ቢቸግረኝ እንጂ ለሦስት አካላት ሊያውም በቦታም በአስተሳሰብም ለሚራራቁ ዐይንና ናጫዎች በአንድ ጦማር “ይድረስ” ማለት ሰማይን ከምድር አጣብቆ የመስፋት ያህል ነው፡፡
እውነቴን ነው ከሰሞነኛው አጓጉል ክራሞቴ እንደዛሬ ጧት የተደሰትኩበት ጊዜ የለም፡፡ የደስታየ ምንጭ ደግሞ ኢሳትና ኦኤምኤን ናቸው፡፡ ይልመድባቸው፤ ብዙዎችን አስደስተውናል፡፡
እንደምታውቁት ሊቀ ጥልሚያኮስ ወሕወሓት መለስ ዜናዊ ከሞተ ወዲህ በተለይ ከየቋጥኙ ጋር እየተላተመ በዕውር ድምብር የሚጓዘው ወያኔ ይሄን ሰሞን ሁሉን የዜና አውታር ዘጋግቶ ዐይናቸውን እንዳልከፈቱ የውሻ ቡችሎች አድርጎናል፡፡ በዚህ መሀል ግን ኢሳትና ኦኤምኤን (ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ) የኢትዮጵያን የጥቅምት ነፋሻማ አየርና የወያኔን አፈና ተቋቁመው መረጃ እያደረሱን ነው – ይህ አንደኛው ግን በአንጻራዊነት አነስ ያለው የደስታየ ምንጭ ነው፡፡ ይገርማችኋል – ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔት በመዘጋቱ ፌስቡክ የለ ኤሜል፣ ዩቲዩብ የለ ትዊተር … በቃ … በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ 100 በማይሞሉ የትግራይ ማፊያዎች በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ለመኖር ተገደናል፡፡ መረጃ የምናገኘው በስማ በለው ወይም አልፎ አልፎ ብልጭ ስትል በምናገኛት የኢንተርኔት ዕድል ነው፤ የሞባይል ኢንተርኔት ከቆመ ቆዬ – ከዐዋጁ በፊት በጣም ቀደም ብሎ ነው የተዘጋው፡፡ የመስመሩ ግን ብዙ ችግር ስላጋጠማቸው ሁሌ ባይሆንም አልፎ አልፎ ይለቁታል፡፡ እንዲያው ለነገሩ ግን ይሄ “ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ” የሚሉት ጉደኛ ሰውዬ ምን እስክንሆን እየጠበቀ ይሆን? መቼም እየደረሰብን ያለውን ሁሉ ያውቃሉ፡፡ እነሱ ከፈለጉ የበላነውን ቁርስ ከነዓይቱና መጠኑ ሳያውቁ ይቀራሉ? እንዴ፣ የነሱ ዝምታና የወያኔው ጭካኔ ቀጥተኛ ዝምድና ያለው ለመሆኑ እኮ እንኳስ ጡት ያልጣለ የሰው ዘር ጦጣና ጅንጀሮም ሳያውቁት አይቀሩም፡፡
