February 9, 2016
18 mins read

“ደንቆሮ የሰማ ዕለት ያብዳል” አሉ . . . ወይ ብሔረ-ጽጌ! – አከለው የሻነው ደሴ

ጥር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ወደ ብሔረ-ጽጌ መናፈሻ ጎራ ብዬ ነበር። ከቤት ለምን ወጣሁ መሰላችሁ ሕዝባችን ከጎረቤቶቹ፣ ከአካባቢው ሰዎች ነፃነት ይልቅ የራሱን ትንሽ ጉዳይ፣ ፌስታ፣ ደስታ፣ ጩኸት የሚያስበልጥ ገና ኋላቀር እና ጥንታዊ ስለሆነ። በተጨማሪም አገሪቱ አንድ ሰው ከጎረቤቶቹ እና ከአካባቢው ኗሪዎች ረብሻ ነፃ የሚሆንበትን አስተማማኝ ሥርዐት ስላላሰፈነች ይመስለኛል። በአጭሩ ኮንዶሚኒዬማችን ውስጥ አንድ ጉዳይ ያለው ሰው ካለ ከአካባቢው ጠፍቶ መዋል ግድ ነው። አይቻልም እንጅ ሌሊትም ጠፍቶ ማደር ይሻል ነበር። ምክንያቱም ያለው ጩኸትና ዘፈን በፍፁም ሊያስተኛ አይችልምና።

የዛሬ ሳምንት አካባቢ መብራት ለብዙ ቀኖች በጠፋበት ጊዜ እኛ ብሎክ አራተኛ ፎቅ ላይ ሰርግ ነበር። እውነት ለመናገር ሁለት ቀን ሙሉ ቀንም ሌሊትም ሰዎች ጄኔሬተር ተከራይተው በድለቃ፣ በጭፈራ፣ በዘፈን፣ በጨኸት ሕንፃውን ሲያንቀጠቅጡት ውለው አደሩ። ለመሆኑ ኢትዮጵያ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ደንነት፣ሰላምና ፀጥታ በሚመለከት ሕግ የላትምን ከሌላት በጣም ያሳፍራል፤ ካላት ግን መንግሥት በተግባር እንዲያውለውና እንዲታደገን እንማፀናለን። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ አራተኛ ፎቅ ላይ ባለሰርጎቹ ሲዘሉ ልክ አናታችን ላይ የሆነ ነገር የፈነዳ ይመስለን ነበር። እንዲህ ዐይነት ተግባር ለሕንጻውስ ዕድሜ ጥሩ ነው ወይ ሰው በሰላም የመተኛት መብቱ የሚከበርለት መቼ ነው የጋራ መኖሪያ ሕንፃ ላይ አንድ ሰው የፈለገ ጉዳይ ቢኖረው ፎቅ ላይ መጨፈር፣ መዝለል፣ መጮህ፣ ማቅራራት ይገባዋልን ሕዝቤ ሰልጥኖ ከራሱ የግል ጉዳይ አልፎ ስለ ሰዎች ነፃነት እና ሰላም ማሰብ የሚጀምር መቼ ይሆን መንግሥትና ፖሊስስ አንድን ነገር እንደ ጥፋት (ወንጀል) የሚያዩት ሰው አናቱን ሲገመስ፣ ሲደማ ወይም ሲሞት ብቻ መሆን አለበት ትላላችሁ

እኔ ግን ከዚያ ሌላ የሚያሳስበኝ ብዙ ነገር አለ። አንድ ሰፈር ውስጥ (ኮንዶሚኒየም መሃል) መኪና አቁሞ ጆሮ እሚሰነጥቅ ዘፈን (መዝሙር) ከፍቶ ሰው መረበሽ፣ መንገድ ላይ አላፊ አግዳሚውን ስለ ሃይማኖት በመስበክ ነፃነቱን መጋፋት፣ እግዚአብሔር ያለ ድምፅ ማጉያ ካልተነገረው የማይሰማ ይመስል አገር እስቲናጋ እና እቤቱ በሰላም የተኛ ሰው እስቲንቀጠቀጥ ድረስ ከየእምነት ቤቶች የሚለቀቀው ድምፅ ሁሉ በኔ ግምት ከኋላ ቀርነት እና ከኔ ውጭ ስላለው ሰው ምናገባኝ ከሚል በራስ ዙሪያ ብቻ ከታጠረ አስተሳሰብ ጋር የተያያዙ ተግባራት ናቸው። እናም እኔ እነሱ ሁሉ አካላዊ ባይሆኑም መንፈሳዊ ጥፋቶች ናቸው ባይ ነኝ። በመሆኑም እነሱን ሥርዐት የሚያስይዝ ዘመን አንድ ቀን እንደሚመጣ አምናለሁ፤ ዛሬም አጥብቄ እመኛለሁ። ያን ጊዜ ከሚናፍቁት ምስኪን ኢትዮጵያዊያን አንዱ ነኝ ማለት ነው።
ከትናንት ወዲያ ቅዳሜ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ባለሰርጎች ሙሽሪትን ምላሽ ጠርተው እና ደግሰው ለምሳ እንድንገኝ ጋብዘውን ነበር። የምላሹ ድግስ ከፎቅ ወደ ምድር ተዛወረ። እኛ እምንኖርበት ሕንፃ ላይ የልብስ ማስጫ ቦታ አለ። ከዚሁ ጠባብ ቦታ በስተግራና በስተቀኝ ሁለት መሽሎኪያ መውጫ መግቢያዎች አሉ። ለዝግጅቱ ሲባል ግን ተጠርቅመው ተዘጉ-በሸራ ታጠሩ። መሃል ለመሃል ልብስ ማስጫውን ሰንጥቆ የሚያልፈው መንገድ በድንኳን ታጥሮ የዝግጁት ዋና መድረክ ሊሆን ተወስኖበታል። እናም ቀኑን ሙሉ በጩኸት ከምሰቃይ እና መውጣትና መግባት ስፈልግም መንገድ አጥቼ ከምቸገር በሚል የተጠራሁበትን ግብዣ ትቼ መዋያዬን በሃሳብ አፈላለግኩ።
በዚህ አጋጣሚ እዚያው አጠገቤ በእግር ሃያ ደቂቃ ብቻ በመጓዝ የማገኘው መናፈሻ ስላለ፤ ወደሱ ለመሄድ ወሰንኩ። በቆስጣ ሠፈር የአቃቂን ወንዝ ግማት እየሳብኩ እና እዚች አገር ላይ የየፋብሪካው ቆሻሻ የማይለቀቅበት ወንዝ ማየት የምንችልበትን ዘመን ከየረር ተራራ ባሻገር እያየሁ ቀይ አፈር በሚባለው ሰፈር ወደላይ ወጣሁ። በአብዮት ፋና ትምህርት ቤት እና በሃይላንድ ውኃ ፋብሪካ (በሃገራችን የመጀመሪያው ፋብሪካ በመሆኑ ውኃ የሚታሸግበት ጠርሙስ መጠሪያ የሆነ ፋብሪካ ነው-ሃይላንድ) መካከል ተጉዤ ብሔረ-ጽጌ መናፈሻ ደረስኩ።

በር ላይ ሁለት ብር ከፍዬ የተሰጠኝ ቲኬት ‹‹በየካ ክፍለ ከተማ የፈረንሳይ ፓርክ፣ መግቢያ ዋጋ አንድ ብር›› ስለሚል፤ ትንሽ ቆም ብየ በማሰብ የካ ሳይሆን ነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መሆኔን አረጋገጥኩ። መናፈሻውም ፈረንሳይ ሳይሆን ብሔረ-ጽጌ እንደሆነ ለራሴ ምስክርነት ሰጠሁ። የመግቢያ ዋጋው አንድ ብር ተብሎ ሳለ ሁለት ብር መክፈል ኢትዮጵያ ውስጥ እና ለአንድ ኢትዮጵያዊ ምንም ማለት እንዳልሆነ ራሴን አሳመንኩ። ከዚህ ውጭ ጥያቄ ማብዛት ቅብጠት እንደሚሆን በተጨማሪም በአስተናጋጁ፣ በፖሊሱ ወይም በደንብ አስከባሪው ባህርይ እንዲሁም በሰሞኑ የአየር ጠባይ እና በሃገራችን የፖለቲካ ስሜት የሚወሰን በመሆኑ አልፎ አልፎ ሊያስገላምጥ እንደሚችል ስላላጣሁት ዝም ብዬ ወደውስጥ ገባሁ።

መናፈሻው ውስጥ የማየው ነገር እንግዳ እና አስደንጋጭ ሆነብኝ። ብዙ ዕድሜ ጠጋብ ዛፎች እየተገነደሱ ከወደቁ በኋላ ተቆራርጠው ተነስተዋል። ከሥር ያለው ሣርና ቅጠላቅጠልም በእሳት ይቃጠላል። ግራ ገባኝ። ዛፎች ለዚውም መቶ ዓመታትን የዘለቁ አንጋፋ ዛፎች ምን አጥፍተው እንደሚቆረጡ መገመት አቃተኝ። እዚያው እመናፈሻው ውስጥ አቃቂን ወንዝ ተሻግሬ ታችኛውን የመናፈሻውን አካባቢ ተዘዋውሬ አየሁት። በጣም ያሳዝናል፣ ያሳፍራል። ዛፎች አልቀዋል፤ አካባቢውን ለማፅዳት የተመደቡት ሰዎች በመቁረጥ፣ በማቃጠል እና በማንሳት እጅግ ይባትላሉ። ቸኩለዋል፤ ቢጠሯቸው አይሰሙም። ምናልባት መናፈሻውን ሜዳ ሆኖ የሚያዩበት ጊዜ ሳይርቅባቸው የቀረ አልመሰለኝም።

