June 8, 2017
15 mins read

ሰውም እንደ ጊንጧ፤ – ይገረም አለሙ

ጊንጥ በመስክ ላይ ሆና በድንገት አካባቢው በውኃ ይጣለቀለቅና ነብስ ውጪ ነብስ ግቢ ጭንቀት ውስጥ ትገባለች፡፡ህይወቷን ለማትረፍ የምትችልበት መንገድ  ፍለጋ ዙሪያዋን ስትቃኝ በቅርብ ርቀት ኤሊን ታያትና ኤሊ ሆይ! እባክሽ አንች ውኃ አያጠቃሽምና አድኒኝ፣ ጀርባሽ ላይ አድርጊና ከዚህ መአት አውጪኝ ብላ ትማጸናታለች፡፡ ኤሊም የጊንጥን ባህርይ  ታውቃለችና ማዳኑን አድንሽ ነበር ነገር ግን አንች የንክሻ አመል ያለብሽ ዘሮቼን በንክሻ የጨረሽ ነሽና ትነክሽኛሽ አይሆንም  ትላታለች፡፡ ጊንጧም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ  አድኒኝ ብዬ ለምኜሽ እንዴት እነክስሻለሁ አላደርገውም እባክሽ ህይወቴን ታደጊያት በማለት አጥብቃ ስትለምናት በዛ ሁኔታ ጥላት ለመሄድ ዔሊ ሆዷ አልጨቅን ስላለ ጀርባዋ ላይ አስቀምጣ ዳር ስታደርሳት ከውኃው መውጣቷን ከአደጋው መዳኗን ያረጋገጠችው ጊንጥ ትነክሳታለች፡፡ ኤሊም የፈራችው፣ የጠረጠረችው ንክሻ ሲደርስባት ምን ብለሽ ነበር እንዴት ትነክሽኛለሽ ስትላት የጊንጧ ምላሽ አዝናለሁ ላለመንከስ መተው አልቻልኩም አመሌ ስለሆነ የሚል ነበር፡፡

ዙሪያ ገባችንን ስንቃኝ፣ የሚጻፍ የሚነገረውን ስናይ እንደ ጊንጧ አመል ሆኖባቸው አለያም ስራቸው ሆኖ ክፍያ የሚያገኙበት ወይንም በሎሌነት አድርው ለጌቶቻቸው እጅ መንሻ የሚያቀርቡት  ካልተናከሱ መኖር የማይችሉ ብዙ ሰዎችን እናገኛለን፡፡ጊንጧ ዔሊዋን እንደነከሰቻት በአካል አግኝቶ መንከሱ ባይሆንላቸውም ካሉበት ሆነው ከሚስቶቻቸው ጉያ ተሸጉጠው አለያም ከማጀት ሳይወጡ ምላሳቸውን ስለው ብእራቸውን አሹለው ለምንና ማንን  እንደሚናደፉ እንኳን በውል ምክንያት ሳይኖራቸው የሚራመደውን ትንሽም ቢሆን እንቅስቃሴ የሚያደርገውን ሁሉ  በቃላት የሚናደፉ በብልግናቸው የሚወርፉ ብዙ ብዙ እያየን ነው፡፡ በተለይ የሀገር ቤቱ ትግል ሲያተኩስ የፖለቲካው መድረክ ሲሟሟቅ በተግባሩ እነርሱ የሉበትምና በመድረኩ ላይ በሚታዩት በመስኩ ላይ በተግባር በሚገኙት ወገኖች ላይ ይዘምታሉ ሎሌዎቻቸውን ያዘምታሉ፡፡ እንዲህ የሚያደርጋቸው ታዲያ አመላቸው ወይንም ቅናታቸው ወይንም ክፍያቸው ነውና ነክሰው ማድማት ነድፈው ጉዳት ማድረስ ባይችሉም  ግዜ እየጠበቁ ብቅ ከማት አይቦዝኑም፡፡

ከሚናገሩት ከሚጽፉት (ከዚህ የዘለለ ተግባር የላቸውም) ድርጊታቸው  ማረጋገጥ እንደሚቻለው እነዚህ የጊንጥ ባህርይ የተላበሱ ወገኖች  ከወያኔ ተስማምቶ አለያም ጎመን በጤና ብሎ የሚኖረውንም ሆነ እኔ ከደላኝ ምን አገባኝ አለም ደህና ሰንብች ብሎ የተኛውን ወይንም በአፉ ከማውገዝ በመግለጫ ከመፎከር ያለፈ እንቅስቃሴ የማያሳየውን መንደፍ አይደለም እስከ መኖሩም አያውቁትም፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪው ዓለም በጎሳም ሆነ በሀራዊ ስም የሚጠሩ ብዙ ድርጅቶች አሉ፣የራዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎችም እንዲሁ፣ ተዲያ ጊንጦቹ መንከስ መንደፉ ባይሆንላቸውም የቃላት አረራቸውን የሚተኩሱት የሀሜት አሉባልታ ናዳቸውን የሚለቁት በእነማን ላይ አንደሆነ የአደባባ ምስጢር ነው፡፡ ግን ለምን?

