ሞረሾች አንድነት ከማን ጋር፣ አንድነት ለምን፣ አንድነት መቼ? በሚል ያወጡትን መግለጫ አንብቤ መሀል አናቴን በዘነዘና የመቱኝ ያህል ሲያመኝ፣ ጆሮዬ እውውውውው እያለ ሲጮህ ተሰማኝ።
ከአፍ የሚወጣ ነገር ጠላትን ከሚያቆስለው በላይ በራስ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ይበልጣል። በክፉ ያየነውን ሰው ለመወረፍ ወይም ለማሸማቀቅ የምንወረውራቸው ቃላት ለተመልካችም የሚጎረብጡ ስለሚሆኑ ከምንም በላይ ራስን ያስገምታል። አንዳንድ ሰዎች አስበው የሚናገሩ ሳይሆን ከተናገሩ በኋላ ሀሳብ የሚወዘውዛቸው ናቸው። ያም ቢሆን ህሊና ያላቸው ከሆኑ ነው። ይኸ የጠረባ ፖለቲካ ቢቀር ምናለ? በጅምላ የመወንጀል አባዜ ቢበቃ ምናለ?
“— ተደጋግሞ በተሄደበትና ምንም ዓይነት አዎንታዊ የሆነ ገንቢ ውጤት ባልታየበት መንገድ ደጋግመን እንድንጓዝ የሚገፋፉ ቡድኖች፣ለአንድነችን የጓጉ ሳይሆኑ፣ ልክ እንዳለፉት ሁሉ ውድቀታችን የናፈቃቸው መሆን አለባቸው።” ይላሉ ሞረሾች አማራው በአንድ ጠንካራ ድርጅት ሥር ብቻ እንዲሰባሰብ የሚጠይቁትን ሁሉ።
በዚህ ፍረጃ ውስጥ እኔም አለሁ፤ ምክንያቱም እኔም አንድ ጠንካራ የአማራ ድርጅት ብቻ ተፈጥሮ የሕዝብን ሁለንተናዊ አቅም እንዲያስተባብር ስለምፈልግ። በቡድን ከፋፍላችሁ ሃይላችንን አትበትኑ እያልሁ ስለምከራከር። በጣም ያሳዝናል! ምናለ
“ሳንጠናና ውህደት መፍጠሩ ለትግላችን መሰናክል ሊያመጣ ስለሚችል ጊዜ ወስደን ማን ምን እንደሆነ ማየት ስለሚኖርብን ወገኖችቻችን ይህን እንድትረዱልን እናሳስባለን” ቢባል።
በመሰረቱ ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ ብሎ የሚነሳ ማንኛውም ድርጅት የስልት ካልሆነ በቀር የአላማ ልዩነት አለው ብየ አላምንም። አዎ! ከጣሊያን ጋር ወግነው ኢትዮጵያን ያደሙ ብዙ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። የዛሬው ግን ይለያል። አማራው መጥፋት አለበት ተብሎ እየተሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት የራሱን ቤተሰብ ከጠላት ጋር ወግኖ ለማጥፋት የሚተጋ ጤነኛ ሰው በምንም አይነት ስሌት ሊኖር አይችልም። በብአዴን ውስጥ ያሉት አማሮችም ቢሆኑ በወገናቸው ላይ የሚወርደው መአት የማይሰማቸው አይደሉም። የምናካሂደው ትግል እነሱንም የሚጋብዝ ቢሆን የተሰጣቸውን ተልዕኮ ሊወጡ የሚችሉ፣ መረጃ በማቀበል የሚያግዙ አይጠፉም። ዋናው ነገር ሁሉም አማራ የተጠነሰሰበትን ሴራ አውቆ የሚታገለው ለራሱ እንደሆነ አምኖ እንዲቀበል ከማድረጉ ላይ ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው ያገኘውን ሁሉ የሚለክፍ ሳይሆን በዕውቀት እና በአመለካከት የዳበረ የራቀን የሚያቀርብ፣ ያለን የሚያጸና አሳታፊ የሕዝብ ግንኙነት ሲኖር ነው።
ይህን ስል ዝርክርክ መሆን አለብን ለማለት አይደለም። ለጥንቃቄ ያህል ወሳኝ የሆኑ ቦታወች ላይ የሚሰማሩ ሰዎችን ብልሀት በተሞላበት መንገድ መርጦ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑ የሚያከራክር አይሆንም። ሚስጥራዊ ሰነዶችን ማንም ከማይደርስባቸው ቦታ ማስቀመጡም ተገቢ ነው። ያም ቢሆን የማንንም ስሜት ሊረብሽ በማይችል መንገድ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።
ሁሉም አማራ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው እና በነጻነት ተሳትፎ እንዲያደርግ ዴሞክራሲያዊ አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል። አደረጃጀት እና የርስ በርስ ግንኙነቱ በውስጠ ዲሲፕሊን እየተመራ በሂደት ግንኙነቱ እየጠበቀ፣ ችግሮች እየጠሩ የሚመጡበት ሁኔታ መልክ እንዲይዝ አድርጎ ማቀድ ያስፈልጋል። የሆነ ጥርጣሬ ቢያድርብን እንኳ ማንንም ሊያሸማቅቅ በማይችል መንገድ በክትትል እና ግምገማ ማጥራት ተገቢ ነው። ያ ካልሆነ በአንድ ተጠርጣሪ ላይ የሚደርሰው ወከባ በሌላው ላይ የሚያሳድረው አፍራሽ ተጽዕኖ ስለሚኖር ለአንዱ የተወረወረው ምዝግዝግ ሌሎችንም ሙጭ የሚጠርግ ይሆን እና በቁጭት ተነሳስተው በደምና በአጥንታቸው የአማራውን ህልውና ለማስጠበቅ የቆረጡትን ግለሰቦች ቀስ በቀስ የሚያሸሽ ይሆናል። የፖለቲካ ሥራ በደም ፍላት የሚተገበር ሳይሆን ጥበብ እና ማስተዋልን የሚጠይቅ፣ ከጉልበት ይልቅ ሳይንሳዊ ዕውቀት መላበስ የሚሻ ሥራ ነው።
በፖለቲካ ውስጥ ልብን አሻክረው ከሚበትኑ ነገሮች መሀል ዋናው የስልጣን ጥያቄ ነው። የስልጣን ጥያቄ አይደለም በውህደት አንድ ሊሆኑ በሚደራደሩ የተለያዩ ቡድኖች ዘንድ ይቅርና በአንድ ወጥ ፓርቲ አባላትም መሀል የሚከሰት መቸም፣ የትም፣ የሚያጋጥም ጤናማ የሆነ ወይም ያልሆነ ፍላጎት ነው። ነገር ግን ስልጣን የሚያዝበት አግባብ እና የመተዳደሪያ ደምቡ አሻሚ አለመሆን ለችግሩ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ ይሆናሉ። ሁሉም አባል የሚገዛው ለመተዳደሪያ ደንቡ ከሆነ ለኃላፊነት የሚያሳጨውም ሆነ በሀላፊነት የሚያስጠይቀው ወይም የሚያስቀጣው በህጉ ላይ የሰፈሩትን ቁምነገሮች አክብሮ በመስራቱ ወይም በማዛነፉ ማለትም በሥራው ይሆናል። ሞረሾች የስልጣን ጥያቄን እንደስጋት በማየት «ትንሽ አሻሮ ይዘን ወደ ቆሎ በመጠጋት የሌለ ሥልጣን ለመጋራት መሆን የለበትም።” በማለት ለውህደት የሚመጡት ቡድኖች የስልጣን ፍላጎት ምቾት አይሰጥም በሚል መልኩ ለመዋሀድ እንደአንድ መሰናክል አድርገው ያቀርቡታል። በተጨማሪም ተዋህደናል ወይም ግምባር/ቅንጅት ፈጥረናል ብለው ብዙም ሳይራመዱ ፍርስርሳቸው የወጣውን ድርጅቶች በስም እየጠቀሱ እንደማስረጃ በማቅረብ ሳይተዋወቁ በአንድ ዕዝ ስር መሰባሰቡ ችግር እንዳለው ሊያሳምኑን ሲሞክሩ በውህደት የተገኘ ጠንካራ ሰብአዊ፣ ቁሳዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስለመኖሩ ግን ሊያስረዱን አልደፈሩም። ደርግ እስከመጨረሻው እስትንፋሱ የዘለቀው በሰደድ ሰዎች ብቻ እንዳልሆነ ሊነግሩን አልፈለጉም።
በትግል ወቅት ከፊት መሰለፍ አደጋ እንጅ ጥቅም አያስገኝም። በትግል ጊዜ ስልጣን ትልቅ ሸክም እንጅ ሹመት አይደለም። አሁን የሚያስፈልገው ተባብሮ የተደራጀውን የጠላት ኃይል መመከት ብሎም በሕዝባችን ላይ መከራ እያወረደ እንዳይቀጥል ከነጭራሹ ለማስወገድ መስራት ነው። በአምባገነኖች ሥር የመተዳደር ታሪክ ያላትን ሀገር ወደተሻለ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመቀየር የአንድ ወቅት ትግል ሳይሆን ጊዜ የሚወስድ የቅብብሎሽ ትግል ማድረግን ግድ ይላል። በዚህ የትግል ወቅት ብዙ ውጣ ውረድ ይኖራል። ትግሉን የጀመሩት በመስዋዕትነትም ሆነ በሌላ መልክ እየተለዩ መጨረሻ ላይ የሚገኙት በአብዛኛው ቆይተው የተቀላቀሉ ይሆናሉ። ወያኔ በረሀ ሲወርድ በአመራር ላይ ከነበሩት ሰዎች መሀል ከድል በኋላ በህይወት የተገኙ ወይም ስልጣናቸውን አስጠብቀው በአመራርነት የዘለቁ ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። ደርግን በመመስረትና በመምራት ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ወታደራዊ ሃላፊወች በተለያየ መንገድ ሲገለሉ/ሲወገዱ ብዙ ጊዜ አልወሰደም። ቶሎ ውጤት ማየት ያልቻሉ ሰዎች ከተወሰነ ጉዞ በኋላ ራሳቸውን ከትግሉ አግልለው የግል ህይወታቸውን ለመኖር የሚወስኑ እንደሚኖሩም የሚጠበቅ ነው።
ደጋግሜ ለማስገንዘብ እንደሞከርሁት ማንም እየተነሳ ወያኔ ይህችን ቀን፣ ወር፣ ዓመት አያልፋትም እንደሚለው ሳይሆን እጅግ መራራ እና እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ እንደሚጠብቀን ግምት ውስጥ አስገብቶ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ይህ ዘረኛ መንግሥት ቢወድቅ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በተፈጸሙት ወንጀሎች ተጠያቂ እንሆናለን፣ ካላግባብ ያካበትነው ሐብት ይወረስብናል የሚሉ ብዙ የወቅቱ ተጠቃሚወች ያሉ በመሆናቸው እና እስከመጨረሻው ትንፋሳቸው እንደሚፋለሙ ስለሚታሰብ ነው።
የስልጣን ወፍለቁን ተቆናጥጨ፣ “ታድሸ መጣሁ!” እያልሁ በልጓምና በአለንጋ ገርቸ እጋልባለሁ በሚለው ወያኔ መር ግምባር እና በጠላትነት ተፈርጆ የግፍ ሰለባ እየሆነ ባለው አማራ መሀል የሚደረገው ፍልሚያ እንደሚገመተው ቀላል አይሆንም። አማራውን በፍቅር የማይመለከቱ፣ ሞቱን የሚናፍቁ ሌሎች ወገኖች መኖራቸውንም ታሳቢ ማድረግ የፈተናውን ከባድነት ያስገነዝበናል። ለዚያም ነው የጥቃት ሰለባወች ተሰባስበው ለመመከት መዘጋጀት ግድ የሚሆነው።
ይህ ወቅት ሰው የሚፈለግበት እንጅ ሰው የሚገፋበት ወቅት አይደለም። ይህን ታሳቢ ካደረግን በአሁኑ ወቅት ስልጣን ማለት ራስን አሳልፎ መስጠት፣ ከኋላ ሳይሆን ከፊት መሰለፍ፣ የጥይት አሩርን በደረቱ መክቶ ከጀርባ የተሰለፈውን ወገን ማትረፍ ነው ብሎ ማመን እና በተግባርም ማስመስከር ያስፈልጋል። ዛሬ የፉክክር ጊዜ አይደለም። እንደሚታወቀው ለነጻነት ለሚደረገው ትግል አማራውን ሊደግፍ የሚፈልግ ማንም የጎረቤት ሀገር ወይም ኃይል የለም። በእንዲህ አይነት አስከፊ ሁኔታ ላለ ሕዝብ ነጻነቱን ለመጎናጸፍ ያለው ብቸኛ አማራጭ የራሱ ትግል ብቻ ነው። ስለዚህ በቅድሚያ ጭንቅላታችንን እንጠቀም። እና ከመጥፎም መሀል ቢሆን ጥሩ ነገር እንዴት ማፍለቅ እንደምንችል እናስብ፤ ከዚያም በሀሳቦች ዙሪያ እንወያይ፤ ከሁሉም አቅጣጫ መዝነን የሚሻል ነው ያልነውን ሀሳብ በተግባር ለማዋል እንጽና። የትኛውም አማራ የዐዕምሮ/ የግንዛቤ ችግር እስከሌለበት ድረስ በአማራ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ከማንም በላይ ያብሰለስለዋል።
ብአዴን ሙሉ በሙሉ የወያኔ አገልጋይ የሆነ ድርጅት ነው፤ አባላቱም በሕዝባቸው ላይ የሚደርሰው ዘርፈ ብዙ ግፍ የማይቆረቁራቸው ህሊናም ልቦናም የሌላቸው ባዶ ሆድ የተሸከሙ ፍጡሮች ናቸው ብሎ ማሰቡ ትክክል አይደለም። የአማራ ካባ ደርበው አማራውን ለማስጠቃት በአመራርነት የተቀመጡትን ሳይሆን በተለያዩ አስገዳጅ ሁኔታወች አባል ሆነው ግን እንደማንኛችንም የሚታመሙ ብዙወች ይኖራሉ። አዎ እኔም ብሆን በአማራው ላይ አዲስ ነገር በደረሰ ቁጥር “የወያኔ ተባባሪ ሆነው አስጨረሱን፤ ህሊና የሚባል ያልፈጠረባቸው ከንቱወች” እያልሁ በብአዴን ውስጥ ያሉትን ሁሉ በጅምላ ስከስ ኖሪያለሁ። ይኸ ድርጊቴ ግን ትክክል አልነበረም። በድርጅቱ ውስጥ በተለያየ የስልጣን ደረጃ ያሉትን አማራወች በሚያምኗቸው ሰዎች አማካኝነት ቀርበን እንዲተባበሩ ማድረግ እንችላለን። አማራ እኛ ብቻ ሳንሆን እነሱም ናቸው። ትንሽ ትልቅ የሚባል አማራ ሊኖር በፍጹም አይችልም። ጥቃቱ የጋራ ነው። ይህን በተመለከተ ተቀራርበን መነጋገርና በጋራ መታገል ይኖርብናል። በጣሊያን ጊዜ ከጠላት ወግነው ከጎዱን ይልቅ ከጠላት ተጠግተው የጠቀሙን ይበልጣሉ። ከስሜታዊነት ወጥተን አስፍተን ማሰብ ካልቻልን ጉዟችን ባለንበት መርገጥ ይሆናል።
ስለዚህ የትኛውም የአማራ ተወላጅ የራሱን፣ የቤተሰቡን እና ለመከራ የተጋለጠውን የወገኑን ጥቃት ለመመከት ያስችላል ብሎ ያሰበውን ሀሳብ ቢያካፍል ወይም ተደራጅቶ የድርሻውን ሊያዋጣ ቢነሳ በአሸማቃቂ አነጋገር ቀልቡን ገፍፎ እንዲያፈገፍግ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ነገሮች የሚገለጹባቸው ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ሊኖሩ ይገባል። ሁሉም አማራ እኩል ዕድል ከተሰጠው እያንዳኑ ለድርጅቱ ታማኝ መረጃ አቀባይ እና ተዋጊ ኃይል ሆኖ እንደሚሰለፍ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። እንታገልለታለን የምንለው የሕብረተሰብ ክፍል አባል/አካል ስሜት የሚያደፈርሱ፣ ክብርን የሚገፍፉ ንግግሮችን ማድረግ/ጽሁፎችን ማውጣት ትክክልም ጠቃሚም አይደለም።