April 12, 2016
28 mins read

የእሳት ዲሞክራሲ ፣ የአበባ ሰብአዊነ እና የሰው ነፃነት እንደ ብረቱ ቅላት ነው – ይድነቃቸው ሰለሞን

በገላጣው ዘመን/ ያየ ከጨፈነ በማይተልቅበት

አንድ በሆኑበት/ ግልጡ እና ድብቁ  

ሰሙ ገፅ አይደለም ሸክም ነው ለወርቁ፡፡

(ግጥም፣ በእውቀቱ ስዩም፤ 2001፣127)

‹‹ሰው›› ለመኖር ሲታትር፣ ለማሰላሰል ሲጣጣር እና ለማግኘት ሲፈላሰፍ ለነገሮች የሚሰጠው ፍቺ ተስፋን የሰነቀ፣ መኖርን የሚያበረታታ፣ አብሮነትን የሚቀድስ፣ ሃሴትን የሚያላብስ በአጠቃላይ መልካም የሆነ እንጂ እኩይ ያልሆነ ሊሆን እንደሚጋባው እንስማማ፡፡ ካሂሊል ጂብራን በአንድ የግጥም ስንኙ ‹‹ጨለማ ፀሐይን ስትወልድ ተመልክተሃታልን››/ “Have you seen the darkness giving birth to the sun” ይላል፡፡ ጂብራንን ቀምሰን የሃገራችንን ባለቅኔ እናጣጥም፡፡ በህይወት ዑደት የተቋጨውን የብላቴን ጌታ ፀጋዬ ገብረመድህንን ሁሉን አቀፍ ለኢትዮጵያ ባህል እና ስነ-ፅሁፍ አበርክቶት ለማስታወስ ያህል ከሰፌዱ አንዷን ሰንደዶ በመምዘዝ እንጨዋወታለን- ለሙከራ ስለ መከራ፡፡ ዛሬ የምንስባት ሰበዝ በ1973 ታትሞ ለህዝብ ከደረሰው የግጥም መድብሉ ለመታወቂያነት የተመረጠ ነው፡፡ ይህም ባለቅኔው ለግጥሙ የሰጠውን ቦታ ያሳያል፡፡ በግሌ ይህ ግጥም የመድብሉ አቃፊ ግጥም እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ‹‹የገጣሚ ሞቱ ህይወቱ›› (እንዲል ጂብራን) በስራው ሁለገብነት፣ በስብዕናው እነከንየለሽነት፣ በኢትዮጵያዊነት ኩራት ወደር የማይገኝለትን (ክቡር) የዓለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህንን እናስበው፣ እናስተውለው፣ እንዘክረው ዘንድ ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል፡፡ በዚህ ትንታኔ በእሳት-ወይ-አበባ የተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ከግጥሙ ጭብጥ ጋር ቀርቧል፡፡

ግጥሙ የሰው ልጅ ለነገሮች ስለሚሰጠው ትርጉም ይበይናል፡፡ ይህውም፣ ሰው ለነገሮች የሚያስቀምጠው ትርጉም መልካምነቱን የሚያጣው የውስጡን እውነት ሲገድሉት፣ ነፃነቱን ሲነፍጉት እና እምነቱን ሲነጥቁት ይሆናል፡፡ በተፈጥሮ የታደለው ‹‹ሰው›› በማህበረሰብ፣ በመንግስት፣ በባለዘመን የግል/የቡድን/የሃገር እውነቱን ሲቀማ ባለመታደል የውበት ዓይን ሲታወር፣ ባህረ-ሃሳብ ሲጨልም፣ እግረ-ህሊና ሲደድር ከግጥሙ እንመለከታለን፡፡ ከግጥሙ፣ ማህበራዊ ወይም/እና ተፈትሮአዊ እንስሳው ‹‹ሰው›› የሚያስቀመጠው ህገ-ደንብ ከተፈጥሮ ሲቃረን ውጤቱን እንገነዘባለን፡፡ ‹‹ሰው›› እምነቱን ሲነጠቅ ነገሮችን በይሁንታ እና በጥሩነታቸው ማስተናገድ እና መረዳት ይሳነዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የውስጡን እውነት ሲከለከል ነው፤ በተለይም ተፈጥሮውን ሲሽሩበት፡፡ የማህበረሰብ ህግ ወይም የግለሰብ እይታ ከተፈጥሮ ሲጣላ ‹‹የሰው›› እሳቤ እና እይታ ጭለማ ይሆናል፡፡ ከመገንባት ማፍረስ፣ ከመመረቅ መርገም፣ ከመርዳት መበቀል፣ ከማስታረቅ ማናከስ፣ ከማበረታታት ማናናቅ የሚቀናው ይሆናል፡፡ እናም ብርሃናማነቱን ተነጥቆ ይታወራል፡፡ ተፍጥሮንም ማድነቅ ይሳነዋል፡፡

ባለቅኔው ‹‹ሌሊት›› ጨለማ እንዳይደል በቋንቋ ውበት ከሽኖ፣ በሃሳብ መጥቀት አርቆ፣ አይነኬ ሰማይን አቅርቦ ያስቃኘናል-ውበትን፡፡ የወርሃ መስከረምን ለዓይን ማራኪ ምድራዊ ውበት ከእኩለ ሌሊት ጨረቃ በክዋክብት ታጅባ ከምትፈነጥቀው ሰማያዊ ውበት ጋር ያነፃፅራል፡፡ በሌሊት ክዋክት እንደ ፀደይ ወቅት አበባ ‹‹በቀይ አደይ›› ያጥለቀልቁናል፣ ሰማይ ያማረ ምንጣፍ ተላብሶ ይፈካል፣ ተፈጥሮ በተፈጥሮ ያሸበርቃል፣ ምድር በጨረቃ ብርሃን ይደምቃል፡፡ በወረሃ መስከረም አጋማሽ ማለትም በእለተ መስቀል ከአዝዕርት እና ከአደይ አበባ በሚፈልቀው መአዛ ምድረ-ኢትዮጵያ ይታወዳል፡፡ በዚህ እለት ለደመራ፣ ጨረቃ የሸፈናትን ከል ገፍታ ስትፈልቅ እንደ እንቡጥ ፅጌሬዳ ናት፡፡ በመሆኑም ሰማይ ጨለማ ነው ማለት ውበትን ለማድነቅ አለመታደል፣ የምናብ አለመመጠቅ፣ በህሊናም አለመባረክ ነው፡፡ ይህን ነፀብራቃዊ ውበት ጨለማ አድረጎ መበየን መታወር ነው፡፡ ከብዙ መልካም ነገሮች መካከል ጥቃቅን ጉድፎችን አውጥቶ እንደ ማጉላት ያለ በእኩይነት የተቀነበቡ እውራን ጎራ ያስመድባል፡፡ ያለመታደል ነገር ሆኖ እንጂ ከክዋክብቱ የሚፈነጠቀው ብርሃን ከተለኮሰ ደመራ እንደሚወጣ እሳት ይፋጃል፡፡ የጨለማን ወበት አለመቀበል እቶን እያዩ እሳትነቱን የመካድ ያክል ያስነውራል፡፡

ይህ ገሃድ የወጣ ሃቅ ባለመታደል ካልተገለፀለት ግለሰብ ጋር ከጨራቃና ኮከቦች የፈነጠቀ ጨረረ ውበትን እንዳይመለከቱ የሆኑ አንድ ጉብል እና አንዲት ጉብል እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ክፍል ውስጥ የጨለማን እሳት የለበሰ አበባነት መካዱን ከላይ ባቀረበው ንፅፅር በሚገባ ጥበብ ካስረዳ በኋል በሚቀጥሉት ክፍሎች የጉብሉን እና የጉብሏን ውበት አለማስተዋል፣ በሃሳብ አለመታደል፣ በህሊና አለመጽዳት እንዴት እንደሆነ ይተነትንልናል፡፡

ጉብል በግለ ወግ ከጉብሉ ጋር ለመነጋገር አለመታደላቸውን፣ በማቀብ ስር እንዳሉም እንረዳለን፡፡ ሁለቱ ለየግላቸው በምኞት፣ በሰመመን፣ እና በጭንቀት ከመብሰልሰል በቀር በአብሮነት መወያየት አይችሉም፡፡ ይልቅስ ሁለቱን የሚገልፃቸው በዝምታ ውስጥ ያለ ዝምታ ይሆናል፡፡ ይህ ዝምታ ግን ሰላም የሰፈነበት ፀጥታ አይደለም፤ ለብየብቻ ሳግ እየተናነቃቸው በእንባ የሚርሱበት፣ በፍርሃት ውስጥ ተሸብበው ነፍስያቸውን የሚዘጉበት፣ የዋህነታቸው ያጎናፀፋቸውን የልጅነት እድሜ የሚያባክኑበት፣ በፍጡርነታቸው ፈጣሪ የቸራቸውን እውነታ የሚዘነጉበት፣ በአጠቃላይ መክሊታቸውን ሊያስጥል የታፈነ የውስጥ ሃሳብ እንደመሆኑ መጠን መስተ-ህልይ በርቅሶ ሊወጣ የሚችል አሰቃቂ ዝምታ ነው፡፡ ይህ ሁለቱን አበባ እንዳይሆኑ እሳትም እንዳይሆኑ ያግዳቸዋል፡፡ ጉዳዩን ከላይ ከተመለከትነው እውነታ ጋር ካናበብነው ውበት ማድነቅ ወይም ውበትን መቋደስ አለመቻላቸውን እንገነዘባለን- ሰማይን ጨለማ ነው ሲል አበባ እና እሳት የተጎናፀፈ ውበትን እንደካደው የምናብ ሰው፡፡

የማይወያዩት ሁለት ነብሶች አንድ ናቸው፡፡ ምስኪኖቹ ገፅ-ለ-ገፅ ተያይተው ልብ-ለ-ልብ ይናበባሉ፡፡ ለይቶ ሳይለያያቸው በእይታ እየገደባቸው፣ በይሉኝታ እንዳጠራቸው፣ በአሉ አሉ እንደለያቸው፣ ለይምሰል እንደከፈላቸው፣ ከብ ለካብ እንዳቆማቸው፣ እሳትም ሆነ አበባ እንዳላረጋቸው በቅፅበታዊ የዓይን ንግግር ሰመመናዊ ተግሳፁን ተረድታ የምር በውስጤ አርግዤሃለው ለማለት ጉብሏ ‹‹ሙት›› ብትለው በአንድነት ውስጥ ያሉ ሁለት ፍጡራን መሆናቸው ይገባዋል፡፡ እይታ ከሙት በላይ ምን ሊል ይችላል፡፡ ይህን ከዓይኗ የተረዳው ገጣሚ ግን ምላሷን በቂ ሆኖ አያገኘውም፤ የልብ ጉዳያቸው በአንዱ ጥጋት መነጋገር፣ መመካከር፣ እንደሚያስፈልገው ግን ደግሞ እንደተከለከሉ ግን ደግሞ አንድ እንደሆኑ … ግራ ቢገባው… በቃ ሁሉም ይቅር፤ ‹‹የወፎቹም ዜማ ይቅር››፣ ጨረቃንም ማድነቅ ይቅር ግን ደግሞ በይቅር ብቻ የሚቀር አይደለምና እንዴት ይቀራል፡፡ የማይያዝ፣ የማየጨበጥ ቢሆንበት፣የማያገኙት የማይተውት ቢሆንበት፣ የማይለዩት አብረው ያሉት ቢሆንበት ግራ ቢገባው … ‹‹ትዝታሽን ማሪኝ›› ሲል ይለምናታል፡፡

በይ ሕመምሽን ታረቂኝ

ሰቀቀንሽን ተማፀኚኝ

ሰመመንሽን ይቅር በይኝ

እምትምሪኝ ከሆነማ፣ ማሪኝ ፣ ትዝታሽን ማሪኝ  …

 

ጉብል በዓይኗ አልምርህም ብትለው ዘመን ተሻጋሪውን ቅኔ ይለቀዋል፡፡

ነገሩ አያድርስ ነው፡፡ ወይም የደረሰበት ብቻ የሚገባው ግን ሊገልፀው የማይችለው አይነት ነው፡፡ ሆኖም ባለቅኔው ሁላችንም ፅዋው እንዲደርስብን ያደርጋል፡፡ ደርሶኛል፡፡ በተመስጦ ግጥሙን ያነበብኩት ከሁለት አመት በፊት ሲሆን በደገምኩት ቁጥር ነብስያዬ አንደተረበሸች አለች፡፡ በጭንቅ ወልዳ የልጇን መጥፋት እንደገባት እናት ውስጤ በሃዘን ይጥለቀለቃል፡፡ ግን ደግሞ መቼም ግዜ ካለኝ ምናቤን ከልቤ አስታርቄ በመንፈስ የባለቅኔው ታሪክ ተጋርቸዋለው፡፡ የጥበብን የውበት ጥግ በቅኔው መንኮራኩር ተፈናጥጬ እታደማለሁ፡፡ እሳት እና አበባ እሆናለሁ፡፡

በአንድ ውጥን ያሉ ሁለት ነብሶች ቀርበው የጋራ ውጥናቸውን ለብቻ ከማሰላሰል በቀር ቀርበው ማውጋት አልቻሉም፡፡ ግና በአንድ አጋጣሚ በዓይን ስልምልምታ በተነጋገሩበት ቅፅበት ባለቅኔው የጉብሏ ችግሩን መረዳቷ ቢገባው ‹‹ሙት›› ብትለው ግራ ተጋባቶ ትዝታዋን እንድትምረው፣ ናፍቆቷን እንድታክመው፣ ሰቀቀኑን እንድታስታርቀው ቢለምናት ጉብል መልስ ጠፍቷት ዓይኗ ወጓን ቢገታ፣ ግንባሯ መሬት ቢመታ፣ እንባዋ በልውጣ አልውጣ ቢፈትናት … መልሷን ሳይሽት ከውጠ-ውስጠት በፈለቀ ስሜት ይንገበገባል፡፡ ትንታኔዬን ገትቼ …

ምነው ታድያን ድምፅሽ ራቀ?

ምነው ልሳንሽ ረቀቀ?…

የዓይንሽ ብረሃን ቀለስ አለየእንባ ወዝ እንደቋጠረ

ቃትቶ እንደተውተረተረ

የመከራ የጭንቅ የምጥ ስልባቦት እንዳቀረረ

የደም ወዝ እንደነዘረ

እንደተሰቀቀ ቀረ…

ላቀረበላት ‹‹የትዝታሽን ማሪኝ›› ጥያቄ መልሷ እንደፍላጎቱ ምህረት ሳይሆን አንጀት የሚያላውስ ፍርሃት ይሆናል፡፡ በጥያቄው የምትገባበት ያጣች የጉብሏ ነፍስያ ትንፋሽ ያጥራታል፡፡ የመግባቢያቸው በሯ የደረቀ እንባ አርግዞ፣ ሁለመናዋ በሰቆቃ ደንዝዞ ያማትራታል፡፡ የተረበሸ ውስጠቷ በእንባ መልክ የደም እንክብሎችን ለምድር ሲገብር ይታደማል፡፡ ሊያስተዛዝናትም ይሻል፡፡ እንባዋን አያበሰ አይዞሽ ሊላት ይመኛል፡፡ በዛውም ከአይኗ የሚፈልቁትን እሳታዊ ነበልባሎች ሊሞቅ ያስባል፡፡ አበባ የሆነውን እሳት ለውስጥ ህመሙ ፈውስ ሊፀበል፡፡ ቀርቧት የፊቷን ገፅ መዳበስ ባይችል እንኳን መንፈሳዊነትን በተላበሰ እስትንፋሱ ሊፈፅመው ይዳዳዋል፡፡ መለኮታዊ የሆነበትን ውበት በመለኮት ሊያሳካ፤ መንፈሱን ከመንፈሷ ሊያግባባ፤ ወደ ውስጠቷ ሊገባ፤ እሳት ሊሆን ወይ አበባ! ምክንያቱም ያለፍቅሯ በቀር እንባዋ ፍይዳው አይጠቅመኝም ብሎ ያምናል፡፡ እምነቱ ግን እውን አይሆንም፡፡ በዚህም መቃጠላቸው ቢበቃ ሲል ይደመጣል፡፡ ለቃጠሎ የዳረጉትን ፈጣሪውን፣ ማህበረሰቡን እና እድሉን አብዝቶ ያማራል፡፡ በልቡ የተቋጠረው ፍቅረ-ነገር ከሚችለውና ከአቅሙ በላይ ሲሆንበትም እንገኘዋለን፡፡ ቢበቃው ይመኛል፡፡ ፍላጎቱ ባይሳካ፣ ውጥኑ ግቡን ባይመታ፣ ምኞቱ ከምኞት ባያልፍ፣ አለመቻል ቢወርሰው፣ ህመም ቢተርፈው ቢበቃው ይመኛል፡፡ ከምኞት ፈቀቅ አይልም፡፡ የምኞት ምርኮ፣ የይሉኛታ ባሪያ፣ የፍርሃት አሽከር፣ የሰመመን ባላባት ነው፡፡

አረ ይብቃን መቃጠሉ፥ በዓይን ወላፈን መለብለቡ

ያለፈርጁ ያለባሕሉ፥ እሳት አይጭር ሰው በቀልቡ

ፍም አዝሎ ላይዘልቅ ልቡ፥

አጉል ምን አቀጣጠለን

በሰመመን ሟሟን እንጂ፥ በመውደድ ለምልሙ አላለን

ድባብ እንደራቃት ቆሌ

ባህር እንደገባ አሞሌ

እንዲያው በህልም አባይ ገነን፣ ለቅዠት መራወጥ ፎሌ

አረ ወዲያ ይብቃን  ይቅር

የኸ የአይን ብር ትር

ወዝ አይወጣው ድብን እርር…..

ጉብል ‹‹የምትታይ እንጂ የማትበላ›› የገነት ፍሬ ናት፡፡ እጣ ፋንታዋ በማህበረሰቡ እሳቤ ውስጥ የተቀነበበ፡፡ እሷን መንካት አይደለም መቅረብ የሚያስቀጣው፣ እሱን መቅረብ (በሌሎች) የሚያሳጣት  ነው፡፡ ሁለቱም ግን ይፈላለጋሉ፤ አንዳቸው ባንዳቸው ውስጥ ይነዳሉ፤ በአብሮነት ውስጥ ይጋያሉ፡፡ ሕልም አይከለከል፡፡ ምኞት አይታሰር፡፡ ተስፋ አይቀበር፡፡ እውነት አይገደል፡፡ ግን እሳት-ወ-አበባ መሆን አልቻሉምና ብቻቸውን በብቻነት ውስጥ ይጋያሉ፡፡ የከፈላቸውን ጋሬጣ አሽቀንጥረው አንደነታቸው ማሰሪያ ፍቅር መስራት አለመታደላቸው ያመዋል፡፡ በጋብቻ ከሆነ ለፅድቅ፣ በሴሰኝነት ከሆነም ለኀጢያት አለመታደላቸው ያንገበግበዋል፡፡ ይህን በህልም የሚደረግ እሩጫ፣ የሰመመን ውስጥ ፍጥጫ፣ የውስጥ ህመምን አለመናገር ‹‹መረገም›› ይለዋል፡፡ መረገማቸውም እውነትን በውስጣቸው ቀብረው የውሽት ከማስመሰላቸው አንፃር ይሆናል፡፡ እሷን ወግ ነው አጥሯ፤ እሱ ይሉኝታ ነው ከሉ፡፡ በማህበረሰቡ እንዳይታሙ ሲሉ የነፍሳቸውን እውነት ከፍሬነት ደጃፍ እንዳይደርስ ያጨነግፉታል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የህመማቸው ጥጋት፡፡ መዋደዳቸውን ለሽንገላ ደብቀው፣ መፋቀራቸውን በአደባባይ ክደው የማህበረሰቡ ውቃቢ አምላክ ያይብናል ሲሉ መፍራታቸው ይቆነጥጠዋል፡፡ ለማህበረሰቡ አካሄድ ሲባል ፍቅራቸውን መካዳቸው በመረገማቸው እና ባለመታደላቸው ይሆንበታል፡፡ የስቃያቸው ማብቂያ ግን አይሆንም፡፡ መተጣጣታቸው ማንነታቸውን ሲፈታተን ይዘልቃል፡፡ ያገባሉ፣ ይዳራሉ፣ ይሴሰኛሉ፡፡ የገደሉት መፈላለጋቸው ግን የገቡበት ይገባል፣ ያደሩበት ያድራል፡፡ ይፈትናቸዋል፡፡ የቱን ያህል ቢራራቁ፣ ምንስ ያህል ቢራቀቁ አንዳቸው ካንዳቸው ላይርቁ ነገር፡፡ ብቻ መሳቀቅ ነው፡፡ ሌላዋን እሱ እያቀፈ እሷን ይስላል፤ ሌላውን እሷ እያቀፈች እሱን ታያለች፡፡ ባንዷ አካል ጉብሉን ያግላል፤ ስሟን ከስሟ ያሳክራል፤ በማህፀኗ እሷን ይፀንሳል፤ ታቃፊዋን እቃው ያደርጋታል፤ ከሰውነት ያወርዳታል፤ ኃጢያት ይሰራባታል፡፡ ሁሉም በቁጭት ይለበልበዋል እና ጉብል ቢደርስብሽ ብታይው ይላል፡፡