ይሄ ነው እንግዲህ  ንክሻቸው እንደ ጊንጧ አመል ስለሆነባቸው ነው ከማስባል ይልቅ ለዓላማ የሚፈጽሙት፣ በእቅድ የሚከውኑት ተግባር ነው ለማለት የሚያበቃው፡፡ አመል ከሆነ ከቆመው እንደውም የተኛው ነበር ለንክሻ የሚቀለው ለመንደፍ የሚመቸው፡፡ የእኛ የሰዎቹ ጊንጦች ግን የሚራመደውን እየተከተሉ፣ የሚንቀሳቀሰውን እያነፈነፉ ነውና ንድፊያ ንክሻቸው ጉዳት የማያደርሱ ከመሆናቸው አንጻር ንቆ መተው የሚቻል ቢሆንም የሚሰሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው የሚባልላቸው ባለመሆናቸው ለይቶ ማወቁ፣ ነቅቶ መጠበቁና መጠንቀቁ ቢበጅ እንጂ አይከፋም፡፡

እነዚህ ወገኖች መገለጫ ተግባራቸው ተመሳሳይ አረ እንደውም አንድ ቢሆንም ከእነርሱ ማንነትና ከአሰማሪያቸው ምንነት አንጻር ሲታዩ ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ለሥልጣን እድሜው መርዘም ያዋጣኛል የሚለውን ማናቸውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የማይለውና ለዚህ ይበጀኛል ካለ ከዲያቢሎስም ጋር ቢሆን ከመስራት የማይመለሰው ወያኔ አሰልጥኖ የተለያየ ጥብቆ አልብሶና ርስ በእርስም እንዳይተዋወቁ አድርጎ  የተለያየ ተልእኮ ሰጥቶና ስራ መድቦ በሁሉም ቦታ ያሰማራቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ግራ ቀኝ ማየት፣ ወደ ፊትና ወደ ኋላ ማመዛዘን፣ የሚያዩትን ከተሰጣቸው ስልጠና  ከተነገራቸውና በየጊዜው ከሚነገራቸው ነገር ጋር ማመሳከርና ማመዛዘን የማይፈቀድላቸው ከመነሻውም ይህን ማድረግ የሚያስችላቸውን የአእምሮአቸውን ክፍል የተሰለቡ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው እንድ መቅረጸ ድምጽ የተጫነባቸውን እንደ ገደል ማሚቱ ወይንም በቀቀን የተነገራቸውን ከመናገርና ከመጻፍ ውጪ የሚሰጣቸውን ምላሽ መስማት የሚለገሳቸውን ምክር መቀበል የማይሆንላቸው፡፡ ስለሆነም ለእነዚህ ምላሽ መስጠትም ሆነ አተካራ መግጠም የእነርሱ አጯጯሂ በመሆን ተልእኮአቸውን ከማሳካት ባለፈ የሚፈይደው ነገር የለምና ለይቶ በማወቅ ንቆ መተው ሌላውም እንዲያውቃቸው ማድረግ ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡

ሌለኞቹ እንዲሁ የየራሳቸው ዘርፍ አላቸው፣ ዋንኛ ሊባሉ የሚችሉት እነርሱ ሊሆኑ የሚመኙትን ግን መሆን ያልቻሉትን ሌሎች መሆን ሲችሉ፣ ትንሽ የፖለቲካው አየር ሲያተኩስና መሆን የቻሉት በየመድረኩ ሲታዩ በእውን በህልማቸው የሚቃዡለት የሚቃዡበትን የምን-ይልህ ቤተ መንግስትን የተቀደሙ እየመሰላቸው ከሰይጣናዊ ቅናት በሚመነጭ ምቀኝነት የሚያደርጉት ነው፡፡ ቤተ መንግሥቱ ቢቀር የዚህ ወይንም የዛ ድርጅት መሪ ተብለው በየደረሱበት  ጭብጨባ ሲነጉድላቸው፣ ብሩ ሲጎርፍላቸው፣ አንቱታ ሲቸራቸው ማየትን የሚመኙ ነገር ግን የሚመኙትን ሆኖ ለመገኘት  ለዛ የሚያበቃ ዝግጅቱም፣ ብቃቱም፣ ቁርጠኝነቱም፣ ወዘተ የሌላቸው ሆኖ ሳይሳካላቸው አመታትን ያስቆጠሩ ሌሎች በተግባር እንቅስቃሴያቸው የህዝብ አክብሮት ሲቸራቸው ውዴታና ፍቅር ሲዘንብላቸው ለተግባራቸው ማስተግበሪያ ርዳታ ሲጎርፍላቸው አይናቸው ደም ይለብሳል፣ ጨጓራው በብሽቀት አሲድ ይረጫል፣ ይህን ተከትሎ እንደ ጊንጧ መናከስ መናደፍ እንደ መንደር አውል አሉባለታ ማውራት ስድብና አሽሙር መንዛት ወዘተ ስራቸው ይሆናል፡፡ ብዙ ርቆ መሄድ ሳያስፈልግ ያለፉትን ሁለት አመታት ለአፍታ መለስ ብለን በእክሮ ብንቃኝ በዚህ መስመር የተሰለፉትን ሰዎች ለይቶ ማውጣቱ ብዙም የሚቸግር አይሆንም፡፡ በተለይ ማህበራዊ መገናኛውን የመጠቀሙም የመበለቱም አቅሙ ላላቸው፡፡

