አመት በአል ሲቃረብ ብዙ ነገር ይናፍቀኛል፡፡ ከሁሉም በላይ፤ እንደ አፍላ ጉም የሚሳብ የሉባንጃ እጣን – ብረት ምጣድ ላይ የሚጤስ ቡና -የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን -ብዙ ፍቅር- ብዙ ፈገግታ ውልውል ይለኛል፡፡ ከመከረኛ ህይወታችን ማህል ብልጭ ብሎ የሚጠፋ አመት በአል የተባለ አብሪ ኮከብ ለዘላለም ይኑር!
አመት በአል ቀን ዋናው የደስታና የክብር ምንጭ መብላትና መጠጣት ነው፡፡
ግማሽ ፈረስ ግማሽ መልአክ የሆነው ሰው የተባለው ፍጡር እስኪረካ ድረስ መጠጣት፤ እስኪጠግብ ድረስ መብላት ይፈልጋል፡፡ ግን ምንዋጋ አለው? ባለማችን፤ ይልቁንም በአገራች እንደልብ የሚገኝ ነገር ቢኖር የምግብ እጥረት ነው ፡፡ ብዙ የሚበላ ሰው የሌላውን ድርሻ እንደወሰደ ስለሚቆጠር በማኅበረብ ዘንድ የተጠላ ነው ፡፡ የተፈጥሮን ጥያቄ ባግባቡ በመመለሱ ሆዳም አጋሰስ እየተባለ ይብጠለጠላል ፡፡ በተቃራኒው ከምግብ የሚቆጠቡ ሰዎች ይወደሳሉ ፡፡ ጾመኞች ይቀደሳሉ፡፡
የተከበረ ዜጋ በጎረቤቱ ድግስ ላይ በተጋበዘ ቁጥር እንደ የሰውነቱን ፍላጎት በማርካትና የማኅበረሰቡን የክብር መመዘኛ በማሟላት መሀል ይወጠራል፡፡ ይህንን ውጥረት የሚያረግበው ማግደርደር የተባለው፤ በመጥፋት ላይ ያለ ባህል ነው፡፡ ጋባዥ እንግዳውን አፈር ስሆንልዎ በጊዮርጊስ ”እያለ ይለማመጠዋል ፡፡ ጋሽ እንግዳ“ በቃኝ!”ኧረ በቃኝ ያለ ትንሽ ሲታገል ይቆይና ይረታል፡፡ የምበላው እርስዎ አፈር እንዳይሆኑብኝ ብየ ነው የሚል ገጽታ ተላብሶ ምግቡ ላይ ይወርድበታል፡፡ ይህ ማኅበራዊ ተውኔት ሰዎች ኩራታቸውንም ራታቸውንም እንዳያጡ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
የሆነ ጊዜ ላይ አንዱ ከገጠር ወደ ከተማ ይመጣና ከተሜ ዘመዶቹ ቤት ያንዲት ሌሊት ጥገኝነት ጠየቀ ፡፡ ማታ ዘመዶቹ አጋም የመሰለ ዶሮ አቅርበውለት እንዲበላ ጋበዙት፡፡ ሰውየው ለወግ ያህል “ ፤ አሁን በልቸ ነው የመጣሁ፤ ማርም አልስ ”ካለ በኋላ አጥብቀው እስኪያስግደረድሩት ድረስ መጠባበቅ ጀመረ:) ጋባዦች ግን በልቶ ከመጣ አናስገድደውም ብለው የራሳቸውን እየተጎራረሱ ሞሰቡን ወደ ምድረበዳነት ከቀየሩት በኋላ አነሡት፡፡ ሰውየው ባዶ ሆዱን እሪታ በሳይለንሰር አፍኖ ሲገላበጥ አድሮ ሲነጋጋ ሎንቺና ተሳፍሮ ወደ ገጠር ተመለሰ፡፡ እግሩ ገና የቤቱን ደጃፍ እንደረገጠ ሚስቱን“ አቺ! እንጀራ በጨው አምጭልኝማ ” አላት፡፡ ሚስቱ“ ዋ! በሄዱበት አገር አልበሉም እንዴ !”
ባል – “ኧሯ!አቦና ማርያም የሌሉበት አገር ህጀ ጦሜን ተደፍቸ አደርኩ እንጂ!”
ከተሜ ዘመዶቹ፤ “ ባቦ፤ በማርያም” እያሉ ለማግደርደር አለመሞከራቸው ገርሞት ነው፡፡
ባገር ቤት ጨዋታ ውስጥ ዋና ገጸባሕርይው የቆሎ ተማሪ ነው፡፡ ያገር ቤት የቆሎ ተማሪ የዶንኪሆቴ የማኪያቬሊና የካሳኖቫ ቅልቅል ነው፡፡ ገድለኝነትን ብልጣብልጥነትንና ሴትአውልነትን አስተባብሮ ይዟል ፡፡ ባንድ አመት በአል ስላውዳመቱ ብሎ ሲለምን የቤቱ አባዋራ ገብቶ እንዲጋበዝ ፈቀደለት፡፡ ራት ቀረበ፡፡ ተሜ በልቶ እንደመጥገብ ሲል ሚስትዮዋን ለማጉረስ ይንጠራራ ጀመር፡፡ አባዋራው “ተሜ አርፈህ የራስህን ብላ ፤ ሚሽቴን የማጉረስ የኔ ፋንታ ነው” ብሎ ገሰጸው፡፡ ተሜ ግን“ግዴሎትም ጌታው ላግዝዎት ብየ ነው”እያለ በባልየው ፊት በኩል አመዳም እጁን እያሳለፈ ሚስትዮዋን ማጉረስ ቀጠለ፡፡ ጉዳዩ ትንሽ እየተካረረ መጣና አባዋራውና ተሜ ትግል ተያያዙ፡፡ሚስትዮዋም በመገላገል ፋንታ ሞሰቧን አንስታ ቡናዋን እያፈላች ትግሉን በጥሞና መከታተል ጀመረች፡፡ አባዋራና ተሜ ለረጅም ጊዜ ሲታገሉ ከቆዩ በኋላ ጉልበት ወደ ተሜ እያደላ የባል መገጣጠምያ እየላላ መጣ፡፡ አባዋራው ለማሸነፍ መጣሩን ትቶ ፤ እሱንም አካባቢውንም ሳይጎዳ የሚወድቅበትን ስትራቴጂ መንደፍ ጀመረ፡፡ በተሜ ብብት መሀል ሆኖ፤ ባጭር ባጭሩ እየተነፈሰ ሚስቱን ቁልቁል እያየ “ንሽማ እቃውን አነሳሽው” አላት፡፡
ሚስት ምድጃውን እያራገበች “ሊወድቁ እንዳይሆን?”ስትል ፡፡
“አይ ነብራሬ እና አንቺ ባመጣሽው እዳ ተገትሬ ልደር?
አመት በአሉ ከገላጋይ ኣልባ ጠብ የጸዳ ይሁንልዎት!!