ዲ/ዳንኤል አክራሪ ያሉዋቸው ሰለፊስቶች የሃገራችንን ነባር እስልምና ተከታዮች ቅዱሳን የማይቀበሉ ፅንፈኞች ናቸው ሲሉ አውግዘዋቸዋል። እዚህ ላይ የተቆረቆሩላቸው ለማስመሰል የሞከሩትን የቀድሞዎቹን ሙስሊሞች በዚሁ ንግግራቸው ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር አብረው ሃገር ያደሙ በማለት ሲወነጅሏቸው እንደነበር አድማጭ የዘነጋ ይመስል የዛሬዎቹን ሙስሊሞች ዉንጀላ ጎላ ለማድረግ ለቀድሞዎቹ አጋዥ መስለው ቀርበዋል።
ለነገሩ በቀዳሚነት ሊያሳስባቸው ይገባ የነበረው በሃገራችን የተዋህዶ ኦርተዶክስ ቤተክርስቲያን የምታመልካቸውን ቅዱሳን ከማስተባበል አልፈው የቲዮሎጂ ስነ-ምግባር በጎደለው መልኩ መሳለቂያ እያደረጉ ያሉት አንዳንድ የሃገራችን የፕሮቴስታንት ፓስተሮች ድርጊትና የእርሳቸው እምነት ውስጥ ጉዳዩ ያስከተለው የመከፋፈል ችግርን ነበር ። በዚህም ድርጊታቸው ለአድማጮቻቸው ያላቸን ከፍተኛ ንቀት ይፋ አድርገዋል ።
በንግግራቸው ያነሱት ሌላው ጉዳይ አክራሪዎች የሚሏቸው በአክሱም መስጅድ እንዲገነባ ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው። ከንግግራቸው ለመረዳት የቻልኩት አክሱም ፅላት ያረፈባት ስፍራ በመሆኗ የእስልምና እምነት የአምልኮ ስፍራውን ያረክሰዋል በሚል ህሳቤ ነው። ለዚህ አስተሳሰብ መንስኤው አክሱም ፅድቅነቷ እንዲጠበቅ ከሚያረክሷት ነገሮች የጸዳች ልትሆን ይገባል ከሆነ እስኪ የሚከተሉትን እውነታዎች በሚዛናዊነት ለመዳኘት እንሞክር።
- ሁላችንም የምንኮራባቸው የአክሱም ስልጣኔ መገለጫ ግዙፎቹ ሃዉልቶች ዛሬም የቀደምት ህዝቦቻችን እምነት የሆነውን የጣኦት አምልኮ አሻራን እንደያዙ በአክሱም ከተማ ይገኛሉ። እንደ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ እነዚህ ቅርሶቻችን በተገቢው መንገድ እንዲጠበቁ እፈልጋለሁ ። እዚህ ላይ ግልጽ እንዲሆን የፈለኩት ነጥብ አክሱም ፅድቅነቷ እንዲጠበቅ እንፈልጋለን ባዮች አንድን ቅዱስ ስፍራ ከጣኦት አምልኮ መገለጫ ቅርሶችና ድርጊቶች በላይ እንዴት ሆኖ አንድ አምላክ የሚመለክበት መስጂድ ሊያረክሰው ይችላል ? የሚለዉን ነዉ ።
- የአክሱም ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶች መዳረሻ መሆኗ ይታወቃል። ከዚህም ጋር በተያያዘ መልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዳንኪራ እና ዝሙት የሚፈፀምባቸው ቤቶች በከተማይቱ ውስጥ ይገኛሉ። ዝሙት ደግሞ በመፅሃፍ ቅዱስ ከተወገዙት ሃጥያቶች አንዱ ነው። በእውን ለከተማይቷ ቅድስና የምንቆረቆር ከሆነ ከዚህስ የባሰ የሚያረክስ ጉዳይ ይገኛልን ?
ከላይ የጠቀስኳቸውን ነጥቦች በሚዛናዊነት ከዳኘን በአክሱም የሙስሊሞችን የፀሎት ቦታ መገንባትን የሚቃወሙ ግለሰቦች ለዚህ ሀሳብ ያነሳሳቸው ዋና ምክንያት መንፈሳዊ ገፅታው እንዳልሆነ ለመረዳት አያዳግትም። ይህ ካልሆነ ደግሞ ተቃውሞው ያነጣጠረው የዜጎችን መብት በመግፈፍ ላይ መሆኑ ግልፅ ነው ።
በሃገራችን ህገ-መንግስት አንቀፅ 27 ዜጎች የአምልኮ ስፍራቸውን በነጻነት የመገንባት መብታቸው የተጠበቀ ሆኖ ሳለ ይህን የጠየቁ የአካባቢው ተወላጆችን እና ነዋሪዎችን እንደ ፅንፈኛ መቁጠር ህገ-መንግስታዊ መብትንና ሃገራችን በፈረመቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች የተከበሩ ተመሳሳይ መብቶችን ማስተባበል ጭምር መሆኑን ሊያውቁት ይገባል።
ዲያቆኑ የአክራሪዎች ሌላው መገለጫ ያሉት “ኢትዮጵያ የክርስትያን ደሴት ነች ”የሚለውን ሃሳብ መቃወማቸው ነው በማለት በሃገራችን ኢትዮጵያ የእኩል ባለቤትነት መብት እንዳላቸው የሚገልጹ ሙስሊሞችን ለማሸማቀቅ ሙከራ አድርገዋል ። ይህን አስተሳሰብ ከታሪክም ሆነ ከዜጎች መብት አኳያ መመርመሩ ግንዛቤ ሊያስጨብጥ ስለሚችል የሚከተሉትን ነጥቦች ማየት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የዲ/ ዳንኤልን አጠቃላይ ፅሁፉቸው አንኳር ነጥብ ያነጣጠረው ሙስሊሙን ማህበረሰብ ከሌላ ስፍራ መጥቶ የሃገር ባለቤት በሆነው የክርስትያን ህዝብ መልካም ፈቃድ በአገሪቱ የሰፈረ ውለታ የተዋለለት ባዕድ ህዝብ አድርጎ መሳልን ነው። ይህ ህሳቤ መሰረቱ ክርስትናን ሃገር በቀል እስልምና ግን መጤ አድርጎ በመሳል ላይ የተመሰረተ ታሪክን ያዛባ አቀራረብ ነው። እውነታው ግን ክርስትናም ሆነ እስልምና በመካከለኛው ምስራቅ የበቀሉ እና ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ የገቡ መሆናቸው ነው። ሁለቱንም እምነቶች የተቀበሏቸው ሃገር በቀል ህዝቦች ናቸው። ለዘመናት በግልፅም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ ሲነገር የቆየው እና በህብረተሰብ ውስጥ ለማስረፅ የተሞከረው ህሳቤ ዛሬ ላይ ዲ/ ዳንኤል የደገሙት የተዛበ የታሪክ አቀራረብ ነው። ይህ ህሳቤ ሙስሊሙ እና ክርስትያኑ ማህበረሰብ እኩል የሃገር ባለቤት እና እኩል የሃገር ተቆርቋሪ መሆናቸዉን በማስተባበሉ በጋራ – ለጋራ መብት እንዳይነሳ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬም ይህንኑ ክፍተት ለማስፋት እና የዜጎችን ለጋራ መብት አብሮ መነሳት ለማኮላሸት በሃይማኖት አባትነት ካባ የተሸፈነ አጀንዳ እያራመዱ መገኘታቸው ነው።
ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያ ሃገራችን ዲ/ዳንኤል እንደሚሉት የአንድ እምነት ተከታይ ህዝቦቻችን ብቻ ሃገር ሳትሆን የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ሃገር መሆኗን ነው። ባለንበት በ 21ኛዉ ክፍለ ዘመን ሃገራችን ኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ሃገር ነች ለማለት የደፈሩት ዲ/ ዳኒኤል ኢትዮጵያ የጋራ ሃገራችን ነች የሚለዉን ሙስሊም ወገናቸውን አክራሪ ብለው መወንጀላቸው ለምን ይሆን ? አባባላቸው ቀዳማዊ ሃይለስላሴ እኛ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የማንቆጠርና ይልቁንም የክርስቲያኖች ሃገር በሆነችዉ ኢትዮጵያ የምንኖር መሆናችንን እንዳንዘነጋ በየንግግሮቻቸው “በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች ” እያሉ ይጠሩን የነበረውን አስታወሰኝ ። ልንዘነጋው በማንችለው መልኩ በልቦናችን ይሰርፅ ዘንድ በተረትና ምሳሌ ሳይቀር “የአሞራ ቤቱ ዋርካ የእስላም አገሩ መካ” ሲሉም እንሰማለን። ታዲያ ዲ/ ዳንኤል ይህን ከቀደምት ነገስታቶቻችን ካባ ጎን ለጎን በሙዚየም መቀመጥ ያለበትን ዘመን የሚጠየፈውን ህሳቤ የማንቀበል እና በአገራችን ኢትዮጵያ የእኩል ባለቤትነት መብት ይገባናል ባይ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያንን አክራሪ ሲሉ መወንጀላቸው ምንን ያመላክታል?
ከታሪክ አኳያ፡-
አገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት አገር ነች። በተለያዩ የታሪክ ዘመናትም የተለያዩ የግዛት ክልሎች የነበሯት። በውስጧ የኖሩባትም ህዝቦች የተለያየ የዘር እና የሃይማኖት ስብጥር ፣ የስልጣኔ ደረጃ ፣ የአስተዳደር ስርዓት ወዘተ ነበራቸው ።
በሃገራቸን 3000 ዘመን ታሪክ ውስጥ፡-
- የመጀመርያዎቹ 1300 ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በፊት 900 አመታት እና ከእየሱስ ውልደት በሁዋላ 400 ዓመታት የጣኦት አምልኮ ተከታዮች እና የኋላ ኋላ የተቀላቀሏቸው የይሁድ እምነት ተከታይ ህዝቦቻችን የኖሩባት ሲሆን እነሱም ሁላችንም የምንኮራበትን የአክሱም ስልጣኔን ያስመዘገቡ እና በቅርስነት አስደናቂ ሃውልቶችን ትተውልን አልፈዋል።
- በመቀጠልም የክርስትና እምነትን የተቀበሉ ህዝቦቻችን በ4ኛው ክፍለ ዘመን ከጣኦት አምልኮ ተከታዮች የወረሱትን ስልጣኔ ለ100 ዓመት ካሳደጉት ቡሃላ በ5ኛው ክፍለ ዘመን ስልጣኔው ማሽቆልቆል የጀመረ ሲሆን በ960 በዮዲት ድል እንደተደረገ በታሪክ ተዘግቧል
- በማስከተልም የኩሽ ህዝቦች ዝርያ የሆነው የዛጉየ ስረዎ-መንግስት በ1137 -1270 የተተካ ሲሆን እነዚህ የአገው ህዝቦች የላሊበላን ገዳማት እና አብያተ ክርስትያናት በቅርስነት ትተውልን አልፈዋል
- ከዛጉየ ቀጥሎ የነበረው የንግስና ስርአት ሰለሞናዊው ስርዎ-መንግስት ሲሆን ይህ ስርዎ-መንግስት ከ1270 ጀምሮ የነበረ እና የግዛት ክልሉም በዛሬው ሰሜናዊ የሃገራችን ክልል ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር
ከላይ የተዳሰሰው በዛሬዋ የሃገራችን ሰሜናዊ ክፍል የነበረውን የታሪክ ገፅታ ሲሆን ። በዛሬው የመካከለኛው ፣ የምስራቅ እና ደቡባዊ የሃገራችን ክፍሎች ደግሞ ከ7ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ የሙስሊም መንግስታት (ሱልጣኔቶች) ነበሩ።
- ከነዚህ ውስጥ የሃረር ሱልጣኔት በ7ኛው እና 11ኛው ክፍለ ዘመን መካከል የተመሰረተ ሲሆን መንግስቷም በንግድ የታወቀና የራሷ ገንዘብም የነበራት ነበረች። ከተማይቷ በ2006 በዩኔስኮ የአለም ቅርስነት የተመዘገበች ስትሆን ይህንንም ድርሻ ያሰጧት በ10ኛው ክፍለ ዘመን የተሰሩት ውብ መስጅዶች እና ብዙ የአምልኮ ስፍራዎች ናቸው። ይህ ማለት ደግሞ ከላሊበላም ሆነ ሌሎች ቆየት ካሉ ታሪካዊ የእምነት ቦታዎች ቀዳሚውን ስፍራ ያስይዛታል።
- በሁለተኛ ደረጃ የሚቆጠረው የሸዋ ሱልጣኔት ሲሆን ይህም ከ896 እስከ 1283 የኖረ በጉራጌ ህዝቦች የተመሰረተ ስርዎ-መንግስት ነበር። ግዛቱም ከዛሬይቱ አዲስ አበባ 70 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወለላ ተብላ በምትጠራ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ነበር። ይህ ንግስና ዘጠኝ ሱልጣኖች በተዋረድ የገዙት እና ከ150 ዓመት በላይ የቆየ እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ። በፈረንሳይ አርኪዮሎጂስቶች የተገኙ ሶስት የከተማ ፍርስራሽ እና የመስጅድ ቅሪቶች የሸዋን ኢስላማዊ መንግስት የእድገት ደረጃውዋናም ማረጋገጥ ችሏል።
- በሶስተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የሃድያ ሱልጣኔት ነው። ይህ ሱልጣኔት ከ1300 እስከ 1500ኛው ክ.ዘ የዘለቀ ሲሆን ግዛቱም በዛሬዋ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ድንበሩም በሰሜን በኩል የአባይን ወንዝ የሚነካ ነበር
- የይፋት ሱልጣኔት በመባል የሚታወቀው ደግሞ ከ1285 እስከ 1415 የኖረው ነው። ይህ በአፍሪካ ቀንድ ታላቅ ተብለው ከሚጠሩት የሙስሊም ሱልጣኔቶች ውስጥ አንዱ ነው። ግዛቱም ከዛሬዋ ሸዋ ጀምሮ ባሌን ያጠቃለለ እስከ ምስራቅ ጅቡቲ እና ሰሜን ሶማልያን የያዘ እንደነበር እና ማዕከሉም ዘይላ እንደነበር ታሪክ ያብራራል። ሱልጣኔቱ ሰባት ዋና ዋና ከተሞች የነበሩትና በአስተዳደር ረገድም የረቀቀ እንደነበር መዛግብት ያሳያሉ። በዚህ ረገድ የተለያዩ ያልተጠቀሱ የሙስሊም መንግስታት እንደነበሩ መታወቅ ይኖርበታል እንደምሳሌ፡- የአዳል ፣ ባሌ እና ወዘተ
ከላይ የተመለከተናቸው አጠር ብለው የቀረቡት ታሪኮች በግልፅ እንደሚያሳዩት ዛሬ የኛ ትውልድ የሚኮራባቸው ታሪኮቻችን በዛሬው የሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የኖሩት የጣኦት አምልኮ ተከታይ ህዝቦች የተዉልን ስልጣኔ 1300 ዓመት እድሜ ያስቆጠረ እንደነበር አይተናል። ከዛም የክርስትና እምነት ወደ ሃገራችን የሰሜኑ ክፍል ከገባ ቡሃላ የራሱን ድርሻ አበርክቷል። በተመሳሳይ መልኩ በዛሬው መካከለኛ ፣ ምስራቃዊ እና ደቡባውው የሃገራችን ክፍሎች ደግሞ የእስልምና እምነት የሚከተሉ ህቦቻችን ያበረከቷቸውን ታሪካዊ ስልጣኔዎች እና ቅርሶች ለማየት ሞክረናል። ከዚህ ላይ መረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያ ሃገራችን ዲ/ዳንኤል እንደሚሉት የአንድ እምነት ተከታይ ህዝቦቻችን ብቻ ሃገር ሳትሆን የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ሃገር መሆኗን ነው። ዲያቆኑ ይህን መሰሬታዊ ነጥብ እንኴ ለመረዳት ያለመቻላቸውን አሳፋሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ።
የዲ/ዳንኤል ሌሎች የአክራሪነት ክሶች በጥቅሉ፡- የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በሃገራቸው ያላቸውን ዜግነት እና ህገ-መንግስታዊ መብቶች የጣሱ ናቸው እንደምሳሌ፡-
- እርሳቸው ለአፍሪካ እና ለዓለም ሃዋርያነት እራሳቸውን እና ተከታዮቻቸውን ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው ሲሰብኩ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ወገኖቹን ማስተማሩን እንደ ፅንፈኝነት መገለጫ መቁጠራቸው
- ለራሳቸው ተከታይ ምዕመናን የክርስትና ትምህርትን እንዲያስፋፉ ጥሪ በማቅረብና ህዝበ ኦርቶዶክሱ ሃይማኖቱን በማስፋፋቱ በኩል በንቃት ባለመሳተፋ ወቀሳ ሲያቀርቡ ፥ በሙስሊሞች በኩል ያለዉን በተመለከተ መድረሳዎችን እና የቁርዓን ት/ቤቶችን የሚያስፋፉት አክራሪዎች ናቸው በማለት ወንጅለዋል
- በመላው የሃገራችን ግዛቶች (ክልሎች) በኢስላማዊ ትምህርት በዲግሪ የሚያስመርቅ አንድም ተቋም የሌለ ሲሆን በዲፕሎም ደረጃ አንድ አወልያ ብቻ እንዳለ እየታወቀ አክራሪ ሙስሊሞች በነዚህ ዘርፎች ብልጫ ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው ልናጋልጣቸው ይገባል ሲሉ ለምእመኖቻቸው ጥሪ አድርገዋል። ይህ አባባላቸው እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በሃገራችን ያለንን መብት ለመንፈግ የተደረገ የማን አለብኝነት ስሜት ነው።
”ሽብርተኞቹ ንግድ እና ትምህርትን ቀላቅለው የሚያስኬዱ በመሆኑ መረጃ በመሰብሰብ እና በማጋለጥ ለመንግስት ማሳወቅ ይኖርብናል” ብለዋል። ይህም አባባላቸው ተምረው ራሳቸዉን ፣ ሃገራቸውን እና ህዝባቸውን ለማገልገል የሚተጉ ሙስሊም ዜጎችን ለማሸማቀቅ ብሎም ከትምህርት እና ንብረትን ከማፍራት ለመግታት የሚደረግ ኢ-ፍትሃዊ እና ኢ-ህገመንግስታዊ የዜግነት መብት ጥሰት ነው።
ዲያቆን ዳንኤል እንደ አንድ የሃይማኖት አባት እውነት በመናገር እና ሚዛናዊ ግምገማ በማድረግ አርአያ ሊሆኑ ሲገባ በተቃራኒው የእስልምናን ገጽታ ለማጠልሸት ባላቸው ስሜት በመነዳት በክርስትናም ሆነ በሌሎች ሃይማኖቶች መሃል ግጭቶች የተነሱና ደም ያፋሰሱ እንደ ነበር በመሸሸግ በእስልምና ውስጥ ብቻ ተነሱ የተባሉትን በማጋነን እኛ ሙስሊሞችን ለማሸማቅቅ ሞክረዋል ። እስልምና ከጥንት ጀምሮ ነውጥ ያስከተለ ብቸኛ እምነት ለማስመሰልም
- ሰለፍይ ብለው የሚጠሯቸውን ሲገልፁ -”ጥንት ከጅምሩ የአስተምሮቱ ተከታዮች እስልምናን ከቁርዓንና ከሃዲስ ውጭ ሌላ ጭማሪ ሳይደረግበት መተግበር አለበት የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ የሚያራምዱ ናቸው “በማለት የኮነኑ ሲሆን፣ በተመሳሳይ አካሄድ በክርስትና እምነት ውስጥ የ reformation መሪና የፕሮቴስታንት ዘርፍ መስራች የሆኑት ማርቲን ሉተርን መፅሃፍ ቅዱስ ብቻ (sola scriptura) ማለትም መፅሃፍ ቅዱስ ብቻ የእምነት መመሪያ ሊሆን ይገባዋል በሚል መርህ የፕሮቴስታንት የእምነት ዘርፍን የመስረቱ መሆናቸውን ሸሽገዋል።
- የስለፎች እንቅስቃሴ በአረቢያ እና አካባቢዋ በርካታ ግጭቶችን ያስነሳና ለበርካታ ህይወት መጥፋት ምክኒያት እንደ ነበረ ሲገልጹ እንደ አንድ ታአማኒነት ያለው እዉነት ፈላጊ የሃይማኖት አባት በማነጻጸር ሚዛናው ግንዛቤ እንዲኖረን በሪፎርሜሽን ሳቢያ ተቀስቅሶ አውሮፓን ለ 124 አመታት (ከ 1524 እስከ 1648) የጦርነት አውድማ ያደረገዉንና የጀርመንን ፣ የፈረንሳይን ፣የኦስትሪያን ፣የሃንጋሪን፣የጣሊያንን ፣የፖላንድን ፣ የስሎቫኪያ እና የዩክሬንን 30% ህዝቦች ለእልቂት የዳረገዉን አሰቃቂ ሃይማኖታዊ(ክርስትያናዊ)ጦርነትን ግን ለምን ሸሸጉን ? ሰለፎች ባራመዱት አስተምህሮት ሳቢያ የተፈጠሩትን የህይወትና የንብረት ውድመትን የምያሳዩ ማስረጃዎችን ቢፈትሹ እርሳቸዉም በስሜት ከመነዳት ድነው ሌሎች ወገኖቻችንንም ከስህተት እንዲድኑ ለማድረግ ይችሉ ነበር።
ጥንትም ሆነ ዛሬ የጥፋት ሃይሎች በሁሉም ሃይማኖቶች ስም ወንጀል የሚፈጽሙ መሆናቸው እየታወቀ ዲያቆን ዳንኤል ግን ለጥፋት የተሰማሩ ድርጅቶች በእስልምና ስም ብቻ የሚንቀሳቀሱ ለማስመሰል እንደ አል ቃእዳ ፣ አል ሸባብ ፣ ቦኮ ሃራም ወዘተ ያሉትን የጥፋት ሃይሎች ብቻ ገልጸው በክርስትና ስም ጥፋት ያደረሱና በማድረስ ላይ ያሉትን በሰሜን ዩጋንዳ በክርስትና ስም የምንቀሳቀሰዉን ፣ አስርቱን ቃላት በስራ የማዋል አላማ አለኝ የሚለዉን እና እስከ 150 000 ለሚደርስ ህይዎት መጥፋት ምክኒያት የሆነዉን Lord Resistace Army LRA፣ በኦርቶዶክስ ስም ተንቀሳቅሰው በስረብረኒካ እስ 8 000 የሚደርሱ ሰላማዊ ሙስሊሞችን የፈጁ አክራሪ ኦርቶዶክስ ሰርቦች ፣ በ 2014 Central Africa በብዙ ሺ የምቆጠሩ ሙስልሞችን በግፍ የጨፈጨፉና የጥቂቶቹን ስጋ የበሉ ራሳቸውን የክርስቲያን ሚሊሺያ ብለው የጠሩትንና ሌሎችንም ሸሽገዋል።
በጥቅሉ የዲያቆን ዳንኤል ፅሁፍና አዉድዬ የአንድ ሃገር ዜጋ የሆነ ህብረተሰብን የዜግነት መብት የሚያስተባብል በእምነት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እርስ በእርስ በባላንጣነት እንዲተያዩ በማድረግ ለጋራ ጥቅም እና መብት በጋራ እንዳይነሱ ለማድረግ ያለመ ነው። እንደሃይማኖት አባትነት ወደ ልዩነት ከሚያመሩ ጎዳናዎች ምእመናንን በመከላከል ህዝቦች ተሳስበው ፣ ተከባብረው ፣ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው እንድኖሩ መምከር ስጠበቅባቸው ፣ እሳቸው ግን በተቃራኒው ህዝባችን ተራርቆ ወገኖቻችን የጋራ ሃገራቸውን እንዳይጠብቁ እና እንዳይገነቡ እሳት የመጫር ዓላማ ያነገቡ ናቸው ለማለት እደፍራለሁ።
ጨረስኩ ።
ቸር እንሰንብት!
አብዱላህ
25 March 2015