ለጊዜው እዚያ ቁጭ ብዬ ለመጻፍ ያሰብኩት ጉዳይም አልመጣልኝ ስላለ ዝም ብዬ ወዲያ ወዲህ መዘዋወር አበዛሁ። አልፎ አልፎ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ያሉ እና ታላላቆቻቸውን ያጡ ዛፎች በፍርሃት ድርቅ ብለው ቆመዋል፤ አይንቀሳቀሱም። ውስጡም ከምድረ በዳ አይሻልም። የድሮው ብሔረ-ጽጌ ዛሬ የለም። እሚገርው ግን በገላጣው ቦታ ላይ ተቃቅፈው እግር አንስቶ ዋናውን ጨዋታ መጀመር እስቲቀራቸው ድረስ ወንዶችና ሴቶች አልጋ ላይ የተኙ ያህል በፍቅር ዓለም ሲንከባለሉ ማየቱ ዐይን ማድከሙ ነው። ብሔረ-ጽጌ የድሃ የፍቅር ቦታ መሆኑ ዛሬም አልቀረም-ነገ ግን እንጃ!
ለምሳ ወደ ሳሪስ ደረስ ካልኩ በኋላ እንደገና ቲኬት ቆርጬ ተመልሼ ገባሁ። አሁን አመጣጤ ከመጀመሪያው የተለዬ ነው። የማገኘውን ሰው ሁሉ መጠየቅ እንዳለብኝ ወስኛለሁ።

“ይኸ ፈረንሳይ መናፈሻ ነው እንዴ” ቲኬት የሰጠችኝን ሴትዮ ጠየቅኳት። ቦታ የጠፋብኝ መስሏት (አበሾች ስንባል ከማዳመጥ ለመናገር ለምን እንደምንሮጥ አይገባኝም) “አደለም፣ አደለም። ብሔረ-ጽጌ ነው!” ብታዩአት በአፏ ይቅርና በእጇ፣ በእግሯ፣ በጠጉሯ ምን አለፋችሁ በልብሷ ሁሉ ለመናገር ተጥደፈደፈች።
“ታዲያ ቲኬቱ ለምን ፈረንሳይ ፓርክ ይላል”

“ቲኬት አልቆብን ተውሰን ነው።” ይቅርታ አድርግልን አጥፍተን ነው የሚል ስሜት ቢጠበቅም እሷ ግን የማይገባ ነገር እንደተጠየቀች ሁሉ ቆጣ ብሎ በከንፈሯ ወደ ውስጥ ገፈተረችኝ። ቀስ ብዬ እየተራመድኩ “ዛፉ ደሞ ለምንድነው የተቆረጠ የሚያቃጥሉት ለምንድነው” ጥያቄ ጨመርኩ።
“ወንጀለኛው በዛ፤ የወንጀለኛ መደበቂያ ሆነ።” ስትለኝ ተናደድኩ። ለምን ተናደድኩ መሰላችሁ-የአፍሪካን ፖለቲካ ለመረዳት ገና ሕፃን ስላልሆንኩ። ትክክለኛው ነገር ሰዎች በሉ ተብለው የሚያወሩት እና የሚያስተጋቡት ሳይሆን ከጀርባ የተደበቀው እንደሆነ ስለምገምት።
“እንዴ! መንግሥት የት ሄደ መንግሥት አለ አደል እንዴ” ስል አፏን በጣቷ እየተመተመች “እኔ እንደሰማሁ ሌላ እንዳይሰማ በል ሂድ ግባ!”አለችኝ።
“የኛ መንግሥት መሃል አዲስ አባባ ብሔረ-ጽጌ ላይ ወንጀልን የሚከላከልበት ኃይል አጥቶ መቶ ዓመት የኖሩ አንጋፋ ዛፎችን ይቆርጣል” እያልኩ ሳላስበው የሰጠችኝን ቲኬት ቆራርጬ ጣልኩት።

“ኧረ ቲኬቱን ቀደድከው! ኧረ ቲኬቱ!” ስትል ጥዋት የቆረጥኩትን ከሱሪዬ ምስጢር ኪስ አውጥቼ አሳየኋትና ወደ ውስጥ ገባሁ።
መሃል አካባቢ ቅጠላ ቅጠሉን እና ርጋፊውን እያግበሰበሱ የሚያቃጥሉ፣ የተቆራረጠውን ግንድ የሚያነሱ እና ከእሳት የተረፈውን ልቅምቃሚ የሚጠራርጉ ወጣቶች አየሁ። ስንት ሊከፈላቸው ቃል እንደተገባላቸው ባላውቅም ፍጥነታቸው አስደንቆኛል። ከመንገዱ ሰበር አልኩና ተጠጋኋቸው። “ዛፉ ምን አርጎ ነው የሚቆረጥ” አልኩኝ። “ወንጀለኛ በዛ፤ የወንጀለኛ መደበቂያ ሆነ።” ሥራቸው እንዳይደናቀፍ ለጥያቄዬ ብዙም ትኩረት ሳይሰጡ መለሱልኝ። ኃላፊ የሚመስል በዕድሜ ከአባዛኞቹ ከፍ ያለ ሰውዬ “ምንድነው የሚል” አለ በንቀት። ጠጋ አልኩና “ዛፉ ለምነድነው የሚቆረጥ” ስለው፤ “ወንጀለኛ አስቸገራ!”

ነገሩ የገባኝ እና በራሴ ግምት ዛፉ ለምን እንደሚቆረጥ የራሴን መልስ ያገኘሁ ስለመሰለኝ ከዚያ በላይ መጠየቅ አላስፈለገኝም። ብዙ ሰዎች ተቀድቶ የተቀመጠ የሚመስል ተመሳሳይ ነገር ከተናገሩ ምስጢሩን ለማወቅ ቀመሩ ከባድ አይሆንም። አንዳንድ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ጣቢያዎችን መከታተል የማልወድበት ምክንያትም ምናልባት ይኸው ሳይሆን አይቀርም። ለማንኛውም ቁጥሮችንም እንመልከት ካልን የኢትዮጵያ የመሬት ስፋት 1,127,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን የብሔረ-ጽጌ መናፈሻ የመሬት ስፋት 0.4 ካሬ ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ታዲያ እዚች የበሬ ግንባር እምታህል ትንሽ መናፈሻ ላይ ወንጀልን መቆጣጠር ከዐቅም በላይ ሆኖ መቶኛ ዓመት ልደታቸውን ያከበሩ ጥንታዊ ዛፎችን ካስቆረጠ፤ ቢያንስ ቢያንስ ማዘን ግድ ይሆናል። እናም አዘንኩ-በጣም አዘንኩ። መንግሥቴን ለማገዝም ፖሊስ መሆን አማረኝ!

ዝም ብዬ ሳስበው፤ በዛሬው ጊዜ ከሁለት ሺ ዓመት በፊት ከነበረው ኋላ ቀር የኦሪት ሕግ ጭራሽ ወደኋላ መሄድ ሥልጣኔ አልመስለኝ አለ። የኦሪት ሕግ አንድ ሰው (ዛፍን ተገን አድርጎም ቢሆን) ሰው ከገደለ ገዳዩን ግደለው ይላል እንጅ ዛፉን ቁረጠው አይልም። ዛሬ ወንጀለኛ ዛፉን ተገን አድርጎ ወንጀል ስለሠራ ዛፉ ይቆረጥ የሚል ያልተጻፈ ሕግ እንዴት በኢትዮጵያ ምድር ይፈጸማል ከምኖርበት ሠፈር በወፍ በረራ አንድ ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ላይ ይኸ ሁሉ ሲፈጠር ገና ዛሬ ማየቴ “ደንቆሮ የሰማ ዕለት ያብዳል” እንድል ገፋፋኝ፤ ይኸን ሁሉም አስጻፈኝ። ስንቶቻችሁ ግን ይኸን ነገር ካሁን በፊት ሰምታችሁት ነበር ማጠቃለያዬ እንደሚከተለው ይሆናል። እንቅልፋችንን የጤና አድርጎ፤ “ብሔረ-ጽጌ ይባል እነበረው መናፈሻ ላይ የተገነባው ኮንዶሚኒየም ተመረቀ” የሚል ህልም ወይም “አቶ ሃብቱ ፈጠነ የተባሉ ልማታዊ ባለሀብት ብሔረ-ጽጌ ላይ የገነቡት ፋብሪካ ተመረቀ” የሚል ቅዠት ከመስማት ይሰውረን። በምትኩም “ብሔረ-ጽጌ መናፈሻ ውስጥ አርጅተው የተቆረጡት ዛፎች አቅጥቅጠው ጫካው እንደገና ለምልሞ ሕዝቡ እየተጠቀመበት ነው” የሚል ዜና የምንሰማበትን ጊዜ አያርቅብን።

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop