የመቅደላው ደባ ቋጠሮ
የተቀበረው በቂም ጓሮ
የምስጢሩ ገመና
ለሥልጣኑ ንግሥና
ከጠላት ጋር ወግኖ
በተቸረው ኃይል መቅኖ
መይሳውን አስገድሎ
ለመግዛት ተደላድሎ
በትረ መንግሥቱን ምራጭ ካሳ
የጨበጠበት ድርጊት ጠባሳ
ደረስጌን በውቤ ብሎ
የቂም ብድሩን ከፍሎ
የጎንደሮች መሬት ቁርሾ
የበደሉ ዋይታ ሙሾ
የግፉ ክፋት ገመና
ይደረደራል ገና
በበገና በበገና።
ያችን የሙታን እናት
አጉል ድከሚ ብሏት
ያለ ፋይዳ ከንቱ ልፊ
ዘርሽንም በዘር አጥፊ
ለማለት ይመስላል መለእክቱ
ነገረ ሥራው ኩነቱ።
ለባለ ቀኑ ድሎት
የማይጓደል አቅርቦት
ይረጋገጥ ዘንድ ታልሞ
የራሱን ኩራዝ አጨልሞ
በየመብራቱ ምሰሶ ስር
ዘብ መቆሙ ደብረታቦር
ምፀቱ ለገብርዬ… ለገልሞ
በአግራሞት አስደምሞ
የትንብቱ ቅላጼ መዋዕሉ
ለካስ ጊዜ ኖሯል ባለድሉ።
ለጎንደሮች መከራ
ለባለ ጊዜው ጮራ
ያብርሆት ነገን ሲዘራ
ጊዜ በይኖ ሁሉንም
ሲያበራና ሲያጨልም
ኩራት ለሚሰማት ለባለ ጊዜዋ
ለዕልቂት ዘማሪዋ
ሞቷን በቂም ቋጥራ
መቃብሯን ቆፍራ
ባለቀ ቀን ኗሪ
ልጡ ለተራሰው በዕዳዋ ተጧሪ
ለወራሿ ትውልድ እዘኑ ለቀሪ።
አብርሃም በየነ