እነወያኔች እንዲህ ሁሉን ነገር ዘጋግተው የነሱንም ሞት የሚያረዳ የመገናኛ አውታር እንዳይጠፋና ሞታቸው እንደኛው የውሻ ሞት እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ (የባልና የሚስቱን ቀልድ አዘል ጨዋታ ባጭሩ ላጫውታችሁ – ባልዬው ሚስቱ አናዳው ኖሮ “ሊቀጣት” ይፈልግና የጎጇቸውን በርና መስኮት መዘጋጋት ይጀምራል አሉ፡፡ ቤቱ አንድም ቀዳዳ እንዳይኖረውና ሰው ገብቶ እንዳይገላግለው ብዙ ሲማስን ሚስት ታይና “ግዴለህም – ያን ያህል አጠባብቀህ አትዝጋው፤ ቀዳዳ መኖሩ ላንተ ወይ ለኔ ይጠቅመን ይሆናል” ብላ ብትለምነውም አሻፈረኝ ብሎ ጥርቅም አድርጎ ይዘጋና ድብድቡን ይጀምራል፡፡ ሚስት ሞገደኛ ነበረችና አንዴም ሳትመታ ባሏን መሬት ላይ በመዘረር ትደቃው ጀመረች፡፡ ያኔ ባል “ተጋደልን! ድረሱልን!” እያለ እሪታውን ያቀልጠዋል፡፡ ጎረቤት ይሰበሰባል፡፡ ግን በምን ይግባና ይገላግል? ሁሉም ጭላንጭል ተሸጉሯል፡፡ ከጎረቤቶቹ መሀል አንዱ ነገረኛ “ለይተህ ተናገርና ሰብረን ገብተንም ቢሆን እንገላግል” ይላል፡፡ ይህን የሰማው ባል ጊዜ ሳይፈጅና ጉዳቱ ሳያይልበት “ገደለችኝ! ገላግሉኝ!” በማለት መልእክቱን ከ“ተጋደልን” ወደ“ገደለችኝ” በመቀየር እውነቱን ይናገራል፡፡ ያኔ ሰዎቹ ቤቱን ሰብረው ይገባሉ፡፡ ሚስት ግን የዋዛ አልነበረችምና ባሏ የመንደር ተርቲበኛ ቡና ማጣጫ እንዳይሆንባት ገመናውን ልትከትለት በመፈለግ በአዲስ ጉልበት እንደማይለቃት እያወቀችም ቢሆን ቶሎ ተገልብጣ ከሥር ሆነችለት፡፡ ከገቡት የመንደር ገላጋዮች አንዱ “እንዴ፣ አቶ ማንደፍሮት ተዋት እንጂ! ሴት ልጅ እንዲህ አትመታም” ቢሉት ጊዜ “እባክህ ተወኝ ወንድሜ፣ አዲስ ግልብጥ ናት!” አለው ይባላል፡፡ ከዚህ ይሰውር፡፡)
በትልቁ ያስደሰተኝ ኦኤምኤንን ስከፍት ሁለት እንግዶች ቀርበው (ታዋቂዎቹ የሀገሬ ልጆች አቶ መሀመድ ሀሰንና ያሬድ ጥበቡ ናቸው) በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ መስማቴ ነው፤ “ይሄ ታዲያ ምኑ ያስደስታል?” እንዳትሉ፡፡ ወያኔዎች እሳትና ጭድ ለማድረግ ከ40 ዓመታት በላይ የጣሩት ክፍለ ዘመናዊ ጥረት ላይ ቀዝቃዛ ውኃ የሚቸልስ ፕሮግራም ስመለከት ያልተደሰትኩ መቼ ልደሰት? አሃ፣ በምን ቋንቋ እንደተነጋገሩ አልገለጽኩም ለካንስ፡፡ ወያኔዎች እንዳይናደዱብኝ ሳልናገር ላቆየው፡፡ ጊዜ ካገኘሁ እናገረው ይሆናልና ጠብቁኝ፡፡
(መሀመድ ሀሰን ግን “ሀሰን ዑመር አብደላ” ይሆን እንዴ? መሰለኝ – እግር ጥሎህ ይቺን ጽሑፍ ካነበብክ እባክህን አሳውቀኝማ ወንድማለም)፡፡ አቤት ርቱዕ አንደበቱ! አቤት የሃሳብ ፍሰቱ! ሲናገር ውሎ ሲናገር ቢውል እኮ አይሰለችም፤ የኢትዮጵያ ማሕፀን የተባረከ ይሁን፡፡ በነገራችን ላይ “የወያኔ ጣር(ኮማ) እውን ሆኖ ኅልፈቱን ባይ በጣም ደስ ይለኛል” ሲል እኔም ቆሜ ስለቱን ተጋራሁ፡፡ ያሬድ ጥበቡም የዋዛ ተናጋሪ አይደለም – በበረሃና በከተሞች በትግል ወቅት ያሳለፈው የሕይወት ተሞክሮውም፣ ስለወያኔ ያለው ዕውቀትም … አንደበቱን አስልተውለታል፡፡ ይባረክ፡፡
እጅግ በጣም የመሰጠኝና በሀገሬ ልጆች ሁለንተናዊ ዕውቀትና ግንዛቤ እንድኮራ ያደረገኝ ደግሞ ጋዜጠኛው ነው፡፡ ተጠያቂዎችም እስኪደመሙበት ድረስ ያ ልጅ ያሳየው የግንዛቤ ደረጃና የአነጋገር ለዛ እጅግ የሚደነቅ ነው – በውነቱ በደስታ እየተፍነከነክሁ ነው ያን ዝግጅት የተከታተልት – ግን በዚያው ሰዓት ኢሳት ላይም ቆንጆ ፕሮግራም ነበርና – ሌላ ጊዜ አየዋለሁ – እነዚህ የሐዝብ ሀብት የሆኑ ጣቢያዎች እየተናበቡ ቢሠሩ ደስ ይለኛል፤ ለምሣሌ እዚህ አማርኛ ሲሆን እዚህኛው ኦሮምኛ፤ እዚህ ዜና ሲሆን እዚህኛው ሀተታ ቢሆን ማለቴ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ተጀምሮ ስለደረስኩ የዚያን ድንቅ ጋዜጠኛ ስም መያዝ አልቻልኩም፡፡ የቢቢሲ ወይም የሲኤንኤን የኢኮኖሚ ትንታኔ እስፔሻሊስት እንጂ የአንድ አፍሪካዊ ሚዲያ ሊያውም የምሥራቅ አፍሪካ ከዚያም በባሰ የኢትዮጵያ ጋዜጠኛ አይመስልም – እንዴ፣ ገድለውናል እኮ፤ አሁን ደርግ ማለቴ ጋዜጠኛ በኢትዮጵያ አለ ማለት ይቻላል እንዴ? ይህ ልጅ ምሥጋና አበዛህብኝ ብሎ እንዳይጠላኝ እንጂ ልቅም ወርቅ ነው፡፡ ኮራሁበት፡፡ ሁሉም የሀገሬ ጋዜጠኛ እንደሱ እንዲሆንልኝም ተመኘሁ፤ ብዙዎች በባዶ ጭንቅላት ይገቡና ቃለ መጠይቃቸው እጅ እጅ እንዳለ በተጠያቂዎች ምሕረት ማለትም የበላይነት ይቋጫል(ኦ! በውጪማ እነሲሴና እነአቤም እኮ አሉ ታዲያ)፡፡ … ስለምትጠይቀው ሰው፣ ስለምትጠይቀው ርዕሰ ጉዳይ አንብበህና ሰው ጠይቀህ ካልገባህ ራስህ ጦጣ ትሆንና ትዝብት ላይ ትወድቃለህ – ዛሬ ሰው ነቅቷል ልጄ፤ ጥያቄ ቀድሞ የሚሰበሰብበትና ተንጓልሎ የሚመረጥ ብቻ የሚመለስበት የነመለስ ዘመን እያከተመ ነው፡፡ ያ ሣተና ግን ጥያቄውን ፈትፍቶ የማጉረስ ያህል ነው፡፡ ያሬድም ሙያው ኢኮኖሚ አለመሆኑን ጠቅሶ ጋዜጠኛውን በማድነቁ ወድጄዋለሁ – ይህ መደናነቅና አለማወቅን አውቆ ማሳወቅን ልንለምደው ይገባል፡፡ “ይህን ነገር አላውቀውም፤ ጠይቄ/አንብቤ ልምጣ፤ አንተ ወንድሜ በዚህ ላይ ያለህ ግንዛቤ የሚደነቅ ነው – አስተምረኸኛልና አመሰግናለሁ…” መባባል የዐዋቂነትና የብስለት ዓይነተኛው ምልክት ነው፡፡ “ሀበሻ ጉረኛ፣ ሀበሻ ሁሉን ዐዋቂ …” እየተባባልን በከንቱ መኮፈስንና አላዋቂነትን በዲግሪ ጋጋታ መሸፈንን ዕርም እንበል፡፡ በዚህ ምድር ስንኖር ከምናውቀው ይልቅ የማናውቀው በእጅጉ ይበዛልና ሁሉንም ወይም ማንኛውም ነገር የማወቅ ውዴታ እንጂ ግዴታ እንደሌለብንም እንገንዘብ – አእምሯችን በዕድሜ፣ በአቅም፣ በተሞክሮና በትምህርት አረዳድ ውስን መሆኑንም አንርሳ፡፡ ራስን መሆንን ከፈረንጆቹ እንማርና ይቺን መልካም ምግባር እንያዛት ‹ፕሊዝ›፡፡ እኔማ “ይህን ነገርስ አላውቀውም” የሚል ግልጽ ሰው ሳገኝ ነገሩን አውቆት ከሚያስረዳኝ ሰው ባልተናነሰ ነው ከልቤ የማደንቀው፡፡
ወያኔ እሳትና ጭድ ያደረጋቸው ሰዎች ተቀራርበው እየተወያዩ ነው፡፡ ኦሮምኛን በኢሳት ሳገኘው በደንብ እንደማልረዳው እያወቅሁ ዝም ብዬ ብቻ በደስታ ፕሮግራሙን እከታተላለሁ – ከልጆቼ ጋር እየተጣላሁ ጭምር እኮ ነው ታዲያ፡፡ “የማታውቀውን ቋንቋ እንዴት ትከታተላለህ?” እያሉ ወደ “ጥቁር ፍቅራቸው” የትውልድ ገዳይ ቃና ቲቪያቸው ለመሄድ ይጨቀጭቁኛል – (ይሄ ቲቪ ከወያኔ ባልተናነሰ አገር እያጠፋ ነው እባካችሁ፡፡) እኔ ግን እንዳለመታደል ሆኖ ቋንቋውን በምፈልገው ደረጃ መረዳት ብቸገርም በደስታ ሰክሬ ማየቴን እቀጥላለሁ፤ ዘፈን ከመጣም ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ነውና በዚያም ላይ የሀገሬን ዘፈኖች በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ እወዳለሁና በስሜት እከታተላለሁ፡፡
በገደምዳሜ የነገርኳችሁ ጉዳይ ነው እንግዲህ የደስታዬ መሠረት፡፡
ኦሮምኛ በሚነገርበት ትግርኛ ይነገር፡፡ አማርኛ በሚነገርበት ኦሮምኛ ይነገር፡፡ ኦሮምኛ መፈክር በሚደመጥበት ሥፍራ ሁሉ አማርኛም ትግርኛም ሌላ ሌላውም ያገራችን ቋንቋ ሁሉ ይነገር፡፡ ቢገባን እሰዬው፡፡ ባይገባንም የኛው ነውና በደስታ እናዚመው፤ እንፎክረው፣ እንዝፈነው፡፡ ያንዳችን የሁላችንም፣ የሁላችንም ያንዳችን ነውና ያንዱ አእምሯዊና ቁሣዊ ሀብት ለሌላኛችን መኩሪያና መመኪያ በመሆኑ ከልብ ተቀብለን እንውደደው፡፡ “ይሄ እኔን አይመለከትም፤ የእነእንትና ነው” ማለት ከእንግዲህ ይቅርብን፡፡ እነእንትና እኛው ነን፤ እኛም እነእንትና፡፡
እዚህች ላይ ስለኦኤምኤን ኃላፊ ከዕድሜ አኳያ ልጄ ስለሚሆነው ጃዋር መሀመድ በወቅቱ ወያኔያዊ አማርኛ አንዳንድ ነገሮች ሲባሉ እሰማለሁና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘና ሲገኝም አባቶች ምክርና ተግሣጽ እንለግስ (ይቺ “ጥቂት” አሸባሪዎች፣ “አንዳንድ” የአዲስ አበባ ነዋሪዎች … የምትል ወያኔ ከደርግ ወርሶ ያዳበራት አገላለጽ በጣም ትገርማለች፣ ዐይን ያወጣ ውሸት በአንዳንድና በጥቂት እየተቀባባ ይናፈሳል …)፡፡ ልጅ ያቦካው ለራት የሚበቃበት ዘመን መምጣት አለበት፡፡ ልጆችን ስናማ መኖር የለብንም፡፡ ትግስት፣ መቻቻል፣ መደማመጥ፣ ታሪክን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ሣይሆን ከሁሉም አቅጣጫዎች መፈተሸና እውነቱን ከውሸቱ፣ ገለባውን ከፍሬው፣ የጥላቻውን ከፍቅሩ፣ የፍቅሩን ከጥላቻው … አብጠርጥሮ ማወቅን ከወጣት የነብር ጣቶች በጉጉት የምንጠብቀው የምንጋግራቸው ቂጣዎች ሁሉ ምጣድ ላይ ከማረፋቸው እያረሩብን ክፉኛ በመቸገራችን ሳቢያ ያን መጥፎ ጠባሳ ለማስወገድ ነው፡፡ ምራቅ የዋጡ ኦሮሞዎች፣ ምራቅ የዋጡ ትግሬዎች፣ ምራቅ የዋጡ አማሮች፣ ሶማሌዎችና አፋሮች ወዘተ. … ያስፈልጉናል እንጂ ዛሩ እንዳልሰከነለት ባለውቃቢ በስሜት የሚናጡ በወጣቶች ቋንቋ የፖለቲካ ፍንዳታዎች ዕድል ካገኙ ወይም ሶበር እንዲሉ ካልተመከሩ ለተጨማሪ 25 የመከራና የስቃይ ዓመታት እንዳረጋለን፣ እናም የይኔን “ሰከን” እንዘምርና የጦር መሣሪያዎቻችን ከአፎታቸው ሳይወጡ እዛው ተቀጥቅጠው ለማረሻነት ይዋሉ፡፡
እጅግ በጣም እርግጠኛ ነኝ – የፈለገ ሰው ጉረኛ ቀርቶ ጠባብ ወይም ትምክህተኛ ይበለኝ – ወጣት ፖለቲከኞቻችን የኢትዮጵያን ሕዝብ የኔን ያህል አያውቁትም፡፡ በየትኛው ተራክቧቸው? አሁን ማን ይሙት – ልጅ ተክሌና ጃዋር የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደኔ ያውቁታል? የትኛው ድራፍት ቤት፣ የትኛው አረቄ ቤት፣ የትኛው የዕድርና የዕቁብ ስብስብ፣ የትኛው ማኅበራዊ ግንኙነት፣ የትኛው ልቅሶና የዐርባና ሰማንያ ድግስ፣ የትኛው ሰደቃ ቤት፣ የትኛው ፍጥምጥምና ሠርግ እንዲሁም መልስና ቅልቅል፣ አሃ – ሕዝብን ለማወቅ እኮ ከቲዮሪና ከስሜታዊ ጫጫታ ባለፈ በብዙ መንገዶች ልታገኘው ይገባል፡፡ እኔ እኮ ከነደቻሳ፣ ከነዘበርጋ፣ ከነፍትዊ፣ ከነስንሻው፣ ከነኡጅሉ፣ ከነቶማስና ከነማዴቦ ጋር ከልደታ እስከባታ ቢራና ድራፍት፣ ከዚያ ውጪ ባሉ ቀናት ደግሞ ዘወትርም ባይሆን በሀገር ተወላጆቹ በነቁንድፍቲና ጠላን በመሳሰሉ ወንድሞቿ የልብ የልባችንን እየተጫወትን በእግራቸው ገብቼ በአናታቸው የምወጣ ሰው ነኝ፤ ይህን ዕድል ጃዋር ያገኘዋል? አይመስለኝም፡፡ የብዙዎቻችን ፍላጎት አንድና አንድ ነው፤ እሱም – ማንም ምንም ይበል – የኢትዮጵያ አንድነት ነው፤ ሌላ ምርጫ የለንም፣ የላቸውም፡፡ ኅልውናው የሚረጋገጠው ኢትዮጵያ የምንላት ሀገር ታፍራና ተከብራ ስትኖር ብቻ መሆኑን ጤነኛ ነኝ የሚል የሁሉም ዜጋ ፍላጎት እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከወጣት ፖለቲከኞቻችን ጥቂት የማይባሉት ግን ከዚህ ማኅበረሰባዊ ግንዛቤና እምነት በመውጣት የተለዬ ሁከት ለመፍጠርና ከሕዝቡ መሠረታዊ ፍላጎት ያፈነገጠ አዲስ የአስተሳሰብ ዘይቤ ለማስፋፋት ይሞክራሉ፡፡ እንምከራቸው፤ እነሱም ሳይጎዱና እኛንም ሳይጎዱን በእንጭጩ እንመልሳቸው – አሁን በእንጭጭ ደረጃ አሉ ብለን የምናምን ከሆነ፡፡ ያደገን ዛፍ ማረቅ አስቸጋሪ ምናልባትም የማይቻል ሊሆን ይችላልና በ“ዕንቁላሌ በቀጣሽኝ”ን ብሂል በተለይ ዐዋቂዎች ማለትም ትልልቆች መዘንጋት አይገባንም፡፡
ሕወሓትን እንዲህ ብዬ “ልምከረው”ና ልሰናበት፡፡
የሕወሓትን ነፍስ አውሎ ለማሳደር የሚከሰከሰው የሀገር ሀብትና የሚገበረው የወገን ደም ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ ወያኔዎች ለአቅመ ጥፋት ከደረሱ ከ68 ዓ.ም ጀምሮ በሀገርና በሕዝብ ላይ ያስከተሉትን አጠቃላዩን ሀገራዊ የሕይወትና የንብረት ውድመት ለማስላት ምንም ዓይነት ሒሣባዊ ቀመርና ማሽን (ካልሌተር) ብንጠቀም አንደርስትም፡፡ ሽንፈታቸውን ባለማወቅ፣ የጀምበራቸውን ማዘቅዘቅ ባለመረዳት አሁን ድረስ እየፈጸሙት ያሉት ወንጀልና የክፋት ሥራ ትውልድም እግዚአብሔርም ይቅር ከሚሉት መጠን በእጅጉ የበለጠና ለውድድር የማይበቃ ነው፡፡
ስለዚህ እንዲህ እላቸዋለሁ፡፡ የእሳከሁኑ ይብቃችሁ፡፡ አሁን በዚህ በጨለመ የመጨረሻ የሚመስል ዘመናችሁ እንኳን ለልጆቻችሁ አስቡ፡፡ አዝራመው ሊከተት የመኸር ሰዓቱ ተቃርቧል፡፡ ሁሉም ነገር አልቋል፡፡ የምትሠሩት ሁሉ መቃብራችሁን ከማፋጠንና ከማራቅም ባለፈ የሚፈይድላችሁ የለም፡፡ ፀሐያችሁ እየጠለቀች እንደሆነ የናንተው የነበሩ እንደዶክተር አረጋዊና እነ ጄኔራሎች አበበና ፃድቃንን የመሳሰሉ የቀድሞ ታጋዮች በግልጽ እየመሰከሩ ነው፡፡ ወደ አቅላችሁ ተመለሱና በአለቆቻችሁ ትዕዛዝ የምትፈጽሟቸውን የዕልቂትና የመከራ ዘመቻዎች አቁሙ፡፡
