በሚያዝያ 2005 ዓ.ም. ለሚደረገው የአካባቢ፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምርጫ በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር ቦረና ዞን ነዋሪዎች በግዳጅ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ቢደረግም እስካሁን ኢህአዴግን ጨምሮ የትኛውም ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ እንዳልቀረበ ተጠቆመ ሲል ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዘገበ።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ መጠናቀቁ ቀደም ሲል በተለያ መገናኛ ብዙኃን ቢገልፅም ቦረና ላይ አንድም ተወዳዳሪ አልተመዘገበም፡፡ ኢህአዴግ ብቻውን ተወዳድሮ እንዲሳተፍ ተደርጎ በተዘጋጀው በዚህ ምርጫ ገዢው ፓርቲ በቦረና ተወዳዳሪ አለማቅረቡ ቢታወቅም የምርጫ ቦርድን አሰራር በመጣስ ጥቂት ቀናት ውስጥ እጩ ሊያስመዘግብ እንደሚችል ከስፍራው የተገኙ መረጃዎች ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
በቦረና ዞን ዕጩ ላለማስመዝገቡ ተጠያቂ የተደረጉት የአካባቢው የኦህዴድ/ኢህአዴግ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ከመደበኛ ስራቸው መባረራቸው የተጠቆመ ሲሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን የጊዜ ሰሌዳው ካለፈ በኋላ ኢህአዴግ እጩዎችን እንዲያቀርብ እየሰራ መሆኑን ምንጮቻችን ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍልም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስማ ጅሩን ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም በተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ ነኝ የሚል ምላሽ ሰጥተውናል ሲል ፍኖተ ነፃነት ዘገባውን አጠናቋል።