ጠላታችን ነግሶ በደም የሚኖረው ሰው-በላው ስርዓት
የወያኔ መንግስት ህጻናት ገዳዩ በትረ-አጋዚ ህውሃት፣
ምን ነክቷቸው ይሆን የጥበት ቁንጮዎች እነ አባ ሜንጫ
ምሁር ነን የሚሉ የጥላቻ ጠበብት የሰይጣን መፈንጫ፣
አውሬው ተቀምጦ የሁላችን ጠላት
እምዬን ጠመዱ ተመካከሩባት
አገሬን ሊያጠፉ ዘግተው አሴሩባት
የናት ጡት ነካሾች ኢትዮጲያን ሊያፈርሷት፣
ዥጉርጉሯ ነብር ቁስል ቢበዛባት
ጅቦች ተጠራሩ ቁርሳቸው ሊያደርጓት፣
ቀን አይቶ እንዲነሳ ተላላፊ ተውሳክ ጥገኛ በሽታ
እምዬ ስትደክም የገባች መስሏቸው ከሚሞቱት ተርታ
ልጆች እንደሌሏት ቀድመው የሚሰዉ ሊሆኗት መከታ
ዘረኞች ፎከሩ፣ ተስማሙ፣ እማማን ሊያጠፉ በመለስ በሽታ፣
ያለቀውን ወጣት መሰላል አድርገው
ኢትዮጲያዊነትን አጥላልተው ተዋግተው
ተረት ተረት ታሪክ፣ ጥላቻ አሰራጭተው
እቅዳቸው ሆኗል፣ ንጉሣን ሊሆኑ በየመንደራቸው፣
ደም እንደጎርፍ ፈሶ፣ በሃረር በባሌ በሸዋ በአርሲ በጎንደር በጎጃም
የወላጆች እንባ ወደ አምላክ ሲፈስ ፍትህን ፍለጋ ከእውነተኛው ዓለም
ለአገር የተሰዉት ቃላቸው ይህ ነበር፣ ለሞት ያበቃቸው፣ የወጣቶቹ ህልም
ፍትህ እንዲሰፍን በኢትዮጲያ ምድር፣ ዘረኝነት ጠፍቶ ሰብዓዊነት ይቅደም፣
የወጣቶቹ ራዕይ ወዳው ተካደና እንዳልሆነ ሆኖ ጭራሽ ተቀያይሮ
ጥላቻ ተዘራ በህሊና ቢሶች ሰልጥነው በወጡ ከወያኔ ጉያ ከገንጣዮች ጓሮ፣
የመለስ በሽታ በነሱ ላይ ሰፍሮ ቤቱን ሰርቶባቸው
በጭንቅላታቸው የጥላቻውን ድር ስላደራባቸው
እምነትን ከእምነት፣ ዘርንም ከዘሩ ማጣላት ስራቸው
ተምረናል ቢሉም፣ ከዘረኝነት ዉጭ ማሰብ ተሳናቸው
በሚነግሩንና በሚያከናዉኑት እኩይ ተግባራቸው
በሩቅ ይኑሩ እንጂ፣ ከወያኔ ጋራ ፍጹም አንድ ናቸው።
ወለለተ አገሬ
ታህሳስ 24፣ 2009 ዓ. ም