ምነው ደርሶብሽ አይተሸው

የኔን ግፍ በሰው ውለሽው

የፍትወት ግብር ልትከፍይ የፈፀምኩትን ፈፅመሽ

በሰው አካል እኔን አቅፈሽ

በሰው ጭንቀት እኔን ፀንሰሽ፣

መውደዳቸውን ለወጉ አግዳ፣ ፍቅርን ለቧልት ክዳ፣ ለደስታ ሀዘናቸውን ሰንቃ፣ ለዘርየለሽ ገለባ አስታቅፋ፣ ለፍሬአልባ ወሬ ዳርጋ፣ ላይጠጣ የመነጨ ምንጭ አቅርባ፣ ላይፈጠር በተቀጨ ልጅነት ውስጥ፣ የማይወለድ ፅንስ አስቋጥራ፣ መኖራቸው ተንጉዳለች፡፡ ሕይወት መች ኬላ አላት፡፡ አትቆም ነገር፡፡ በቁዘማ ውስጥ ታልፋለች፡፡ ‹‹በተገማሸረ መስክ ውስጥ እንደሚብሰከሰክ ውሃ›› አለ ደራሲው፡፡ ሕይወት ሹሉክሉክ ትላለች፡፡ ስንቶቻችን ነን የሕይወታችንን ሽሉክሉኪት ለመታደም የሞከርን፡፡ እውነታቸውን በፍርሃት ውስጥ ሽሽገው፣ ፍቅራቸውን ለወግ ገብረው፣ ስሜታቸውን ለይሉኝታ ቸርችረው፣ እሳት ወይም አበባ፣ ፅድቅ ወይም ኩነኔ፣ ሳይደሰቱ ወይም ሳያዝኑ፣ በቁማቸው ሲቆዝሙ እድሜ ይሉት ነገር ድርስ ብሎባቸው እርጅት ቢሉ ምን ይውጣቸው፡፡ ‹‹ሾላ በድፍን›› እንደሆኑ ሳይተነፍሱት፣ ሣይናገሩት፣ እንዳማጡት ባክነውት አረፉት፡፡ ልጅነታቸውን ላይረባቸው እንዳልባሌ ቆሻሻ ደፉት፡፡ እንደተብከነከኑ ባከኑ፡፡ እንዲህ ሆኑ፡፡ ላይሆኑ ሆኑ፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹የከንቱ ከንቱ›› እንደለው ሆኑ፡፡

ልጅነትሽን ሳታካብች፥ ዕድሜሽን ምን ሳትሰሪበት

አባከንሽው ባከንሽበት፥

ልጅነቴን ሳላካብት፥ እድሜዬን ምን ሳልሰራበት

አባከንኩት ባከንኩበት፤

እሷን በውስጡ አዝሎ ላይ-ታች እንዳለ፤ ከልጅነት እስከ እውቀት እንደተብከነከነ፣ ምንም ቁምነገረ ሰይፈፅም ከእራሱ እንደተጣላ፣ ማንነቱ እንደተሳከረበት፣ የውስጡን ሰላም እንደ ተቀማ፣ በውበቷ እንደተሸበረ፣ እንዴት እንደሆነ ሳይገባው መባከኑ ግን ገባው፡፡ ልጅነቱን ከጎኑ አጣው፡፡

ተስፋና ምኞት ለፀጋሽ፥ ምዕጥንቱን በቻ ሳውቅበት

ነፍሴን ለነፍስሽ መስዋዕት፥ ግዳይ ስጥል ባደግኩበት

ሳንፈጠር በሞትንበት

ሳናብብ በረገፍንበት

ሳንጠና ባረጀንበት

አበባ ወይንም እሳት፥ መሆን ብቻ አጣንበት፡፡…

እንዳይሆን የለም፣ በመጨረሻ ውበትን ማድነቅ ይሳናቸዋል፡፡ ሕሊናቸው ባዶ ይሆንባቸዋል፡፡ ሁለመናቸው ከሰውነት ጎራ ይለያል፡፡ እናም ሰማይን ጨለማ ነው እንዳለው፣ አይኑ ስር ያለን እውነት እንደካደው፣ ውበትን ማገናዘብ እንደተሳነው፣ እግረ ሕሊናው እንደከረረበት ሰውዬ ይሆናሉ፡፡ ከምድር ሃሴት ይገለላሉ፡፡ አበባ ወይም እሳት መሆን እንደተመኙ፣ ስለመቀራረብ ዘውትር እንደተብሰለሰሉ፣ ስለአብሮነት እንዳለሙ፣ ለፍሬ ለመብቃት እንደታተሩ፣ ሳይሳካላቸው ይቀራሉ፡፡ ይባክናሉ፡፡ ባካናዎች ይሆናሉ፡፡

እናም የግጥሙ ማሰሪያ የሚሆነው የታፈነ እውነት ገዳይነት፣ የተደበቀ ማንነት አጥፊነት፣ ለወግ እና ለይሉኛታ የሚደበቅ ሃቅ እኩይነት፣ የድፍረት ማጣትን እዳነት፣ የአስመሳይነትን ዋጋቢስነት፣ ….ሌላም….ሌላም…ሌላም ሊሆን ይችላል፡፡ ማንነትን ከማጣት ቅጣት፣ እውነትን ካለመፈለግ መዓት፣ በሃሰት ከመሸሸነጋገል ሃጢያት እና ውበትን ካለማድነቅ ክፋት ይሰውረኝ፣ ይሰውራችሁ፡፡ ካልሰወረን ግን ማረፊያችን ወይም እርግማን ነው፣ ወይም አለመታደል ነው፣ ወይም ፍርሃት ነው፡፡

በውልደት እና ሞት መካከል በታጠረች መኖራችን ውሰጥ ተፈጥሮ እኩልነትን እንዳልነፈገን ይሰማኛል፡፡ ተፈጥሮ የመልካምነት ተምሳሌት ትሆናለች፡፡ ለምሳሌ፣ ሰብዓዊነት ውበት አለው፡፡ እንደ አበባ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ዲሞክራሲ ውበት አለው፡፡ እንደ እሳት ነው፡፡ አበባ እሳትም ነው፡፡ ሰብዊነት ዲሞክራሲም ነው፡፡ እሳትም አበባ ነው፡፡ ዲሞክራሲም አበባ ነው፡፡ ሁለቱን አቃፊ ሶስተኛው ነፃነት፣ ነፃነት፣ ነፃነት ነው፡፡ እንደ ብረቱ ቅላት ነው፡፡

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop