November 28, 2014
39 mins read

የወያኔ ምርጫ – ገረጭራጫ! (ሥርጉተ ሥላሴ)

ይሄ አዲስ የሚሉት የነጮቹ ዓመት ደግሞ አይደክመው መጣሁ እያለ ሃገር ምድሩን አካሎታል። አልኳችሁ እሱ ለሚመላለሰው፤ የእሱ ጫማ እልቅ ለሚለው እኔኑ ድክም – ግን አልገርምም?! ህም – ስገርም። እርግጥ ነው ለእነሱ አዲስ ነው – ያደላቸው።

ወይ አቶ ምርጫ፤ ወይ አንተ ወይ እኛ አንደክም ያው አራት አመትህን እዬጠበቅህ ለማጥበቅ – ለማክረር በገረጭራጫ ባህሪ ለመቁላትና ለመፍጨት መጣሁ – መጣሁ ትለናለህ። እኔ የማዝነው በፍታዋራሪ ሂደት ነው። ባዶን አዝሎ እስከ መቼ እንደሚዳክር ግርም ይለኛል።

እንደ እኔ እንደ ሥርጉተ ምርጫ የሚመረጥ ነገር ሲኖር ወይንም ለማማረጥ የሚያስችል ጠረን ሲኖር ነው። በምድረበዳ ላይ – … ግን እኔ እንጃ ነው – ሁልጊዜ ኩታራ፣ አንድም ቀን ግርጫ ጸጉሩ በመንፈሱ ላልሰከነ አረግራጊ ዬጎጥ ማንፌስቶ ሩህ መባዘን ግን – ህም ነው እም።

አሁንም እኔው እላለሁ ምርጫ መከባበሩም፣ መደማመጡም፣ ትብስ ትብሺ መባባሉ፣ ቀና ፉክክሩ ሲኖር ነው ለዛ ወግ የሚደረሰው። ግን ግን ክብረቶቼ ከላይ ከደርቡ ጉብ ያደረኳት እርእስ ቃሏ አዲስ ከሆነች ትርጉሟ እንዲህ – „ገረጭራጫ“ ፈጽሞ – ለምንም ነገር የማይመች – ጸባዬ ጎርባጣ፣ ጸባዩን ለመተርጎምም የማይቻል – ውጥንቅጥ፤ ወጣገብ የሆነ፤ ቁርጥርጥ ያለ ሥነ ምግባር ያለው፤ ቋሚ ባህሬ የሌለው፤ ነጭናጫና ሰላምን ፋቂ፤ የሚወራጭ – ተናካሽ ጦሮ* እንደ ማለት ነው በጥቂቱ። ጥሎበት ደግሞ የወያኔ የምርጫ ሂደት እኔ ከሰጠሁት ትርጓሜ በከፋ ሁኔታ እጅግ ወልደ -ግራ ወልጋዳ ነው። የሆነ አይሉት በረዶ አይሉት እሳት አይሉት እረመጥ አይሉት ወጀብ- በቃ መቀቀያ ኮንቴይነር ነገር፤ ውሎው ጉዞው የማይታወቅ ቅብጥርስ – ምንትስ ነው … እንደ ተፈጥሮው ….

የወያኔ የምርጫ ሂደት መሰረቱ የስታሊን ዶክተሪን ነው። በዚህ መስማማት አለብን። እኛ ብቻም ሳንሆን ብድሩንም እርዳታውንም የሚያጎርፉለት የውጭ ሀገር ዲታዎች፤ በአንድ በኩል ፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር አይንህ ላፈር እያሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጎጡን ሶሻሊሳታዊ ጎፈሬ የባጣጥራሉ እነ-አሜሪካ። ስታሊን ማን እንደሆነ ደግሞ አቶ ጉጉል ቢጠዬቅ ቀልጣፌ ዘረጋግፎ ከነዝክንትሎ በቃኝ እስክትሉ ድረስ ያመጣዋል …. ለሚፈልግ ማለት ነው። የሾሻሊዝም ርዕዮት ብዙኃኑን የዳቦ እኩል ተጠቃሚ ይሆናል ከሚል እሳቤ የመነጨ ቢሆንም ወደ ተግባር በስው እጅ ሲድበለበል ግን ፍጹም ነጭናጫና አንባገነን፤ ገርጭራጫና አውሬ ባህሪ ነው ያለው። ይወራጫል – ይፎነጫጭራል – ይናከሳል – ያቆስላል — በአሳቻ* ከአገኝም አጋድሞ – ቅርጥም።

ምርጫና ሾሻሊዝም /ምርጫን ህብረተሳባዊነት።/

ምርጫ የሚባለው ነገር በሶሻሊዝም ሽሙንሙን ብለው፣ ዝንጥ ባሉ ቄንጠኛ፤ እንደ ዘመነኛው የፋሽን ዕይታ ሽቅርቅር ባሉ ብራናዎችና – ብዕሮች ይሰተናገዳል። ከህገ መንግሥቱ ጀምሮ መዋቅሩ፣ የአፈጻጸም መመሪያው ማኒፌስቶው ኩሉም ሻዶውም ሳይቀርባቸው አምረው ሽክ ብለው ይሰናዳሉ። የተግባር ሂደቱ ግን አሹቅ ነው። የመንግሥት መዋቅር ለመዘርጋት ከታች ወደ ላይ ምርጫው የሚከናወነው ንጥር ባለ ድርጅታዊ ሥራ ነው። ማጣሪያውም ድርጀታዊ ሥራ በቃ! ገዢው ፓርቲ የህዝቡን ፍላጎት ሳይሆን የፓርቲውን ህልውና ሊያስቀጥሉ የሚችሉትን፤ ለፓርቲው ፍላጎት ጥበቃ ሊያድርጉ ይችላሉ የሚላቸውን የራሱን ደምና ሥጋ ከታች እስከ ላይ የሚደረድረው ከዓመት በፊት ነው። ቀድሞ። ፎቷቸው ቢያምረውም ባያምረውም – ብቻ አንቀልባ ይሁኑለት።

ዬምርጫ ውድድር ላይ ተወዳዳሪዎች ከዝቅተኛው ክፍልም እዬተባለ ከሚኒስተሮች ጋር እኩል አንድ የእኔ ቢጤ አቧራ ላይ ያለ እጩ ተወዳዳሪ ይሆናል። ታዲያላችሁ ከምርጫው ቀደም ብሎ አንድ ጉልበታም ተግባር ይከወናል። ያም ምስኪኑ ለህዝብ ቀርቦ እኔ ከውድድሩ እራሴን አግልያለሁ – በፍቃዴ እንዲል ይደረጋል። በተጨማሪም ከእኔ ይልቅ አቶ ወይንም ጓድ እከሌ የበለጠ ለሀገራዊ ጉዳይ ወሳኝ ናቸውና እሳቸውን ምረጡ ብሎ ለተወዳዳሪው ካድሬ ሆኖ እርፍ … በርድ – ብርድ። ወይንም እጩ ተለጣፊው ተወዳዳሪ ወይንም ማሳሳቻ አዘናጊ ተወዳዳሪው ጤናዬ ተጓድሏ፤ ወይንም ፍላጎቴ በኗል፤ ብቻ አንድ የቀደመ ጠንካራ ምክንያት ተፈጥሮ ከህዝብ የወጣው እጩ እንደራሴ እራሱን ያሰናብታል – በፈቃዱ። ፈቃዱ ግን ስውር ነው። ለውድድር እጩ የሚሆነውም በስውር ዬሚሰጠውን የቤት ሥራ ለመከወን መሆኑን – ያውቀዋል። ከአንድ የሀገር መሪ የፕሮቶኮል ሹም ጋር ተወዳድሮ እንደማያሸንፈው …. ይሄ እንግዲህ የሶሻሊዝም የተቀበረ ዬነፃነት ግበዐተ – መሬት  ንድፈ ሃሳብ ነው። አረሙ ወያኔም የሚመራውም በዚህ ነፃነት በተጎረጎረበት – በተቦረቦረበት መንፈስ ነው …. 100%

የምርጫው ውቂ ደብልቂ በድለቃ ይከወናል። በታቀደው መሰረት። ተማራጩም ቃል ኪዳኑ – ውሉ ለህዝብ ፍላጎት ተፈፃሚነት ሳይሆን በድርጅታዊ ሥራ ቦታውን ሆነ ሥልጣኑን ላስገኘለት ገዢ ፓርቲ ይሆናል። ምደባ ነው እንጂ በሶሻሊዝም ምርጫ ፈጽሞ ኑሮ አያውቅም። በምርጫና በምደባ መካከል ያለው ልዩነት በሰውና በእንሰሳት መካከል እንዳለው ያህል ነው። ቀድሞውን ነገር ተማራጮች የህዝብ ጉዳይ ቁባችውም አይደለም። ስለምን? በህዝብ ድምጽ ሳይሆን በድርጅታዊ ተግባር ነው የተመደቡትና። ስለዚህ ተቆርቋሪነታቸው ምደባውን ወይንም ሹመቱን ላፀደቀላቸው ድርጅት ያዘነበለ ይሆናል።

መቼም የጹሑፌ ታዳሚዎች እንደምታውቁትም በጣም ከጥቂቶች በስተቀር ጥቅሙን የሚፃረር ተጠቃሚ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም። እንግዲህ ከዚህ ላይ  ህዝብ የተራበው ተስፋ መክኖ ይቀራል። ራህብተኛው ከተስፋው ጋር በዚህ በሰላ ደባ ይተላለፋል። ይህን ሂደት የሚያውቁት በውስጡ ያለፉና የኖሩ ሰዎች እንጂ ሰፊው ህዝብ ይህን ድብልብል ጉድ አያውቀውም። የምርጫው ወረቀት ሲቆጠር አንድ ብቻውን የተወዳደረ ሰው ብቻ ይሆናል የሚያሸንፈው። የምርጫ ዳንኪራው ማስመሰልን ለመሞሸር ብቻ ነው። የሀገር ሃብት የሆነው ወጪውም – ጉልበትም – ሃይልም የቅስቀሳና የፕሮፖጋንዳ ሆነ ዬምርጫ ኮማንድ ፖስቱ ትርምስ – ለምንም! እርግጥ ለውጪ ሚዲያ ብርንዶ ነው።

እራሳቸውን ሳያገሉ ለቁጥር ማሟያ በሚቀጥሉትም ላይ ቢሆን፤ ገዢው ፓርቲ በፈለገው መስመር ገብቶ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ሊሰጡበት የሚገባ ቀጭን ትእዛዝ በድርጅታዊ ሥራ መስመር አስቀድሞ ይነግራቸዋል። ስለዚህ ዝንባሌው ተጣቃሎ የገዢውን ፓርቲ በርሚል ቲፍ አድርጎ ይሞላዋል። ማሟያዋች ተንሳፈው ይቀራሉ። ይህ ቁልጭ ያለው የሶሻሊዝም የለበጣ ጅዋጂዊቱ ነው። ሃሳብ ሲያቀርቡም የዝንጀሮ ቆንጆ ተስራታ አዳራሽ እንደ መጣች ያህል ይላገጥባቸዋል። ክብራቸው ያለ ይግባኝ ይጨፈላለቃል። ለስብሰባው ሆነ ለጉባኤው ባይታዋር መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ግልምጫው እስኪባቃው ድረስ ይከተክታቸዋል። ስለምን? በነሱ ባልሆነ ህዋ ውስጥ ስለሚኖሩ። የሚያሳዝነው ለዚህ ትራጀዲ ትዕይንት ደግሞ ብዙሃኑ ታስሯል፤ ተገርፏል፤ ተሰዷል – ሙቶለታል። በገበሬ መንደር በ97 ምርጫ ቅንጅትን የደገፉት እስካሁን ድረስ ያልተፈቱ እንደሚኖሩ በጣም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ከዛም በኋላ በተካሄደው ምርጫ ቢሆን አስተውሉ ለአንድ ተማላ ገበርዲን ለባሽ ተመረጭ ወይንም የህዝብ እንደራሴ መጠነ ሰፊ መስዋዕትንት ተከፍሏል። እነኝህ ብዙኃን ደመ ከልብ ናቸው። በዝርዝርም አይታወቁም። እኛ የምንጮኽላቸው ማዕከል ላይ ለሚታሰሩት ወይንም ለሚገደሉት መረጃው ለተገኘላቸው ብቻ ይሆናል። ምክንያቱም የእኛም አቅም ውስን ነው፤ በዛ ላይ በፍላጎት በነፃ በትርፍ ጊዜ እንደ ሆቢ ነው የነፃነት ትግልን ያህል አውራ የህልውና ጥያቄ፤ በኽረ የሰብዕዊ መብት ጉዳይ የሚሠራው፤ በመደበኛ እዬተከፈለው የሚሠራ የለም።  ይህ ማለት የህዝብን መብት የሚጠበቅ ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊነቱን በሚገባ ያብራራል። የሚያስፈልገንም ሀገራዊ እንክብካቤና ጥበቃ ከገጠር እስከ ከተማ እኩል ለዜጎቹ የሚያደርግ ሥርዓትን መገንባት ነው። ምርጫ በመጣ ቁጥር ተስፋን አገኛለሁ በማለት ተስፈኛው ቀድሞ በከሸፈ ውድድር በዬጊዜው መሬት አልባ የሆነው ወገን ስፍር ቁጥር የለውም – የተፈናቀለው – በድብደባ ህይወቱ ያለፈው። ይህን ሁሉ ጥሰው ተስረክርከው የሚገቡ ቢኖሩም ፍላጎታቸው ሰምጦና ረግቦ ነው የሚቀረው። ለምን? ምክንያት

  1. አናሳ ናቸው – በፐርሰንት ሲሰሉ ከቁጥር በታች ናቸው ….
  2. በሌላ በኩል ደግሞ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች – ከስብሰባው በፊት ቀደም ብዬም እንደገለጽኩት ተለይተው የተለዬ ግዳጅ ይሰጣቸዋል። ይህ ማለት በድርጅታዊ ሥራ የፓርቲውን ተግባር እንዲከውኑ አስቀድሞ በጉዳዩ ዙሪያ ይደራጃሉ። አዳራሽ ውስጥ የሚታዬው ነገር ሁሉ ውስጡ ተለብዶ በአለቀ – በተወሰነ – ቀድሞ በጸደቀ ጉዳይ ላይ ነው የድጋፍ – የተቃውሞ እጂ ሲነሳና ሲወርድ ወይንም ጭብጫባው ሲደለቅ ዬሚታዬው …. ተግባባን ይሆን ውዶቼ ….
  3. በሶሻሊዝም ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ህብረ ብሄር ፓርቲ ብሎ ነገር አልተፈጠረም በራሱ በቲዎሪው። እንደ ወያኔ ሸንኮፍ ወይንም መሸፈኛ ልጣጭ ነገር በመስራት ካልሆነ በስተቀር። በሶሻሊዝም የምርጫ ህግ አንድ ሰው እስከ ህልፈቱ ድረስ በምርጫ አሸናፊ ተብሎ እንደ ገዘገዘ እንዲኖር ይፈቀድለታል።

ከዚህ ያፈነገጡ የተሻለ ራዕይ ያላቸው ምሰሶዎችን (pilars) ደግሞ ቀድሞ ነው ገረጭራጫማው የሶሻሊዝም አንባገነናዊ የምርጫ ሰረጋላ የሚጠቀጥቃቸው። ድብዛቸውን – ጥፍት። ንጹህ አዬርም በተዕቅቦ በሆነበት የካቴና ስንቅ ያደርጋቸዋል። ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚዲቅሳ፣ አቶ አንዱ አለም፣ አቶ ናትናኤል፤ አቶ በቀለ፣ አቶ ሃብታሞ አቶ ዳንኤል አቶ የሺዋስ … አብርሽ  ወዘተ … ናሙናዎች ናቸው / ለምስል – ለምልክት የሆነ ነገር እሲከጣፋ ድረስ … ይሄ „አሸባሪነት“ የሚለው የወያኔ ፍላጎት ተሸካሚ ባይረስ እኮ አጨዳውን የሚጀምረው ገና ከማለዳው ነው። … አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ወግ አሰኝቶኛል? ልለው ነው። ይሄው  ….

ሁለት የኩርድሽ የነፃነት ታጋዬችን አውቃለሁ። አንዷ ሁለት እግሯን ትግል ላይ አጥታለች። በጣም ጓደኛዬም ናት። ሌላዋም ሙሉ ዕድሜዋን እንደ ባከነች የኖረች ናት። ለራሷ ብጣቂ ጊዜ የላትም። ሁለቱም የራዲዮ ጋዜጠኞች ናቸው። የጣይቱ ልጆች ዓለምአቀፉን የሴቶችን ድምጽ ሲያሰተጋቡ የደረሰባቸውን ነገርኳቸው። አብረንም ቪዲዮውንም አዬን። እና ስለ ዓለምአቀፍ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዝምታም ትንሽ አወጋጋን። ከዛ እኔ „እኛ ጥቁሮች ነን። ለነጻነት የሚደረግው ትግልም „በአሸባሪነት“ ተመድቧል። የነፃነት ትግሉ ቤተሰቦች የሆኑት እንኳን በነፃነት ትግል ሂደት ውስጥ ገዢው ፓርቲ „በአሸባሪነት“ የሚመድባቸውን መለዬት የሚቸግራቸው ይመስለኛል። እራሳቸውን ጨምረው በተሳሳተው ዬውንጀላ ክሱ ውስጥ የሚደረቡት ይመስለኛል አልኳቸው።“ ከነሙሉ አካሏ ያለችው የነፃነት ታጋይ ለዘመናት የሚሆን ነገር ነበር የነገረችኝ „ ለነፃነት ዬሚደረግ ትግል የቆዳ ቀለሙ ጥቁር ነው። እኛ ቆዳችን ነጭ ነው። ነገር ግን የምንታዬው በአውሮፓ ኮሚሽን ግን እንደ ጥቁር ነው። የምንገለለውም ልክ እንደ እናንተ ነው። በተጫማሪም እንደ አሸባሪነት ነው የምንታዬው። አዎን ለነፃነታችን አሸባሪዎች ነን። በዚህ እደግፍቸዋለሁ። የነጭ ጥቁርነቴንም ለነፃነቴ ስለሆነ ተቀበይዋለሁ። ቆዳዬ ነጭ መንፈሴ ግን ጥቁር ለለበሰ ነፃነት ፅድቅ የሚታገል። በዚህም እኮራለሁ“ አለችኝ። ለዛውም እሷ በተፈጥሯዋ የተረጋጋ መንፈስ የላትም። ቡና እዬሄደች ነው የምትጠጣው፤ ምግብም በመንገድ እዬሄደች ነው የምትበላው፤ ስታናግርም ሌሎች ነገሮችን እዬሰራች ነው። …. የነፃነት ራህብ እንዲህ እራስን ያሰረሳል …. ብክን ያደርጋልም።

ወያኔ ለነፃነታቸው ራሳቸውን የሰጡትን „አሸባሪ“ ቢል አይደንቀኝም። እሱም ያውቀዋል በዓለም ዐቀፉ የአሸባሪዎች ዝርዝር ማን እንዳለ። እሱ ነው ጉብ ብሎ ቀይ መብራቱ ቦግ ያለበት። ወስጤ ቁስል – እርር – ኩምትር የሚለው ግን ለእኛ ንጹህ አዬር፤ ለእኛ የተረጋጋ የቤተሰብ ምሰረታና ኑሮ፤ ለእኛ የህግ ጥበቃና ከለለ፤ ሁሉንም ለሆኑት – ለሰጡት፤ ወጣትነታቸውን ሳይሳሱለት – ለገበሩት፤ የጥበብ ፍቅራቸውን ለነፃነት ትግሉ ላበረከቱ አርበኞቻችን ፍርጃ ውስጥ የእኛው አካል በወያኔ የቅጥፈት ውንጀላ ቃል ማህጸን ውስጥ መጸነሱ ወይንም የውንጀላው እትብተኛ መሆኑ ነው። የአራዊት ፍላጎት ወዝ – ጠገብ ከመሆን ምን ይሻላል ትላላችሁ የኔዎቹ?! …. ብቻ እንዲህ ያለ የተሙረቀረቀ ያለዬለት ሰብዕና የአካሌ ጥግ ሲሆን አዝናለሁ ዬሚለው ቃል ውስጤን አይገልጸውም – ፈጽሞ። እያለሁ እሳቱ በላኝ ወይንም የቁጭቱ ነዲድ ገረፈኝ ልበል ይሆን? ወይንስ እንደ ልብ አምላኩ ነብይ „የቤትህ ቅናት በላኝ“ እንዳለው „ለጧፎቹ የተለኮሰው ቃጠሎ እኔንም በሞፈር ዘመት አነደደኝ“ ልበልን?! ምጥና – ማጥ ነው ጉዳችን።  ዓላማውን ከሳተ ከተሳሳተ የነፃነት ቁልፍ መክፈቻነት አንድነኝ ነው። ማህከነ-ተሳህለነ-ማረን ….ኧረ ማረን ፈጣሪ … አይሰማ ጉድ የለ … ህም! የትናንቱ “አሸባሪ” የዛሬ የዓለም የነፃነት አባት የተከበሩ ሟቹ ኔልሴን ማንዴላ ነፃነታቻውን ያስገኙት በእስር ላይ ሆነው ነው። እስራቸው ጉልበታም ነበርና። ዬእኛዎችም የነፃነት አርበኞቻችን የሚከፍሉት መከራ በራሱ የነፃነታችን አስገኝ ጉልበታም ኃይል አለው። አረበኞቻችን ለምትከፍሉት መስዋእትነት ከክብር ጋር እናመሰግናለን። ታሪካችንም ናችሁ!

የወያኔ ምርጫ እጅግ ብስጩ – ገረጭራጫ – ተንኳሽ እንዲሁም ቁጡ ስለሆነ፤ ነገ ከነገ ወዲያም ይቀጥላል ማናቸውም ዓይነት ጥቃቱ። ያው ጥቃቱ ማህተሙ እስኪመታለት ድረስ እኛው – እኛን እንታገላለን። የካቴና ፊርማ መፈረሙ ሲረጋገጥ በቃ ምን ሲገደን የአለም ውብ ውደሳዎች መደርደር ነው። „ጀግና – አርበኛ – ሰማዕት – በተግባር የጸደቀ ..“ አሁን ወጣት ፓለቲከኛው አቶ ይድነቃቸው የበሰለ ሃሳቡን – ግንዛቤውን – ዕይታውን በድፍረት እዬገለጸ ነው። አቅምን ዋጮው ወያኔ ደግሞ በዓይነ ቁራኛ እዬተከታተለው ነው – እሰከ ቤተሰቦቹ – ወገኖች ድረስ። ጉልበታም ትችቱን – ወያኔ አይወድለትምና። ነገ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና በህይወቱ አንድ ነገር ቢደርሰ ፎቶውን ይዘን አደባባይ … አካውንታችን ሁሉ የእሱ ፎቶ …. በቃ። አቶ ሃብታሙ አያሌው በፓናል ውይይቶች ሁሉ የሚቃርባቸው ስልጡን ሃሳቦቹ ውስጥ ነበር። ያን ጊዜ ምንም ነበር – ለእኛ። ዛሬ ደግሞ በላይ ዘለቀ። በላይ ዘለቀ ማለት የሀገር አንጡራ ታሪክ ማለት ነው። ለወጣቶቻችን ሻማነት ቢያንስ ለሚከፍሉት መስዋዕትን ቅርብነት እንኳን አቅም ያነሰዋል። ለእኔ ወጣት ይድነቃቸውና ሳልጠግበው እንደ ሳሳሁለት የካቴና እራት የሆነው ቅኑ የግንባር ሥጋው አቶ ሃብታሙ አያሌው አኩል መስመር ያሉ፤ መሳ ለመሳ የሚገኙ የነገ ፀሐዮቻችን ናቸው – ሌሎችም። ውድ የሀገሬ ልጆች አቅማችን አናሳፍፈው – ወይንም አንጋፋው – እባካችሁን። ፍላጎታችነንም አንገቱን አናስደፋው__ አራዊቱ ወያኔ ይበቃቸዋል።

ወጣቶች ግለኞች አይደሉም። ወጣቶች መንፈሳቸውን ለህዝብ ፍቅር ፈቅደው የሚለግሱ ሻማዎች ናቸው። እያሉ እንኳን እስኪ እናክብራቸው – እስኪ እንወደዳቸው – እስኪ እናበረታታቸው – ነፃነት ማለት እናት ማለት ነው። ምድር ሁሉንም የሚችል ሁሉንም የሰጠው ነው። ስለዚህ መሬት በእናት ትመሰላለች። እኛ ሊርብን የሚገባው ነፃነትም እናት ሆድ መሆን አለበት። ስለዚህ ሃሳባቸውን – ራዕያቸውን – ዕይታቸውን – ፍላጎታቸውን ያለገደብ ያለ ተዕቅቦ ይስጡ … ቢያንስ ያ ካቴና እስኪቀማን ድረስ። …. ወይንም በሆነ ነገር መንፈሳቸውን …. እህ …. እ! ቀደም ባለው ጊዜ ርትዑ አንደበት በተሰጠው በአቶ  ሃብታሙ ላይ፤ በብዕረኞች በአብርሽ ላይ ሆነ በተሜ ላይ የነበረባቸውን ነገር እናውቀዋለን። አሁን ደግሞ „አንድ ዓይን ቢኖር አሱንም በዘነዘና“ ይላል ጎንደሬ ሲተርት። አብሶ በጋለ ምጣድ ላይ እንደ አሹቅ ለሚቀቀሉት አትኩሮት – የመንፈስ ድጋፍ ጥበቃ ማድረግ ይገባል። ይመስለኛል። መሽቶ በነጋ ቁጥር – የስጋት ዝግን … ነው ዕጣ ፈንታቸውን እዬፈተለው ያለውና።

ምርጫው የወያኔ ሃርነት ትግራይን ፍላጎት ለማስቀጠል ነው። ሌላው ቀርቶ በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፊያለሁ የሚለው ባለ – ጎራዴም ቢሆን አድፍጦ የተቀመጠው ወያኔ ቢያዳልጠው ያንኑ የተገኘውን ነባር ጥቅም ለጎጥ ፍላጎቱ ለማስጠበቅ ተብሎ ነው። ከመንጋ አስተሳብ የህዝብ ጥቅም ዕሳቤ ይመነጫል ብሎ ማለሙ ሂሳቡ – ቀመሩ – አምክንዮው ለእኔ አይገባኝም።

በተረፈ እሳት ላይ ያሉት እነሱ፤ ቋያ ላይ ያሉት እነሱ፤ ወላፈኑ የሚገርፋቸው እነሱ ስለሆነ እኛ አስተያዬታችን እንደ ዜጋ ልንሰጥ ብንችልም „ከባለቤቱ ያወቀ … “ እንዳይሆን የኖሩንበትን የወያኔ አጨዳ በአዟሪት ትዕይንት እናድሰዋለን ካሉ፤ መካራውን እንችለዋለን፤ ትክሻችን ደንዳና ነው ካሉ ምርጫውም – መብቱም የእነሱ ነው። ድካሙ ግን ለሁለት ቢበዛ ለ5 ተማራጭ ነው። ወረዳና አውራጃ ገበሬ መንደር ደግሞ ሺዎች ይህ ዕውን ይሆናል ብለው ሁሉንም ይቀባላሉ። ዛሬም፣ የዛሬ አራት ዓመትም፤ የዛሬ ስምንት ዓመትም፤ የዛሬ 16 ዓመትም ወዘተ …  ከሶሻሊዝም ለዛውም ከጎጥ ሶሻሊዝም ብናኝ የብዙሃን ነፃነት ይገኛል ብሎ መጠበቅ ቀን እንደ ሆነ ሳይጨልም ተውሎ ይታደራል ማለት ነው – ለእኔ።

በምርጫ ማሸነፍ ሲባል በነፃ መሬት፤ ዬብዙኃኑ የድምጽ የበላይነት አቅም የማግኘት ተጨባጭ ሁኔታ መኖር ሲቻል ብቻ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ለጥቂት ግለሰቦች መንፈስ ሊሆን የሚችል ፍርፋሪ ሊገኝ ይችል ይሆናል። ለዛውም ከተቻለ። አንድ ሰው አንድ ነው – በድምጽ ሥርዓት። በተለያዩ የወያኔ ምርጫዎች በወያኔ ሸንጎ ወንበር ያገኙ ወገኖች ምን አሻሻሉ? ምን አስለወጡ? ምን ፈጠሩ? ምን ተጽዕኖ የማሳደር ሆነ የመፍጠር አቅም ነበራቸው? ካለፉት ጊዜያቶች መስቀያ ገመዱን ፤ ማቃጠያ ቤንዚኑን፤ ማሳደጃ ህጉን፤ ቀነሰን? ላላን? ተሻለን? ትንፋሽን መሰብሰብ ተቻለን? ይህን ህሊና ያለው ወገን ሁሉ ቁጭ ብሎ ይመዝነው። ጥያቄዎችን ከታሰሩበት በትክክለኛ ብይን ይፍታህ ይበላቸው። አይደለም ጥቅል ማንፌስቶ መቀዬር የጎጥ ስያሜውን እንኳን ማስቀዬር አልተቻለም – እንዲያውም ህዝብ ሃብቱን አደቫቫዩን ተቀማ። አይፈቀድለትም መስቀል አደባባይ ላይ የመሰብሰብ የመናገር << አንዲት አንቀጽ እንዲሻሻል አቅም አልተገኘም …. ልዩነቱ የቀደሙት ለህዝብ ጥቅም ያደሩት ጨለማ ውስጥ፤ ሁለመናቸውን በትነው ምሰሶዎችን (pilars)  እዚያው አይሆኑ ሆኑ። ውክልና ያገኘው ደግሞ ከቀዮዋ በር ሳይደርስ …. !

እኔ እንጃ እንዴትና እንዴት ልንገናኝ እንደምንችል። ገና የመንፈስ ውህደታችን እኮ „ለአቅመ አዳም አልደረሰም“ በጥቅስ ያስገባሁት ወያኔን „ለአቅመ አዳም አልደረሰም“ የሚል ከሥነ ጥበብ አንባ ከማከብረው ወንድሜ የወሰድኩት ስለሆነ ነው። እውነት መስዋዕትነቱን ማድመጥ ብንችል ምንኛ መልካም በሆነ ነበር። የሰማዕቱ የኔሰው ገብሬ ይበቃ ነበር። አቶ ሃብታሙ ታሟል መባልን ሰምቻለሁ … ርዕዮት ውብሸት ስቃያቸው ከህመም ጋር …. የትናንትኗ ወጣት ሃና ሰቆቃ ብቻ አይበቃም?! የሚያክም ሃኪም እስክታጣ ድረስ – የነገ ቀንበጥ ተስፋ …. እንድትሞት ተፈረደባት። ማነው የዚህች ዕንቡጥ ጠበቃው?! ስለምንስ ያ የአለም ዬሥነ ጹሑፍ መብራት ሊቀ – ሊቃውንት ጧፉ ሃይሉ ጎመራው እንደ ወጣ መንፈሱ ከጣዕሙ ጋር ሳይገናኝ አፈር ሆነ?! …. እውነት እውነትን ብናምነው ወያኔ መቀጠል የሌበት ድርጅት በሆነ ነበር። ለዚያውም ደግሞ እንዲህ የእሱ የማጥቂያ ተውኔት የመድረክ ታዳሚ በመሆን … እህ!

ሁለትና ከዚያም በላይ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን፣ መርሃቸውን፣ ተስፋቸውን፣ ይዘው ከዋና ጠላታቸው ወይንም ከአጋር ፓርቲዎች ጋር መንፈስ በማደራጀት መፎካከራቸው መልካም ነው። ሃሳብን በሃሳብ ማታገል የተገባ ነው። ውጪ ሀገርም የምናዬው ይሄንኑ ነው። ከጥላቻና ከቂም በቀል በጸዳ ሁኔታ። ይህ ግን ነገን ለማራቅ ወያኔ ባሰበው አስመሳይ ቀለበት ገብቶ ሳይሆን እንዲያውም በጎን ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው እዬተደጋገፉ ጠላታቸውን እርቃኑን ለማስቀረት በጊዜያዊ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በዘላቂ ፍላጎት ላይ፤ በግለሰቦች ክብርና ፍላጎት ላይ ሳይሆን ይልቁንም በፓርቲዎች ራዕይና በህዝቡ ፍላጎት መሃከል የጸና የመንፈስ ድልድይ – እንዲኖር ማደረግ ነው ቀዳሚ ተግባር ሊሆን የሚገባው እንጂ  ….

የጎንዮሽ መደጋጋፍ አለመኖር ለአረሙ ወያኔ የሃይሉ የቁጠባ ባንክ ነው የሚሆንለት። ላሜ ወለደች ዓይነት፤ በዬተራ መድቦ እዬነጠለ ስለሚያድክም፤ አጋጣሚዋን ሲያገኝ በአንዱ ላይ ለማዳካም የሚሰነዝረው ጥቃትን ለሌላ ስውር ተግባሩ ያውለዋል። ስለምን? የእሱ የጋራ ተቀናቃኞች አካላቸውን – አካላቸው በመንፈስ ስለሚያዳክምለት። ስለሚተችለት፤ ስለሚያገልለት፤ ስለሚያዝልልት አራት ኪሎው ሆኖ ችርስ ነው … ወያኔ ብዙ ነገር ይቆጥብለታ – ላ። ብዙ የማይታዩ ትርፎችን ይዝቅበታ- ላ። ይዝናናበታል – ጭንቀቱንም ውጥረቱን ያረግብበታል ….

ፍቅር የሚባለው ነገር ቅፅበት ነገር አይመስለኝም። ቅፅበቱ አጀንዳ ለመሆን ያለው ደወሉ ወይንም የብልጭታ ጊዜው ነው። ጠቃሚው ነገር ግን በውስጥ ያለን የወልዮሽ ዬነፃነት ፍላጎት ፍቅር ኮትኩቶ ከማሳደጉ ላይ ነው። ለፍላጎታችን ተመሳሳይ የፍቅር ሙቀት ሰጥቶ ኮትኩቶ የማሳደግ ክህሎትን በአጽህኖት ይሻል። ካለፈው ጊዜ በተሻለ መልኩ ከነጠረው ፍላጎት ጋር ያለው መተሳሳር መከራውን እንደ መንገድ ጠራጊነት አይቶ፤ ፍቅርን መጋራቱን – ሃይል አመንጪ፤ አቅም ጨማሪ ማድረግ ያስፈልግ ይመስለኛል። ያሳልፍናቸው ሶስት ዓመታት እጅግ ጎምዛዛ – ሃሞት ነበሩ። እነዚህ መራራ ጊዜያቶች ለራዕያችን እውንነት መዋለ ንዋይ የማድረግ ብልህነት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ዕንባ ነገን አጉብጦ ለማስቀጠል ሳይሆን የጎበጠውን ቀን ቀና — ቀና — ቀና እያደረገ ቁሞ እንዲሄድ የማድረግ ሥልጡን ተግባር ያስፈልገዋል። ለዚህ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ የአምልኮ ቦታዎች፤ ማህበራት ሁሉ በዚህ የፍቅር ጅረት ቢጠቃለሉ ሞገዳማ ማዕበልን ወይንም እሳተ ጎመራን ይፈጥራሉ። ለዚህ ነው ከወቅቱ ጋር በፍጹም ሁኔታ የሰመረውን የጸሐፊ አቶ ዮፍታሄን ፍላጎት እንድናዳምጥ፤ ከልብ ሆነን ጠረኑን እንድንመገበው በአጽህኖትና በተደሞ በትህትና ደጋግሜ የማሳስበው።

ክውና። መጀመሪያ እኛና እኛ እንተዋወቅ። በዚህ ቁልፍ የፍላጎታችን ስምረት ይሆናል – ታዲያ መተዋወቁን በመቁንን ሳይሆን በገፍ ካደረግነው ነው። ግን ግን በነገራችን ላይ ፍቅር ነው ወይንም ዕምነት መጣል እውር የሚያደርገው ይሆን? ጨርስኩ – የልብ አድራሼን ዘሃበሻ አመስግኜ። የኔዎቹ – መሸቢያ ሰንበት – ኑሩልኝ።

መቅደምና መቀደም ልዩነታቸው ለገባው የነፃነት አርበኛ ዬፍላጎቱን መንገድ ከማፍታታ ይጀምረዋል፤ …  ከዛ – ሩጫውን

መፍቻ

  • ጦሮ … እጅግ ኃይለኛ የነፋስ ቁጣ ነው። ጦረኛው ነፋስ ቁጣው ሲነሳ የሚቀረው የለም። ያገኘውን ሁሉ እዬጠረገ የትሜና ይሰደዋል። ቆርቆሮውን እዬነቃቀለ፤ ክብርን እዬገለበ አቧራ ባዘለ ፉጭቱ ቅጣቱን እስኪበቃው የለርህራሄ ያነደዋል። የወያኔ የምርጫ ዘመቻም ለዚህው ለጦሮ ባህሬው እርገት ነው። – እንስማማ።
  • አሳቻ ባለፈው ፁሑፌም ገልጨዋለሁ „አሳሳች“ ከሚለው መሰረታዊ ቃል የተራበ ነው። ማሳሳቻ የተሰወረ መንገድ እንደ ማለት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 

 

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop