“የተራቡትን መርጠን ከምንቸገር ያው የጠገበው ይሻለናል” የሚል መልክት ያላት ማዘናጊያ ሀሳብ በየፌስ ቡክ ላይ ተበትናለች። ሲጀመር በልቶ ጠገብኩ የሚሉ መቼ ነገሱብንና። በዛ ላይ ያለአባከና በሰፊው የለመደ ሆድ ለሌላ አምስት አመት ከበሉን ለመረጃ እንኳ አጥንታችንም አይጋኝም አትቀልዱ። የሚኖር አይመስለኝም እንጂ በዚህና “ድምጽ መሰረቁ ላይቀር” አይነት አንድምታ ባላቸው ምክንያቶች ተንተርሶ ለወያኔ ድምፁን የሚሰጥ ካለ በቁሙ የሞተ ነው። ውጤቱ ምንም ሆነ ምንም እሱና አምላኩ ብቻ በሚያውቁት መደበቂያ ውስጥ ሆኖም እንኳ የማነበትን ማድረግ ካልቻለ “ሙትቻም” ያንሰዋል።
በተመሳሳይ ተቃዊሞዎች ሰርተውት፤ አድርገውትና፤ ሆነውት ቢሆን ስንል የምናነሳቸው ሀሳቦች በሙሉ እዚህ ጊዜ ላይ ሲደርስ ለጊዜው የግድ የሆነ ቦታ አስገብተን ልንቆልፍባቸው ግድ ይላል። በይበልጥም ካለንበት ተጨባጭ አገራዊ እውነታ አኳያ ድምጻችንን ለመስጠት መሰረት የምናደርገው ድርጅቶች የላቸው አገራዊ እቅድ፤ ጥቅላላ ጥንካሬያቸውና ያሳዩት ቁርጠኛነት እንዲሁም ፖለቲካዊ ፍላጎታችን ብቻ ከሆነ ብዙ ተቃዋሚ ለምርጫ በቀረቡበት ድምጻችንን ስለሚከፋፈል አሁነም ወያኔ ተጠቃሚ ሊሆንበት የሚችልበት ጎን አለው። እንደምንመርጥበት ክልል ፤ በምንመርጥበት ጣቢያ እንደቀረቡት ተቃዋሚ እጩዎች አይነትና ብዛት፤ ያእጩው ጥሩ ግለሰባዊ ስብእና ባጠቃላይ ለመመረጥ ያለ የተሻለ እድል፤ በምንመርጥበት አካባቢ ነዋሪ የሆነው የበዛው የማህበረሰባችን ክፍል ፖለቲካል ዝንባሌና ፍላጎት የመሳሰሉ ቁም ነገሮችን ግምት ውስጥ አስገብቶ ድምጻችንን መስጠቱ ላሁኑ አዋጭ ብልጠትም ያለበት ያደርገዋል።
ይህን የምለው ተቀናቋኝ ድርጅቶች በአንድ ሆነው ለምርጫው ባይቀርቡም ዜጎች ከውስጣቸው አንዳቸውን ብቻ ምርጫ አድርገው ሊያወጡ የሚችልበት ነባራዊ ሁኔታ ቢኖር ኖሮ እመክረው ነበር። ባስበው ባስበው ላሁኑ የሚቻል አይደለም ወይ ስላልታየኝ ነው። ወደ ሁለት ማጥበብ ግን ይቻላል። ያም ሆኖ በድርጅትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከፍላጎት በዘለለ የሚቻልበት መሬት የረገጠ በቂ ነባራዊ ሁኔታ አለ የሚል ካለ ሀሳቡን ወደ ህዝብ ሊገፋው ጊዜው አሁን ነው።
በግልፅ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። በአገራችን ጥርት ብሎ የወጣ በግልፅ ለማናችንም የሚታይ ሁለት አይነት ፖለቲካዊ ፍላጎቶች አሉ። እነዚህን ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ሙሉ በሙሉ አይወክሉም ሊሉ የሚችሉ ሊኖር ቢችሉም በበቂ የያዣቸውና ጎልተው የወጡ ሁለት ተቀናቃኝ ድርጅቶች አሉ። ሰማያዊ ፓርቲና መድረክ። ላማሸነፍና ለውጥ ላማምጣት ድምጻችንን የምንሰጥ ከሆነ በመጀመርያ ሌሎቹን በሙሉ ላሁኑ እንደሌሉ አድርገን እንነሳ። በሁለተኛ ደረጃ ሰማያዊና መድረክንም ምርጫዎቻችን ለማድረግ የምናፎካክር ከሆነም አሁንም ሂደቱ ወያኔን ይጠቅማልና ድምፅ ለመሰጠት የምንወስንበት ሌላ አይነት ስሌት ልንቀምር የግድ ይገባል።
አዲስ አበባ፤ አማራ ክልል፤ ማህበረሰባዊ ስብጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ትላልቅ ከተሞች ላይ በሙሉ ለሰማያዊ ፓርቲ ያለ ድጋፍ በዝቶ እስከታየ የመድረከም ሆነ የሌሎች ፓርቲ ደጋፊዎች ድምጻችሁን ለሰማያዊ ፓርቲ ምንም ሳታንገራግሩ ስጡ። ብልጥ ለሆነና ጨዋታው ለገባው ሰማያዊ ፓርቲ የሚኒልክን ስርአት ሊመልስ ነው ተብሎ የተነገረውና ያመንንም ብንኖር። እንዲሁ የመድረክ ደጋፊዎች በብዛት ያሉበት አካባቢ ሆኖ የመድረክ እጩ ከሌለ ለሰማያዊ በመቀጠል ለሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በደረጃ ባበረ መንገድ ድምጻችሁን ለመስጠት ዶልቱ።
ሌላህም ከአዲስ አበባ ውጪ የመድረክ እጩ ቀርቦ ሰማያዊ ፓርቲ እንደማያሸንፍ እያወክ ድምፅህን ለሰማያዊ ፓርቲ ብጭራሽ አትስጥ። ድምፅችንን በተባበረ ምንገድ ለመድረክ ለመስጠት እንዶልት። አሁን ያለውን ፌደራላዊ አከላል አምርረህ የምትቃወምም ቢሆን። በአማራ ክልልና በትላልቅ ከተሞች የሰማያዊ ፓርቲ እጩ እስካለ ሳታንገራጋር ለሰማያዊ ፓርቲ ድምጽህን ስጥ። የሰማያዊም የመድረክም እጩ ከሌለ ብቻ ለመኢአድ ከዛም ለሌሎች ተቀዋሚዎች በደረጃ ድምጽህን ስጥ።
ባጠቃላይ የትኛውም ተቀናቃኝ እጩ እንደማያሸንፍ እያወክ እጩው ወንድምህ ወይ እህትህም ብትሆን የፈለከውን ያህል የድርጅቱ አፍቃሪ ብትሆን ድምፅህን አትስጣቸው። ምክንያቱም ላሁኑ ፋይዳ የሌለው ነው። እንደውም በመጨረሻ ውጤቱ የምንጎዳበት ነው የሚሆነው። ወያኔን ለማዳካም ህዋዋትን ማዳካም ብቻ ሳይሆን ተለጣፊዎቹንም ማዳከም ግድ ይላል። ድምፅህን ለሰማያዊ ከምትሰጥ ለኦፒዲዬ ስጥ አያዋጣም። ይህን የሚሉት አንድም የመራራ ጠንክሮ መውጣት ያስፈራቸው ወያኔዎች ወይ ትግሉን ኦሮሞ ከሌላው ኢትዬጵያዊ ጋር በማድረግ አደጋውን ሳያዩ ጠብ የሚል ትርፍ ይኖራል ብለው በተሳሳተ መንገድ የሚያሰሉ ናቸውና አትስማ።
በዚህኛው ስሌት ከተንቀሳቀስን ብቻ ሲጀመር በየግል መንግስት ለመመስረት የሚበቃ እጩዎችን ያላቀረቡ ቢሆንም የሰማያዊና የመድረክን እጮዎች በሙሉ አሸናፊ ለማድረግ ይቻለናል። በሁኔታዎች ተገደው ጥምር መንግስት ለማቆም ያሚያስችላቸውን እድል መፍጠር እንችላለን። በዛ ላይ ፖለቲካዊ ወገንተኛነታችንና ፍላጎታችን ሰላማዊ ህጋዊና መንግስታዊ በሆነ አግባብ በትክክል እንዲወከል አደረግን ማለት ነው። ዘላቂነት ባለው መንገድ ዲሞክራሲን ባገራችን ለማስጀመር ይህን ወሳኝ የሆነ ስራ ከወንን ማለት ነው።
ይህ ስሌት ተግባራዊ እንዲሆን የሰማያዊና የመደርክ አመራሮች በጋራ የሚሰሯቸው ፖለቲካዊ ስራዎች ቢኖሩ ጥሩ ነው። ያም ካልተቻለ ካመራሮቹ የሚመጡ አመላካች ንግግሮች አጋዥነታቸው አሌ አይባልም። ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶችና ሜዲያዎች ይህን አይነት ስሌቱ ምርጫው ከሚደረገብት ጠቅላላ አገራዊ ሁኔታ አኳያ ማለፊያ ነው በሚል ቢደመጡ እንዲሁ ያግዛል።