April 14, 2016
13 mins read

ወያኔና ትግሬ | መስፍን ወልደ ማርያም

ሚያዝያ 2008

አዳም በበደለ መድኃኔ ዓለም ካሠ፤ የተጠቀሰውን አባባል የማያውቅ ክርስቲያን ያለ አይመስለኝም፤ ለእስላሞችም ቢሆን አዲስ ነገር አይሆንባቸውም፤ አዳም ትእዛዝ ጥሶ ዕጸ በለስን በላና ተረግሞ ከገነት ወጣ፤ አዳም በደለ የሚባልበት ምክንያት ይህ ነው፤ አዳም በገነት ባካሄደው አብዮት የተነሣ የሰው ልጆች ሁሉ ከገነት እንደወጡ የሚቀሩ ሆነ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አዘነ፤ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወረደና ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ እግዚአብሔር ይህንን በማድረጉ ሰዎች ከአዳም የወረሱት የጅምላ ኃጢአት ተሻረ፤ ከዚያ በኋላ ኃጢአት የግል እንጂ የጅምላ መሆኑ ቀረ፤ ይህ የሆነው መድኃኔ ዓለም የሰው ልጅን ከራሱ ጥፋት ለማዳን በመሰቀሉ ነው፤ ሃይማኖት ለመስበክ ሳይሆን የጅምላ አስተሳሰብ ቀና እንዳልሆነ እግዚአብሔር እንዳስተማረን ለማመልከት ነው፤ በዚህም መሠረት ፍትሐ ነገሥት ልጅ በአባቱ ወንጀል አይጠየቅም፤ አባቱም በልጁ ወንጀል አይጠየቅም ይላል፤ በአስተሳሰብና በፍትሕ ጉዳይ የሰው ልጅን የእድገት በር የከፈተው ይህ ነው፤ እያንዳንዱ ሰው የሚመዘነውና የሚፈረድለት ወይም የሚፈረድበት እሱው ራሱ በሠራው ነው፤ ይህ ቁም-ነገር ዛሬ በሠለጠኑ አገሮች ሁሉ ሕግ ሆኖ የሚሠራበት ነው፤ ወደማኅበረሰብ ደረጃ ሲወርድ ቁም-ነገሩ ሰፊውን ሕዝብ አዳርሷል ለማለት ያስቸግራል።
ከላይ እንደመግቢያ ያቀረብሁት አስተያየት ከወያኔ ጎሠኛ አስተዳደር ጋር ተያይዞ የመጣ አንድ የአስተሳሰብ ግድፈትን ቢቻል ለማረም ነው፤ ይህ መሠረታዊ የአስተሳሰብ ግድፈት በአጠቃላይ የሰው ልጅን ሁሉ የሚመለከት ቢሆንም ኋላ-ቀሮችን ይበልጥ ያጠቃል፤ በተለይ ደግሞ በአንዳንድ ልዩነቶች ላይ ጎልቶ ይታያል፤ ለምሳሌ ወንዶች ሁሉ ስለሴቶች ያላቸው የተዛባ አመለካከት ከአካላዊ ልዩነት ተነሥቶ አእምሮንና መንፈስንም ጨምሮ ሴቶችን ከወንዶች በታች ያደርጋል፤ ዛሬ ሴቶች ያልገቡበትና ያልተደነቁበት ሙያ ባይኖርም አንዳንድ ወንዶች አሁንም አሮጌ አስተሳሰብን ይዘው የቀሩ አሉ፤ እንዲሁም ስለጥቁሮች ያረጀ አስተሳሰብ ይዘው የቀሩ ነጮች አሉ፤ ክርስቲያኖችም፣ እስላሞችም እንዲሁ፤ በእውቀት ዓለም አጠቃላይ ወይም የጅምላ አስተሳሰብ የሚፈቀድበት ጊዜ አለ፤ ይህ የሚሆነው ተጨንቀው፣ ተጠብበው፣ ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ነው ወደማጠቃለያው የሚደርሱት፤ ሁለት ነጫጭ ውሻዎችን ያየ ሰው፣ ሁለት ነጫጭ ውሾች አየሁ ቢል እንቀበለዋለን፤ ነገር ግን ውሾች ሁሉ ነጫጭ ናቸው ወደሚል ማጠቃለያ ቢደርስ የከረረ ሙግት ይነሣል።

የቀለም ልዩነት ባለበት አገር ሁሉ ቀለም ለአስተሳሰብ ግድፈት መነሻ ይሆናል፤ ነጮች ጥቁሮችን ይንቃሉ፤ የሚንቁት አንድ ደደብ፣ ወይም አስቀያሚ፣ ወይም ባለጌ … ሆኖ ያገኙትንና የሚያውቁትን አንድ ጥቁር ሰው አይደለም፤ እንዲሁ ሾላ በድፍን አይተውት የማያውቁትን ጥቁር ሰው ሁሉ ያለምንም ሚዛን በአንድ ከረጢት ውስጥ ጨምረው ነው፤ እውነትን ለሚፈልግ በአውቀት መለኪያ ከብዙ ነጮች የሚበልጡ ጥቁሮች ይኖራሉና ጥቁሮችን በጅምላ ደደብ ማለት ልክ አይደለም፤ በውበት መለኪያም ቢሆን ያው ነው፤ በሌላ በማናቸውም ነገር ቢሆን የጅምላ ሳይንሳዊ ፈተናዎቹን ያላለፈ የጅምላ አስተሳሰብ ቁም ነገርን ያበላሻል፤ እንዲህ ያለው የአስተሳሰብ ግድፈት የሚያቀራርብና የሚያሳድግ አይደለም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደርግና ወያኔ የእውቀትን ደረጃ ሰባብረው ጉልበትን የደረጃ መለኪያ በማድረጋቸው የአስተሳሰብ ግድፈት እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ነው፤ መነሻው ጥላቻ ነው፤ ወያኔ ጥላቻን በስልቻ ቋጥሮ አመጣና በኢትዮጵያ ላይ ዘራው፤ የማሰብ ችግር ስላለ የተዘራው ጥላቻ ፊቱን አዙሮ ወደራሱ ወደወያኔም እንደሚደርስ አልተገነዘበም ነበር።

አሁን ብዙ ሰዎች የወያኔ የአእምሮ ሕመም ተጋብቶባቸው ትግሬዎችን በሙሉ ወያኔ በማድረግ ያላቸውን ጥላቻ በመረረ ቋንቋ ይገልጻሉ፤ በቅርቡ አንድ ሰው ይህንኑ እኔ በሽታ የምለውን ስሜት በፌስቡክ ላይ ገለጠና የሚከተለውን ሀሳብ ጫረብኝ፤

የእኔ አመለካከት እንደሚከተለው ነው፤ ትግሬን የማየው በሁለት ከፍዬ ነው፡– ወያኔ የሆኑ ትግሬዎችና ወያኔ ያልሆኑ ትግሬዎች፣ ወያኔን ደግሞ እንደገና ቢያንስ ለሁለት እከፍለዋለሁ፡– ዘርፎ የከበረ ወያኔና ደሀ ወያኔ፤ ዓይኖቹን ከፍቶ ደሀ ወያኔዎችን ማየት ያልቻለ ሰው ከአለ እኔ ለማሳየት ዝግጁ ነኝ፤ ጥቅም ያቅበዘበዘው ወያኔ ዘራፊው ነው፤ ግን ሲዘርፍ ያልዘረፈውን ወያኔ መሣሪያ አድርጎ ነው፤ ለምሳሌ በማእከላዊና በቃሊቲ ያሉ ጠባቂዎች ወያኔዎች የዘራፊዎቹ መሣሪያዎች ናቸው፤ ከተዘረፈው ሲንጠባጠብ ይለቅሙ ይሆናል እንጂ እነሱ መናጢ ደሀ ናቸው፤ የዘረፉ ወያኔዎች በመቀሌ ሕዝቡ ‹‹የሙስና ሰፈር›› ብሎ የሰየመውን የሀብታሞች መንደር ሠርተዋል፤ በአዲስ አበባም ‹‹መቀሌ›› ተብሎ የተሰየመውን የሰማይ-ጠቀስ ፎቆች መንደር ሠርተዋል፤ በሻንጣ የአሜሪካን ብር ወደውጭ ይልካሉ፤ ሌላም ብዙ አለ፤ እነዚህ በዘረፋ ሀብታም የሆኑ ወያኔዎች ረዳት መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙባቸው ሌሎች ደሀ ወያኔዎች እንዳሉ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ የተባረሩም ወያኔዎች እንዳሉ አውቃለሁ፤ የተባረሩበትንም ምክንያት አውቃለሁ፤ ወደመቀሌ የሚሄዱበት የአውቶቡስ መሳፈሪያም የሰጠኋቸው ነበሩ፤ ለሚያምኑኝ ሰዎች እነዚህን መረጃዎች የምሰጠው ለመመጻደቅ አይደለም፤ እውነቱን እንዲረዱልኝ ነው፤ እውነትን ለማየት የሚችሉ ሰዎች እንዳይሳሳቱ ለመርዳት ነው፡፡

ስለወያኔ ግፈኛነት፣ ዘራፊነትና ጭካኔ ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ ያላልሁት ያለ አይመስለኝም፤ ነገር ግን እንኳን ትግሬን በጅምላና ወያኔንም በጅምላ ለመኮነንና ለመርገም የአእምሮ ብቃትም ሆነ የኅሊና ጽዳት ያለው ሰው የለም፤ የወያኔን ፍርደ-ገምድልነት የሚጠላ በፍርደ-ገምድልነት በትግሬ ሁሉ ላይ አይፈርድም፤ ጥላቻ ኅሊናን ያቆሽሻል፤ ጥላቻ አእምሮን ያሰናክላል፤ ጥላቻ ወደኋላ እንጂ ወደፊት የማየትን ችሎታ ይጋርዳል፤ ጥላቻ በተለይ በማቆጥቆጥ ላይ ያለውን ወጣት እንደበረሀ ጸሐይ እርር ድብን አድርጎ ያጫጨዋል፡:

በአጠቃላይ ስለ ወያኔ ገዳይ፣ ዘራፊ፣ ቀማኛ … መሆን አንካካድም! ልዩነታችን ትግሬ ሁሉ ወያኔ ነው፤ ስለወያኔ የምንናገረው ሁሉ ለትግሬዎች ሁሉ ይሆናል የሚለው የተሳሳተ አሰተያየት ላይ ነው፤ እኔ በማእከላዊም ሆነ በቃሊቲ ጎንደሬዎች፣ ጎጃሜዎች፣ ወሎዬዎች፣ አሮሞዎች፣ ወላይታዎች … የወያኔዎች አገልጋዮች ሆነው እስረኞችን ሲያሰቃዩ አይቻለሁ፤ ትግራይም ሄጄ ከሌለው የኢትዮጵያ ክፍል የተዘረፈው ሀብት ሁሉ እንኳን ለትግሬ ሁሉና ለወያኔዎች ሁሉ እንዳልተዳረሰና ገና ከጥቂት አልጠግብ ባዮች ወያኔዎች እንዳልወጣ አይቻለሁ።

በሌላ በኩል ሲታይ ወያኔም የተነሣው ‹‹አማራ›› የሚባል ጭራቅ በዘበዘን፤ ብቻውን እየወፈረ እኛን አከሳን በማለት በ‹‹አማራ›› ላይ ወፍራም ጥላቻውን እያስፋፋ በአፈ-ጮሌዎቹ በመለስ ዜናዊ፣ በረከት ስምዖንና ዓባይ ጸሐይ ስብከት ጀሌዎቹን አሳምኖ ነው፤ ወያኔዎች ገና ሰሜን ሸዋ ሲዘልቁ የሚያዩአቸው ሰዎች፣ የሚያዩአቸው ቤቶች ውሸታሞቹ ጮሌዎች እንደነገሯቸው አለመሆኑን ሲገነዘቡ ጥያቄ ያነሡ እንደነበረ ሰምተናል፤ ዛሬም ሌሎች የመለስ፣ የበረከትና የዓባይ የመንፈስ ደቀ መዝሙሮች ኢላማውን ገልብጠው በትግሬዎች ላይ በጅምላ እያነጣጠሩ ነው፤ አንድን ከአንድ መቶ፣ ዝርዝርን ከጅምላ፣ ፖሊቲካን ከዘር መለየት የሚችል አእምሮ ሳይኖር ከአለንበት ሁኔታ አንወጣም፤ ብንወጣም ከጣልነው ጋር ለመንከባለል ነው፤ ወያኔ ደርግን ጥሎ አልተነሣም፤ እዚያው ከሬሳ ጋር ሲንከባለል ተዳከመ! የተሻልን እንሁን!
ወያኔ ሁሉ ትግሬ ነው፤ ትግሬ ሁሉ ወያኔ አይደለም፤ የወያኔ ዘረፋ እንኳን ለትግራይ ሕዝብና ለወያኔዎች በሙሉ አልደረሰም፤ በየዕለቱ በጠዋት እየተነሣች ምን እንደሆነ የማላውቀውን ዕቃ አዝላ ወደትምህርት ቤት ከሚሄዱ ልጆችዋ ጋር ከቤትዋ እየወጣች ከሰዓት በኋላ ዕቃውን አዝላ የምትመለስ ወያኔ አውቃለሁ፤ ይቺ ወያኔ (ትግሬ አላልሁም፤) በወያኔ ሥርዓት ተጠቅማለች የሚለኝ ሰው ወደሀኪም ዘንድ መሄድ ያስፈልገዋል።

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop