ከተስፋኪሮስ ኣረፈ
ያስከብረናል ያልነው ግድብ ውርደት ሳይሸምትልን፣ ያኮራናል ብለን የገዛነው ቦንድ ኣንገታችንን ሳያስደፋን ኣይቀርም- የኣርበኛው የዮሃንስ 4ኛ መንፈስ ይጠብቀን፤
ግብፅ ከኣባይ ጋር ያላትን ስጋትና ንትርክ ለኣንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት የመጣላት ሃሳብ የግብፅን ድንበር እስከ ጣና መግፋት ነው፡፡ የመረጠችው ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ ሉኣላዊነት ሊደራደሩ የማይችሉት የኣፄ ዮሃንስ ስልጣን ሳይደላደል ኢትዮጵያን መውረር ነበር፡፡ የተከተለችው ስልት ድግሞ ራሳቸውን ንጉሰ ነገስት ብለው በመሰየም ከማእከላዊ መንግስት ተነጥለው የቆዩትና ገና ለኣፄ ዮሃንስ ያልገበሩትን ኣፄ ምኒልክንና የወሎ ኢማሞችን ከጎኗ ማሰለፍ ነው፡፡ ጣናን የግብ ፅ ድንበር ወይም ኣካል ማድረጉ ባይሳካላትም ከጎኗ የሚሰለፍ ሃይል ግን ኣሁንም ኣላጣችም፡፡ ኣለመታደል ሆኖ የኛ ኢትዮጵያውያን ፖለቲካ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ ኣይብቀል በሚል ብሂል የሚመራ ስለሆነ በብሄራዊ ጥቅሞቻችን ቁማር የሚጫወትና የሚደራደር ሃይል ኣይታጣም፡፡
ኣፄ ዮሃንስ በሁለት ሳምንት (15 ቀን) ዝግጅት የስልጣናቸው ኣለመደላደልና የተከፋፈለች ኣገር ተገን ኣድርጎ የመጣባቸውን የኢስማኤል (የግብፅ) ሃይል ድል ኣድርገው የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት ማስከበራቸውና ዳግም ኣንሰራርቶ ኢትዮጵያን የመውረር ምኞቱ መቅጨት ብቻ ሳይሆን በኣገሩም ስልጣኑ እንዲያከትም ሆኗል፡፡ ከኣፄ ዮሃንስ ወዲህ ግን ሃገራችን ኢትዮጵያ የተሟላ ሉኣላዊነትና ኣንድነቷ ኣጣጥማ ኣታውቅም፡፡
1. በኣፄ ምኒልክ ወቅት ኤርትራን ለጣሊያን ኣሳልፋ በመስጠት ሉኣላዊነትና ኣንድነቷ ገብራለች፣
2. ኣፄ ሃይለስላሴ ከጨርጨር (ማይጨው ኣልደረሱም) ፈርጥጠው ከኣገር በመኮብለል ሃገራችን ለኣምስት ኣመታት በጣሊያን ቁጥጥር ስር ውላለች፣
3. ፕሬዚደንት መንግስቱ ሃይለማሪያም እንደ ኣፄ ሃይለስላሴ ፈርጥጠው ከኣገር በመኮብለላቸው ኤርትራ በህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (EPLF) እጅ ሙሉ በሙሉ ልትወድቅ በመቻሏ የኣፄ ሃይለስላሴን የዲፕሎማሲ ጥረት ኣፍር ድሜ ኣብልቶት ኤርትራ ዳግም ልትነጠል ችላለች፡፡
4. ኣሁን ያለው ሁኔታ በኣፄ ዮሃንስ ዘመን እና ከመስዋእትነታቸው በኋላ የተከሰተው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት ኣለው፡፡ የክስተቶች ተመሳሳይነት የሚገርም ነው (እንደምታውቁት ኢህኣዴጎች የኣፄ ምኒልክ ዲፕሎማሲ ኣድናቂ ናቸው-ያው ከምታደንቋቸው ንጉስ የተለየ ኣልሰራንም ለማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የኣፄ ምኒልክ ኣድናቂ ሆኖ ኢህኣዴግን መውቀስ በDouble Standardነት ያስከስሳል/ያስገምታል)፡፡
ሀ. ኣፄ ምኒልክ የጣሊያን ሽርክ ነበሩ፡፡ ስልጣን በወጡ በሁለት ወራቸውም ኤርትራን ገበረሉት፡፡ ህወሓት (በኋላ ኢህኣዴግ) የህዝባዊ ግንባር ሽርክ ነበርና እሱም እንደ ኣፄ ምኒልክ ስልጣን በጨበጠ ማግስት ህዝባዊ ግንባርን እንደ ኣንድ ኣገር መንግስት/መሪ በማስተናገድ የኤርትራን መነጠል ኣበሰረ፡፡ ታሪክ ራሱን ድገም ቢለው እንጂ መሆን የነበረበት ህዝባዊ ግንባር የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ኣካል፣ ኤርትራም እንደ ኣንድ የኢትዮጵያ ክልል ይሆኑና ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ህዝበ ውሳኔ ማካሄድ ነበር፡፡
ለ. ጣሊያን በውጫሌ ውል ያገኘችው ኣልበቃ ብሏት እየተንፏቀቀች ተጨማሪ መሬቶችን መያዝ ጀመረች፡፡ ኣፄ ምኒልክም ዝም በሏቸው እያሉ ከውሉ ውጪ የተያዙ መሬቶች በኋላ የውጫሌ ውል በጣሊያን ኣገር ሲፈረም በጊዜያዊነት በውሉ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል ( እነዚህ የውሉ ኣካል ያልሆኑና በጊዜያዊነት የተቀጠሉት ኢህኣዴግ በድርድሩ እንዴት እንዳስተናገዳቸው ኣይታወቅም- የኛ ኣይደለም ብሎ የመለሰው ከእነዚህ መሬቶች ኣንዱ ሊሆን ይችላል)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ህዝባዊ ግንባር (ህግዴፍ) በኢህኣዴግ የተሰጠውን ገፀ በረከት ኣልበቃ ብሎት የኢትዮጵያን ድንበር እየተሻገረ መተናኮስና ኢትዮጵያውያንም ማንገላታት ጀመረ፡፡
ሐ. የኣፄ ምንልክ ሸሪኳ ጣሊያን ኢትዮጵያን በይፋ እንደ ወረረች፣ የኢህኣዴጉ ሸሪክ የኤርትራ መንግስትም ኢትዮጵያን ወረረ፡፡
መ. የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጣዊ ልዩነቱን በይደር ኣቆይቶ በኣንድነት ዓድዋ ላይ ጣሊያንን ድል ኣደረገ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በኢህኣዴግ ዘመንም የኤርትራ ጦርን ባድመ ላይ ኣሸነፈ፡፡ ነገር ግን ኣፄ ምኒልክ እስከ መጨረሻው ጣሊያንን መግፋት ስላልፈለጉ የጦሩን ግስጋሴ ስላስቆሙት ድሉ ያልተሟላ ኣደረገው፡፡ በዚህ ምክንያት ጣሊያን ከ40 ኣመታ ዝግጅት በኋላ ዳግም ወረራ በመፈፀም ኢትዮጵያን ለኣምስት ኣመታት ልትቆየጣጠር ችላለች፡፡ በተመነሳሳይ መልኩ የኢህኣዴጉ ቁንጮ ኣቶ መለስ የኢትዮጵያ ጦር እንዲቆም በማድረጋቸው ባድመ ላይ የተገኘ ድል የተሟላ ሊሆን ኣልቻለም፡፡ ኤርትራ ኢትዮጵያን ዳግም የመውረር እቅዷም ኣልሞተም፡፡
ሠ. እንደ ራስ እምሩ ኣባባል ኣፄ ምኒልክ የባህር በር ጥቅም ኣልገባቸውም ነበር፡፡ ኢህኣዴግም እንዲሁ የባህር በር እንደ ተራ ሸቀጥ ነው የሚመለከተው፡፡ ኣሁን እነ ኳታርና ሳውዲ ኣረቢያም ወደ ቀይ ባህር መጠጋታቸው ሸቀጥ ሊሸምቱ ወይም ግመሎቻቸው ውሃ ሊያጠጡ ነው ሳይለን ኣይቀርም፡፡ ቢያንስ የባህር ወደብ የሌለው ኣገር ኣይፀናም የሚሉት የኣፄ ዮሃንስን ግንዛቤና ኣቋም እንኳን መያዝና ማፀባረቅ ኣልተቻለም፡፡ ለህወሓት ከኣፄ ዮሃንስ ይልቅ ኣፄ ምኒልክ ቅርብ ናቸው ፡፡ ለዚህም ነው ኣፄ ዮሃንስን በጠላትነት ኣፄ ምኒልክን ደግሞ በኣርአያነት የሚፈርጇቸው፡፡ ኣንዳንድ የትግራይ ልጆች እዚሁ ፌስ ቡክ ላይ ህወሓትን በተለይ ትግራይ ላይ የምትከተለውን የህዝቡን ኣንድነት፣ ማህበራዊና የኢኮኖሚ ኣቅሙን የማዳከምና የድህነት ኣዙሪት የማስገባትና ከመሃል ኣገር የልማት እቅድ የመነጠል ሁኔታ እያዩ ነው መሰል ህወሓሽ( ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ሽዋ) እያሉ ሸንቆጥ ያደርጓታል፡፡
ረ. ኣፄ ምኒልክ ገፍቶ ለመጣ ሃይል መሬት እየቆረሱ ይሰጡ ነበር( በምስራቅ በኩል ለጣሊያንና ለፈረንሳይ በገንዘብ የተለወጡትን እንደ ኣብነት ማንሳት ይቻላል)፡፡ ኢህኣዴግም ባድመን ኣሳልፌ ባለመስጠቴ ምቀኛ ሆናችሁብኝ እስከ ማስባል ደርሷል፡፡ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውንም ተጠቃሚነት ቢቀጥል ኖሮ ለጦተርነት ኣንበቃም ነበርና የኢትዮጵያ ጥቅም ማስከበር ኣለብን ብላችሁ ወደ ጦርነት ከታችሁኛል ብሎ እስከ መክሰስ ደርሷል፡፡ ሉኣላዊነትና የኣገር ብሄራዊ ጥቅም ማስከበር የሚያስወቅስ፣ የኣገር ብሄራዊ ጥቅም ኣሳልፎ መስጠት ደግሞ ደረት የሚያስነፋ ተግባር ተደርጎ የሚቆጠርበት ዘመነ ግርንቢጥ ደርሰናል፡፡ ኢህኣዴግ ለሱዳን መሰጠት ያለበት መሬት ወስኗል፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የተጠናከረ መንግስት ቢኖራቸው ኖሮም መሬት ቆርሶ ከመስጠት ኣይቦዝንም ነበር፡፡
ሰ. እንግሊዝ ሱዳንን ወክላ መዋዋልዋ በጀን እንጂ ( ከማይመለከታት ግብፅ እንጂ ለጊዜው ከሱዳን የውሉ ይከበርልኝ ጥያቄ ኣልቀረበም) ኣፄ ምኒልክ ኣባይን ላለመገደብ የተስማሙ ሲሆን ኢህኣዴግ ደግሞ ግድቡ መብራት ሃይል ከማመንጨት ውጭ ለሌላ ኣላማ ኣልጠቀምም ብሎ ከመስማማት ኣልፎ ግድቡን ውሃ ኣልሞላም እስከ ማለት ደርሷል፡፡ ይኸ ሁሉ ግድቡ የሚይዘውን የውሃ መጠን ለማስቀነስ ነው፡፡ ኢህኣዴግ መጪውን ትውልድ እጅ ከወርች ኣስሮ ብሄራዊ ጥቅማችን ኣሳልፎ የሚሰጥ ውል ከሚፈፅም የኣባይ ግድብ ባለበት ቢቆምና መጪው ትውልድ ቢያጠናቅቀው ይመረጣል፡፡
ኢህኣዴግ የፖለቲካ ትኩረት ለማዛባት ጥናቱ ሳይጠናቀቅ የኣባይ ግድብ ግንባታ ጅማሮ ይፋ ማድረጉን፣ ኣሁን ባለው የኣገሪቷ ኣቅም ግድቡን ማጠናቀቅ ከባድ መሆኑን እና ግድቡ የመስኖ ልማት እንደማያካትት እያወቅኩም ቢሆን የግድቡ ግንባታ ደጋፊ ነበርኩ፣ ኣሁንም ነኝ፡፡ ምክንያቱም ኣባይን በራሳችን ገንዘብ መገንባት ከቻልን በትውልድ ላይ ሊፈጥር የሚችለው በራስ የመተማመንና የመነቃቃት መንፈስ ይኖራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ግድቡ በውሃ ከሞላ ድንበር ተሻጋሪ ሚሳኤል ነው የሚሆነን፡፡ ግብፅ የኢኮኖሚ ኣቅማችን ከፍ በማድረግ ፀጥታንና ብሄራዊ ጥቅማችንን ማስከበር የሚያስችል ወተዳራዊና የቴክኖሎጂ ቁመና እንዳይኖረን ነው የምትጥረው፡፡ ኢትዮጵያ የኣስዋን ግድብ ላይ የሚደርስ ሚሳኤል መፍጠር ብትችል ግብፅ ከኛ ይልቅ ለኣደጋ ተጋላጭ ትሆናለች፤ እስከዚያው ኣስዋን ላይ ሊደርስ የሚችለው የኣባይ ግድብ ሊያጠራቅመው የሚችል ውሃ ነው፡፡ ኢህኣዴግና ኣፄ ምኒልክ የስልጣን ሃይሎች በመሆናቸው ለውጭ ተፅእኖ መንበርከካቸው ለብሄራዊ ጥቅማችንና
ሉኣላዊነታችን መሸራረፍ እንደ ኣንድ ምክንያት ቢወሰድም ከኢህኣዴግ የውጭ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ድክመቶች በስተጅርባ ያሉ ጭንጋፍ ኣስተሳሰቦች መፈተሹ ኣስፈላጊ ነው፡፡
ኢህኣዴግ በኢትዮጵያ ሉኣላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም እያልፈሰፈሱት እና እያደራደሩት ያሉት ጭንጋፍ ኣስተሳሰቦች ምንጫቸውና ምንነታቸው:-
1. ‹እብሪትና ድንቁርና› እና ምንጫቸው
ማርክስ ኮሙኒዝም የሚሰፍነው በብዙሃኑ ህዝብ ንቃተ ህሊና ነው ይላል፡፡ በኋላ ላባዳር እንደ መደብ ያልተፈጠረባት ራሻ በኮሙኒዝም ኣቅንቃኞች እጅ ትወድቃለች፡፡ እነ ሌኒን የራሻ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ፈጥሮ ላባደር እንደ መደብ እስኪፈጠር ድረስ ስልጣኑን ለቡርዧ መደብ ኣሳልፎ መስጠት ኣላስቻላቸውምና ኮሚኒዝም በጥቂት የነቁ ፋኖዎች (Vanguards) ማምጣት ይቻላል ብለው የሙከራ ሶሻሊዝም (Experimental Socialism) በራሻ ላይ በመመስረት ማርክስ ያሰበውን የሶሻሊዝም ውልደት ኣጨናገፉት፡፡ ከዚያ በኋላ በየኣገሩ የተፈጠሩ ሾሳሊስት ነን ባይ ቡድኖች ራሳቸውን የነቁና ተራማጅ ኣድርገው በመቁጠር የተማሩና ኣቅም ያላቸውን ዜጎችን በማግለል እና ዜጎችን እንደ ግኡዝ በመቁጠር በይል ጠፍጥፈው ሶሻሊስት ማህበረሰብ ለመፍጠር ዳከሩ፡፡ ቫንጋርዶች ራሳቸውን ከሌላው ዜጋ የተሻለ ንቃተ ህሊና፣ ቆራጥነትና ህዝብን የመለወጥ ኣቅም ያላቸው እና ሌላው ከነሱ የሚለይ ሃይል ደግሞ ኣድሃሪ ኣድርገው ስለቆጠሩ እነሱ የሃሳብ ኣመንጪና ኣስራፂ በመሆናቸው የተለየ ሃሳብ የሚያቀርበውን በማግለልና በማስወገድ እና በህዝቡ ላይ በሃይል ሃሳባቸውን በመጫን የተግባር ኣንድነት ለማምጣት ይተጋሉ፡፡ የንቃትና የኣቅም ደረጃ የሚለካው ደግሞ ብትምህርትና በልምድ በተገኘ ተጨባጭ ኣቅም ሳይሆን ቁንፅል የሌሊንዝም ቃላትና ሃረግ ማንብነብ በመቻል ነው፡፡
ኢህኣዴግ እንደ ኣንድ የሌሊንዝም ኣቀንቃኝና ግርፍ ሃይል ራሱን ተራማጅ፣ የነቃና የተደራጀ እውቀት ባለቤት ኣድርጎ በመቁጠር ብቸኛ የሃሳብ ኣመንጪና የሚያሰርፅ ቡድን ነኝ በማለት የተማሩና ኣቅም ያላቸውን ዜጎችና ምልኣተ ህዝቡን ከሂደቱ በማግለል ሃሳቡና እቅዱን በሃይል ለመጫንና ለመተግበር ይጥራል፡፡ እውነታው ግን የኢህኣዴግ ቁንጮዎች በንድፈ ሃሳብ፣ በእቅድ፣ በዲፕሎማሲ፣ መንግስታዊ መዋቅርን ኣቀናጅቶ በመምራትና ለውጤት በማብቃት
ዝቅተኛ የሚባል ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ የሚገርመው ደግሞ የፈለገ ፊደል ቢቆጥሩም የባህሪ ለውጥ ማምጣት ኣለመቻላቸው ነው፡፡ ለዚህም ነው ምሁራንና የዲፕሎማሲ ልምድ ያላቸውን ዜጎች በማግለል በቁንፅል ግንዛቤ እየገበቡበት በዲፕሎማሲው ሜዳ ኢትዮጵያ እየተሸነፈች ብሄራዊ ጥቅሟን እያራገፈች ያለችው፡፡
2. የውስጥ ቀጋ የውጭ ኣልጋ (ድንበር የለሹ የኢህኣዴግ ህዝባዊነት ኣስተሳሰብ ምጩና መዘዙ)
የኣገሮችና የተደራዳሪ ወገኖች ስነ ልቦና ለመጠበቅ የውጭ ዲፕሎማሲና ድርድር በእኩልነት ደረጃ የሚካሄድና ሁሉም ወገኖች ኣሸናፊ ሆነው የሚወጡበት ነው ቢባልም በተጨባጭ ግን ኣገሮች በሌሎች ጉዳት ላይ ብሄራዊ ጥቅማቸውን እስከ ማስከበር ይሄዳሉ፡፡ የድርድር ውጤት የሚወስነው በተደራዳሪዎች ኣቅምና በኣገሮች የሃይል ሚዛን ነው፡፡ የውጭ ፖለሲና ዲፕሎማሲ መርህ በብሄራዊ ጥቅም እንጂ በሰብኣዊነትና በህዝባዊነት ኣይመራም፡፡ እያንዳንዷ ግንኙነት፣ እርዳታም ጭምር ብሄራዊ ጥቅም ከማስከበር ኣንፃር ያላት ጠቀሜታ ነው የምትመዘነው፡፡
ኢህኣዴጎች ውስን የመደራደሪያ ኣጀንዳዎች/ነጥቦች በመያዝና እና በመረጃ ሳይደራጁ የጠየቅነውን ኣናጣም በሚል በየዋህነት ወደ ድርድር ይገባሉ፡፡ ከዛ ኣይደለም ለኣገራቸው የተሻለ ጥቅም ሊያስከብሩ የራስንም ኣስረክበው ባዶ እጃቸው እያጨበጨቡ ይመለሳሉ፡፡ ባድመ በዚህ መልኩ ነው የተበላነው፡፡ ኢትዮጵያ ይገባታል የተባለ መሬትም የኛ ኣይደለም በማለት የኛ የሚሉትንም ጥለው መጡ፡፡ ከሱዳን ጋር ያለውም ሁኔታ ገና ወደ ድርድር ሳይትገባ ኢትዮጵያ የሚገባትን ሳታስከብር ለሱዳን መሰጠት ስላለበት መሬት ኣሳውቀዋል፡፡ ከእንግዲህ ሱዳን ለተጨማሪ መሬት ወደ ድርድር ካልገባች በስተቀር ከድርድሩ በፊት ውጤቱ ታውቋል፡፡
ኢህኣዴጎች ለምን እንደዚህ ኣይነት የጅል ዲፕሎማሲና ድርድር ትከተላላችሁ ሲባሉ የኛ ህዝባዊነት ድንበር የለውም የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡት፡፡ ከዚህ ኣልፈው የውጭ ግንኙነታችን ብሄራዊ ጥቅም ሳይሆን ህዝባዊነት ነው የሚመራውና የሰው ኣገር ጥቅም ኣንነካም ይላሉ፡፡ የሌሎች ኣገሮች ጥቅም ከምንነካ የራሳችን ብናጣ ይሻላል እንደ ማለት ነው፡፡
ለዚም ነው በተደራዳሪነት ቢሰማሩ ብሄራዊ ጥቅማችንን የሚያሳጡን፣ በኣደራዳሪነት ቢሰየሙም የማይሳካላቸው፡፡ በኤርትራ ያለውን ሁኔታ ብናይ የኤርትራ መንግስትን በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እናሸንፈዋለን ብለው ያስባሉ፣ እቅዳቸውም በኤርትራ ለኢትዮጵያ የሚመች ሃይል ስልጣን ላይ ማውጣት ሳይሆን ህዝባዊ ግንባርን ከስልጣን ከማውረድ ስለማይዘል የሚሰበሱቧቸውና የሚደግፏቸው ተቃሚዎች በኣመለካከት ደረጃ ከህዝባዊ ግንባር ይብሱ እንደ ሆን እንጂ ኣይሻሉም፡፡ ውጤቱም ኤርትራና ትግራይን በማህበራዊና በኢኮኖሚ ከማድቅና በኢትዮጵያ መቋጫ የሌለው የፀጥና የፖለቲካ ስግኣት ከመፍጠር የዘለለ ኣይደለም፡፡ ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ የሚመች የፖለቲካና ወታደራዊ ኣመራር የመፍጠር እድሉ እያለ ነው ከእጃችን የወጣችው፣ የሶማሊያም ሁኔታ መጨረሻው ሊያምር እንደማይችል መተንበይ ኣይከብድም፡፡
የኢህኣዴግ ኣመራር በጨቅላነት እድሚያቸው የያዙት ጭንጋፍ ኣስተሳሰብ ሰለባና እስረኞች ናቸው፡፡ ማርክስ ሰራተኛው መደብ ድንበር የለውም ብሎ ባስተማረው መሰረት በኣንደኛው የኣለም (የምእራባውያን) ጦርነት ወቅት ኮሙኒስቶች ሃገራዊ ብሄርተኝነት ከኛ ኣይጠበቅምና ራሳችንን ከጦርነቱ ማግለል ኣለብን፣ ጦርነቱም የብርዧ መድብ ነውና መወገዝ ኣለበት የሚል ኣቋም እናራምድ ብለው ነበር፡፡ የራሻ ጦር ሲያፈገፍግ ወታደሩ ተቋውመውን ለመግለፅ በእግሩ ድምፅ ሰጥቷል የምትለዋ የሌኒን ዝነኛ ኣባባል ትታወሳለች፡፡ ነገር ግን ኮሙኒስቶቹ እንንደተጠበቀው ሳይሆን ሃገራዊ ብሄርተኝነት ጠለፋቸውና ከኣገራቸው ጋር ተሰለፉ፣ ኮሙኒስት ኣለም ኣቀፋዊነትም ኣፈር ድሜ በላች፡፡ ኢህኣዴጎች በኢትዮጵያ ውስጥ ከመደብ በታች በኣከባቢያዊ ብሄርተኝነት ቢደራጁም ኮሙኒስት ኣለም ኣቀፋዊነት ኣራማጅ ነኝ ብለው ይመፃደቃሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ የኛ ህዝባዊነት ድንበር የለውም በማለት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ኣሳልፎ ለመስጠትና ከኢትዮጵያውያን በላይ የጎረቤት ኣገር ህዝቦችን ለመንከባከብ፣ የሌሎች ኣገሮችን ብሄራዊ ጥቅም ሽንጣቸውን ገትረው ለመመጎትና ኢትዮጵያውያን በውጭ ለሚደርስባቸው እንግልት፣ ውርደትና ሞት ግድ የለሽ ለመሆን እንደ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ያው የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ቢያቀነቅኑና ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ቢንቀሳቀሱ ኮሙኒስት ኣለም ኣቀፋዊነት ኣቀንቃኝነታቸው ይሸረሽረዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ነው ኦህኣዴግ የውስጥ ቀጋ የውጭ ኣልጋ ሊሆን የቻለው፡፡ ኢህኣዴግ ኣካባቢያዊ ብሄርተኝነት እያቀነቀነ ሃገራዊ ብሄርተኝነት ላይ ሲድርስ ግን ኮሙኒስት ኣለም ኣቀፋዊነት ኣራማጅ ነኝ ብሎ ወገቤን ይላል፡፡ ደግሞ እኮ ኣገር ውስጥ የሌለ ህዝባዊ ባህሪ ለሌላ ኣገር ሲሆን ከየት እንደሚመጣ ነው፡፡ ኣሽቃባጭነት ቢባል ሳይሻል ኣይቀርም፡፡
3. ድርድርን ወደ እውነታ/ሃቅ መቀየር
ይህ ኣመለካከት ከኢህኣዴግ ተግባር ተነስቼ እንጂ የኣመለካከቱ ምንጭና ጭንጋፍ ኣስተሳሰቡ በኢትዮጵያ ሁኔታ እንዴት ሊመነዘር እንደቻለ ለማግኘት ኣልቻልኩም፡፡ እዚህ ላይ የእናንተ እገዛ ኣስፈላጊ ነው፡፡
ሁኔታውን በተጨባች ምሳሌ ለማስደገፍ ያህል ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ኤርትራን ህዝበ ውሳኔ ሳይካሄድ ለመነጠል እንዲያመቸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች ድጋፍ ፍለጋ ሲቀርቡት እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያቀርበው የኤርትራ ጥያቄ የቀኝ ግዛት ጥያቄ እንደሆነና በነፃነት/በመነጠል መፈታት እንዳለበት ተቀበሉ የሚል ነው፡፡ የኢህኣፓ ኣመራር ልኡኳን ቅድመ ሁኔታውን ተቀብለው ለማፅደቅ ወደ ፓርቲያቸው ሲያቀርቡት ተቀባይነት ኣጣ፡፡ ውሳኔውን ተከትሎም ኢህኣፓ ከህዝባዊ ግንባር ድጋፍ ተነፈገው፡፡ ቀጥለው የህወሓት ልኡኮች ወደ ህዝባዊ ግንባር ሄደው ተመሳሳይ ቅድመ ሁኔታ ቀርቦላቸው ምንም ሳያቅማሙ ቅድመ ሁኔታውን ተቀበሉት፡፡ በዚህ መሰረት የተሓህት (ህወሓት) መስራቾች በህዝባዊ ግንባር የወታደራዊ ስልጠና እና የተወሰና የመሳሪያ ድጋፍ ሊሰጣቸው ቻለ፡፡ ህወሓትም የኤርትራ ህዝብ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ስለሆነ በነፃነት/በመነጠል መፈታት የሚል ኣቋም ማራመድን ተያያዘችው፡፡
እንግዲህ በህወሓትና በህዝባዊ ግንባር መካከል የተደረገው ድርድር እንጂ ቀደም ብሎ የተያዘ እውቀትና ኣቋም የሚያሰቀይር ሳይንሳዊ ኣውደ ጥናት ኣይደለም፡፡ የህወሓት/ኢህኣዴግ ኣመራር ግን በድርድር የተቀበሉትን በእውቀት የያዙት ኣቋም ለማስመሰልና የተቀበሉትን ኣቋም ትክክለኛነት ለማስረዳት መፅሃፍ እስከ መፃፍ የደረሰ የፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ላይ ተጠምደዋል፡፡ የራሳቸው ኣቋም ይመስልም ለኤርትራ መነጠል ከህዝባዊ ግንባር በላይ ያገባናል፣ ያሳስበናል ማለትንም ተያያዙት፡፡ ኣንድ ኣገር ወይም የፖለቲካ ሃይል በድርድሩ ወቅት በሚኖረው ኣቅም እና ሃይል ሚዛን ብሄራዊ ጥቅምን መስዋእት ያደረገ ውጤት ሊቀበል ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ለሚነሱ ጥያቄዎች ከደርድሩ የተገኙ ውጤቶችን ለኣገር ያላቸውን ፋይዳ በማጉላትና ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችም ከተቻለ በኣርምሞ ማለፍ፣ ካልሆነ ደግሞ እነዛን በማጣት የተገኘ ጥቅም በማስረዳት ይታለፋል እንጂ የተቃራኒ ተደራዳሪ ወገን ትክክለኛነት ለማስረዳት መዳከር በዲፕሎማሲያዊ ኣለም የተለመደ ኣይደለም፡፡ ይደረጋል የሚል ካለም ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ ኢህኣዴግ ግን ኢትዮጵያ ከድርድሩ ስላገኘችው ጥቅም ሳይሆን ብሄራዊ ጥቅም ኣሳልፎ መስጠቱ ምን ያህል ትክክለኛ እንደ ሆነ በማስረዳት ላይ ነው የሚጠመደው፡፡ በዚህ መሰረት ከኤርትራ ጋር ስላለው ሁኔታ ሲነሳ ኤርትራ ባለመብት ስለመሆኗ፣ ከሱዳን ጋር ያለው ድንበር ሲነሳ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች የሱዳን ድንበር ጥሰው ስለመስፈራቸውና ማረሳቸው እንጂ ኢትዮጵያ ከድርድሩ ስለምታገኘው ጥቅም፣ ለድርድሩ ያደረገችው ዝግጅት፣ የድርድሩ ይዘትና እና የኢትዮጵያን ኣቋም ሲያስረዳ ኣይታይም፡፡