በዚህ ጎራ ያሉት ሌሎቹ  ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ ዝም ብለሽ ተቀበይ የሰጡሽን ብቻ አይነቶች ናቸው፡፡ ከላይኞቹ ጋር የተዛመዱበት ወይንም የታጠበቁበት ምክንያት ባይታወቅም ከእነርሱ የሚነገራቸውን ብቻ እየተቀበሉ በሉ በተባሉት ልክና መጠን የሚጮሁ ከቻሉም የሚናደፉ ናቸው፡፡ ስለሚናጋሩትም ሆነ ስለሚጽፉት ምንነት፣ ስለሚሳደቡት ሰውም ሆነ ድርጅት ማንነት ቀርቶ ስለሚያሰማሩዋቸው ሰዎች ዓላማን ግብ ተልኦኮና ድርጊት መረዳት ቀርቶ  በመጠኑ እንኳን የማያውቁ  አለማወቃቸውም ደንታቸው የማይሰጣቸው ናቸው፡፡ እንደ ሰው ሲያስቡት ሰው ዝም ብሎ የሚጮህ (ምን እንበለው)? ሲሆን  አሳዛኝም አሳፋሪም ነው፡፡ ህሊና የሚባልን ትልቅና ታላቅ ነገር እንዲህ እንደ አልባሌ እቃ አውጥቶ ማስቀመጥ ይቻላል እንዴ! ውሻ እንኳን ባለቤቱ ጃስ ሲለው እንዲነክሰው ጃስ የተባለበትን ሰው የሚያውቀው ከሆነ በባለቤቱና በሰውየው መካከል ሆኖ ግራ በመጋባት ስሜት ጅራቱን በማወዛወዝ ይቆማል የጌታው ትእዛዝ ቢበረታበት ግፊቱ ቢያይልበት ወደ ሰውየው ዞር እያለ በለሆሳሳ  ይጮኻል እንጂ ለመናከስ አይጋበዝም በጌታው ትእዛዝ ተደፋፍሮ ሰውየው ላይ ልከመር አይልም፡፡ እንዴት የሰው ልጅ ከዚህ ያንሳል፡፡

ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን እንዲህ መያዣ መጨበጫ ያጣው የተቃውሞው ጎራ ነገር ግራ ቢገባው የሚነገረው የሚሰራው እንቆቅልሽ ቢሆንበት እንዲህ ብሎ ነበር፡፡                                 .                                                                                                                  « እኛ ምሁራን የምንባለውና ተቀዋሚ ፖለቲከኞች እሚባሉት ጭምር የዓለም ህብረተሰብ እንቆቅልሽ ነን፡፡ ለስሟ መጥሪያ ቁና ሰፋች ብቻ ነን፣ህዘቡን ርስ በርሱ እያጨፋጨፍን በዲስኩርና በድርሰት ብቻ አፍ ስንካፈት እያንዳንዳችን በሀቀኝነት የህዝቡ ወገን ሆነን የምንቆምበት ጀንበር እየጠለቀብን ነው፣ እንቆቅልሽ ነን፡፡  »  ጸጋየ በአካል ከተለየን አሰራ አምስት አመታት አልፈዋል፡፡ የባሰ እንጂ የተሻለ ነገር የለም፤ እንቆቅልሻችን እንዲህ ፈቺ አጥቶ ይልቁንም ተባብሶ ተመሳጥሮ ነገሩ ለከት አጥቶ ቢመለከተው ምን ይል ነበር፡፡

ይሄ እንቆቅልሻችንም መሰለኝ ጌትነት እንየውን እኛው ነን ብሎ ስንኝ ለመቋጠር ያበቃው፡፡

ካሳለፍነው ህይወት ካለፈው መከራ
መማር የተሳነን ደመና ወራሾች፣
የሞትነውም እኛ ያለነውም እኛ
ከፋይም ተቀባይ እኛው ነን ባለእዶች፡፡

 

 

 

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop