ቁድራ ቢዠልጣት ሲጥ ማለቷ አይቀርም፡፡ ዐይጢት የተማመነችው የአማራን ትግስት እንዲሁም የአማራን ከጠባብ የጎሠኝነት ስሜት የጠራ መሆንና የውጭ ኃይሎችን ሁለንተናዊ ድጋፍ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ታሪክ ሊዘመዘም፣ ምድር የሚከብዳት ተዓምርም ሊገለጥ ጥቂት ጊዜ ቀርቷል፡፡ ይህን የማይቀር ነባራዊ እውነት ጠላትም ወዳጅም ይወቀው፡፡ እንዲህ የምለው ለጉራም ሆነ ለማስፈራራት እንዳልሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክሬ ነው፡፡
አለምክንያት የሚሆን ምንም ነገር የለም፡፡ ሁሉም የሚሆነው በምክንያት ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ምክንያቶችን ማገድ የሚቻለው የለም፡፡ ለምሣሌ የልጆቻችንን ወለጋ ውስጥ መታገት ምክንያቱና ሂደቱ እንዲሁም የሚፈጥረው ኅሊናዊና አካላዊ ቁስል በቃላት የማይገለጽ እጅጉን ከባድ ቢሆንም ማን ያውቃል እንደዚህ የሆነው ፈጣሪ በውጤቱ ኢትዮጵያን ከተዘፈቀችበት አረንቋ ሊያወጣት ሽቶ ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል የነዚህ ልጆች መስዋዕትነት እንደፈረንጅኛው አባባል “የግመሊቷን ወገብ የሰበረው የመጨረሻው ገለባ ወይም የሣር አንጓ” ሊሆን ይችላል፡፡ ፈሊጦችና አባባሎች በምንጭ ቋንቋቸው ይበልጥ ይጥማሉና እነሆላችሁ – “The last straw that breaks the camel’s back.” የሞላ ብርጭቆ በአንዲት ጠብታ ምክንያት ይፈሳል፤ 99 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሞቀ ውኃ አንዲቷን ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ካላገኘ አይፈላም፡፡ ሕይወት እንዲህ ናት፡፡….
ከአቢይ አህመድና እርሱ ከሚወክለው ቡድን፣ ከአዴፓና ከትህነግ፣ አዜማ ከሚባለው የከሰሩ ፖለቲከኞች ስብስብና መሰል አዘጥዛጮች በስተቀር በአሁኑ ወቅት ስለነዚህ የታገቱ ልጆቻችን ድምጹን የማያሰማ የለም፡፡ ቦኮ ሃራም በኢትዮጵያ ተከስቶ አዲስ ታሪክ እየጻፍን እንገኛለን፡፡ በነገራችን ላይ ሥልጣንና ስመ-ጥርነት ያሰከራቸውና ከዚያም አልፎ በለዬለት ሁኔታ በግልጽ ያሳበዳቸው ወገኖች በተለይ አማራን ጥምድ አድርገው የያዙበት ምክንያት ሲፈተሸ ብዙዎቻችንን ላይገባን ይችላል፡፡
ለሦስተኛ ዐይን ባለቤቶች ግን ጉዳዩ ብዙ ምርምርን የማይሻ በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡
አንድ ነገር አይኑርህ፡፡ ድሃ ሁን ወዳጄ፤ ድህነትንም አትጥላው፡፡ አንድ ነገር ኖሮህ ሰው እንዲቀናብህ የሚማጠነውን የ“ምቀኛ አታሳጣኝ”ን የአማርኛ ተረት ለጊዜው ተወው፤ የማትሸከመው ዕዳ ያመጣብሃልና፡፡ አማራ እንዲህ ቁም ስቅሉን የሚያየውና ቤተስኪያን እንደገባች ውሻ በማንም መደዴ የሚሳደደው ሀብታም በመሆኑ ነው፡፡ ሀብታምነቱ የሚጀምረው በባዶ እግሩ የሚሄደው ገበሬ፣ ቀዳዳ ጨርቅ የሚለብሰው ገበሬ፣ ለጎኑ ማረፊያ የሣር ፍራሽና አጎዛ እንኳን የሌለው ምሥኪን ገበሬ እቤቱ ብትሄድ እግርህን አጥቦ መደቡን ለቅቆ በክብር ያሳድርሃል፣ ተንከባክቦም ይሸኝሃል እንጂ ክፉ ፊት እንኳን ላለማሳየት እጅግ የሚጠነቀቅ፣ ዐረመኔና ይሉኝታ ቢስም አለመሆኑን ስትታዘብ ነው፡፡ አማራ በርግጥም ሀብታም ነው፡፡
ፈሪሃ እግዚአብሄር ያለው የታችኛውና ማንም ዋልጌ የሚረግጠው አማራ ሳይማር የተማረ፣ እንደ አለት የፀና ግሩም ሥነ ልቦናዊ መደላድል ያለው፤ ለሰው በተለይም ለእንግዶች የሚራራና በተፈጥሮው ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡ ይህን ስል ስለአማራ እንጂ ስለሌላ ስላልተናገርኩ ፀጉር የሚሰነጥቅ ሸውራራ እንዳይኖር ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡
ይህ ሕዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ እያለ፣ በሃይማኖቱ የፀናና ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለአፍሪካ ኅብረትና ውኅደት ደጀን የሚሆን ይህን መሰል የአንድነት አቀንቃኝ ሕዝብ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እያለ ዕንቅልፍ የማይወስዳቸው በፈረንጅኛው አጠራር Big Brothers ወይም Uncle Sammy የሚባሉ የNegative Energy ዋና ምድራዊ አምባሳደሮች አሉ፡፡ በዚያ ላይ ከአባይና ጣና እንዲሁም ከፀረ-ተንበርካኪነት የጥቁር ኩሩ ሕዝብነት ጠባያችን፣ ከዐድዋ ድልና ከመሳሰለው የአሸናፊነት ታሪካችን ጋር የሚገናኝ ብዙ ጣጣም አለብን፡፡ በእግረ መንገድ ለመጠቆም ያህል የነሱም ኃይል የሚዝልበት ዘመን እጅግ ተቃርቧልና ደስ ይበለን፡፡…
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከእሥር እንደተለቀቀች ጥጃ እንዳሻቸው እየፈነጠዙ የሚገኙት ከዚህ አፍራሽ ኃይል ጋር በአንድ ወይ በሌላ መንገድ ጡት የተጣቡና ነፍሳቸውን ለሲዖል ሥጋቸውን ለሀብትና ለሥልጣን የገበሩ የውስጥና የውጭ ምንደኞች ናቸው፡፡ አዳሜ መድረክ ላይ ቢቅጠፈጠፍና እዚህ እያሳገተ ከውጭ እስረኞችን ይዞ ቢመጣ እውነት እንዳይመስልህ፡፡ ሊቀ ሣጥናኤልም የእግዚአብሔርን ሥልጣን የሚገዳደር ኃይልና ግርማ ሞገስ እንደነበረው መዘንጋት አይገባም፡፡ ስለሆነም በአቢይ ዲስኩር መነፍለል ማለት የዲያብሎስ ምርኮኛና አምላኪ መሆን ነውና ተጠንቀቁ! ይህ ሰው በኢትዮጵያ የአጋንንት ወኪል ነው፡፡ የምታመልኩት አምልኮታችሁን ቀጥሉ፤ አልቃወምም፡፡ ሰው በወደደው መቁረቡ፣ ወደው የዋጡት ቅልጥምም ከብርንዶ ይልቅ መጣሙ አሁን አልተጀመረምና ስትፈልጉ ጽላትም አስቀርጻችሁ ስገዱለት፡፡ እነእዩ ጩፋስ ሕዝቡን ሣር እያስጋጡት አይደል! ዘመኑ እኮ የመልቲዎች ነው – የአጭበርባሪዎች፡፡ በሀገራችን የሚታየው ጉድ እኮ መፈጠርን ያስጠላል፡፡
አማራው ሩቅ በማሰብ ምጣዱ እንዳይሰበርበት ሲጠነቀቅ መቆየቱን ገልጫለሁ፡፡ ለምጣዱ ሲል ታናናሾች ሲያዋርዱት፣ ቅሌታሞች ራሳቸው ቀልለው ሲያቀሉት ሁሉንም በመታገስና እየሆነበት የነበረውንና አሁንም እየሆነበት ያለውን ሁሉ በማመንና ባለማመን ሰመመን ውስጥ ገብቶ ብዙ ጊዜ አሳልፏል – ታዛቢን እስኪገርም ድረስ፡፡
ከአሁን በኋላ ግን ይህ ለአጋንንት ውላጆች ወርቃማ የሆነው የጨለማ ዘመን በብርሃናማ ዘመን ሊተካ ዳር ዳር እያለ ነው፡፡ ያለ መስዋዕትነት ደግሞ ድል የለም፡፡ የመስዋዕትነቱን መጠንና የትግሉን የጊዜ እርዝማኔ አንድዬ ያሳንስልን ብሎ መጸለይና ሁሉም የሚጠበቅበትን ማድረግ እንጂ “እንዲህ ሆንኩ፤ እንዲህ አደረጉን” እያሉ ማላዘኑ እነሱን ከማስደሰት ባለፈ ጠቀሜታ የለውም፡፡ እንግዲህ እነአቢይ ያበጠው ይፈንዳ ብለው በአማራው ላይ የጦርነት ፊሽካቸውን ነፍተዋል፡፡ ሰው ሊያደርገው የሚችለውን መጥፎ ድርጊት ሁሉ (All the evil that men can do!) በአማራው ላይ እየፈጸሙ ነው፡፡ የወሬ ቋቱ ኢዜማ ተብዬው ሳይቀር የት ይደርሳሉ የተባሉ ጥጆችን ሉካንዳ ቤት እንዲልከሰከሱ እያደረገ ገንዘብ የተጫነች አህያ በርግጥም የማትደረምሰው ምሽግ እንደሌላት ለብዙኛ ጊዜ እንድናረጋግጥ እያደረገ ነው፡፡
ለማንኛውም ዐውድማው ተለቅልቋል፡፡ በልግና መኸሩም ሊወቃና ምርትና ግርዱ ሊለይ ዝግጅቱ በመገባደድ ላይ ነው፡፡ … ማበራየቱ ትንሽ ሊዘገይ የሚችለው – ለወራትም ቢሆን – እነዚህ ልጆች በሕይወት ከተገኙ ብቻ ነው፡፡ ይህም አጠራጣሪ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ባተሌ ጠ/ሚኒስትር ላኪዎቹን ለማስደሰትና የማስመሰል ድራማውን ለመተወን እዚያና እዚህ እንደባዘነ በኃጢኣታችን ምክንያት ለርሱ የተሰጠችውን ትንሽዬ ጊዜ ወደማጠናቀቁ የተጠጋ ይመስላል፡፡ “ከተሣፋሪ ጋር ቲኬት ቆርጦ ሄደ” እያሉ ከበሮ ሲመቱለት ይገርመኛል፡፡ እንደዚህ ሰው ያለ ቲያትረኛ በዓለም አልነበረም፤ ወደፊትም የሚኖር አይመስለኝም፡፡
ምን አለፋችሁ ያልተሞከረ በሬ ይፈተናል፡፡ ይህን የታሪክ ፈተናም በድል ይወጣል፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያዊነት እንደጥንት እንደጧቲ ያብባል፤ አዝመራውም ይጎመራል፡፡ የሆኖ ሆኖ ልጆቻችን ሞተውም ከሆነ ነፍሳቸውን በአብርሃምና በያዕቆብ አጠገብ እንዲስቀምጥልን እንጸልይ፤ ካልሞቱም በቅርብ ቸር ወሬ ያሰማን፡፡ የሚያስለቅሰን የአሟሟታቸው ጉዳይ እንጂ እኛስ ከነሱ በምን ተሻልን? በቁም ገድለውን የለም እንዴ? እነ አቢይ ግን ልጅ አይውጣላቸው፤ ማንም የኢትዮጵያ ጠላት ጥቁር ውሻ ይውለድ – አንተ ወንድሜ ደግሞ “መጽሐፉ ‹ተራገሙ› አይልም” አትበለኝ – መራገም አንዳንዴ ይፈቀዳል እባክህን – ኢዮብ የተፈጠረባትን ቀን ረግሞ የለ?