May 5, 2014
32 mins read

‹‹ትንሹ›› ተስፋዓለም (ከጽዮን ግርማ)

በአነጋገሩ ቀጥተኛና በጠባዕዩ ገራገር ነው፡፡ ‹ጥርስ ያሳብራሉ› በሚባሉ ስብሰባዎች፣ በኃይለ ቃል በተሞሉ የኤዲቶሪያል ውይይቶችና ግምገማዎች ሳይቀር ስሜቱን ውጦ በተረጋጋ መንፈስና በለዘብታ ቃል መመላለስ ጸጋው ነው፡፡ በኤዲቶሪያል ጠረጴዛዎችና ዴስኮች ዙሪያ በሐሳብ ለመግባባት ከሚደረጉ ግብግቦች ውጭና ባሻገር ቂምና በቀል አያውቅም፡፡ በደሙ ውስጥ ከሚዘዋወረውና ራሱን ከሰጠለት የጋዜጠኝነት ሞያውና የጋዜጠኝነት መርሕ የተነሳ ሌላ ዓለም፣ ሌላ ጥቅም፣ ሌላ ኑሮ ያለም አይመስለው፡፡ ለእርሱ ኑሮው፣ ለእርሱ ዓለሙ ተጨባጭ መረጃን ከወገናዊነት በጸዳ መልኩ ለሕዝብ ማድረስ ነው – ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፡፡
አሁን ተስፋዓለም በማኅበራዊ ደረ-ገፅ ላይ ‹‹ዞን 9›› በሚል መጠሪያ ገጽ ከፍተው በመጦመር ከሚታወቁ ስድስት ጦማርያንና (Bloggers) ኹለት ጋዜጠኞች ጋራ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ከታሰረ ዛሬ ዘጠኝ ቀን ኾኖታል፡፡ ተስፋለምን ጨምሮ ዘጠኙ ተጠርጣሪዎች የታሠሩት፤[ራሱን የመብት ተሟገች ነኝ ብሎ ከሚጠራ የውጭ ድርጅቶች ጋራ በሐሳብና በገንዘብ በመረዳዳት ማኅበራዊ ድረገፆችን በመጠቀም ሕዝቡን ለአመፅ ለማነሳሳት የተለያዩ ቀስቃሽ መጣጥፎችን ለማሰራጨት ሲዘጋጁ ተደርሶባቸዋል፡፡] በሚል እንደኾነ ፍርድ ቤት የቀረቡበት የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት አርብ ሚያዚያ 17 ቀን ማምሻውንና ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን ነው፡፡ እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ነበር፡፡ በመዝገብ ቁጥር 118722 የቀረቡት የ‹‹ፎርቹን›› ጋዜጣና ‹‹የአዲስ ስታንዳርድ›› መጽሔት ፍሪላንስ ዘጋቢ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ከፍተኛ አዘጋጅ ከአስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምሕርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት ለ29/08/2006 ተቀጥረዋል፡፡በመዝገብ ቁጥር 118721 የተካተቱት የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ የነበረችው ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎቹ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ብርሃነ ሲሆኑ ለ29/08/2006 ተቀጥረዋል፡፡ እንዲሁም በመዝገብ ቁጥር 118720 ሦስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ኃይሉና ማኅሌት ፋንታሁን ለሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የምርመራ መዝገቡን ያዩት ዳኛ፣ ተጠርጣሪዎቹ በቀጠሮው ዕለት ጧት አራት ሰዓት እንዲቀርቡ አዘዋል፡፡
ተስፋዓለም ተይዞ በተወሰደበት ዕለት ምሽት ድርጊቱን በአካል ተገኝቼ ተመልክቻለኹ፡፡ ጎረቤታሞች እንደመሆናችን የተስፋዓለም አንድ ትርፍ የቤት ቁልፍ በእኔ ቤት ይገኛል፡፡ እናም የቤቱ ቁልፍ በአጋጣሚ አንድ ሌላ ጓደኛችን ጋር ነበር፡፡ ባለፈው ዓርብ ሚያዚያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ አካባቢ የቤቴ በር ተንኳኳ፡፡ በወቅቱ ሰዓቱ መሽቶ ስለነበር እኔም ኾነ ቤት ውስጥ የሚገኙት እኅቶቼ በጣም ደነገጥን፡፡ በሩን ከመክፈቴ በፊትም ያንኳኳውን ሰው ማንነት ጠየቅኹ፡፡
ማንነቴን በስም ከጠራ በኋላ እንድከፍት አዘዘኝ፡፡ በድጋሚ ማንነቱን ጠየቅኹ፡፡ የተስፋዓለምን ስም ሲጠራ ደነገጥኹና ተንደርድሬ ከፈትኹ፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለ ጥሪ አጋጥሞኝ ስለማያውቅ ችግር ገጥሞት ሊሆን ይችላል ብዬ ጠረጠርኹ፡፡ ተደናብሬ ስወጣ ፊቱ በቁጣ የሚንቀለቀል ወጣት ተስፋዓለም ስለተያዘ እንደምፈለግና ወርጄ እንዳናግር አዘዘኝ፡፡ እየሔድን መረጋጋት ስላቃተኝ ማንነቱንና የተፈጠረውን ነገር እንዲነግረኝ ጠየቅኹት፡፡ ‹‹ማንነቴ ምን ያደርግልሻል፤ እርሱን በኋላ ታውቂዋለሽ፤ አኹን ወደ ተጠራሽበት ሒጂ፤›› አለኝ፡፡
ቅርብ ለቅርብ ስለነበርን ወዲያው ደረስን፡፡ ትንሹ ተስፋዓለም ከእርሱ በገዘፉ ወጣቶች ተከቦ ሜዳ ላይ ቆሟል፡፡ ከእግሩ ሥር በፌስታል የተቆጣጠሩ ነገሮች ተቀምጠዋል፡፡ ኹለቱ ፌስታሎች የሚለበሱ ነገሮች መኾናቸውን አስተውያለሁ፡፡ ኹኔታው በእጅጉ ግራ ስለገባኝ ምን እንደተፈጠረ መወትወት ጀመርኹ፡፡ የተፈጠረውን የሚነግሩኝ ሳይሆን የሚቆጡኝ ድምፆች በረቱ፡፡‹‹የሚነገርሽን አዳምጪ፤ አንድ ትርፍ የቤት ቁልፍ አንቺ ጋር አለ አይደል?›› አሉኝ፡፡ ቁልፉ እኔ ጋር እንዳለ ነገር ግን የሚገኘው ሌላ ጓደኛችን ጋር እንደሆነ ነግሬ እኔን ወደ አሳሰበኝ ጉዳይ ተመለስኹ፡፡
ተስፋዓለምን ለምንና የት እንደሚወስዱት ለማወቅ ጎተጎትኹ፡፡ ሁለት እጆቹን በደረበው ሹራብ ኪሱ ውስጥ ከቶ መካከላቸው የቆመው ተስፋዓለም የሚሔደው ማእከላዊ እንደኾነና ከሥራ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መኾኑን እንደተነገረው ነገረኝ፡፡ ከያዙት ወጣቶች መካከል ጭንቀቴን የተረዳው አንዱ ይህንኑ ደግሞ ኹለት የፖሊስ ልብስ የለበሱትን ሰዎች አመጣና ‹‹የሚወሰደው ሕጋዊ ቦታ መኾኑን እነርሱን አይተሸ አረጋግጪ››፤ አለኝ፡፡ ቤቱ ቢከፈትና ንብረት ቢጠፋ ተጠያቂ መኾኔን ከማስጠንቀቂያ ጋር በመንገር ትንሹን ተስፋዓለምን ብዙ ኾነው ይዘውት ሔዱ፡፡

ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አባይ ምንጭ እና ተስፋ ኮከብ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች፣ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በ‹‹ከፍተኛ አራት›› አጠናቅቋል፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር የሚገኘው የቀድሞው ማስሚዲያ ማሠልጠኛ ኤጀንሲ የጋዜጠኝነት ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ ‹‹ሰብ ሰሃራን ኢንፎርመር›› የተባለ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ላይ በገጽ ሥራና ቅንብር ባለሞያነት ተቀጠረ፡፡
ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም የመዝናኛ ዜናዎችን በማዘጋጀት የጋዜጠኝነት ሥራን በዚኹ ጋዜጣ ላይ መሥራት ጀመረ፡፡ ቀጥሎም ‹‹ፎርቹን›› በተባለው ሳምንታዊ እንግሊዘኛ ጋዜጣ ላይ ተቀጥሮ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ዘገባዎችን መሥራት ጀመረ፡፡ የ‹‹ፎርቹን›› ጋዜጣ አደረጃጀትና ኤዲቶሪያሉ ጠንካራ ስለነበር የጋዜጠኝነት ችሎታውን ለማሳደግ በጋዜጣው ላይ የሠራባቸው ዓመታት አግዘውታል፡፡
ከ‹‹ፎርቹን›› በኋላ የቀድሞው የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ባለቤት የነበሩት ዶ/ር ፍሥሓ እሸቱ ባለቤትነት የሚዘጋጅ ደረጃውን የጠበቀና በዲዛይን ውበቱ ትኩረት ሳቢ የነበረውን ‹‹ማይ ፋሽን›› የተሰኘ እንግሊዘኛ መጽሔት ገጾች ዲዛይን ይሠራ የነበረው ተስፋዓለም ነበር፡፡ ከዚኹ መደበኛ ሥራው ጎን ለጎን የአሶሺየትድ ፕረስ የዜና ወኪል ረዳት በመኾን ለውጭ ሚዲያዎች መሥራት ጀመረ፡፡
‹‹ማይ ፋሽን›› መጽሔት ከተዘጋ በኋላ በከፍተኛ ደረጃ ተነባቢነት የነበረውን ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ ከሞያ ጓደኞቹ ጋራ መሠረተ፤ የጋዜጣው የዜናና ማኅበራዊ ፊቸር ገጾች አርታዒም ነበር፤ በዚኹ ወቅትም በተባበሩት መንግሥታት ሥር ለሚገኘውና በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ዜናና ትንታኔ ለሚያቀርበው ዓለም አቀፉ ኢሪን (IRIN) የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ኾኖ ይሠራ ነበር፡፡
በመንግሥት ጫና ምክንያት የአዲስ ነገር ጋዜጣው ከመዘጋቱ አንድ ወር በፊት በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ጋዜጠኞች (EEJA) ማኅበር በኩል በዩጋንዳ የአንድ ዓመት የሥራ ላይ ልምድ ልውውጥ ዕድል አግኝቶ ስለነበር ወደዚያው አመራ፡፡ በፕሮግራሙ አጋጣሚና ከልምድ ልውውጡ ጎን ለጎን በዩጋንዳ የተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎችና ‹‹ሩድሜክ›› በተባለ ሚዲያ ላይ ለአንድ ዓመት በሞያው ሲሠራ ቆይቷል፡፡
በዩጋንዳ የነበረውን የአንድ ዓመት የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም ካጠናቀቀ በኋላ ቆይታውን በማራዘም ‹‹ሐበሻዊ ቃና›› የተባለ መዝናኛ ላይ የሚያተኩር ባለቀለም የአማርኛ ጋዜጣ ማዘጋጀትና ማሳተም ጀመረ፡፡ ጋዜጣው በአቅም ማጣት ምክንያት እስከተዘጋበት ጊዜ ድረስ በዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያና ደቡብ ሱዳን ውስጥ ይሰራጭ ነበር፡፡
በመጨረሻም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ የጋዜጠኝነት ሥራውን ፍሪላንስ ኾኖ በመቀጠል ለ‹‹አዲስ ፎርቹን›› እና ‹‹አዲስ ስታንዳርድ›› የእንግሊዘኛ ጋዜጣና መጽሔት መሥራት ጀመረ፡፡ ቢቢሲን (BBC) ጨምሮ ከተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች ጋራም በፍሪላንሰርነት መሥራቱን ቀጠለ፡፡ ከወራት በፊት የ‹‹ቢቢሲ››ዋ ዜና በዳዊ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ጋራ በአዲስ አበባ ያደረገችውን ‹‹ሃርድ ቶክ›› የቴሌቭዥን ፕሮግራም በረዳትነት ያዘጋጀው ተስፋዓለም ነበር፡፡
ተስፋዓለም የሚሠራው ዘገባ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የሶማልያ ቀውስ በተባባሰበትና የኢትዮጵያ ጦር በአልሸባብ ላይ በዘመተበት ወቅት ስፍራው ድረስ ተጉዞ ዘገባዎች አስነብቧል፡፡ በተለይ ለምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጥ ሲኾን የሰሜንና ደቡብ ሱዳን ጉዳይን በሚመለከት በቦታው ተገኝቶ በቅርብ እየተከታተለ በ‹‹ፎርቹን›› ጋዜጣ ላይ ዘገባዎቹን አቅርቧል፡፡ ተስፋዓለም የወቅቱ የአካባቢ ጥበቃ ጋዜጠኞች ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ከመኾኑም በላይ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፍረንሶች ላይ በመካፈል ዘገባዎችን ሠርቷል፡፡
በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ጋዜጠኛ ከየትኛውም ዓለም አቀፍ የዜና ተቋም ጋራ ሲሠራ ለኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አሳውቆ ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ የየትኛውም ድርጅት የዜና ወኪል ይኹን ጥናት አድራጊ የውጭ ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ ለሥራ ሲገባ ስብሰባው ወይ ጥናቱ የት እንደሚካሔድ፣ ማንን እንደሚያናግር አሳውቆ ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡ በዚህ አሠራር መሠረት ተስፋዓለም ከበርካታ ዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎችና አጥኝዎች ጋራ የነበረው ቆይታ ከኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ዕውቅና ውጭ አልነበረም፡፡
ተስፋዓለም በዕድሜው ሠላሳ አንድ ዓመቱ ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሞያ ላለፉት ዐሥር ተከታታይ ዓመታት አገልግሏል፡፡ ሥራ ሲጀምር በጣም ትንሽ ስለነበር ‹‹ትንሹ ተስፋዓለም›› የሚል ቅጽል በጓደኞቹ ተሰጥቶታል፡፡ በልጅነት ገጽታው ታላላቆቹ፣ ታናናሾቹም ኾኑ የዕድሜ አቻዎቹ እንደ ወንድም ስለሚቆጥሩት ‹‹ትንሹ›› የሚለው ቅጽል እስከ አሁን የሚታወቅበት ነው፡፡
ተስፋዓለም ግን ከስያሜው በላይ በእጅጉ ልቆ በሞያው ትልቅ ኾኗል፡፡ በሞያው የረገጣቸው አባጣ ጎርባጣዎች አብስለውት በሳልና በካር አድርገውታል፡፡ አንባቢነቱ፣ ነገሮችን በትኩረትና በተለየ መንገድ መመልከቱ፣ የማይሰለች ጠያቂነቱ፣ ተግባቢነቱና ጋዜጠኝነቱ ሰብእናውን አግዝፈውታል፡፡ ኹለቱንም ወላጆቹን በትምህርት ቤት ሳለና ገና ሥራ በጀመረበት ወቅት በሞት በማጣቱ እርሱና በሥሩ ያለችውን እኅቱን አይዟችኹ የሚላቸው ሰው አልነበረም፡፡ እናም ተስፋዓለምን በወጣትነቱ ማለዳ የተሸከመው የቤተሰብ ሓላፊነት እንደ አለት አጠንክረውታል፡፡ ‹‹ትንሹ›› ተስፋዓለም ማኅበራዊ ሓላፊነቱን ከኋላ ተሸክሞ እውነተኛ ጋዜጠኝነትን ለመተግበር በአያሌው ተግቷል፡፡
ተስፋዓለም ከኢትዮጵያ ውጭ ለመኖር የሚያስችሉት በርካታ ዕድሎች አዘውትረው ከፊቱ ይመጣሉ፡፡ እርሱ የሚመርጠው ለጋዜጠኝነቱ እገዛ ሊያደርጉለት የሚችሉ አጫጭር ሥልጠናዎችን እየወሰደ ወደ ሀገሩ መመለስ ነው፡፡ አገር ውስጥ የሚሰጡ ሥልጠናዎችም ተስፋዓለምን አያልፉትም፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ከወጣኹ ከሞያዬ እለያያለኹ›› የሚል ስጋት ስለሚያድርበት አገሩ ላይ ኾኖ ክፉውንም ደጉንም እየተጋራ፣ ለሞያው ሥነ ምግባር ራሱን አስገዝቶ በሀገሩ ቁጭ ብሎ ይሠራል፡፡
ለሥራው ጥራት፣ ተጨባጭነትና ሚዛናዊነት ሟች የኾነው ተስፋዓለም የሚጠቅመውን መረጃ ለማግኘት ማንኛውንም መሥዋትነት ስለሚከፍል ሠርቶ ከሚያተርፈው ደመወዙ ይልቅ መልሶ ለሥራው የሚያውለው ወጪ ይበልጣል፡፡ እርሱ ኹሌም የገንዘብ ድኻ ነው፡፡ ያጠለቀው ጫማ በላዩ አልቆ እስኪቀደድ ድረስ ራሱን ለሥራው አሳልፎ የሚሰጥ የሳንቲም ድቃቂ የጨርቅ ዕላቂ ድኻ ነው!! ለዚህ ጠባዕዩና አኗኗሩ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የሚያውቁት በርካታ ጓደኞቹ በምስክርነት ሳይቆጠሩ ምስክርነታቸውን ሰጥተውለታል፡፡
የተስፋዓለም ጓደኝነት ስለማይቆረቁር ባልንጀርነቱ ለብዙዎች ነው፡፡ ጋዜጠኝነት ከሚሰጣቸው ዕድሎች ዋነኛው ሠርክ አዲስ ሰው መተዋወቅ ነው ብሎ ስለሚያምን ወዳጆቹ በርካታ ናቸው፡፡ ኹሉንም ጓደኞቹን እንደየባሕርያቸው እስከአሁን አብሮ አቆይቶአቸዋል፡፡ ሰው ያሻውን ያኽል እንኳ ቢያስከፋው እንደ መሬት ነገር ቻይ እንጂ መከፋትን፣ መበቀልንና መቀየምን አያውቅም፡፡
እኔና ተስፈዓለም የምንተዋወቀው ፎርቹን ጋዜጣ በሠራንበት ወቅት ነው፡፡ ለጋዜጠኝነት እጃችንን ካፍታታንበት ፎርቹን ጋዜጣ ጀምሮ እስከ አሁንም ድረስ የልብ ጓደኛሞች ነን፡፡ ካለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጀምሮ ደግሞ ጎረቤታሞች ኾነናል፡፡ተስፋዓለም መረጃ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ሁሌም አደንቀዋለኹ፡፡በኦሞ የተከሰተው ጎርፍ በኮረንጋት ደሴት የሚገኙትን ዳሰነችና ኛንጋቶም ቀበሌ ነዋሪዎች ጠራርጎ እየወሰዳቸው መኾኑን እንደሰማ በቦታው ተገኝቶ ዘገባውን ለመሥራት፤ጭነት በያዘ አይሱዙ መኪና ላይ ከጭነቱ ላይ ተቀምጦ ሌሊቱን በሙሉ በመጓዝ አርባ ምንጭ ገብቶ ያደረውን መቼም አልረሳውም፡፡
ተስፋዓለም የመታሰሩ ወሬ እንደተሰማ ስለተስፋዓለም አስተያየት የሰጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይ በየፌስ ቡክ ገጾቻቸው እየወጡ ስለእርሱ “one of the prominent journalist” በሚል የመሰከሩለት የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ የኹሉም አስተያየት ግን እርሱ ለጋዜጠኝነት ሞያው የሚሰጠው ክብርና ዋጋ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
የረጅም ጊዜ ጓደኛውና የቀድሞ የሥራ ባልደረባው ስመኝሽ የቆየ (ሊሊ) ‹‹ተስፋዓለምን የተዋወቅኹት ሥራ እንደጀምርኹ እርሱ ፎርቹን እኔ ደግሞ ሰብ ሰሃራን እየሠራሁ ነው፡፡ ገና ስቀጠር በጊዜው የሥራ ባልደረባዬ የነበረ ጋዜጠኛ እንዴት ጠንካራ ጋዜጠኛ መኾን እንዳለብኝ እየመከረኝ በየመሀል እንደ ትልቅ ምሳሌ ያደርግ የነበረው አንድ ሰው ተስፋዓለም የሚባል ፎርቹን የሚሠራ ጋዜጠኛ እያለ ነበር፡፡ ጽሑፎቹንም እንዳነብና እንዴት የተሟላ ዘገባ መጻፍ እንደምማር ይመክረኝ ነበር፡፡›› ትላለች፡፡
አያይዛም‹‹ከሳምንታት በኋላ ተስፋዓለምን ሳገኘው ከተባለው በላይ ለሞያው ያለውን ታታሪነት በተግባር አየኹት፡፡ በሥራው ላይ ምንም ነገር ጣልቃ እንዲገባበት አይፈቅድም፤ አካሉም፣ አእምሮውም ልቡም ለጋዜጠኝነት የተሰጠ ነው፡፡ ጓደኝነታችን ጠንክሮ ዐስር ዓመት ሲዘልቅም አንድም ቀን ገንዘብ ሳያጓጓው አብዛኛውን የሕይወቱን ክፍል ከሰጠለት ሞያ በሻገር የዋህነቱን፣ ቀጥተኛነቱን፣ ለሰው ደራሽነቱን እና ጠንካራነቱን እያየሁ አብረን ኖርን፡፡ ተስፋለም ለኔ ከሞያ ባልደረባ አልፎ ጓደኛና ወንድም ኾነኝ፡፡›› ብላለች- ለፋክት በሰጠችው አስተያየት፡፡
‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ ይዤ የመጣሁትን ዜና እንዲያርምልኝ ሰጥቼው፤ ወደጀመርኩት የኢኮኖሚ ጽሑፍ ተመለስኩ። ነገር ግን አፍታም ሳይቆይ በንዴት እየቀዘፈ መጥቶ “አሁን በዚህ ሌሊት ይህ ዜና ተብሎ ይሠራል….›› አለኝ ተስፋዓለም ለሞያው የሚቆረቆር። አንዳች ስሕተት መስሎ የሚሰማውን ፊት ለፊት ከመናገር የማይቆጠብ ነው፡፡ያን ሌሊት በብዙ ጭቅጭቅና ንትርክ ዜናው ተሠርቶ ወጣ። አጋጣሚው ግን ልዩነታችን በጋዜጠኝነት ፍልስፍና ላይ እንደኾነ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር። እርሱ “ሚዛናዊ” ብሎ የሚሟገትለት ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት አንዳች የማያራምድ ይልቁንም ጋዜጠኝነትን አሽመድምዶ ልሳን የሚሸብብ መኾኑ ሊያግባባን አልቻለም። እኔ “balanced journalism is a zero-sum game in Ethiopia” ብዬ እሞግተዋለኹ፤ እርሱ በየትኛውም የመንግሥት ሥርዓት ቢኾን የጋዜጠኝነት ሕግጋት የማይጣሱ ደንቦች ናቸው ይላል። ይህን ደግሞ በሥራው ያሳያል፡፡ጋዜጠኝነትን ሕይወቱ ያደረገው ተስፋዓለም በምንም መልኩ ቢኾን ሞያው በትምህርት ቤት ያገኛቸውን የጋዜጠኝነት መርሖዎች እንዲቃረን አይፈልግም። ዜናዎች ሲያዘጋጅ “ሚዛናዊነት” የሚለው መርሕ አለመጣሱን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው ወሬው የኅትመት ብርሃን የሚያየው።›› ሲል በፌስ ቡክ ገጹ ስለ ተስፋዓለም ያሰፈረው የቀድሞ የ‹‹አዲስ ነገር›› የሞያ አጋሩ ጋዜጠኛ ዘሪሁን ተስፋዬ ነው፡፡
ከተስፋዓለም ጋር አብሮት የሠራው የቀድሞ የ‹‹አዲስ ነገር›› ባልደረባ ዳኝነት መኮንን፣ ‹‹ኹሌም ስለጋዜጠኝነት አለባውያን፣ መሠረታውያን፣ ቀመርና ሥነ ምግባር አብዝቶ የሚጨነቅ ምናልባትም ብቸኛው ጓደኛችን ነው። ጋዜጠኝነት ማለት accuracy, balance, clarity, and neutrality ከኾነ የማውቀው አንድ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ ነው። የዜና ዘለላ መቁጠር፣ የፊቸር አለላ ማሰባጠር ማን እንዳንተ ተስፍሽ! ዜናና ታሪክ ሲሠራ ቀዳሚና ፊተኛው፤ እስረኞችን ቃሊቲ ወርዶ በመጠየቅ ታታሪው ወንድሜ ጠያቂና ስንቅ አሳሪ ያብዛልኽ።›› ብሎታል፡፡
‹‹ተስፋዓለም የግል ፖለቲካዊ አመለካከቱ ከጋዜጠኝቱ ጋራ እንዳይጋጭበት የሚጠነቀቅ ወጣት ነው። ለጋዜጠኝነት ከፍ ያለ ክብርና ዋጋ ይሰጣል። አንዳንዴ እቀናበታለኹ። ስለሚዛናዊነት፣ ስለተገቢነትና ስለእውነተኛ ዘገባ አብዝቶ ይጨነቃል። ማንኛውም ዐይነት ዘገባ ከትክክለኛው ወንዝ ተቀድቶ እንዲፈስ ይመኛል፤ ያደርጋል፤ ይጓዛል። መጀመርያ ለሞያው ታማኝ መኾንን ያስቀድማል። ከተስፋዓለም ጋራ ሳወራ ከታናሽ ወንድሜ ጋራ የማወራ ነው የሚመስለኝ። ኢሕአዴግ እንደ ተስፋዓለም መሥመራቸውን ጠብቀው ለሚሠሩ ሰዎች የማይመለስ ይኾናል ብዬ አስቤ አላውቅም። አኹንም መታሰሩን ማመን እውነት አልመስልኽ ብሎኛል! የሚሰማኝ፣ እልኽ፣ ቁጭት፣ ተስፋ ቢስነትና ቁጣ ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ተስፋዓለም የማንም ወገን አይደለም። ብቻውን በራሱ የቆመ ጋዜጠኛ ነው፣›› ያለው የቀድሞው የ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ ባልደረባው ማስረሻ ማሞ ነው፡፡
ከጋዜጠኝነት ት/ቤት ጀምሮ እስከ አኹን ጓደኛው የኾነው ጋዜጠኛ ደረጀ ብርሃኑ÷ ‹‹ተስፋዓለም ከኹሉም ጋራ ለመግባባት የሚሞክር፣ በት/ቤት በነበረበት ወቅት ጋዜጠኛ ለመኾን ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው ሥራ የጀመረው ከኹላችንም ቀድሞ ትምሕርቱን ሳይጨርስ ነበር፡፡ ተስፋዓለም ኹልጊዜም አብረውት ቢኾኑ የማይሰለች፣ ጓደኝነቱና ጨዋታው የሚናፈቅ፣ ስለ ጋዜጠኝነት መሠረታዊ ቀመርና ሥነ ምግባር ቢያወራ የማይታክተው ጋዜጠኛ ነው፤›› ብሎታል፡፡
በ‹‹ሰብ ሰሃራ››ና ‹‹ማይፋሽን›› በሠራበት ጊዜ አለቃው የነበረው ዓለማየሁ ሰይፈ ሥላሴ፣ ‹‹ተስፋለም በየዕለቱ ለመለወጥ የሚጥር ታታሪ ልጅ ነው፤ ፍጹም ሞያዊ ጋዜጠኝነት ለማምጣትና ሚዛናዊ የኾነ ዘገባ እንዲሠራ ለማድረግ የሚጣጣርና የሚተጋ ጋዜጠኛ ነው፤ ይህን የሚያደርገው ደግሞ ራሱ ብቻ ሳይኾን ሌሎችን በመጎትጎት ጭምር ነው፡፡ የጋዜጣና የመጽሔት ዲዛይኖች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ኾነው እንዲሠሩ ለማደረግ የሚጥር፣ ከሌሎች ልምድ የሚቀስምና የራሱን ልምድ ለማካፈል ወደኋላ የማይል ጠንካራ ጋዜጠኛ ነው፤›› ብሎታል፡፡
የእውነትም ‹‹ትንሹ›› ተስፋ ዓለም ይኸው ነው፡፡ ማኅበራዊና ግላዊ ችግሮቹን ተቋቁሞ ስለ ጋዜጠኝነት ማውራትና ጋዜጠኛ ኾኖ መኖር የማይሰለቸው የአማናዊ ጋዜጠኝነት ተስፋ – ተስፋ ዓለም!!

Latest from Blog

ከቴዎድሮስ ሐይሌ ትግል ዘርፈ ብዙ ጎኖች አሉት:: ዲፕሎማሲ ሚድያ የፖለቲካ ; ካድሬዎች ; ወታደራዊ ባለሙያዎች ;የሕዝብ አደረጃጀት እና ሌሎችም ተጏዳኝ ዘርፎችን እና ሌላም ብዙ ተቋማዊ ባህሪያት እንደ ትግሉ ጸባይና ሁኔታ ሊያካትት ይችላል::

የአማራ ሕዝባዊ ድርጅት ያደረገው ውይይት ወይስ ድርድር?

January 27, 2025
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)  ጥር 19፣ 2017(January 27, 2025) ሰሞኑን እስክንድር ነጋ “እመራዋለሁ የሚለውን የፋኖ ክንፍ” በመወከል ከአቢይ አህመድ አገዛዝ ጋር፣ እሱ እንደሚለው ውይይት፣ በመሰረቱ ድርድር እንዳደረገ በተለይም እነ ሀብታሙ አያሌው በሚቆጣጠሩት የኢትዮጵያ 360 ዲግሪ ሚዲያ ሰምተናል። ከመንግስት ጋር

እስክንድር ነጋ በታዛቢዎች አማካይነት ከአቢይ አህመድ ጋር የሚያደርገው ድርድር የአማራውን ህዝብ የተሟላ ነፃነት የሚያጎናፅፈው ወይስ ለዝንተ-ዓለም ኋላ ቀር ሆኖና ኑሮው ጨልሞበት እንዲቀር የሚያደርገው ?

ትግላችንን ለዳግም ባርነት ለሚያመቻቹን የብልጽግና እሳቤ አራማጆች አሳልፈን አንሰጥም!!! ቀን፦ ጥር 18/2017 ዓ.ም ትግላችን የኅልውና፣ የፍትሕ፣ የነጻነት፣ የሰብዓዊ ክብር ሆኖ እያለ ከፋፋይነት፣ ብልጣብልጥነት፣ አወናባጅነት፣ ከምንም በላይ በሕዝባችን ላይ የፖለቲካ ቁማርተኝነት እሳቤዎችን ከጀርባቸው

በወቅታዊ ጉዳይ ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ መግለጫ

January 26, 2025 ጠገናው ጎሹ ከቅኝ አገዛዝ (colonial rule) ነፃ መሆንን ከማወጅ ያለፈ የውስጥ ነፃነት ፣እኩልነት፣ ፍትህ እና እደገት/ልማት እውን ማድረግ ባለመቻል ምክንያት በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም የኋላ ቀርነት እና ለመግለፅ

አህጉራችን እና እኛ

ከሰሞኑ ታዛቢዎች በተገኙበት ከመንግስት ጋር ውይይት እንዳደረገ እና ለድርድር ዝግጁ እንደሆነ የገለፀው በእስክንድር ነጋ የሚመራው የፋኖ ክንፍ ድርድሩ በውጭ ሀገራት እንዲሆን እየጠየቀ መሆኑ ታውቋል። የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደተናገሩት ታጣቂ ክንፉ ድርድሩ በአውሮፓ

በእሰክንድር ነጋ የሚመራው ፋኖ’ ከመንግስት ጋር ለመደራደር ተዘጋጅቷል

January 26, 2025
Go toTop