ማንኛውንም ዜጋ አታሰቃዩ፤ ያሠራችኋቸውን ባስቸኳይ ፍቱ፡፡ በየበረሃው፣ በየግለሰብ ቤቶች፣ በየከርቸሌዎቻሁ፣ በየባዶስድስታችሁ ደብቃችሁ የሲዖልን ሰቆቃ የምታደርሱባቸውን ንጹሓን ዜጎች ዛሬውኑ ልቀቁ፡፡ በማሠርና በመግደል ዕድሜያችሁ ቢረዝም ኖሮ አንድም የሚቃወማችሁ ዜጋ ዛሬ ላይ ባልታዬ ነበር – ደብረ ዘይት ላይ ያ ሁሉ በሚሊዮን የሚገመት ኢትዮጵያዊ ደባደቦውን የጭራቅ ባንዲራችሁን ይዞ ባጨበጨበላችሁ ነበር፡፡ ግድያና ስቃይ ዕድሜን እንደማይቀጥል እናንተ ራሳችሁ እየተረዳችሁት ነው፡፡ ማሰር ብትፈልጉ እንኳን ሳታሰቃዩ እሰሩ – ኢሰብኣዊ ድርጊቶችን በቁጥጥራችሁ ሥር ባሉ ምሥኪን ዘጎች ላይ መፈጸሙን ግን ተውት፡፡ አይጠቅማችሁም ብቻ ሣይሆን ይከማችና በመጨረሻው ከፍላችሁ ለማትጨርሱት የመከራ ሕይወት አሳልፎ ይሰጣችኋል፡፡ በዘር ሐረግ ፕሮፓግንዳ አሳውራችሁና በተዘረፈ የሀገርና የወገን ሀብት አስክራችሁ ያሠማራችኋቸውን የአጋዚና የሚሊሻ ወታደሮች አሁኑኑ ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው መልሷቸው – ሕዝብንና ፈጣሪን ላታሸንፉ እንዲሁ አታስፈጇቸው፡፡
እያንዳንዷ የጭካኔ ተግባራችሁ ሁሉ ታስፈርድባችኋለች፡፡ የምታሰቃዩዋቸውና የምትገድሏቸው ዜጎች ለጊዜው የተሰቃዩና የተገደሉ ይምስሏችሁ እንጂ በታሪክና በትውልድ ሲዘከሩ የሚኖሩ ሰማዕት ናቸው፤ እናንተ ግን ለሥልጣንና ቂም በቀልን ለመወጣት ስትሉ በምትፈጽሙት ግፍና በደል ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እርግማንን ታስተላልፋላቸሁ፡፡ እስኪ አሁን እንኳን መብራህቱ ሥዩምን አስቡ፣ እስኪ አሁን እንኳን አወት ስብሃትን አስቡ፤ እስኪ ዛሬ እንኳን መዐሾ ዐርከበን አስቡ፤… የነዚህ ልጆቻችሁ የወደፊት ሕይወት በእናንተ ዐረመኔያዊ ተግባር ሲጨልምባቸውና መጪዎቹ የኢትዮጵያ ትውልዶች “አየሃቸው እነዚህን የሀገር ሻጭ ልጆች! አየህልኝ እኚያን የፋሽስት ልጆች! አየኸው ይሄን ጉማሬ የመሰለ ሰው አራጅ የነበረው ተስፋጋብር ዲቃላ…” እያሉ ሲያሳቅቋቸው አይታያችሁም? እስኪ አሁን እንኳን ሰው ለመሆን ሞክሩ!
እባካችሁ ከጥላቻ መንፈስ ውጡ፤ በቅድሚያም ከራሳችሁ ጋር ታረቁ፡፡ በጀመራችሁት ሕዝብን የማሰርና የማፋጀት እንዲሁም በጥይት የመረፍረፍና በእሳት የማጋየት ትልም የትም አትደርሱም፡፡ ምክሬ ያጥፋችሁና ሰውነታችሁን ከሚያንዘረዝረው የቂም በቀል ጥላቻ ውጡ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሂዱን አልቅሱ፤ ሙስሊምም ከሆናችሁ መስጊድ፡፡ “ጌታ ሆይ ለምን ተውከኝ? ለምንስ የሕዝብና የሀገር ስቃይ ምንጭ አደረግኸኝ? አያት ቅድመ አያቶቼ ምን ቢበድሉህ ይሆን ይህን መራራ ዕጣ ለኔ የሰጠኸኝ?” ብላችሁ አልቅሱበት – መሓሪ ነውና ልመናችሁን መና አያስቀርባችሁም፡፡ ለዚህ ግን ድፍረት ያስፈልጋችኋል፡፡ ከአምልኮተ ሰይጣን ባፋጣኝ ወጥታችሁ ደብዛውን ወዳጠፋችሁት ቤተ እግዚአብሔር ብትመለሱ ደግሞ ለእናንተም ለሀገራችሁ ሕዝብም ይበጃልና ይህን አጥፍቶ የመጥፋት ሰይጣናዊ መንገድ ዛሬውኑ ክዳችሁ ወደ ጠባቡ መንገድ ግቡ፡፡ ወንድማዊ ምክሬ ይሄው ነው – ጊዜ የለንም፤ እንኳስ ለእናንተና ለእኛ ለዓለምም ጊዜ የላትም፤ የእናንተ ንግርታዊ ተግባር ለዚህ ድምዳሜየ አንዱ ምስክሬ መሆኑንም አልሸሽጋችሁም፡፡
ማንም ላይሰማኝ እንዲሁ ደከምኩ፤ ግዴለም፡፡ ከኔ ብቻ አይቅር፡፡ በመጨረሻም ቀሪ ኢትዮጵያውያንን እግዜር ያጽናችሁ እላለሁ፡፡ ከተተኪ የስቃይ ዘመንም ያድናችሁ፡፡ ለቀጣይ ስቃያችን በሙሤው መዝገብ ወር ተራ ያስያዙና “ማነህ ባለሣምንት፣ ያስጠምድህ ባሥራ ስምንት” እያስባሉ የሚገኙ የማያርማቸው ጉዶች መኖራቸው አይቀርምና እንኳን ከፎከረ ከወረወረም የሚያድነው አምላክ ይጠብቀን – መቼስ ሀገሪቱ ኢትዮጵያ ሕዝቧም እኛ አይደለን? ለዚህ ለዚህማ አንታማም፡፡ (ኧረ እንዲያው ግን ይሄን የሥልጣንና የንዋይ እንዲሁም የዝናና ዐውቆ የመደንቆር ሱስና አባዜ በምን ጠበል እናስወገድ?)
ይድረስ ለኢሳት፣ ለኦኤምኤን እና ለሕወሓት በያላችሁበት – ምሕረቱ ዘገዬ (አዲስ አበባ)
Latest from Blog
በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና
ሰው ሆይ!
“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።” መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን
ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች
\በጎንደር እና ወታደራዊ ውጥረት / ፋኖ በላሊበላ ኤርፖርት ዉጊያ/ ባለሃብቱ በአዲስ አበባ ታሰሩ የቀድሞው መከላከያ አመራር ፋኖን ሸለመ || ሻ/ቃ ዝናቡ ስላወቅሁ ደስ ብሎኛል || ጥር 7 አዲስ ቪዲዮ
በጎንደር እና ወታደራዊ ውጥረት / ፋኖ በላሊበላ ኤርፖርት ዉጊያ/ ባለሃብቱ በአዲስ አበባ ታሰሩ
አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ
አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም
ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ
የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ
ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ አንድ አባውራ ምንነቱ ያልታወቀ እህል ከገበያ ገዝቶ ለሚስቱ አምጥቶ ሰጣት አሉ፡፡ ከሰጣትም በኋላ ሚስቱ ያንን እህል ፈጭታ ቂጣ ላርግህ ብትለው፣ እንጀራ ላርግህ ብትለው፣ ገንፎ ላርግህ ብትለው … ምን አለፋህ
ወሰንየለሽ ኦሮሙማዊ ዕብደት!!
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን
የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ
ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?
የቀጠለው ውጊያና የፋኖ ድሎች / የግብፅ ፣ሶማሊያ ፣ኤርትራና ሱዳን ውሳኔ / “የህወሓት መከፋፈል ገደለን “|EN