ህሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም.(26-12-2015)
በትናንትናው ዕለት የህወሃት/ኢሕአዴግ ጠ/ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ህወሃት በሚቆጣጠረው ፓርላማ ተገኝቶ መንግስቱ በወጠነው የአምስት ዓመት መመሪያና በተለያዩ ርዕሶች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የታቀደውን የኤኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን በተመለከተ የግብር አሰባሰቡ በበለጠ እንዲያድግ የሚያስገድድ ሕግ እንደረቀቀ፣በገጠሩ የልማት እንቅስቃሴና መጠነኛ የእንዱስትሪ ተቋማት እንዲጎለብቱ የልማት ባንኩ ብዙ ካፒታል መድቦ ዘርፎችን በመዘርጋት ለመንቀሳቀስ እንደታሰበ ያብራራ ሲሆን በአለፈው የአምስት ዓመቱ ዕቅድ የባከነውን ገንዘብና የአገር ሃብት ከቁጥር ውስጥ ሳያስገባ እንዳልነበረ አድርጎ ሸፋፍኖ አልፎታል።የልማት ባንኩ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ጥቅምና አገልግሎት ቢጠቅስም፣ብድርና ድጋፍ የሚያገኘው የህብረተሰብ ክፍል በግልጽ አልተቀመጠም።በማንኛውም አገር 90በመቶ የሚሆነውን የስራ ዕድል የሚፈጥረው የግል ክፍሉ ነው።የግል ክፍሉ ይህን ለማድረግ የሚችለው የሚሰራበት መሬት፣የአጭር፣የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ብድር በተፈለገው መጠን ለማግኘት ሲችልና በአገሪቱ ክፍሎች በሙሉ ያለምንም ገደብ ለመንቀሳቀስ ሲችል ነው።በተጨማሪ አገር ተከልና አገር ወለድ የግል ክፍል ከፍተኛ ሚና ሊኖረው የሚችለው መንግሥት ለውጭ ኢንቬስተሮች የሚሰጠውን አድላዊ ድጋፍና እንክብካቤ በመቆጠብ ለኢትዮጵያውያን ፊቱን ሲያዞር ነው።
ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የታየው ግን ገዢው ፓርቲ ያልተቆጠበ ድጋፍ የሚሰጠው ለገዢው ፓርቲ ድርጅቶች፤ በተለይ ለህወሓት/ ኢሕአዴግ ለፓርቲውና ለመንግስት ለባለስልጣናቱ ቅርበት ላላቸው ነው። አሁንም እነዚህ ክፍሎች ዋና ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም። በዚህ ዙሪያ የተሰጠው ማብራሪያ ለብዙ ዓመታት ተደጋግሞ የተለፈፈ በመሆኑ የማታለያ ባዶ ዲስኩር እንጂ ለሕዝቡ ኑሮና ለአገሪቱ ሰላም፣አንድነትና እድገት ታስቦ የተነደፈ፣በተግባር የሚተረጎም እንዳልሆነ ካለፉት ተመክሮዎች በመነሳት መናገር ይቻላል። በመጀመሪያውም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሶስት ጊዜ በልቶ ለማደር የሚያስችለው መመሪያ እንደሆነ የህወት መሪ በነበረው በመለስ ዜናዊ ተሰብኮበት ነበር።ውጤቱ ግን እንኳንስ በቀን ሶስት ጊዜ ቀርቶ አንድ ጊዜም በልቶ ለማደር የማይቻልበት አልፎ ተርፎም ከሌላው ጊዜ የበለጠ ከፍተኛ ቸነፈር የሰፈነበት ሰው ሰራሽ መቅሰፍት የወለደ ሆኖ ተገኝቷል።
የቸነፈር(ከፍተኛ እርሃብ) መከሰትና ስላደረሰው ጉዳት እንደ እስከዛሬው ዓይኔን ግንባር ያርገው ብሎ ለመካድ የሚፈቅድለት ሁኔታ ባለመኖሩ ያደጋውን ስፋትና ችግሩን ለማሶገድ ያሉትን መንግስታዊ ድክመቶችና መዋቅራዊ ችግሮች አምኗል። እርሃቡን ለመቋቋም ብዙ መንገዶችን እንደዘረጋ ቢተነትንም ከብዙ ጊዜ በፊት የተሰነዘረውን የሕዝብ አስተያየትና ምክር ባለመቀበሉ የተፈራው ችግር ለመንሰራፋቱ መንግስት እራሱ ተጠያቂ እንደሆነ ቢታወቅም ድክመቱን አላመነም። ምንም እንኳን የደርግ መንግሥት “የመሬት ለአራሹን አዋጅ” አውጥቶ፤ በሕዝብ ስም መሬትን ወደ መንግሥት እጅ ቢያዛውርም፤ ዛሬ ህወሓት/ኢህአዴግ ሰፊውን በግብርና የሚኖር ሕዝብ “ጭሰኛ” አድርጎታል። መሬቱን በፈለገው ዘዴ ለግል ክፍሎች ይቸረችረዋል። የሕዝቡን በተለይም የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄና የማምረት አቅም ግንባታን አላመቻቸውም። የአገሪቱ ዜጋ በፈለገበት ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመስራት የሚያስችለው መብት የለም። የክልል ገዢዎች ነዋሪዎችን በረባ ባልረባው ከቀያቸው እንዲባረሩ አድግቿዋል። ከተሜው ሆነ አራሹ በዜግነት መብቱ ማግኘት የሚገባውን መንግሥታዊ ድጋፍ በድርጅት አባልነቱና በብሔሩ የሚያገኝና የሚያጣው በመሆኑ ለርሃብና ለስደት እንዲጋለጥ አድርጎታል። የተፈጥሮ ድርቅ የሚያመጣውን ጉዳት እንደዋና ምክንያት አድርጎ በማቅረብ መንግስቱ ከሚኖርበት አላፊነትና ቀድሞ የመዘጋጀት ግዴታ ለማፈግፈግ ሞክሯል። ቀደም ሲል ለገጠሩ እድገትና የእርሻ መስክ የመስኖ ስራዎች መጎልበት ሲኖርባቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ ለመስኖው ስራ መዳከምና ለርሃቡ ዝናብና የቆቃ ግድብ ሳይቀር ተጠያቂ ሆኖ ቀርቧል። የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሃብቶች ለሚያንቀሳቅሱት፣ ለውጭ አገር ገበያና አገልግሎት ለሚውሉ የአበባና የመሳሰሉት ምርቶች እንዳለፈው ሁሉ ወደፊትም ትኩረትና ቅድሚያ እንደሚሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጧል። ይህ ዕቅድ ለውጭ አገር ከበርቴዎች፤ ኪራይ ሰብሳቢዎችና አቀባባይ ነጋዴዎች ጥቅም የሚሰጥ ለገዥው ህወሀት/ኢህአዴግ ደግሞ ገንዘብ መሰብሰቢያ እንጂ ለደሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ለሰፊው አርሶ አደር ጥያቄ መልስ የሚሰጥ አይደለም። እርሃብንም ለመዋጋትና ለማሸነፍ አያግዝም።ስለሆነም መዋቅሩን ለመለወጥ ፓሊሲውን መለወጥ አለበት።
በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞና እምቢ ባይነት በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥቂት ስርዓተ አልበኞችና ሽብርተኞች ቅስቀሳ ውጤት ነው በማለት ሲያጣጥለው፣እንዳለፉት ስርዓቶች በድንፋታ ተወጥሮ “ደካሞችና ነውጠኞች አቧራቸውን አራግፈው ብቅ ያሉበት፣የሕዝቡን እንቅስቃሴ ጠምዝዘው ለመጠቀም የቋመጡበት ነው” በማለት እንደለመደው ለማዳከምና በሃይል ለመደፍጠጥ የሚመራው መንግስት መጠነ ሰፊ ዕቅድ እንደዘረጋ ለህወሓት/ኢሕአዴግ ምክር ቤት አስረድቷል። የሕዝብ ንቅናቄ መሆኑን ካመነ ዘንዳ ለምን ሕዝቡ ተነቃነቀ ብሎ መጠየቅና መልስ መሻት በተገባው ነበር። ለአገር እድገት፣ለሰላምና አንድነት፣ እንዲሁም የዲሞክራሲንና የመልካም አስተዳደርን ስርዓት ለመመስረት ቆርጦ የተነሳ ስብስብ እመራለሁ ከሚል ጠ/ሚኒስትር የጥፋትና የጥቃት አዋጅ አይጠበቅም ነበር። አላፊነት የሚሰማው መሪ ቢሆን ኖሮ ሁሉንም የተቃዋሚ ክፍሎች የሚያሳትፍ ድርድር፣መግባባት፣መነጋገር የሚያስችል ሁኔታዎችን ፈጥሮ ለሰላምና ለእርቅ የሚጋብዝ ጥሪ ማድረግ በተገባው ነበር። ሆኖም ግን በጥፋት ላይ መሰረት ካደረገ መንግስትና ቡድን ቀናነትና የተሻለ አመራር ይገኛል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በጠቅላይ ምኒስትሩ የታወጀው የጥቃት እርምጃ አገሪቱንና ሕዝቡን ይበልጥ ወደቀውስ የሚከት አላፊነት የጎደለው፣የማንአህሎኝነትና ትእቢት የተመላበት አቋም ነው።
በእኩልነት ስም በሰሜን ጎንደር አካባቢ ለዘመናት በሰላም የሚኖረውን ሕዝብ ቅማንትና አማራ በማለት ሸንሽኖ ቀውስ ውስጥ የከተተው እራሱ በህወሃት/ኢሕአዴግ የበላይነት የሚመራው መንግስት መሆኑ እየታወቀ ለደረሰው የሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም ተጠያቂነቱን በሕዝቡ ላይ ጥሎታል። በዚህም በዚያም ብሎ በተቃዋሚው ላይ ዱላውን ለማሳረፍ ዝቷል። ሰሞኑን በኦሮሚያና በሙስሊሙ ማህበረሰብ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ጥያቄ የጥቂት ነውጠኞችና ሽብርተኞች ደባ ነው ሲል ከማውገዝም በላይ የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁነቱን አረጋግጧል። በዚህ የበቀል እርምጃ በሰላማዊ ትግል አምነው የተሰለፉትን የፖለቲካ ድርጅቶችንና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን ለማጥፋትና ለመደምሰስ መታሰቡን ፍንጭ ከመስጠትም በላይ ለፖሊስና ለደህንነት ተቋማት ገደብ የሌለው ስልጣንና ትዕዛዝ መስጠቱን ይፋ አድርጓል። ከአገር ቤት ሾልኮ የሚወጣው መረጃ እንደሚያረጋግጠው በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎች እንደተገደሉና ኦሮምያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ብቻ ከሶስት ሽህ በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችን በእስርቤት እንደታጎሩ፣ቁጥራቸው ያልታወቁትም በመሰደድ ላይ እንዳሉ ያመለክታል።የሕዝቡም ንቅናቄ ወደከፈተኛ የትጥቅ ትግል እንዳይሻገር በድንበር አካባቢ ያለውን ቁጥጥር ለማጠንከርና የትጥቅ ማስፈታትም እርምጃ በመላ አገሪቱ በሰፊው ለማካሄድ ያለውን ዕቅድ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በዝርዝር አስረድቷል። እዚህ ላይ የደርግ ተመሳሳይ ድርጊት ሲደገም ማየቱ የስርዓት ለውጥ አለመደረጉን ያሳያል።
ሙስናን በተመለከተ፣እራሱ በሚመራው መንግስት ውስጥ በጥልቀት መስፈኑን ባይክድም በደፈናው ሙስናን ለመዋጋት ደፍረን ከተነሳን ውሎ አድሯል ብሏል። ግን በእውነት ሙስናን የሚታገል መንግስት የሚመራ ቢሆን ኖሮ ለይስሙላ አብሮ ተካፍሎ ለመብላት ያስቸገሩትን ጥቂቶቹን ነካ ነካ አድርጎ ከማለፍ ባሻገር የሙስናው አውታር የሆኑትን የስርዓቱን ቀንደኛ መሪዎችና ተባባሪዎች ማጋለጥ፣ማሶገድና መቅጣት በተገባ ነበር።ግን ስርዓቱ ይገረሰስበታልና ያንን ለማድረግ አይደፍርም።ያንን ሊያደርግ የሚችለውና የሚደፍረው ለሕዝብ መብት የቆመ፣ሕዝብን ከዃላው ያሰለፈ መንግስት ብቻ ነው።
የድንበር መሬትን ቆርሶ ለሱዳን የመስጠቱን ጥያቄ በሚመለከት የሌለ ችግር እየፈጠሩ የሚያስተጋቡት ተቃዋሚዎች እንጂ መንግሥት በዚህ እረገድ ያደረገው ውልና ስምምነት የለም በማለት ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብሏል። የድንበር መሬትን በሚመለከት ሱዳኖች ታጥቀው በገዛ መሬቱ ላይ ለዘመናት ሰፍሮ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ እንዳላባረሩት ሁሉ ምንም ችግር እንዳልተከሰተና እንደውም ኢትዮጵያውያኑ የሱዳኖችን መሬት ቀምተው የሚያርሱ ወንጀለኞች ናቸው በማለት ሱዳኖችን ታጋሾች ኢትዮጵያኑን ወንጀለኞች አድርጓቸዋል። ለራሱ ሕዝብ ጠበቃ በመሆን ፋንታ ህወሓት/ኢህ አዴግ ለሱዳን መንግሥት ዋና ጠበቃ መሆኑ ይዘገንናል። ታላቅ ቁጣንም ይቀሰቅሳል። ድንበሩን ቆርሶ ለመስጠት በስተጀርባ ያደረገውን ውልና ስምምነት ተቃዋሚዎች፤ በተለይ የኢትዮጵያ የድንበሮች ኮሚቲ ላለፉት ስምንት ዓመታት በተከታታይ ያደረጉትን ከፍተኛ ጥረት የውሸት ቅስቀሳ ነው ከማለቱ ጋር አያይዞ እዛው በዛው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ድንበር ለመካለል ሥራ መጀመሩን አልካደም። አሁንም ደግመን ደጋግመን ህወሃት/ኢሕአዴግ በአጼ ምኒሊክ፣በአጼ ሃይለስላሴና በወታደራዊው መንግሥት ተከብሮ የቆየውን ዳር ድንበር ማስከበር ብሔራዊ ግዴታው ነው እንላለን።የሱዳን መንግሥት አጣዳፊ ጉዳይ ነው ብሎ አቤቱታ ያላቀረበበትን ጉዳይ ገዢው ፓርቲ እንዳጣዳፊ ጉዳይ ማድረጉ አግባብ የለውም።በእኛ ግምትና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕገወጥ መንገድ የሱዳንን መሬት አልቀማም፤ለመቀማትም አያስብም።ድንበሩን አስከብሮ ከሱዳን ሕዝብ ጋር ከወያኔ በፊት እንደኖረው ወደፊትም ከወያኔ በዃላ ይኖራል። የሀገር ድንበር ጉዳይ ከፖለቲካ ጨዋታ በላይ ነው። በመሆኑም ይህ እጅግ ሀላፊነት የጎደለው ሀገርን ቀስበቀስ ቆራርሶ ለባእድ የማስረከብ ስራ ማስቆም ደግሞ የሁሉም ዜጋ ሀላፊነት ነው። ይህ አጥፊ ተግባር አሁኑኑ ሊቆም ይገባዋል።
ስለመልካም አስተዳደር፣እርቅና ሰላምም አንስቶ ነበር፡፤ግን ለሰላሙ መደፍረስና መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን እንቅፋት የሆኑት ተቃዋሚዎች ናቸው በማለት ዋና ተጠያቂ የሆነውን እራሱ የሚመራውን መንግሥት ነጻ አድርጎ አቅርቧል።
ከዚህ በላይ በጠቅላይ ምኒስትሩ በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር በተነሱት አንኳር የአገር ጉዳዮች ላይ ሸንጎ የተረዳውን ቀንጨብ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ይህ ጥልቀት ያለው ያገር ጉዳይ በአንድ ድርጅት ውሳኔና ፈቃድ የሚከናወኑ እንዳልሆኑ ሸንጎ ያምናል። በስልጣን ላይ ያለው ቡድን አላፊነት አለብኝ ብሎ የሚያምንና የሚቀበል ከሆነ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፤በአገር ቤትና ከአገር ውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ፣የማህበረሰብና የሙያ ስብስቦችን በሚያሳትፍ መልኩ በተግባር ሊተረጉመው ይገባል።እርቅና መግባባት የማይግባቡና በአቋም የተለያዩ ሃይሎችን የሚመለከት ጥያቄ ነው፣ማለትም መንግሥትንና ተቃዋሚ ሃይሎችን።ስለሆነም ተቃዋሚውን ሕዝብና ለሕዝቡ መብት ፣ለአገር አንድነት፣ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈንና ለሕግ የበላይነት የቆሙትን ድርጅቶችን፤ ስብስቦችንና ግለሰቦችን እያሳደደ፣እያገለለ፣ እየወነጀለና ሁሉንም በጠላትነት እየፈረጀ ለእርቅና ለመልካም አስተዳደር የቆምኩ ነኝ ማለት ተቀባይነት የለውም።ለጥያቄው ሁሉ የማይመጥን መልስ ያልቋጠረ ጉንጭ አልፋ የማደናገሪያ ስብከት ከመሆን ያለፈ አይደለም።በጠቅላይ ምኒስትሩ በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና በድርጅታቸው በህወሀት/ኢህአዴግ ለሕዝቡ ጥያቄ የተሰጠውና ለመስጠትም የተዘጋጀው የአመጽ መልስ “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ”የሚለውን የአገራችንን ነባር አባባል ያስታውሰናል።
ሸንጎ በአገራችን የተከሰተውን መጠነ ብዙ ችግር ለመፍታት የሚቻለው በአንድ ቡድን ፍላጎትና ጥረት አለመሆኑን ያምናል። ስለሆነም ሁሉም ተቃዋሚ ክፍሎች በነጻ ተሳትፎ አገሪቱ የተሻለ አቅጣጫ የምትከተልበትንና የተከሰቱት ችግሮች የሚወገዱበትን መንገድ ለመሻት ከሚፈልጉ ሁሉ ጋር ተባብሮ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን ይገልጻል። ይህንንም ሂደት ለመቀየስ የሚያስችል ስብሰባ በአስቸኳይ መደረግ አለበት ብሎ ያምናል፤ ያለንበት ወቅት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለደረሰ፣ለዚህ አገር አድን ተልእኮ ለሚሰለፉና ለሚደግፉ ሁሉ ጥሪ ያደርጋል። ስብሰባው ቢቻል በኢትዮጵያ አለያም በውጭ አገር እንዲካሄድ የብዙሃኑ ውሳኔና ፍላጎት ከሆነ የበኩሉን ለማበርከት ዝግጁ ነው።
የሕዝብ ሰላማዊ ትግል ያሸንፋል!!